ከቢሮ ኪራይ ጋር በተያያዘ ሰማያዊ ፓርቲ ጽ/ቤቱን ለማጣት ከጫፍ ደርሷል

gudayu

 

(ሳተናው) የዛሬ ዓመት በየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 6 የቤት ቁጥር 047 ባለቤት ከሆኑት ተወካዩች ጋር ለአንድ ዓመት የሚቆይ የኪራይ ስምምነት በመፈጸም ቢሮውን በ16.000 ብር ወርሃዊ ክፍያ ለሰማያዊ ፓርቲ ዋና ጽ/ቤትነት ሲጠቀሙበት የቆዩት የፓርቲው አመራሮች የውል ስምምነታቸው ጊዜውን በማጠናቀቁ ውላቸውን በማደስ የሚጠበቅባቸውን የቢሮ ኪራይ መክፈል ይጠበቅባቸው የነበረ ቢሆንም ይህ የዜና ዘገባ እስከተሰራበት ድረስ የፓርቲው ሊቀመንበር ገንዘቡን አለመልቀቃቸው ታውቋል፡፡

የቢሮው አከራዩች ለፓርቲው አመራሮች የውል ማደሻ ደብዳቤ በመጻፍ በዋናነት ለፓርቲው ሊቀ መንበር ኢንጂነር ይልቃል ጌትነት እንዲደርስ ቢያደርጉም ሊቀመንበሩ በመደበኛ ስራቸው መገኘት ባለመቻላቸው ምክንያት ፓርቲው ዋና ጽ/ቤቱን ለማጣት መቃረቡን የመረጃ ምንጮቻችን ያመለክታሉ፡፡

የቤቱ አከራይ ተገቢና ህጋዊ መንገድ በመከተል የመጨረሻ ውሳኔ ላይ መድረሳቸውን የሚጠቅሱት ለፓርቲው ቅርበት ያላቸው ምንጮች ኢንጂነሩ በፓርቲው የስነ ስርዓት ኮሚቴ ጥያቄ ከቀረበባቸው በኋላ ወደ ጽ/ቤቱ ለመምጣት ፈቃደኛ ሳይሆኑ በመቆየታቸው የፓርቲው የዕለት ተዕለት ስራ መቋረጡን ይገልጻሉ፡፡የቤት ኪራይ ክፍያ እንዲፈጸም የግዴታ ሊቀመንበሩ እንደሚያስፈልጉ የሚገልጹት ምንጮች የቤቱ አከራዮች የላኳቸውን ደብዳቤዎች ለሊቀመንበሩ እንዲደርሳቸው ቢደረግም ‹‹ቢፈልጉ ያሳሽጉት››የሚል ምላሽ መስጠታቸው ሰማያዊን ለዚህ ጽህፈት ቤት አልባ ሊያደርገው መቃረቡን በቁጭት ይገልጻሉ፡፡

በቅርቡ የፓርቲው የስነ ስርዓት ኮሚቴ ኢንጂነሩን ጨምሮ ሌሎች አመራሮችን ከፓርቲው ማባረሩንና ማገዱን የፓርቲው ኦዲትና ኢንስፔክሽን ማገዱና በቅርቡም ጠቅላላ ጉባዔ እንደሚጠራ መገለጹ አይዘነጋም፡፡

ዋና ጽ/ቤቱን በውዝፍ ኪራይና ባልታደሰ የኪራይ ውል ሰበብ ለማጣት የተቃረበው ሰማያዊ ፈተናዎቹን ተሻግሮ ዴሞክራሲያዊ ኃይሉን በማሰባሰብ ጠንካራ ተቃዋሚ በመሆን ነጥሮ እንዲወጣ የብዙዎች እምነትና ተስፋ ቢሆንም ‹‹እኔ ከሌለሁ ሰርዶም አይብቀል ››በሚሉ ራስ ወዳዶች መዳፍ ውስጥ መገኘቱ ተስፋ አስቆራጭ እንደሆነባቸውም ብዙዎች ይናገራሉ፡፡