የወሌ ልጅ- ሌላ፣ ወዲ አርአያ- ሌላ!! (መታሰቢያነቱ ለክቡር “ዶክተር” ገላውዴዎስ አርአያ)

ከኛይቱ ወረቀት ያልፈረመ የለም
መላው ታጥቆ ገባ ግድ የለም ግድ የለም
ትግሬም ገባ አሉ ሰምቶ በፍጥነት
የወሌውን ጉግሳ ሞኙን የኔን ጌታ መፈተኛ አርጎት

(የበጌምድር አዝማሪ)

 

Amhara 456ከፍ ብሎ የተጠቀሰው ግጥም የፈለቀው በ1923 ዓ.ም ገደማ- የአንችም ውግያን ተከትሎ ነው፡፡ የአንችም ውግያ፣ በወቅቱ ወግ አጥባቂና  ተራማጅ ሀይሎች መካከል የተደረገ ነበር፡፡የስሜን-በጌምድር ገዢና የእተጌ ዘውዲቱ ባል የነበሩት ራስ ጉግሳ ወሌ፣ በንጉሥ ተፈሪ (ያኔ ገና ንጉሠ ነገሥት አልተባሉም) ላይ ለማመፅ የምስራቅ ትግራይ ገዢ ከነበሩት ከጉግሳ አርአያ ጋር ይመክራሉ… ትግሬው ጉግሳ ከጎንደሬው ጉግሳ ጋር ወግኖ፣ በራስ ሙሉጌታ የሚመራውን የንጉስ ተፈሪን ጦር ለመውጋት ቃል ይገባል… የቁርጡ ቀን ሲመጣ ግን ትግሬው ጉግሳ በቃሉ አልተገኘም፡፡ ወደ ንጉሱ እቅፍ ገባ፡፡ ወግ አጥባቂው ጉግሳ ወሌም በጀግንነት ተዋግቶ ሞተ፡፡ ጉግሳ አርአያም ከ2 አመት በኋላ በበሽታ ሞተ፡፡ የጎንደሩ አዝማሪም- ሞክሼውን ስለካደው ጉግሳ (የአጤ ዮሀንስ የልጅ ልጅ) መሰሪነት በቅኔው ጠቁሞ አለፈ…

“በሁለቱ ጉግሳዎች ወግ” ጦማሬን የጀመርኩት፣ “የታሪክ ምሁር ነኝ” የሚሉ ሰውዬ፣ ጉግሳ ወሌን በጉግሳ አርአያ ሲያምታቱ በማየቴ ነው፡፡ በእወነቱ ስለሳቸው እጅጉን አፈርኩ፡፡ የዶክትሬት ዲግሪ ተሸክመው በዚህ ደረጃ ስህተት ሲሰሩ ማየት ያሸማቃል፡፡ ቢያምኑም ባያምኑም በቁም ሞተዋል! ጦማሬን ለሳቸው መታሰቢያ ያደረኩትም የሞያ ሞት እንደሞቱ ስላመንኩ ነው፡፡ ለዚህ “ህልፈት” የዳረጋቸው የወልቃይት ትኩሳት እንደሆነ ሳስብ ደግሞ ይበልጥ አዘንኩ፡፡

እኝህ ሰው በVOA ቀርበው፣ ወልቃይት በታሪክ የትግራይ እንደነበረች ለማስረዳት ከጠቀሷቸው ሀሰተኛ መከራከሪያዎች ውስጥ ቀልቤን የሳበው እንዲህ የሚለው ነበር፡-

“…በ20ኛው ክ.ዘ መጀመሪያ… በ1930 አካባቢ (የትግራዩ) ራስ ጉግሳ ወልቃይትን ያስገብሩ ነበር፡፡ ነገር ግን ከተፈሪ ጋር ጦርነት ገጥመው ስለተሸነፉ ወልቃይት ተቆርሶ ወደ ስሜን በጌምድር ገባ፡፡ ከዚያ በኋላ ወልቃይት የትግራይ ሆኖ አያውቅም… ከረዥም ጊዜ በኋላ ደግሞ አሁን እንደገና የትግራይ ተብሏል”

ወይ መበላሸት! የምስራቅ ትግራዩ ገዢ ራስ ጉግሳ መቼ ከተፈሪ ጋር ተዋጋና ወልቃይትን ተቀማ!? አጅሬ እንኳን ተፈሪን ሊገጥም፣ ሞክሼውን አጋፍጦ፣ የይልማን (የተፈሪ ወንድም) እህት አግብቶ መከላከያ ምሽግ ገነባ እንጂ! የወልቃይት፣ ስሜን በጌምድር ገዢ የነበረው ጎንደሬው፡ ጉግሳ ወሌ ብጡል ሀይለማርያም እንጂ፣ ትግሬው፡ ጉግሳ አርአያ ስላሴ ዮሃንስ አይደለም!!! በሚገርም ሁኔታ፣ ይህ ስህተት “የአፍ ወለምታ ይሆን እንዴ?” ብዬ አሰብኩና፣ ስለ “ዶክተር” ገላውዴዎስ ማንነት ትንሽ መፈተሸ ጀመርኩ… ወጤቱ አስደንጋጭ ነበር! ከ4 ዓመት በፊት ሰውየው ከEthioobserver ጋር ያደረገውን ቃለመጠይቅ አገኘሁት… ሰሙኑን VOA ላይ በትግርኛ የተሳሳቱትን (የዋሹትን ላለማለት ነው) ቀድመው በእንግሊዘኛ አስኪደውታል! ሰውዮው ከስህተታቸው እንዳልተማሩ ገባኝ!

የEthioobserver  ጥያቄ ሲተረጎም ከሞላ ጎደል እንዲህ ነበር፡- “..ከጎንደርና ከወሎ ተነጥቀው ወደ ትግራይ ስለተካለሉት የወልቃይትንና የአላማጣ-ወልድያ አካባቢዎችን በተመለከተ ስላለው አለመግባባት ምን ይላሉ?” (Ethioobserver January 17 2012)

“ዶክተሩ” ይህንን ጥያቄ ሲመልሱ ፡-

“…in the early 20th  century, both Wolkait & Tselemti were paying tribute to Ras Gugsa of Tigray, whose power was terminated in 1930 when the Prince Regent Ras Teferi was crowned as Emperor Haile Selassie of Ethiopia.  Consequently, Tselemti & wolkait were gradually incorporated (1930-1957) into Gonder area…”

‘እዋይ’ ዶክተር እቴ! የቪኦኤው ምሁር የወልቃይት፣ የጠለምትና የስሜን-በጌምድር ገዥ ጉግሳ ወሌ እንጂ ጉግሳ አርአያ እንዳልነበር እንዴት አላወቁም? ስልጣኑን በ1930 እ.ኤ.አ በጦርነት ምክንያት ያጣው የወሌው ጉግሳ መሆኑን እንዴት ሳቱ? እውነት ወልቃይት ከጉግሳ ወሌ በፊትም በኋላም የስሜን በጌምድር አካል-እንደነበር  የታሪክ መዛግብት እንደሚመሰክሩ ሳያውቁ ቀርተው ነው? በዚህ ደረጃ ለመውረድ እንዴት ደፈሩ? እንዴ! የሚሰሩበት ኮሌጅ ዝም ቢል እንኳ፣ በሰሚ ህሊና ዲግሪያቸውን የሚያስቀማ ስህተት ተዚ በላይ የለም እኮ! ወይስ ንቀት ነው? ለነገሩ የአማራ ምሁር ተብየ የማንንም ጎፈሬ እየዞረ ሲያበጥር አይደል የሚውል… ማን ሀይ ይላቸዋል! (“እነሱ ምን ያርጉ ከኛ ሰዉ ሲታጣ” እንዲል ፋሲል)

እስኪ አሁን ደግሞ ወልቃይትን የትግራይ ለማድረግ የፈበረኳቸውን ተጨማሪ ተረቶችን በስሱ እንመልከት፡- ((ተረት ስል ምን ትዝ አለኝ … የዛሬ ስድስት አመት ገደማ… ጤነኛው ትግሬ (ዶ.ር ጌታቸው ረዳ) “ገላውዴዎስ አርአያ ከተረት አባቶች አንዱ ነው” ብሎ ያለው… ልክ ነበር!)) ለማንኛውም በስፋት እስክመለስባቸው ድረስ ለሰውየው ተረቶች አጫጭር መልሶችን ሰጥቼ ልሰናበታችሁ፡፡

  1. “ትግርኛ እያወሩ ትግሬ አይደለሁም ማለት ስህተት ነው”

(እኔ- አሃ ፈረንሳይኛ እያወሩ “እኛ ሴኔጋላዊ እንጂ ፍሬንች አይደለንም” የሚሉትም ተሳስተዋላ!)

  1. “የወልቃይት ህዝብ ባህል፣ ታሪክና ቋንቋ ከትግሬ ጋር አንድ ነው”

(እኔ- በህግ አምላክ! ወልቃይቴ ሚሻሚሾ እንጂ አሸንዳ አያውቅም… በአማርኛ እንጂ በትግርኛ አይዘፍንም፣ አያለቅስምም… በታሪክና በዘር- ከከለው/አቢስ ወገን አማራ እንጂ፣ ከሳባ/ትግሬ አይደለም!)

  1. “የወልቃይት ቦታዎች ስያሜ በሙሉ ትግርኛ ነው”

(እኔ- ዶክተር ይረጋጉ! ወፍ አርግፍ፣ አንዳይቀዳሽ፣ ዳንሻ፣ አምባ ጋላ፣ ገንዳ ውሃ፣ ሹምመሪ፣ ግጨው፣ ቤት ሙሉ… ወዘተ ትግርኛ ነው እንዴ!?  TPLF ከ1972 ጀምሮ በትግረኛ ስሙን ሲተካ የኖረው ቦታስ ተረሳ? ደግሞስ “ትግርኛ ስም ያለው  ቦታ ሁሉ የትግሬ ነው” የሚሉት “ሎጂክ” ያዋጣል ጋሼ? አደራ “አዎ!” ብለው ጉድ እንዳይሆኑ! ምክንያቱም፣ አማርኛ ስም ይዘው  ወደ ትግራይ የተካለሉ ቦታዎች መአት ናቸውና! ለምሳሌ፡- ስንቃጣ፣ ሽሬ፣ ላጨ፣ አይናለም፣ አላማጣ… ወዘተ… ለማንኛውም ስለ አካባቢው የቦታ ስያሜ አወጣጥ ታሪካዊ ዳራ ካላወቁ ይጠይቁ!)

  1. “Manoel Barradas (ከ1624-34 ኢትዮጵያ ውስጥ የነበረ ሚስዮናዊ) ‘A 17th Century Historical & Geographical Account of Tigray, Ethiopia’ በተሰኘ ድርሰቱ ወልቃይት የትግራይ ነች ብሏል!”

(እኔ- ውሸት በርሶ እድሜ አያምርም! Manoel  እንዲያ አላለም! ደግመው ያንብቡት! “በስተምዕራብ- ስሜን ትግራይን ያዋስነዋል” ማለት፡ “ስሜን/ወልቃይት ትግራይ ነው” ማለት አይደለም፡፡ በነገራችን ላይ በአጼ ሱስንዮስ ጊዜ (1606-1632) እንኳን ትግሬ ወልቃይትን ሊያስገብር፣ የአጼ ሱስንስ ወንድም (ራስ ስእለ ክርስቶስ) ትግራይን በቀጥታ ያስተዳድር ነበር! ባጭሩ በ17ኛው ክ.ዘ ወልቃይት እና መላው ሰሜን በጌምድር በጎንደር ነገስታት እጅ እንጂ በትግሬ መሳፍንት ቁጥጥር ስር አልነበረም፡፡ የአገር ውስጥም የውጭም ጸሀፍት ወልቃይትን የትግሬ ነው ያሉበት አንዳች መረጃ እንኳን አታገኝም፡፡ ወልቃይት የአማራ ስለመሆኑ ግን የፈረንጅም የአበሻም፣ የአማራም የትግሬም ምሁራን የጣፉትን ታሪክ፣ የሳሉትን ካርታ፣ ‘በቃን’ እስክትሉ ሰሞኑን በተከታታይ እናቀርባለን፡፡ እስከዛው ግን ገድለ አበርሀ ወአጽበሀ (በትግርኛም አጥሮ ተተርጉሞልዎታል)፣ የአለቃ ታየን፣ የፕ/ር አለሜን፣ የፕ/ር ታደሰን፣ የፕ/ር ስርግውን፣ የፖል ሄንዝን ስራዎች ያገላብጡ… ደህና ይሰንብቱ “ዶክተር”!)

Comments are closed.