የወልቃይትን፣ የጠገዴን፣ የቃፍታ ሑመራን፣ የጠለምትን መሬት ለባለቤቱ የማስመለስ ጥረትና የሕዝበ ውሳኔ ስሕተት!

10446511_732158520254558_6644492532900070872_nሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው

አሁን ላይ ወያኔ “ወልቃይትን፣ ጠገዴን፣ ቃፍታ ሑመራን፣ ጠለምትን የትግራይ ነው!” እያለ የሚያወራው የበሬ ወለደ ሙግቱ እንኳን የሌላ የራሱ ጆሮም የማይገባለት፣ በሁሉም ዘንድ ተአማኒነት የሌለው የወሬ ድሪቶ መሆኑን፣ ምንም ዓይነት ወሬ ቢያወራ የዚያ አካባቢና የትግሬ ግንኙነት የቅርብ ጊዜ ከመሆኑ ጋርና መሬቱ የማን መሆኑ ሊስተባበሉ የማይችሉ ተጨባጭ መረጃዎች ያሉት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ይሄንን ጉንጭ አልፋ ክርክር ሊረታ ሊያሳምን እንደማይችል ተረድቶ ይሄንን ከንቱ ሙግቱን ትቶ ሌላ ፈሊጥ ይዟል፡፡

ይሄንን ስላቹህ በእነዚህ በተጠቀሱት ስፍራዎች ውስጥ “ትግሬ የሚባል የለም!” ማለቴ አይደለም፡፡ ነገሩ እንዲህ ነው፡- ዓለማቀፉ ገበያ ኢትዮጵያ የተጠቀሰውን አካባቢ በመጠቀም የቅባት እህልና የጥጥ ምርትን ለውጪ ገበያ ለማቅረብ ያላትን ከፍተኛ አቅም አውቆ በቀዳማዊ ዐፄ ኃይለሥላሴ ወቅት መንግሥት ወይም ባለሀብቶች አካባቢውን እንዲጠቀሙበት መገፋፋት ከመጀመሩና አገሬውም ባለሀብቶችም አካባቢውን ማልማት ከመጀመራቸው ጋር ተያይዞ የአካባቢው ቁጥቋጦ እየተመነጠረ በትራክተር (በአራሽ ተሸከርካሪ) ማረስ ይሄንንም ተከትሎ ሰፊ የሰው ኃይል ፍላጎት በአንገብጋቢ ደረጃ ማደግን ተከትሎ ሥራ ለመሥራት ሲሉ በርካታ ዜጎች ከትግራይና ከባሕረ መድር (ከኤርትራ) መግባት ጀመሩ፡፡

ይህ ለልማት የተፈለገው ቆላማ በረሀ ስፍራ በጣም ለኑሮ የማይመችና አደገኛ አውሬዎች የሞሉበት በመሆኑ እንዲህ ዓይነት ሰፋፊ የእርሻ ልማት መናኸሪያ ከመሆኑ በፊት ድንግል መሬት እንደሆነ ጠፍ ሆኖ ይኖር ነበር እንጅ የሚያርሰውም አልነበረም፡፡ በዚህም ምክንያት ሰው የሚኖረው በደጋውና ወይና ደጋው የአካባቢው ሥፍራዎች ላይ ብቻ ነበር፡፡ እነዚህ ኗሪዎች ደግሞ ሙሉ ለሙሉ አማሮች ናቸው፡፡ እነኝህ አማሮች የአገሬው ኗሪዎች ወደዚያ ቆላማ ሥፍራ ሊሔዱ የሚገደዱበት ብቸኛ አጋጣሚ ቢኖር ይህ የቅባት እህልና የጥጥ ምርት የዓለም አቀፍ ገበያ አስቀድሞ ሱዳን ውስጥ ገብቶ ስለነበር የእርሻ መሬት ፍለጋ ሱዳኖች እንደፍልፈል በየጊዜው ድንበር እያለፉ መሬት የመውሰድ፣ ድንበራቸውን ለማስፋት ጥረት ስለሚያደርጉ እነሱን አልፈው ከገቡበት ሥፍራ አስለቅቆ ድንበሩን ለማስከበር ብቻ ነበር አገሬው (አማራው) በረሀውን የሚረግጠው፡፡
በዚህ የዓለም አቀፍ ገበያ ፍላጎት ገፋፊነት ሰፋፊ ዘመናዊ እርሻ ከተጀመረም በኋላ ጠፍና ድንግል የነበረውን በረሀማ የቆላውን መሬት ደገኛው (አማራው) ተከፋፍሎ በእርሻ ወቅት እየሔደ እያረሰ ሰብሉን ሰብስቦ ሸጦ ወደ ቋሚ መኖሪያው ደጋው ይመለሳል እንጂ ኑሮውን በዚያ አልመሠረተም ነበር፡፡ ከሀገሬው የቁጥር አነስተኛነት የተነሣ ሊለማ የሚችለው ሰፊ መሬትና ገበያው የሚጠይቀው ምርት በሀገሬው አቅም እየቀረበ ካለው ጋር ፈጽሞ የማይመጣጠን ስለነበርና የእርሻ ልማቱ ሰፊ የሰው ኃይል ስላስፈለገው ሠራተኛ ከአጎራባች ክፍላተ ሀገራት በርካታ የሰው ኃይልን ለማስገባት ጥረት ይደረግ ጀመር፡፡

አቅም ያላቸው ባለሀብቶች እንዲያውም ሠራተኞችን ከትግራይና ከባሕረ ምድር (ከኤርትራ) በርካታ የትግሬ ተወላጅ ሠራተኞችን ያለ መጓጓዣ ክፍያ በነጻ እያመጡ ከፍ ያለ ደሞዝ በመክፈል ያሠሩ ስለነበር ትግሮቹ በዚህ መልክ እየገቡ ሠርተው ጠቀም ያለ ገንዘባቸውን ቋጥረው የመመለስ ዕድል አገኙ፡፡
ይህ ምርት የሚመረትበት ሀገር ለኑሮ በጣም የማይመችና አደገኛ ወባን ጨምሮ በሽታ የበዛበት አደገኛ በረሀ ስለሆነ እዛ ቦታ መጥቶ የሚሠራ ሠራተኛ ማግኘት እጅግ ፈታኝ ነበር፡፡ ከሠራተኛ እጥረት የተነሣ አብዛኛውን ጊዜ ሰብሉ ሰብሳቢ እያጣ አገሬው የተቻለውን ያህል ሰብስቦ ቀሪው እዛው ረግፎና ተበላሽቶ የሚቀርበት አጋጣሚ በርካታ ነበር፡፡ ይሄ በረሀ ለኑሮ የማይመች ከመሆኑ የተነሣ ሠራተኛ ብርቅ በሆነበት ሀገር ሠራተኛ ለማምጣት የማይሞከር ነገር አልነበረም፡፡ ሠራተኛን ከአጎራባች ክፍላተ ሀገራት ማምጣት ብቸኛው አማራጭ ስለነበርና የሚመጡት ሠራተኞች ትግሮች በመሆናቸው በዚያ ሠራተኛ ብርቅ በሆነበት ሀገር ሠራተኛን ተሻምቶ ለማሠራት ብዙ ዓይነት ማባበያና ጥቅማጥቅም በመስጠት ሥራ የማሠራት ፉክክር ቀላል አልነበረም፡፡ አገሬው ትግርኛን ሳይወድ በግድ ከነዚያው ከሠራተኞቹ ተምሮት ለመናገር የበቃው ሁኔታው በፈጠረበት አስገዳጅ ሁኔታ ነው፡፡
እነዚህ ከትግራይና ከባሕረ ምድር (ከኤርትራ) እየመጡ ሠርተው ጠቀም ያለ ገንዘባቸውን እየቋጠሩ ይሄዱ የነበሩ ሠራተኞች ከዓመት ዓመት እያደሩ ከአገሬውም ከሀገሩም ጋር መላመድ መግባባት ሲችሉ መመለሱ እየቀረ ኑሯቸውን እዚያው ለኑሮ በማይመቸውና አደገኛ እባብ ጊንጥና አደገኛ ወባ ሌሎች አውሬዎችም ሞልተው ባሉበት ለኑሮ የማይመች የእርሻ ሥፍራ ኑሯቸውን መመሥረት ጀመሩ እየተበራከቱም ሔዱ፡፡
ይህ ሁኔታ ትግሮቹ ተቀጥረው ይሠሩ የነበሩበትን ሁኔታ ቀይሮ ለጋራ የማምረትን (ተጠማኝነትን) ማለትም አገሬው መሬቱን ይሰጣቸዋል እነሱም አርሰው ዘርተው ጎልጉለው አጭደው ወቅተው ወይም ለቅመው (ጥጥ ከሆነ) መጨረሻ ላይ እንደ ውለታቸውና እንደሁኔታው የምርቱን ግማሽ ሲሦ ወይም ሩብ የመካፈልን ሁኔታ ፈጠረላቸው፡፡
እስከ ደርግ መምጣት ድረስ ሁኔታው በእንዲህ እንደቀጠለ “ደርግ የመሬት ላራሹ” አዋጅን ማወጁን ተከትሎ እነዚያ ተጠማኝ የነበሩ ትግሮች መሬቱን የመውረስ ዕድል አገኙ፡፡ እነሱም ብልጥ ናቸው ከሀገራቸው ዘመዶቻቸውን እየጎተቱ አዋጁ ያወረሳቸውን መሬት ይዘው ለመቅረት ማጠንከር ያዙ፡፡
እንዴትና መቸ የጋራ መግባባት እንደያዙ አይታወቅም በፊትም ጀምረው ለአካባቢው ሥፍራዎች የትግርኛ ሥያሜዎችን እያወጡ አገሬው ሳይቀር ያንን ሥያሜ እንዲጠቀምበት ማድረግ ችለው ነበር፡፡ ከጊዜ በኋላ በይፋ “ወደ ትግራይ እንጠቀልላለን!” ማለት ሲጀምሩ ነበር ሁሉ ነገር ለአገሬው ግልጽ ሆኖለት “አሃ! ለካስ ከድሮውም ይሄንን ዓለማ አንግበው ስለነበረ ኖሯል ከበፊቱም ትግርኛ ሥያሜ ከማውጣት ጀምሮ ለዚህ የሚረዳቸውን ነገሮች ያደርጉ የነበሩት! እንዴት ተቄልን! በነብሳችን ነው የተጫወቱብን!” የማይል ያገሬው ሰው አልነበረም፡፡
ይህ ሁሉ ከመሆኑ በፊት ግን ትግሮቹ የትግራይ ድንበር ተከዜ መሆኑን እነሱም ስደተኞች መሆናቸውን አውቀው በስደት መጥተው እንደሚኖሩ አውቀው አደብ ገዝተው ይኖሩ ነበር እንጅ ዛሬ የሚሉትን ነገር የሚናገር አንድም ሰው አልነበረም፡፡ በተለይ ወያኔ በረሀ መግባቱን ተከትሎ ነው የዚህን መሬት ጠቀሜታ በመረዳት ወያኔ ስልታዊ አቅድ አውጥቶ እዚያ በስደት የመጡ ወገኖቹን በኅቡእ ወይም በሥውር እያደራጀ የዘር ማጥፋትና ማጽዳት ወንጀሎችን ስልታዊ በሆነ መንገድና በግልጽም በመፈጸም መሬቱት የመውረስ ግብ አንግበው መንቀሳቀስ የጀመሩት፡፡
ትግሮቹ ምን ዓላማ እንዳላቸውና ምን ግብ ለመምታት ምን ይሠሩ እንደነበር ምንም የሚያውቁት ነገር ያልነበራቸው ያገሬው ሰዎች ትግሮቹ በሀገሩ አዳዲስ ትግርኛ የቦታ ሥያሜዎችን በማውጣት በቆላው አብሯቸው የሚኖረውን አማራ ባሕሉን ቋንቋውን ውጦ በመጠቅለል አካባቢውን ትግሬ ለማድረግ በማሰብ ሲንቀሳቀሱ በላዩ ላይ እየተፈጸመበት ያለውን ጦርነት ምንም ካለማወቁ የተነሣ አማራው በይሉኝታም በምንም በማያውቀው ጦርነት ተማርኮ የትግሬ ማንነት እስከመላበስ ደረሰ፡፡ ይህ ሸረኛ ሴራ ገብቷቸውም ባይሆን ለማንነታቸው ጠንካራ ትኩረት የሚሰጡትንና ለመለወጥ የማይፈቅዱትን አማሮችን ግን ስልታዊ በሆነ መንገድ እንዲጠፉ ይደረግ ነበር፡፡ ነገሩ ፈጦ ከመውጣቱና ከመታወቁ በፊት ይሄ ሁሉ ሲሆን አማራው ምንም የሚያውቀው ነገር አልነበረውም፡፡
ደጋውና ለኑሮ ተስማሚውን አማራው ብቻውን መያዙ ቆላውንና ለኑሮ እጅግ አስቸጋሪ የሆነውን ደግሞ ሁኔታዎች የፈጠሩላቸውን ምቹ አጋጣሚዎች ተከትሎ ባመዛኙ ትግሬ የሚኖርበት ሆኖ መገኘቱ በራሱ የሚናገረው አንድ እውነት አለ፡፡ የመሬቱ ባለቤት አማራው መሆኑን ይናገራል፡፡
ወያኔ ሥልጣን መጨበጡን ተከትሎ ብዙ ሲሠራበት የኖረውን የዚያም ወሬት ገጽታ ቀይሮ በማን አላብኝነት ወደትግራይ ከልሎታል፡፡ ይሄንን አንባገነናዊ ውሳኔ ተከትሎ ያገሬው ነዋሪ ወያኔ ይሄንን ካወጀበት ጊዜ ጀምሮ በመቃወም የተለያየ እንቅስቃሴ ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ በዚህ ወቅትም እንደምናየው የወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ ተወካዮቹን አሠማርቶ በሕጋዊ መንገድ መብቱ እንዲጠበቅለት ለማድረግ ጥረት እያደረገ ይገኛል፡፡
የሚያሳዝነው ነገር ግን ይሄንን ሕጋዊ መብቱን ሊያስጠብቅ የሚችል ሕግ ለይስሙላም እንኳን ቢሆን በሀገሪቱ አሁን ሥራ ላይ ባሉ ሕጎች ተጽፎ የሌለ መሆኑ ነው፡፡ ወያኔ ይሄ እንደሚመጣ አስቀድሞ አውቆት ነበርና ይሄንን መሬት ነጥቆ ዘርፎ ለማስቀረት የሚያስችለውን ለውንብድናው ለዘረፋው የሚመች የዘረፋ ሕግ ሥልጣን እንደተቆጣጠረ አርቅቆ ሥራ ላይ አውሏልና፡፡
እሱም ምንድን ነው:- ወያኔ በዘረጋው ቋንቋን የብሔረሰብ ወይም የጎሳ አሰፋፈርን መሠረት ባደረገው የራስ ገዝ (የፌደራል) አሥተዳደር ሥርዓት አንድ ብሔረሰብ ወይም ጎሳ ከአጎራባቹ ጋር የድንበር ውዝግብ ውስጥ ቢገባ “ውዝግብ የተነሣበት መሬት እዚያ ቦታ ላይ መኖር ከጀመሩ አምስት ዓመት የሆናቸውን ኗሪዎች ጨምሮ በአካባቢው በሚኖረው ሕዝብ ውሳኔ የሚወሰን ይሆናል!” ብሎ ለዘረፋው ለውንብድናው አመቻችቶ አስቀምጦታል፡፡
በዚህ ሕግ መሠረት ውዝግብ የተነሣበት መሬት የማን መሆኑን የሚያረጋግጡ የሚያስረዱ ታሪካዊ መረጃዎች ቦታ የላቸውም፡፡ አንድን ቦታ ለአምስት ዓመታት ያህል ተሰዶ ወይም ወሮ የያዘ ከሌላ አካባቢ የመጣ የሆነ ጎሳ ወይም ብሔረሰብ ቡድን ተሰዶ መምጣቱ ወይም ወሮ መያዙ እየታወቀም ቢሆን ተሰዶበት ያለበት ወይም ወሮ የያዘው ቡድን መሬት ባለቤት የሚሆንበት የውንብድና ሕግ ነው፡፡
አረና ትግራይን ጨምሮ የወልቃይትን፣ የጠገዴን፣ የቃፍታ ሑመራን፣ የጠለምትን ሕዝብ ጥያቄ ይደግፋሉ ተብለው የማይጠበቁ አካላት ይንን ጥያቄ የደገፉ መስለው ጥያቄያቸው ተቀባይነት አግኝቶ በጥያቄያቸው መሠረት ሕዝበ ውሳኔ እንዲደረግበት ድጋፍ የሚሰጡት የወልቃይት፣ የጠገዴ፣ የቃፍታ ሑመራ፣ የጠለምት ወሬት ያለአግባብ ወደትግራይ መከለሉን ስለሚቃወሙ ሳይሆን ወያኔ ከበረሀ ጀምሮ የዘር ማጥፋትና ማጽደት ወንጀል በመፈጸም በተለይ ሥልጣን ከያዘ በኋላ ወገኖቹን ከትግራይ እያጋዘ በማስፈር መሬቱን በእንግዶቹና በግፈኞቹ እንደሞላ እንዳስያዘ በሚገባ ስለሚታወቅ በሚደረገው ሕዝበ ውሳኔ ውጤት መሬቱ ወደትግራይ እንዲከለል የሚያስችል እንደሚሆን በመገንዘብ ነው “አዛኝ ቅቤ አንጓች!” የወልቃይትን፣ የጠገዴን፣ የቃፍታ ሑመራን፣ የጠለምትን ሕዝብ ጥያቄ የደገፉ መስለው የሚለፈልፉት፡፡
ሰሞኑን አረና ትግራይ የወልቃይትን፣ የጠገዴን፣ የቃፍታ ሑመራን፣ የጠለምትን መሬት በተመለከተ ይፋ ያደረገውን አቋሙን ይፋ ከማድረጉ በፊት የወልቃይት ጠገዴን መሬት በተመለከተ ከዓመታት በፊት ጀምሬ በጻፍኳቸው ጽሑፎች የአረና ትግራይና የትሕዴን አቋም ከወያኔም የባሰ መሆኑን የሚያስረዱ ንግግሮቻቸውን በመጥቀስ “አይ! አቋማችን እንዳልከው አይደለም!” የሚሉ ከሆነ ግን አቋማቸውን ይፋ በማድረግ ከፍትሕና ከግፍ ሰለባዎች ጎን በመቆም እውነተኛ የፍትሕ፣ የዲሞክራሲ (የመስፍነ ሕዝብ)፣ የእኩልት፣ የነጻነት፣ የሰብአዊ መብት ታጋይነታቸውን እንዲያረጋግጡ ደጋግሜ መጠየቄ ይታወሳል፡፡
አምና ቅሊንጦ እስር ቤት በነበርኩበት ወቅት ይሄንን የአረና ትግራይን አቋም የአረና ትግራይ አመራር ከሆነው አብርሃ ደስታ ጋር የወልቃይትን፣ የጠገዴን፣ የቃፍታ ሑመራን፣ የጠለምትን መሬት በተመለከተ በትግራይ ልኂቃን ዘንድ “የትግራይ ሕዝብ አቋም ነው!” ስለ መባሉና ወደ ትግራይ ስለመከለሉ አግባብነት ጉዳይ ያለውን አቋም እንዲገልጽልኝ ጠይቄው ባደረግነው ውይይትና ክርክር ነው አውቄው የነበረው፡፡
ከብርሃ ደስታ ጋር ስንነጋገር ያለኝ የነበረው፡- “አይ ወያኔ ከወደቀ እኮ ቋንቋንና ዘርን መሠረት ያደረገ የፌደራል (የራስ ገዝ) አሥተዳደር አስፈላጊ እንዳልሆነ የጋራ መግባባት ስላለ ይሄ ያንተ ይሄ የኔ የሚባል የብሔር ክልል ስለማይኖር ችግሩ በዚህ የሚፈታ ነው የሚመስለኝ” አለኝ፡፡ እኔም “እኮ! እነዚያ በሸፍጥ በግፍ በሴራ እንዲጠፉ እንዲፈናቀሉ እንዲሰደዱ የተደረጉ ወገኖች እንደተፈናቀሉ እንደተሰደዱ?” ስል ጠየኩት፡፡ እሱም “አይ! እነሱማ የእርሻ መሬታቸውን ማግኘት ይኖርባቸዋ!” ሲለኝ “የእርሻ መሬታቸው እማ በሠፋሪዎች ተወስዷል እኮ!” አልኩት ከዛ እሱም “አይ እኔ ግን ይሄ የአማራ ነው ይሄ የትግሬ ነው ይሄ የምንትስ ነው የሚባል ነገር መቅረቱ ነው መልካምና መፍትሔ የሚመስለኝ፡፡ ቋንቋንና ዘርን መሠረት ያደረገ አሥተዳደርን እየተቃወምን ይሄ ያማራ ነው፣ ይሄ የትግሬ ነው፣ ትግሬ ይውጣ! ከተባለ ለዚህች ሀገር ችግር መፍትሔ መስጠት የሚቻል አይመስለኝም!” አለኝ፡፡
እኔም “አይ እኔ እኮ ሰፋሪዎቹ ወደ ሀገራቸው ይመለሱ አላልኩም፡፡ እኔ ያልኩት እነዚህ ሰፋሪዎች የያዙት መሬት ወያኔ አገሬውን አሳዶ አፈናቅሎ አጥፍቶ በፈጸመው ግፍ የተወረሰ መሬት ነው እንዲሰፍሩበት የተደረገ መሬት በመሆኑ መሬቱን እንዲፈናቀሉ እንዲሰደዱ ለተደረጉት ለባለቤቶቹ ለቀው ወደ ሀገራቸው ሳይመለሱ ባለቤት የሌለው መሬት ካለ እዚያ ላይ እንዲሠፍሩ መደረግ ነው የሚኖርበት፡፡ ምክንያቱም የዚያን ግፍ የተፈጸመበትን ሕዝብ የፍትሕ ጥያቄና ጩኸት ሳንሰማና ትክክለኛና ፍትሐዊ ምላሽ ሳንሰጥ ምንም ዓይነት ፍትሐዊና መስፍነ ሕዝባዊ (ዲሞክርሲያዊ) ሥርዓት ልንመሠርት አንችልምና ነው፡፡ ይሄ ያማራ ነው! መባሉ እንዳልከው ሌላ ትርጉም የሚያሰጠው ከሆነ ይሄ ያማራ መሬት ነው ወደ አማራ መመለስ አለበት! ማለቱን ትተን ይሄ መሬት የጎንደር ነው ወደ ጎንደር መመለስ አለበት ወደሚለው ልንቀይረው እንችላለን ችግር የለውም፡፡ ይሄም የማይመቸው ወገን ካለ ግን ችግር መኖሩን ነው የሚያሳየው፡፡ የጎንደር መባሉ የማይመቸውና የጎንደርን መሬት ለጎንደር መመለስ የሚከብደው ኢፍትሐዊ በሆነ መንገድ የትግራይ እንደተባለ ይቀጥል! የሚል ካለ የፍትሕንና የሰብአዊ መብተትን ጥያቄ ረግጠን ከመደፍለቃችን በተጨማሪ ቅድም የኮነንከውን ዘርን መሠረት ያደረገ የራስ ገዝ (የፌዴራል) አሥተዳደር ሙጥኝ ማለት የሚሆነው ይሄኔ ነው” አልኩት፡፡
ከዚያም አብርሃ ደስታ “አይ ከዚህ ሁሉ እኮ” አለና አረና ትግራይ በቅርቡ ይፋ ያደረገው “ሕዝበ ውሳኔ” ማድረግ ነው ጥሩው መፍትሔ ሲል ተናገረ፡፡ ነገር ግን “ወያኔ የወልቃይትን፣ የጠገዴን፣ የቃፍታ ሑመራን፣ የጠለምትን ሕዝብ ስልታዊ በሆነ አረመኔያዊ መንገድ ከሞላ ጎደል አጥፍቶ፣ አፈናቅሎ፣ አሳዶ ሀገሩን በእንግዶች የሞላ መሆኑ በሚገባ የታወቀ በሆነበት ሁኔታ ሕዝበ ውሳኔ እንዴት ነው ፍትሐዊና ትክክለኛ መፍትሔ ነው ማለት የምንችለው?” የሚል ጥያቄ ካነሣሁበት በኋላ በወቅቱ ትክክል መሆኔን ገልጾልኝ ነበር ውይይት ክርክራችን የተቋጨው፡፡ እናም ያኔ ነበር ይሄንን የአረናን ብልጣብልጥ አቋም ለመረዳት ችየ የነበረው፡፡
ስለዚህ ትክክለኛና ፍትሐዊ የሆነ ሕግ በሌለበትና የውንብድና ሕግ ሥራ ላይ በዋለበት ሀገር “በሕጋዊ መንገድ ሔደን መብታችንን እናስጠብቃለን!” ማለት ፈጽሞ የማይቻል ሊታሰብም የማይገባ ነገር ነውና እየተደረገ ያለው እንቅስቃሴ ወያኔን የሚጠቅምና ሕዝበ ውሳኔ ቢደረግም የሚገኘውን ወያኔን ተጠቃሚ የሚያደርግ አግባብነትና ተቀባይነት የሌለው ውጤት ተከትሎ የዚህን የመሬት ጉዳይ ይባስ የተወሳሰበ ችግር ላይ የሚጥለው በመሆኑ ወያኔ መሬቱን ኢፍትሐዊና ወንጀል በተሞላበት መንገድ እንደያዘው መቆየቱ በኋላ ለሚወሰደው ሕጋዊና ፍትሐዊ እርምጃ ተስማሚና ጠቃሚ በመሆኑ ወያኔን ተጠቃሚ የሚያደርገው “የሕዝበ ውሳኔ ይደረግልን!” ሕጋዊ ጥያቄ ወይም እንቅስቃሴ ቆሞ ወይም ተቋርጦ ለዝርፊያ ለመሬት ንጥቂያ የተመቸ “ሕግ” አውጥቶ “ሕጋዊነትን” የተላበሰ ዝርፊ እየፈጸመ ያለውን የወንበዴ ቡድን በሚገባው ቋንቋና በተተወልህ መብትሕን የማስከበሪያ ብቸኛ መንገድ ብቻ በማናገር መብትሕን ታስከብር ዘንድ ጥሪዬን ማስተላለፍ እወዳለሁ!!
እያደረከው ያለው ሰላማዊና ሕጋዊ እንቅስቃሴህ “እነማን ናቸው ቅሬታና ጥያቄ ቅያሜ ያላቸው? እነማን ናቸው ቀን የሚጠብቁልን?” ለሚለው ለወያኔ ጥያቄ ጥሩ መረጃና መልስ እየሰጠ ልጆችህን አባቶችህን ለማስበላት ጥሩ አጋጣሚ ፈጠረለት እንጅ ወያኔ እሽ ብሎ ሕዝበ ውሳኔው ቢደረግም እንኳ አንዳችም ነገር ላንተ የሚፈይደው ቁምነገር ስለሌለው “እሾህን በሾህ” ነውና የልብህን በልብህ እያደረክ የተቀናጀ ኅቡእ የትግል ስልት ቀይሰህ ሳትታወቅ ባካባቢህ ያለውን የወያኔን ሥራ አስፈጻሚ እያነክ መጣልን ጨምሮ ብረት አንሥተህ በደምህ መብትሕን የማስከበር የትግል አማራጭ ብትጠቀም ነው ውጤታማ የምትሆነው እንጅ ወያኔን ካልሆነ በስተቀር አንተን የማይጠቅም ጥያቄን እያነሣህ “ማን ነው ይሄንን ያለው?” እየተባልክ እየተለቀምክ ማለቅህ ነፍስህን በከንቱ ማሳለፍህ አይደለም!!
ሞትህ ካልቀረ ሁለትና ከሁለት በላይ ወያኔን ይዘህ በመውደቅ በነፍስህ ቁምነገር ሥራባት! ወያኔ አቅም ሲያንሰው አማራጭ ሲያጣ ሊያስመስል ለጊዜው ካልሆነ በስተቀር ከወያኔ እጅ ፍትሐዊና ሰላማዊ በሆነ መንገድ መፍትሔ አገኛለሁ ማለት ከዝንብ ማር እንደመጠበቅ ፍጹም ዘበት ነውና የዝርፊያና የውንብድና እንጅ የዚህ ተፈጥሮውም ጨርሶ የላቸውምና ጊዜህንና የወገንህን ነፍስ በከንቱ ሳታባክን መብትህን ሊያስከብርልህ ለሚችለው ትግል ባጭር ታጥቀህ ተነሥ!!!
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!! ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!!!
ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው
amsalugkidan@gmail.com

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.