በአዲስ አበባ ኦነግ አደራጅቷቸው ከመንግሥት ጋር ለመዋጋት ሲዘጋጁ ተደርሶባቸዋል የተባሉ ተጠርጣሪዎች ተከሰሱ

OLFበአዲስ አበባ ከተማ ቦሌ ቡልቡላ አካባቢ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የወጣቶች ክንፍ ‹‹ቄሮ ቢልሱማ›› በሚባል መጠሪያ የሽብር ድርጅት ሴል አደራጅተው፣ ከመንግሥት ጋር ለመዋጋት ሲዘጋጁ ተደርሶባቸዋል የተባሉ 33 ተጠርጣሪዎች ክስ ተመሠረተባቸው፡፡  ‹‹ያለንን ገንዘብ፣ ዕውቀትና ጉልበት በማቀናጀት ከመንግሥት ጋር መዋጋት አለብን፤›› በማለት የሽብር ተግባር ለመፈጸም ኦነግ አደራጅቷቸው ሲንቀሳቀሱ ተደርሶባቸዋል የተባሉት እነዚህ ተጠርጣሪዎች፣ መጋቢት 29 ቀን 2008 ዓ.ም. ነው ክስ የተመሠረተባቸው፡፡

በተጠርጣሪዎቹ ላይ የሽብርተኝነት ክስ የመሠረተው የፌዴራል ዓቃቤ ሕግ በክሱ እንደገለጸው፣ ተከሳሾቹ ቦሌ ቡልቡላ በግለሰቦች መኖሪያ ቤት ‹‹የማርያም ፀበል ዕድር›› በማለት ከተሰባሰቡ በኋላ፣ ‹‹ቄሮ ቢልሱማ›› የሚባለውን የወጣቶች ክንፍ ሴል አደራጅተዋል፡፡ አባላትን በመመልመልና የመሰብሰቢያ ቦታዎችን በመለየት ከነሐሴ ወር 2007 ዓ.ም. ጀምሮ መሰብሰብ መጀመራቸውን ክሱ ያስረዳል፡፡

ተሰካሾቹ ከኦነግ የተሰጣቸውን ተልዕኮ ለማስፈጸም እርስ በርሳቸው ቃል ከተገባቡ በኋላ፣ ‹‹የኦሮሚያን መሬት አሳልፈን ለአዲስ አበባ ማስተር ፕላን አንሸጥም፡፡ መንግሥት የኦሮሞን መሬት እየቆራረሰ በመሆኑ የኦሮሞ ሕዝብ እጅና ጓንት ሆኖ በመነሳት መንግሥትን መዋጋት አለበት፤›› በማለት ለሕገወጥ ተግባር ሲንቀሳቀሱ እንደነበር የዓቃቤ ሕግ ክስ ያስረዳል፡፡

ክስ የተመሠረተባቸው የወጣቶች ክንፍ ሊቀመንበርና ምክትል ሊቀመንበር በመሆን የተመረጡት ሀብታሙ ሚልኬሳ ጫሊ እና ረዳት ሳጅን ጫላ ፍቃዱ አብደታ በዋነኛነት እንደሚጠቀሱ የሚጠቁመው የዓቃቤ ሕግ ክስ፣ ሁለቱ ተከሳሾች ሌሎቹን ተከሳሾችና አባላት የመንግሥት ሠራተኛ የሆኑ መንግሥት የሚያወጣውን መመርያ እንዳያስፈጽሙና እንዳይፈጽሙ፣ አሳልፈው ለእነሱ እንዲሰጣቸው፣ የፀጥታ አባል ከሆኑ ደግሞ ከመንግሥት ዕርምጃ እንዲወስዱ ትዕዛዝ ሲሰጧቸው መሣሪያቸውን ወደ መንግሥት በማዞር ጥቃት እንዲፈጽሙ ትዕዛዝ ሲሰጡ እንደነበር ተብራርቷል፡፡

የወጣቶች ክንፍ አባላት ለተቃውሞ ሲወጡ የመንግሥት ተሽከርካሪዎች ፈጥነው እንዳይደርሱ መንገድ የመዝጋት ሥራ እንዲያከናውኑ ትዕዛዝ መስጠታቸውን፣ ድርጅቱን አባላት በገንዘብ እንዲረዱና መዋጮ እንዲያዋጡ ሁለቱ ተከሳሾች በዋናነት ትዕዛዝ ሲሰጡ እንደነበር ክሱ ይገልጻል፡፡ የገቢ ማሰባሰቢያ በማለት የኦነግን ዓላማ የሚመለከቱ የካሴት፣ የመጻሕፍትና የባንዲራ ሽያጭ እንዲከናወን በማድረግ አባላቱ እንዲንቀሳቀሱ ማድረጋቸውንም አክሏል፡፡

ቦሌ ቡልቡላ አካባቢ በሚገኘው መልካሙ ታደለ በሚባል ግለሰብ ግቢ ውስጥ 60 የሚሆኑ የሽብር ድርጅቱ አባላት በመሰባሰብና የኦነግን ባንዲራ እንዲይዙ በማድረግ ለድርጅቱ ለጊዜው መጠኑ ያልታወቀ ገቢ ማሰባሰባቸውንም ዓቃቤ ሕግ በክሱ ጠቁሟል፡፡ በየስብሰባው ከፖሊስ ሠራዊት፣ ከመንግሥት ቢሮዎችና ከአገር መከላከያ ሠራዊት አባላት እንደሚገኙ ሊቀመንበሩ በመግለጽ፣ ብዙ ደጋፊዎች ማፍራት እንዳለባቸውና በኦሮሞ ሕዝብ ላይ እየደረሰ ያለውን ጭቆናና ሥር የሰደደ ጥቃት ማስቆም እንዳለባቸው በመንገር ለአመፅ ሲያነሳሱ እንደነበር በክሱ ተብራርቷል፡፡

ዓቃቤ ሕግ ክስ የመሠረተባቸው ተጠርጣሪዎች 33 ቢሆኑም በተለይ አንደኛና ሁለተኛ ተከሳሽ የሆኑት ሀብታሙ ሚልኬሳ ጫሊ እና ረዳት ሳጅን ጫላ ፍቃዱ ቅስቀሳ በማድረግ፣ በመመልመል፣ በአጠቃላይ የኦነግ አባል በመሆንና በአገር ውስጥ የሽብር ድርጅት ሴል ቄሮ ቢልሱማ በሚል መጠሪያ በማደራጀትና አመራር በመስጠት በፈጸሙት በሽብር ድርጅት ውስጥ መሳተፍ ወንጀል፣ በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 19ኛ ወንጀል ችሎት ክስ ቀርቦባቸዋል፡፡ ሁሉም ተጠርጣሪዎች ኅዳር 19 ቀን 2008 ዓ.ም. በስብሰባ ላይ እያሉ ቦሌ ቡልቡላ መልካሙ ታደለ (24ኛ ተከሳሽ) ቤት ውስጥ በፀጥታ ኃይሎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውም በክሱ ተገልጿል፡፡

ለሁሉም ተከሳሾች ክሱ ከደረሳቸው በኋላ ፍርድ ቤቱ ‹‹አማርኛ ቋንቋ የማይችል አለ?›› በሚል ላቀረበላችው ጥያቄ የተወሰኑት እንደማይችሉ በመናገራቸው፣ በቀጣይ ቀጠሮ አስተርጓሚ እንደሚመደብላቸውና በራሳቸው ጠበቃ ማቆም የማይችሉ ካሉ መንግሥት ተከላካይ ጠበቃ እንደሚመድብላቸው ትዕዛዝ በመስጠት ለሚያዝያ 7 ቀን 2008 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

ምንጭ – ሪፖርተር

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.