በዘላለምና ዳባ ደበሌ ላይ የኦህዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ እንዲወስን እየተጠበቀ ነው

zelalem

(ሳተናው) የኦህዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ በአዳማ ለአምስት ቀናት ባደረገው ኮንፈረንስ የተለያዩ ውሳኔዎችን በማሳለፍ ሁለት የድርጅቱን ከፍተኛ ባለስልጣናት ማንሳቱን ባሳለፍነው ወር ማሳወቁ አይዘነጋም፡፡ሁለቱ ባለስልጣናት ከቦታቸው እንዲነሱ የተደረጉትም ከአመራር ጉድለት ጋር በተያያያ መሆኑን ድርጅቱ ያወጣው መግለጫ ማስታወቁ አይዘነጋም፡፡

የኦህዴድና የኢህአዴግ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል፣የኦህዴድ ዋና ጽ/ቤት ኃላፊና የክልሉ ምክትል ፕሬዘዳንት የነበሩት ዳባ ደበሌ ከስልጣናቸው እንዲነሱ ቢወሰንም የኦህዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል እንደሆኑ ይቀጥሉ ተብሎ ነበር፡፡

እንደ ዳባ ደበሌ ሁሉ የአህዴድና የኢህአዴግ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል የነበሩትና በኦሮሚያ ክልል የተፈጥሮ ሐብት ቢሮን ሲመሩ የቆዩት ዘላለም ጀማነህ ከሁለቱም የማዕከላዊ ኮሚቴ አባልነታቸውና ከስራቸው እንዲነሱና ድርጅቱ በቀጣይ የሚያሳልፈውን ውሳኔ እንዲጠባበቁ ተነግሯቸዋል፡፡

ሁለቱ ከፍተኛ ባለስልጣናት በተባረሩበት ወቅትም የክልሉ የደህንነትና የአስተዳደር ቢሮ ኃላፊ የሆኑት ሰለሞን ቁጩም መባረራቸውን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ተባራሪዎቹ የኦህዴድ ከፍተኛ ባለስልጣናት እስካሁን ላልበረደው የህዝብ ተቃውሞ መባባስ ምክንያት ተደርገው ተወስደዋል፡፡የህዝቡን ጥያቄ በፍጥነት ለመመለስና መፍትሄ ለመፈለግ በመዘግየታችሁ እዚህ ደርሰናል ተብለው መወቀሳቸውንም ለማወቅ ተችሏል፡፡

የኦህዴድ ዋና ጽ/ቤት ኃላፊ የነበሩት ዳባ ደበሌ የተቃውሞ እንቅስቃሴውን በተመለከተ በየጊዜው ለጋዜጠኞች መረጃዎችን በመስጠትና ህዝቡ ያነሳው ጥያቄም ተገቢና ኦህዴድም የሚያምንበት መሆኑን ሲናገሩ መቆየታቸው አይዘነጋም፡፡

ዳባ ደበሌና ዘላለም ጀማነህን በተመለከተ ኦህዴድ የወሰደውን ውሳኔ በመደገፍም የፌዴራል መንግስቱ የኮሚኒኬሽን መስሪያ ቤት አስተያየቱን መስጠቱ ተስተውሏል፡፡የኮሚኒኬሽን መስሪያ ቤቱ በሰነዘረው አስተያየት ‹‹ሰዎቹ የተባረሩት በአቅም ማነስ፣የስራ ኃለፊነትን በአግባቡ ባለመወጣትና በኪራይ ሰብሳቢነት ተገምግመው የታገዱ ናቸው››ብሏል፡፡

የኮሚኒኬሽን መስሪያ ቤት በይፋዊው የማህበረሰብ ገጹ ባሰፈረው መልእክት ዘላለም ጀማነህ በህግ የሚጠየቅበት አግባብ ሊኖር እንደሚችልም አመልክቷል፡፡

ለሳተናው እንደደረሰው መረጃም ከሆነም በቅርቡ የኦህዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት የተሰናበቱትን ሰዎች በተመለከተ ሊወሰድ ስለሚገባው ህጋዊ እርምጃ በመነጋገር ውሳኔ ያሳልፋሉ ተብሎ ይጠበቃሉ፡፡ጉዳዩ አፋጣኝና እልባት ማግኘት የሚገባው ሆኖ በመገኘቱም በይደር መተው የለበትም በማለት የተከራከሩ አባላት ቢኖሩም በቀጣይ በሚደረገው አስቸኳይ ስብሰባ ውሳኔ እንደሚሰጥ መነገሩንም ምንጮች ይጠቁማሉ፡፡

አቶ ዘላለም ጀማነህ የቁም እስር በሚመስል መልኩ የመንቀሳቀስ መብታቸው ተገፉ እንደሚገኙ የሚናገሩ የሳተናው ምንጮች ዳባም ከመኖሪያ ቤታቸው ውጪ ብዙም እንደማይታዩ ይናገራሉ፡፡በጣም በቅርቡ ኦህዴድ በሚያደርገው ስብሰባም በዋናነት ዳባና ዘላለም የእጅ ካቴና ሊጠልቅላቸው እንደሚችልም ምንጮቻችን ግምታቸውን ያሰቀምጣሉ፡፡

ምንጭ ሳተናው

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.