ሰብለ-ወንጌል ዘአማራ ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት፣ የአሜሪካ ድምጽ ራዲዮና ወልቃይት ጠገዴ

welkeit - satenaw 3አንዳንድ ማህበራዊ ሚዲያው ላይ የወያኔ ወኪል ነን የሚሉ ግለሰቦች የአሜሪካ ድምጽ ራዲዮ ኢትዮጵያን እያተራመሰ ነውና ሃይ ባይ ያስፈልገዋ፥ል ስለዚህ ፒቲሽን እንፈርምና ለአሜሪካ መንግስት እናስገባ ይላሉ። እነሱ የሚወግኑለት መንግስት ዲሞክራሲን ባፍጢሙ የደፋና የመናገርም ሆነ ሌሎች ሰብዓዊ መብቶችና ነጻነቶችን የማያከብር ነው። የእነሱ እይታም ከሚወግኑት መንግስት የዘለለ ስላልሆነ የመናገር ነጻነትና ሰብዓዊ መብት ምን ማለት እንደሆነ በኢ-ሊበራል መንግስት እያታ ነው የሚያዩት። አሜሪካ ሊበራል ዴሞክርሲያው ሃገር ናት። ማህበረሰቡም ዴሞክራሲያዊ ህዝብ ነው። የመናገር ነጻነትን እዚህ ደረጃ ላይ ለማድረስ ብዙ ተለፍቶበታል። አውሮፓ ውስጥ ያሉ ሃገራት ለመናገር ነጻነት ከሚሰጡት ከለላና ጥበቃ በላይ፣ የአውሮፓ የሰብዓዊ መብት ፍርድ ቤት ለመናገር ነጻነት ከሚሰጠው ቦታ በላይ አሜሪካን ውስጥ ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት ትልቅ ቦታ ይሰጠዋል። ያለመናገር ነጻነት ዴሞክራሲ በሁለት እግሩ ሊቆም አይችልም፥ሊያብብም አይችልም ብለው ትልቅ ትኩረት ይሰጣሉ። ለምሳሌ የአውሮፓ የሰብዓዊ መብት ፍርድ ቤት ለመናገር ነጻነት ያለውን ቦታ ሲያሳይ እንዲህ ሲል ይገልጸዋል። Freedom of expression constitutes one of the essential foundations of [ a democratic] society, one of the basic conditions for its progress and for the development of every man. የመናገር ነጻነት የዴሞክራሲያዊ ማህበረሰብ ወሳኝ መሰረት ነው። የመናገር ነጻነት ለሰው ልጅ እድገትና መጎልበት አይነተኛ ሚና የሚጫወት መብት ነው ብሎ ፍርድ ቤቱ ሁሌም የመናገር ነጻነትን ጉዳይ የሚመለከት ውሳኔ ባሳለፈ ቁጠር ይደጋግመዋል። ፍርድ ቤቱ ሌላ ሁሌም እንደመርህ ወስዶ የሚደጋግመው አባባል ደግሞis freedom of expression is applicable not only to “information” or “ideas” that are favourably received or regarded as inoffensive or as a matter of indifference, but also to those that offend, shock or disturb the State or any sector of the population. የመናገር ነጻነት ምንም አይነት ትንኮሳ ለሌለባቸው፣ ገለልተኛ ለሆኑ ወይም መልካም (አውንታዊ) ለሆኑ ሃሳቦች (መረጃወች) ብቻ ሳይሆን የሚያገለግል መንግስትን ወይም የተወሰነ የማህበረሰብ ክፍልን ሊያናድዱ የሚችሉ፣ ሊበጠብጡ የሚችሉ ወይምሊተነኩሱ የሚችሉ ሃሳቦችም እንደሃሳብ ተቆጥረው ከለላ ይሰጣቸዋል ይላል። ነጻ የሃሳብ መንሸራሸር ሲኖር ነውና እውነት የሚወጣ፥ ባልታፈነ ማህበረሰብ ውስጥ ነውና ዴሞክራሲ ተዘርቶ የሚበቅል እንዲሁም የሰው ልጅ ተፈጥሯቂ የሆነ ራስን የመግለጽ መብት ስላለው የመናገር ነጻነት ሊከበር ይገባል ይላል። ወደ አሜሪካ የሲቭል ሊበሪቲስ (Civil Liberties) ድንጋጌዎች ስንመጣ ደግሞ የህገ መንግስቱ የመጀመሪያው ማሻሻያ የመናገር ነጻነትን የሚከለክል ምንም አይነት ህግ መውጣት እንደሌለበት ያመላክታል። ያም ሁኖ ግን የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ባዳበራቸው ኬዞች (Case Law) አንዳንድ ሃገርንና የሌላን መብት የሚጋፉ ድርጊቶች ሲከሰቱ የመናገር ነጻነት ሊገደብ ይችላል ይላል። ነገር ግን ይህም ሁኖ እንደወያኔ በፈለገው መንገድ ሳይሆን ህግና ስርዓትን ተከትሎ የመናገር ነጻነትን ማፈን የሚያመጣው ተጽዕኖና አንድ ሃሳብ ቢነገር (ለሶስተኛ ወገን፣ ለሚድያ ወይም ለህዝብ) ቢተላለፍ ምን ሊያመጣ ይችላል የሚለው ነገር ተመዝኖ ነው። በብዙ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ውሳኔዎች እንደተመለከተው ለመናገር ነጻነት የሚሰጠው ከለላ አሜሪካ ውስጥ እጅግ ከፍተኛ ና ከአውሮፓም የበለጠ ነው። ለምሳሌ በ Pentagon Paper case ላይ የዋሺንግተን ፖስትና የኒዮርክ ታይምስ ጋዜጣና መጽሄት በመንግስት ጥብቅ ሚስጥር ተብሎ የተፈረጀን መረጃ ያገኛሉ። መረጃው ስለቬትናም ጦርነት ነው። ሚድያዎች ሊያትሙት ሲሉ የፕሬዚዳንት ኒክሰን መንግስት የፍርድ ቤት እግድ ትዛዝ አወጣ። መረጃው ከታተመ የሃገሪቱን ጥቅም ይጎዳል፣ ወታደሮቻችን እንዲሞቱ ያደርጋል፣ በዲፕሎማሲ ረገድ እንድንሸነፍ ያደርጋል ለጠላቶቻቸን ሃይል ይሆንና ተጋላጭነታችንን ይጨምራል ወዘተ የሚሉ የሃገራዊ ደህንነት ጉዳዮችን እንደመከላከያ አነሳ። ነገር ግን የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ የመንግስትን አቋም ሳይሆን የደገፈው የሚድያዎችን አቋም ነው። ከ7000 በላይ ገጽ የጥናት ወረቀቶች ያውም ጥብቅ ሚስጥር ተብለው የተፈረጁ መረጃዎች ለህዝብ ይፋ እንዲሆን ፈረደ። በዚህ ውሳኔ የተነሳ ኒክሰን impeachment ሳይመጣ ብሎ ስልጣኑን ለቀቀ። የቬትናም ጦርነትም ቆመ። ብዙ ማዕበል ያስነሳ ውሳኔ ነው።
========================================
ይህን ሁሉ ያልኩበት ምክንያት የወያኔ ጋሻ አጃግሬዎች ነጻነትን ወያኔ በሰጣቸው መነጸር ወይም እንዲያዩ በፈቀደላቸው ቁንጽል እይታ እየተመለከቱ የአሜሪካ ህዝብ የታክስ ገንዘብ ኢትዮጵያን አደጋ ላይ እየጣላት ነውና የአሜሪካ ድምጽ ራዲዩ አደብ ሊገዛ ይገባል ሲሉ ግዜ ነው። በመጀመሪያ ረገድ የአሜሪካ ድምጽ ራዲዩ ስለወልቃይት ህዝብ ሲዘግብ የታፈነ ብሶትን ነው ያወጣ። የራዲዩ ጣብያው ለዘመናት ሲካሄድ የቆየን ግዙፍ የሆነ የሰብዓዊ መብት ጥሰትን (Systemic Human Rights Violation) ለማስቆምና ለአለም ለማጋለጥ ነው የተነሳ። ያንንም ጉዳይ እያደረገ ይገኛል። ራዲዮ ጣብያው የአሜሪካ ህግና ህገ መንግስት በሰጠው ነጻነት እንጂ የወያኔ መንግስት በቀደደለት ቦይ አይደለም የሚፈስ። የራዲዩ ጣብያው ሚዛናዊ የሆነ አዘጋገብን ለመከተል ብዙ ግዜ ጥሯል። ብዙ የወያኔ ሃላፊዎች ስልክ ይደወልላቸውና በሚንተባተብ አንደበታቸው ይናገራሉ፥ ከዛም ደዋዩ ከአሜሪካ ድምጽ ራዲዮ መሆኑን ሲነግራቸው ስልካቸውን ይዘጋሉ ወይም አያነሱም። የራዲዮ ጣብያው ለእነ “ዶክተር” ገላውዲዎስ አርያ አይነት ውሸታም ዶክተሮች እንኳ ቦታ ሰጥቷቸው ጉዳዩን ጠይቋቸዋል። ምንም እንኳ ከአካዳሚክ ቁመናቸው ጋር የማይሄድ ውሸት ቢዋሹም ቅሉ (ስለውሸታምነታቸው ነው ዶክተር የሚለውን ማዕረግ በትምህርተ-ጥቅስ ውስጥ ያስቀመጥኩት)። የራዲዮ ጣብያው ከውሸታሙ ዶክተር በፊትም ዶክተር ማሃሪ ረዳኢንና ሌሎች ሙህራንን አቅርቦ ስለጉዳዩ ጠይቋቸዋል። መሃሪ ረዳይ ትግሬ ስለሆነ ብቻ በወያኔ መንግስት የራሱን ጥቅም ለማስጠበቅ ያወጣው ህግ ተፈጻሚ መሆን አለበት አለን። በዛው ላይ አሁንም ጉዳዩን መጀምሪያ የክልል ምክርቤቶች ሊያዩት ይገባል ከዛ ነው ወደ ፌደሬሽን ምክር ቤት መምጣት ያለበት ብሎ መሰረታዊ የህግ መርሆችን ሳይናገር አለፈ። ለምሳሌ ከታች ተቋማት ላይ ያሉ የመፍትሄ አማራጮችን ሳይጨርሱ ወደላይ ወዳለ የፍትህ አካል መሄድ አይቻልም የሚል መርህ አለ (Exhaustion of available local remedies)። ዶክተር ማሃሪ ይሄንን ሲጠቅሱ የዘነጉት (ሆነ ብለው የዘለሉት ነገር አለ)። ከስር ካለው ውሳኔ ሰጪ አካል መፍትሄ ይገኛል ወይ? (Available local remedies) ጉዳዩ ያለበቂ ምክንያት ረጂም ግዜ ይወስዳል ወይ (prolongation of the case)? የመሳካትና ፍትህን የማምጣቱ ጉዳይ ምን ያህል እርግጠኛ ነው (reasonable prospect of justice)? ከነዚህ አንዱ የሚኖር ከሆነ እንኳ ከስር ያለን የውሳኔ ሰጪ አካል ውሳኔ ሳይጠብቁ ወደላይኛው አካል መሄድ የሚቻልበትን መንገድ አላስቀመጡም።
እንዲያው ለማለት ያህል አልኩኝ እንጂ የወልቃይት ጉዳይ ወያኔ ባወጣው ህግ የሚዳኝ ጉዳይ አይደለም። የአሜሪካ ነጮች ህግንና ህገመንግስትን ከለላ አድርገው የነጭ የበላይነትን ለማረጋገጥ በጥቁሮች፣ በላቲኖች፣ በቻይናና በጃፓናውያን ላይ በደል ሲፈጽሙ እንደኖሩት ሁሉ፥ የወያኔ ህጎችና ህገመንግስትም critically ከታዩ የአንድ ቡድን ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ፣ ፓሊቲካዊና ወታደራዊ የበላይነትን ለማስጠበቅ የሚወጡ ናቸው። ስለዚህ በነዚህ ህጎች፥ ከነዚህ ህጎችና በነእርሱ መሰረት ከተቋቋሙ ተቋማትም ፍትህን አንጠብቅም።
=============================
ወደተነሳሁበት ጉዳይ ስመለስ የአሜሪካ ድምጽ ራዲዮ ፍትሃዊ አዘጋገብን ለመከተል ብዙ ኳትኗል። አሁንም በወልቃይት ጉዳይ ከማንኛውም አካል የሚነሳ ጥያቄን ለማስተናገድ በራችን ክፍት ነው እያሉ ባለብት ሁኔታ ሃገር ውስጥ በለመደ አካሄዳቸው የመናገር ነጻነት ይታፈንልን ብሎ ለመጠየቅ መሞከር እብደት ነው። የአሜሪካ መንግስት የወያኔ መንግስት አይደለም። የመናገር ነጻነት እስከምን ድረስ መከበር እንዳለብት ያውቃል። የሚዲያዎችም ተግባር የታፈኑ ድምጾችን እንደገደል ማሚቶ ማስተጋባት፣ በኢ-ሊበራል መንግስትና ማህበረሰብ የሚፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ግፎችን ማጋለጥ ነው ተግባራቸው እንጂ እንደ ኢቢሲ ውሸትን እየደጋገሙ እውነት ለማስመሰል መድጣር አይደለም። የአሜሪካ ህገመንግስት የመጀመሪያው ማሻሻያ (First Amendment) ባስቀመጠው ሰፊ የመናገር ነጻነት መብት ተጠቅመው የአሜሪካ ድምጽ ራዲዩ የወልቃይት ጠገዴን ህዝብ ብሶትና እየደረሰባቸው ያለውን ግፍ ለአለም ለማሳወቅ የሚያደርጉት ጥረት ይበል የሚያሰኝ ነው። አሁንም ቢሆን በወልቃይት ጠገዴ ህዝብ ላይ ግዙፍ የሆኑ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች(grave human rights violations) እየተካሄዱ ስለሆአን የሚዲያ አይንና ጆሮ አይነፈጋቸው ስንል እንጠይቃለን። የሚድያ አንዱ ተግባሩ መንግስትን መቆጣጠር ነው። የሃገር ውስጥ ሚድያዎች ባያደርጉትም ቅሉ የወልቃይት ጠገዴን ህዝብ ሰቆቃ፣ ተቋማዊ በሆነ ሁኔታ በወያኔ አካላት ለሚደርስበት ሞት፣ ስደት፣ እስራት፣ ግርፋር፣ ስደት፣ እንግልት በእውነት ላይ ተመስርታቹህ ለአለም ህዝብ ታደርሱልን ዘንድ እንጠይቃለን።

4 April 2016

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.