ዴቪድ ካሜሮን የጻፏቸው ደብዳቤዎች በአንዳርጋቸው ጉዳይ ለውጥ አለማምጣታቸው ተነገረ

Andy-Tsege

(ሳተናው) የእንግሊዙ ጠቅላይ ሚንስትር ዴቪድ ካሜሮን በ2006 በኢትዮጵያ ኃይሎች ታፍነው የተወሰዱትን አቶ አንዳርጋቸው ጽጌን መጎብኘት እንዲቻል በሁለት አጋጣሚዎች ለኢትዮጵያ ባለስልጣናት ደብዳቤ ቢጽፉም የእንግሊዝ የውጪ ጉዳይ መስሪያ ቤት በኢትዮጵያ በኩል ምንም አይነት የተለወጠ ነገር አለመኖሩ እንዳሳሰበው ተነገረ፡፡

የእንግሊዝ መንግስት ለበዝፊድ የዜና አውታር እንዳረጋገጠው ከ2006 ጀምሮ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለኢትዮጵያ አቻቸው ሁለት ደብዳቤዎችን በመጻፍ አቶ አንዳርጋቸውን በመደበኛነት የእንግሊዝ ተወካዩች እንዲጎበኟቸው ጠይቀዋል፡፡ የሶስት ልጆች አባት የሆኑት አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ በሰኔ ወር 2006 በየመን ታፍነው ለኢትዮጵያ ተላልፈው መሰጠታቸው አይዘነጋም፡፡

በኢትዮጵያ ለውጥ እንዲፈጠር ጥሪ ሲያደርጉ የቆዩት የፖለቲካ አክቲቪስቱ አንዳርጋቸው በሌሉበት በተመሰረተባቸው ክስ በ2001 የሞት ፍርድ ተላልፎባቸዋል፡፡የእንግሊዝ ባለስልጣናት የኢትዮጵያን መንግስት በእስር ላይ ለሚገኙት እንግሊዛዊው በመደበኛነት የመጎብኘት መብታቸው እንዲከበርላቸውና ጉዳያቸው በመደበኛ ፍርድ ቤት በህጋዊ መንገድ እንዲታይላቸው ጠይቀዋል፡፡የእንግሊዙ ጠቅላይ ሚንስትር ያደረጉትን ጣልቃ ገብነት የተመለከተ መረጃ የተገኘው በሐምሌ ወር 2007 ስለተከናወኑ ሁኔታዎች በዳውኒንግ መንገድ የውጪ ጉዳይ ሚንስትሩ ቢሮ ለጋዜጠኞች በሰጠው ማብራሪያ ነው፡፡

በማብራሪያው ባለስልጣናቱ ከ2006 ጀምሮ እንግሊዝ የአንዳርጋቸውን ጉዳይ በተመለከተ የተከተለችው መንገድ ምንም አይነት መሻሻሎችን አለማምጣቱን አምነዋል፡፡‹‹ከኢትዮጵያው የውጪ ጉዳይ ሚንስትር ለውጪ ጉዳይ ሚንስትራችን ከተገባው ተደጋጋሚ ተስፋ ውጪ ያቀረብናቸው መደበኛ የጉብኝት ጥያቄዎች ተቀባይነት አላገኙም››ብለዋል፡፡

ዜናው በቅርቡ አንዳርጋቸው ጽጌ ስለሚፈጸምባቸው ቶርቸር የተባበሩት መንግስታት ልዩ መልእክተኛ የሆኑት ሁዋን ሜንዴዝ ስጋት እንደገባቸው በመግለጽ የሰጡትን አስተያየት ተከትሎ የተደመጠ ነው፡፡ለተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ መብት ካውንስል ባቀረቡት አመታዊ ሪፖርት ሜንዴዝ የኢትዮጵያ መንግስት በአንዳርጋቸው ላይ ቶርቸር መፈጸሙን ፣ህክምና መከልከላቸውን፣ ንጽህናው ባልተጠበቀ ሁኔታና ከማንም ጋር እንዳይገናኙ በማድረግ እንዳሰራቸው የሚያሳይ አስተማማኝ ማስረጃ አለን››ብለዋል፡፡

በተባበሩት መንግስታት የህገ ወጥ እስር ተከታታይ ቡድን፣በአውሮፓ ፓርላማና በለንደን የአንዳርጋቸውን ቤተሰቦች እያማከረ በሚገኘው ሪፕራይቭ(የሰብዓዊ መብት ድርጅት ነው) ኢትዮጵያ አንዳርጋቸውን እንድትፈታ በተደጋጋሚ ጊዜያት ጥያቄ ቀርቦላታል፡፡

የሪፕራይቭ የሞት ቅጣት ተከራካሪ ቡድንን በምክትል ዳይሬክተርነት የሚመሩት ሃሪ ማክኩሎች ‹‹በኢትዮጵያ መንግስት አንዳርጋቸው በህገ ወጥ መንገድ በሌሉበት ተከሰው ሞት ተፈርዶባቸዋል፡፡ከታፈኑ በኋላም እንደ ቶርቸር ያሉ አስገራሚ የመብት ጥሰቶች ተፈጽሞባቸዋል፡፡ከታፈኑ ሁለት አመት ሞልቷቸው እንኳን የዴቪድ ካሜሩን ጣልቃ መግባትና የእንግሊዝ መሰረታዊ ጥያቄ ምንም ለውጥ አለማምጣቱን እየተመለከትን ነው፡፡እንግሊዝ ጠንካራ አቋም በመያዝ የተባበሩት መንግስታትና ሌሎች እንዳደረጉት አንዳርጋቸው ይፈቱ ዘንድ መጠየቅ ይኖርባታል››ብለዋል፡፡

ምንጭ ሪፕራይቭ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.