‘ያለደም ስርየት የለምን? አዲሱን የአማራ ትውልድስ ስለምን ወደጠርዝ ትገፉታላቹህ?’ – ሰበለ-ወንጌል ዘአማራ

welkeit - satenaw 3ቆፍጣናው አቶ አታላይ ዛፌ የወልቃይት የአማራ ማንነት አስተባባሪ ኮሚቴ አባል ነው። ምንም እንኳ ህወሃት ማድረግ የምትችለውን ሁሉ ብታደርግም እስካሁን እስከቆፍጣናነታቸውና እስከነ ልበ-ሙሉነታቸው የአባቶቻቸውን ማንነት፣ በወያኔ እየተደፈጠጠ ያለውን ማንነታቸውን ለማስመለስ ወገባቸውን ጠበቅ አድርገው ደፋ ቀና እያሉ ይገኛሉ–ወልቃይቴዎች። ዛሬ በአሜሪካ ድምጽ ራዲዮ ያደረገውን ቃለ-ምልልስ ሰማሁት። በጣም የሚገርምና እሳት የሆነ ንግግር ነው ያደረገ። እግዜር ይባርክህ ወንድሜ። ከንግግሩ ውስጥ ያሉት መልካምነቶች ደግሞ የበለጠ ደስ ይላሉ። ምንም እንኳ ወያኔ ይህንን ሁሉ መጥፎ ነገር በወልቃይት ህዝብ ላይ እያደረሰች ቢሆንም ሃሳቡንና ጥያቄውን በመልካም አንደበት፣ በመልካም ቃላት ለመግለጽ ያደረገው ጥረት እጅጉን ደስ ይላል። በሰለጠነው አለም፣ በዲሞክራሲያዊ ማህበረሰብ ውስጥ ሃይልና ጉልበት ቦታ የላቸውም። ነገር ግን በወያኔ መንግስት ውስጥ ሁሉንም ነገር በሃይለ ለመደፍጠጥ የሚደረግ ጥረት በጣም ያሳዝናል። ህጋዊ ጥያቄዎች በህግ አግባብ በተዘረጋው ስርዓት መመለስ ሲገባቸው፥ ስልጣንን በጥመንጃ አፈሙዝ የተቆናጠጠችው ወያኔ አሁንም ለሁሉም ጥያቄዎች መፍትሄ የጠብመንጃ ምላጭ መሳብ ይመስላታል። ጠብመንጃ ብዙ ነገሮችን ሊያበላሽ እንደሚችል፣ ከትርፉ ጉዳቱ እንደሚያመዝን፣ የአፈሙዝ አካሄድ የትኛውንም ህዝብ ሊጠቅም እንደማይችል እስካሁን የተገነዘቡት አይመስለኝም። ትናንት ሰርተነው መጥተናል የሚሉት የትግል ጀብድ የማሰቢያ ጭንቅላታቸውን ደፍኖባቸው አተያያቸው ሁሉ፣ መፍትሄያቸው ሁሉ መሳሪያ ሁኗል። ይህ አካሄዳቸው የወጣቱን አዕምሮ በመበረዙ የተነሳ በሰላም ተነጋግሮ መግባባት ከባድ እየሆነ ያለበት ሁኔታ ነው ያለው። እውነታው ግን እውነትን በመሳሪያ አፈሙዝ ማዳፈን አይቻልም። እውነታው ግን የመሳሪያ ቃታ መሳብ ህዝብን እንደህዝብ የሚጠቅም ነገር አይደለም። እውነታው ግን በህዝብ ላይ የጦርነት ነጋሪት መጎሰም ይዘገያል እንጂ ውድቀትን ማቀድ ነው። የአማራ ህዝብ በወያኔ መንግስት እንደ ጠላት ከተፈረጀ ጀምሮ እጅግ የሚዘገንኑ ግፎች ተፈጽሞበታል። ሁሉንም ተሸክሞት ኑሯል። ወንዱ ወደውስጡ ሲያነባ ኑሯል። ሴቶች መቀነታቸውን አደግደገው፣ ነጠላቸውን ዘቅዝቀው እንባቸውን ወደፈጣሪያቸው ሲረጩ ኑረዋል። ነገር ግን አሁንም የወያኔ ግፍ አልበረደም። የግፉ ጽዋ ሞልቶ እየፈሰሰ እያዩ እንኳ ነግ በኔ አላሉም። ትናንትናና ዛሬም የአማራ ህዝብ መበደላቸውን ተያይዘውታል። ነገም ይህንኑ ግፍ እንደሚፈጽሙ እየዛቱብን ይገኛሉ። የወልቃይት ህዝብ ማንነቴ፣ ነጻነቴና መሬቴ ይከበርልኝ ሲል በሰላማዊ መንገድ ነው የታገለ። በሰላማዊ መንገድ ሲታገል ግን ግፍ ስላልደረሰበት አይደለም። ለመሸከም የሚከብዱ በደሎች ስላልደረሱበት አይደለም። ነገር ግን በ21ኛው ክፍለ-ዘመን በሰላማዊ መንገድ ጥያቄን ማንሳት ስልጡንነት ነው ብሎ ስላሰበ እንጂ። ይሁንና ለዚህ የሰለጠነ አካሄድ ከትልልቅ የወያኔ ካድሬዎች እስከ ትንንሽ ውርንጭላ ካድሬዎች ድረስ መልካም ያልሆኑ ነገሮች እየተደረጉበት ነው። አለም በአወቀው፣ ጸሃይ በሞቀው አደባባይ ላይ በአማራ ህዝብ ላይ “እናጠፋቹሃለን” የሚል መፈክር ይዘው ወጥተዋል። መፈክራቸንም ላለፉት አራት አስርት አመታት ተግባራዊ ሲያደርጉት ኑረዋል። አሁንም እያደረጉት ነው። ነገር ግን ይህ አካሄዳቸው የወልቃይት ብሎም ጠቅላላ የአማራን ህዝብ ወደአልተፈለገ አቅጣጫ እየገፉት እንደሆነ አልታወቃቸውም ወይም ሆን ብለው ዘንግተውታል። አዲሱን የአማራ ትውልድ በጥላቻ እየበረዙት እንደሆነ አልታወቃቸውም ወይም ሆን ብለው ዘንግተውታል።
“ኢትዮጵያ ውስጥ ያለደም ስርየት የለምን?” ሲሉ አቶ አታላይ ዛፌ ጠይቀዋል። እኛም እንጠይቃለን ያለደም ሰላማዊ መፍትሄ የለምን? በሰላማዊ መንገድ ጥያቄ የሚጠይቀውን ሁሉ ወደ ጠርዝ መግፋት ማንን ሊጠቅም ይችላልን? የአማራ ወጣትን አዕምሮ በጥላቻ መሙላቱስ ምን ያደርግላቹሃልን? በጥላቻ ያደገ ትውልድ ነገ ለእናንተ ሰላም የሚሰጣቹህ ይመስላቹሃልን? ዛሬ የገፋቹህት ነገ እናንተን የበለጠ ላለመግፋቱ ምን ያህል ዋስትና አላቹህን? ነገሮችን ያለደም መፋሰስ መፍትሄ ለማበጀት መንገዱ የሰማይን ያህል ለምንስ ራቀባቹህ? ነው ወይስ ዛሬ ያነገታቹሁት መሳሪያ ነገ ሌሎች ላለማነገታቸው እርግጠኞች ሁናቹሃል? ለማንኛውም እናንት ወያኔዎች የአማራን ህዝብ በተለይ አዲሱን የአማራ ትውልድ ወደጠርዝ ባትገፉት መልካም ነው። አካሄዳቹህ ማንንም አይጠቅምምና። ነገ ሌላ ቀን ነውና።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.