የ2008 ዓ/ም የየካቲት 12 የሰማእታት ቀን በዓለም ዙሪያ በ16 ከተሞች ተዘከረ

ዓለም አቀፍ ሕብረት ለፍትሕ – የኢትዮጵያ ጉዳይ

ጋዜጣዊ መግለጫ

የ2008 ዓ/ም የየካቲት 12 የሰማእታት ቀን በዓለም ዙሪያ በ16 ከተሞች ተዘከረ፤

ለነጻነታችን ለተሰዉትና ለታገሉት የኢትዮጵያ አርበኞች ክብርና ምሥጋና ይድረስልን!

የፋሺሽት ወታደሮችና የሰቀሏቸው የኢትዮጵያ አርበኞች

globalogoከልዩ ልዩ አካባቢዎች በደረሱን ዜናዎች መሠረት፤ ባለፉት ጥቂት ዓመታት እንደ ተገለጸው ሁሉ፤ የ2008 ዓ/ም የየካቲት 12 የሰማእታት ቀን በዓለም ዙሪያ፤ ማለት በኢትዮጵያ (በአዲስ አበባ፤ በደብረ ታቦር፤ በደብረ ማርቆስና በባሕር ዳር)፤ በአሜሪካ (በዋሺንግተን ዲ.ሲ፤ በኒው ዮርክ፤ በዳላስ፤ በአትላንታ፤ በሎዛንጀለስ፤ በዴንቨር/አውሮራ፤ በሲልቨር ስፕሪንግ፤ በታምፓና በማያሚ፤) በካናዳ (በቫንኩቨርና በቶሮንቶ)፤ በዩናይትድ አረብ ኤሚቴትስ (በዱባይ)፤ በጸሎት፤ በስብሰባ/በጉባኤ፤ እና/ወይም በሰላማዊ ሰልፍ ተዘክሯል።

ዓለም አቀፍ ሕብረት ለፍትሕ – የኢትዮጵያ ጉዳይ ከላይ በተጠቀሱት ከተሞች የሚገኙ ኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች ክብረ በዓሉን በማዘጋጀት ለፈጸሙት የተከበረ አገልግሎት ጥልቅ ምሥጋናውን ያቀርባል። እንደሚታወቀው፤ ድርጅታችን የሚታገልባቸው ዓላማዎች፤ (ሀ) ኢጣልያ፤ ኢትዮጵያ ላይ ለፈጸመችው የጦር ወንጀል ተገቢውን ካሣ እንድትከፍል፤ (ለ) ቫቲካን፤ ከፋሺሽቶች ጋር ተባብራ ስለ ነበር የኢትዮጵያን ሕዝብ ይቅርታ እንድትጠይቅ፤ (ሐ) በኢጣልያና በቫቲካን መንግሥቶች ይዞታዎች የሚገኙት የኢትዮጵያ ንብረቶች እንዲመለሱ፤ (መ) የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በኢትዮጵያ ላይ የተፈጸመውን የጦር ወንጀል እንዲመዘግብና፤ (ሠ) አፊሌ በምትባል የኢጣልያ ከተማ ለጦር ወንጀለኛው ለሮዶልፎ ግራዚያኒ፤ የቫቲካን ተወካይ በተገኙበት፤ የተመረቀው መታሰቢያ እንዲወገድ ነው።

 

yekatit

 

ሰለ ዓላማዎቻችን አንድ ግልጽ መደረግ ያለበት ነጥብ፤ ለሐገራችን የሚፈለገው ካሣ ለኢትዮጵያ ሕዝብ በቀጥታ በሚጠቅም ተግባር እንዲሆን ይጠበቃል። ይኸውም፤ ለምሳሌ፤ የወደሙትን 2000 ቤተ ክርስቲያኖች በመሥራት፤ እንዲሁም ለኢትዮጵያ ሕዝብ ጥቅም በሚውሉ የልማት ተግባሮች (ፕሮጀክቶች)፤ ወዘተ፤ ይከናወናል ማለት ነው።

የቫቲካን ካሕን የፋሺሽቱን ጦር ሲባርኩ

ክተከናወኑት ተጨባጭ ጉዳዮች አንደኛው፤ በድርጅቱ ድረ ገጽ በwww.globalallianceforethiopia.org ላይ፤ ቫቲካን ይቅርታ እንድትጠይቅ የሚያመለክተው አቤቱታ ከ30 ሐገሮች በላይ በሚኖሩ ሰዎች፤ በኢጣልያ ዜጎች ጭምር፤ በ4839 ሰዎች ተፈርሟል። አንድ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ካርዲናልም ቫቲካን የኢትዮጵያን ሕዝብ ይቅርታ መጠየቅ እንዳለባት የሚያበረታታ ሐሳባቸውን በቅርቡ ገልጸዋል። ስለ የሰሞኑ የኢጣልያ ፕሬዚዳንት የኢትዮጵያ ጉብኝትና የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ የቫቲካን ጉብኝት ድርጅታችን ያሰራጫቸውን መግለጫዎች በድረገጻችን ላይ መመልከት ይቻላል። በተጨማሪም፤ በሕብረታችን ዓላማዎች ላይ የሚያተኩር አንድ ኮሚቲ በኢትዮጵያ እየተቋቋመ ነው።

የድርጅቱ አቤቱታና በኢጣልያ የሚገኙ የኢትዮጵያ ጉዳይ ደጋፊዎች ባስገኙት ተጽእኖ የግራዚያኒ መታሰቢያ ተዘግቷል። ለሥራ ማስኬጃው የተመደበው ገንዘብም ተቋርጧል። እንዲሁም በአፌሌ ከተማ ከንቲባውም ላይ የቀረበው ክስ ፍርድ ቤቱ የፊታችን ሐምሌ ውሳኔ ሊሰጥበት ቀጠሮ ተይዟል።

ለኢትዮጵያ የሚያስፈልገውን ዓላማ ለማሳካት እንዴት መርዳት ይቻላል?

1ኛ/ አውሮፓ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች ለአውሮፓ ምክር ቤት፤ ለኢጣልያ መንግሥትና ለቫቲካን  የጻፍናቸው አቤቱታዎች ተገቢውን ምላሽ እንዲያገኙ፤ ጠንካራ ግብረ ኃይል ማቋቋምና መደገፍ ያስፈልጋል፤

2ኛ/ የድርጅቱ ድረ ገጽ (www.globalallianceforethiopia.org) ላይ የሚገኘውን ቫቲካን የኢትዮጵያን ሕዝብ ይቅርታ እንድትጠይቅ የሚያመለክተውን አቤቱታ መፈረም፤

3ኛ/ በየዓመቱ በሚዘከረው የየካቲት 12 ክብረ በዓል ዝግጅት መሳተፍ፤

4ኛ/ ወጣቱ ትውልድ በኢትዮጵያ ላይ ስለ ተፈጸመው የጦር ወንጀልና ስለሚያስፈልገው ፍትሕ በቂ ግንዛቤ እንዲያገኝ ማድረግ፤

5ኛ/ የመገናኛ ብዙኃን፤ የመንፈሳዊ ድርጅቶች፤ የትምሕርት ተቋማት፤ የማሕበራዊ አካላት፤ ወዘተ፤ ስለ ጉዳዩ ግንዛቤ እንዲሰርጽና ተገቢው ድጋፍና እርምጃ እንዲከሰት ማድረግ ይጠቅማል።

ቸሩ የኢትዮጵያ አምላክ ለሐገራችን የሚያስፈልገውን ፍትሕ እንድናስገኝ ያበርታን።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.