ጂቡቲ ወደብ የደረሱ እህል የጫኑ መርከቦች መንቀሳቀስ አልቻሉም

ወደብ

(ሳተናው) አስቸኳይ የምግብ እርዳታ ለሚፈልጉ ኢትዮጵያዊያን በፍጥነት መድረስ ይገባው የነበረ በአስር መርከቦች የተጫነ 450.000 ሜትሪክ ቶን ስንዴ በጂቡቲ ወደብ አገልግሎቱ ቀልጣፋ ባለመሆኑ ምክንያት ወደ ኢትዮጵያ ሳይሻገር መቆየቱን ብሎምበርግ ዘግቧል፡፡

ስንዴና የበቆሎ ዘርን የጫኑ መርከቦች ከተለያዩ የአለም ክፍሎች ወደ ጂቡቲ ወደብ ቢደርሱም በወደቡ የማስተናገድ አቅም አነስተኝነት የተነሳ መርከቦቹ ረዘም ላሉ ወራቶች እንዲቆሙ መገደዳቸው የጠቀሰው የመረጃው ምንጭ 50.000 ቶን ስንዴ የጫነ መርከብ በቅርቡ ጂቡቲ ወደብ መድረሱንም አትቷል፡፡

‹‹የሴቭ ዘ ችልድረን የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ጆን ግርሃም ‹‹በእህል የተሞሉ ብዛት ያላቸው መርከቦች ጂቡቲ ወደብ ደርሰዋል፡፡ነገር ግን የደረሱት መርከቦችንም በበቂ ሁኔታ ማስተናገድ ባለመቻሉም መዘግየቶች ተፈጥረዋል››ይላሉ፡፡

በሰብ ሰሃራን አካባቢ  ከሚገኙ አገራት ስንዴን በብዛት  በመሸመት የምትታወቀው ኢትዮጵያ ባጋጠማት ድርቅ የተነሳ አለምአቀፉን ማህበረሰብ የአስቸኳይ የምግብ እርዳታ እስከመጠየቅ ደርሳለች የሚለው ብሉምበርግ አገሪቱ ወደብ አልባ በመሆኗ የምታገኘውን ወይም የምትሸምተውን ምግብ በምትፈልገው የጊዜ ፍጥነት ለማግኘት አልቻለችም ብሏል ፡፡

እንደ ሴቭ ዘ ችልድረን ከሆነም በጂቡቲ ወደብ የሚገኘውን እህል ወደኢትዮጵያ ለማስገባት 40 ቀናትን ይወስዳል፡፡በአጠቃላይ እህሉን ገዝቶ በጂቡቲ ወደብ ወደ ኢትዮጵያ በማድረስ ለማከፋፈል 120 የስራ ቀናቶች ይቃጠላሉ፡፡፡

ከአለማችን ደሃ አገራት ዝርዝር ውስጥ በምትገኘው ኢትዮጵያ ካለፈው የነሐሴ ወር ጀምሮ 10 ሚልዩን ሰዎች አስቸኳይ የምግብ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው የተባበሩት መንግስታት አስታውቋል፡፡በዚህ ቁጥር ላይ በመንግስት የሴፍቲ ኔት ፕሮግራም እየተረዱ የሚገኙ 7.9 ሚልዩን ሰዎችን ስንጨምር አሃዙ አስደንጋጭ ይሆናል፡፡በሴቭ ዘ ችልድረን እምነትም በያዝነው አመት ብቻ በጣም የተጎዱ 450.000 ህጻናት የአልሚ ምግብ እርዳታ የሚፈልጉ ይሆናሉ፡፡

በጥቅምት ወር 1 ሚልዩን ቶን ስንዴ መግዛቷ የሚነገርላት ኢትዮጵያ በአሜሪካው የእርሻ ቢሮ ግምት መሰረትም በቅርቡ የተሸመተ 500.000 ቶን ስንዴም እስከቀጣዩ አርብ ወደ ወደቡ ይደርሳል ፡፡

‹‹በእርግጥ ወደቡ በጣም ተጨናንቋል፡፡ነገር ግን እንደ ስንዴና ምርጥ ዘር ያሉት የመጓጓዝ ቅድሚያ ይሰጣቸዋል››የሚሉት የአደጋ መከላከልና ዝግጁነት ኤጀንሲ ኃላፊ ምትኩ ካሳ ናቸው፡፡

ከጂቡቲ ወደብ የደረሱ እህሎችን በቀን ወደመኪና ማሸጋገር የሚቻለውም 3.000 ቶን ያህሉን ስለመሆኑ ተነግሯል፡፡

የወደቡን አገልግሎት አሰጣጥና የአቅም ውስንነት ለማሳየት ያህልም እንደ ምሳሌነት የካርሊ ማኔክስ መርከብ 54.250 ቶን ስንዴ ጭና የካቲት 14 ጂቡቲ ወደብ የደረሰች ቢሆንም እስካሁን ድረስ ጭነቷ አልተራገፈላትም፡፡በእርግጥ ከዚህች መርከብ ቀደም ብላ የካቲት 11 የደረሰች መርከብም በተመሳሳይ መልኩ ከነጭነቷ ትገኛለች፡፡

ተጨማሪ ግዢዎች ወይም በእርዳታ መልክ የሚገኙ ምግቦችን ወደጂቡቲ ወደብ መውሰድም ለበለጠ መጨናነቅ እንደሚዳርግ እየተነገረ ነው፡፡

ለኢትዮጵያ ከጂቡቲ ወደብ ይልቅ የአሰብ ወደብ ከጂኦግራፊ አንጻር ከፍተኛ ቅርበትና በአንድ ግዜ በዛ ያሉ መርከቦችን ማስተናገድ የሚችልበት አቅም ቢኖረውም ገዢው ፓርቲ ከኤርትራው ሻዕቢያ ጋር ግጭት ውስጥ በመግባቱ አሰብን መጠቀም አልተቻለም፡፡

ምንጭ ብሉምበርግ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.