‹‹ከአልሻባብ ጋር እነጋገራለሁ›› ፋጡማ ዳዒብ ትናገራለች

ፋጡማ ዳዒብ
ፋጡማ ዳዒብ

(ሳተናው) ፋጡማ ዳይብ ለፕሬዘዳንታዊው ውድድር ራሷን በማቅረብ የመጀመሪያዋ ሴት ሱማሊያዊት ሆናለች፡፡

በያዝነው ዓመት በነሐሴ ወር እንደሚካሄድ በሚጠበቀው ፕሬዘዳንታዊ ምርጫ ለመሳተፍ የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን በማድረግ ላይ እንደምትገኝ የምትናገረው ፋጡማ በምርጫው አሸናፊ በመሆን አገሪቱን የመምራት ዕድል ካገኘች ከአልሻባብ ጋር ለመነጋገር በጠረጴዛ ዙሪያ እንደምትቀመጥ አስታውቃለች፡፡‹‹ከአልሻባብ መሪዎች ጋር በመነጋገር ችግሮችን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለመፍታት እሞክራለሁ››ብላለች፡፡

ለራዲዩ ዳልሳን ቃለ ምልልስ የሰጠችው ፋጡማ ይህንን ትበል እንጂ አልሻባብ አጥባቂ የእስልምና ህግ ተከታይ በመሆኑና በአገሪቱ ያለው የባህል ገደብ ምኞቷን ማሳካት መቻሏን ጥርጣሬ ውስጥ ይጥሉታል፡፡

‹‹እነርሱ የእኛ ወንድሞችና ልጆች ናቸው፡፡እኛን እየጎዳን በሚገኘው ችግር ዙሪያ መነጋገር ይኖርብናል፡፡ይህንን የማድረግ ስህተት ደግሞ አይታየኝም››ማለቷ ተሰምቷል፡፡

በምርጫው አሸናፊ ከሆነችም ቀዳሚ ተግባርዋ የሴቶችንና የልጆችን አቅም ማጎልበት እንደሚሆን የምትናገረው ፋጢማ ‹‹የሚበዙት የዚህች አገር ልጆች የትምህርትና የጤና ሽፋን ያላገኙ ናቸው፡፡ተገቢውን እንክብካቤ ያላገኙ በመሆናቸውም ይህንን የማድረግ ኃላፊነት አለብን››ብላለች፡፡

አሁን ላሉት የአገሪቱ የፓርላማ አባላት ባስተላለፈችው መልእክትም ከምንም ነገር በላይ ለአገራቸው ጥቅም ቅድሚያ በመስጠት የምርጫው ጊዜ ሲደርስ ድምጻቸውን እንዲሰጡ ተማጽናለች፡፡

የአራት ልጆች እናት የሆነችው ፋጢማ በወንዶች ቁጥጥር ስር በወደቀችው አገሯ ፕሬዘዳንታዊ ውድድር ላይ ለመሳተፍ መፈለጓን በገለጸችበት ቅጽበት የግድያ ዛቻ የደረሳት ቢሆንም ህልሟን ከማሳካት ምንም ነገር እንደማያቆማት አስታውቃለች፡፡

ምንጭ ቢቢሲ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.