የአሰፋ ጫቦ ወጎች (ግርማ አውግቸው ደመቀ)

አስፋ ጫቦ
አስፋ ጫቦ

አሰፋ ጫቦ። 2016 (እግአ)።[i] የትዝታ ፈለግ። ዳላስ፣ ቴክሳስ። ምዕራፍ ብዛት 28 (መግቢያና ቅሱም ‘index’ አለው)፣ ገፅ ብዛት 332፣ ዋጋ $24.95፣ ISBN: 978-0-98983131-4። ይህ ስራ ከላይ የተጠቀሰው የአሰፋ ጫቦ መፅሀፍ ላይ የቀረበ አስተያየት ነው። መፅሀፉ በተለያዩ ወቅቶች በጋዜጦችና በመፅሄቶች ላይ የወጡ መጣጥፎች ስብስብ ነው። ስለስብስቡ አሰፋ እንዲህ ይላል፤ “መጀመሪያ ለጋዜጦች የጻፍኩት የወጣው በ1956፣ […]  ‘ፖሊስና እርምጃው’ ላይ ነበር። […] ከዚያ ወዲህ አልፎ አልፎ ቢሆንም ብዙ የጻፍኩ ይመስለኛል።

“የትዝታ ፈለግ በሚል እዚህ አሁን የተሰባሰቡት ከዚያ የተውጣጡ መሆናቸው ነው። እንደሚነገረኝ ከሆነ ይኸኛው ቅጽ አንድ ይሆንና በተከታታይ የሚወጣም ይኖራል። እንደሚነገረኝ ያሰኘኝ እኔ ምን ያህል እንደጻፍኩ፤ አሁን የትስ እንደሚገኙ አላውቅምና ነው” (ገፅ 1)።

መጣጥፎቹን ያሰባሰበው ደራሲው አይደለምና በምን መስፈርት እዚህ ቅፅ የቀረቡት እንደተመረጡ የነገረን ነገር የለም። ያሰባሰቡትም ሰዎች በዚህ ጉዳይ ላይ ያሉት ነገር የለም። መጣጥፎቹ የተሰደሩበትም ቢሆን በምን መስፈርት እንደሆነ የተገለፀ ነገር የለም። በተፃፉበት/በታተሙበት ግዜ ቅደም-ተከተል እንደሆነ ለመናገር የሚያስችል በቂ መረጃም የለም። አንዳንዶቹን ከራሳቸው ከፅሁፎቹ ይዘት በመነሳት ቢያንስ የተፃፉበትን ዓመት መገመት ይቻል ይሆናል። ይህ ግን በቂ አይደለም።

በይዘታቸው የጉዞ ማስታወሻ፣ ትውስታ፣ ትዝብት/ማህበራዊ ሂስ፣ የማህበረሰብ ገፅታ እና አብዛኞቹ ፖለቲካ ነክ ናቸው። መፅሀፉ የመጣጥፎች ስብስብ ነውና ለምን የተለያዩ ይዘት ያላቸው አንድ ላይ ቀረቡ የሚል የወጥነት ጥያቄ ሊነሳበት የሚገባ አይመስለኝም። በይዘት የሚያራርቃቸውን ያህል የሚያቀራርባቸው ነገርም አለ። ይህም ቋንቋቸው ነው። አሰፋ ጫቦ ከፖለቲከኛነቱ ይልቅ በብዕሩ የሚታወቅ ይመስለኛል።

ሶስት ገጠመኞችን ልጥቀስ፤ አንደኛው፣ የዛሬ ሀያ ዓመት ገደማ አንድ ጓደኛችን አስቴር አወቀ የሌሎችን የዘፈነችውን ሰምቶ፣ ምናለ የሁሉንም ድምፃውያን ዘፈኖች ባዜመቻቸው ማለቱ ነው። እኔም የተስማማሁበት ነበር። ሁለተኛው፣ ብላቴ የጦር ማሰልጠኛ የከፍተኛ ትምህርት ተቋም ተማሪዎች ገብተው በነበረበት ወቅት፣ ካልተሳሳትኩ በየሳምንቱ የኪነት ቡድን ይመጣ ነበር። ከኪነት ቡድኖቹ በፊት ይሁን በኋላ ወይም በየመሀከል አንዳንድ ሰዎች እየተነሱ (አንዳንዴ ግጥምም ቢቀርብም) በዋናነት ስለሀገሪቱ የፖለቲካ ሁኔታና የተማሪው/ሰልጣኙ የወደፊት ድርሻ ምን መሆን እንደሚገባው ንግግር ያደርጉ ነበር። ውይይት ነበረ ለማለት ይከብዳል። ተናጋሪዎቹ በየሳምንቱ አብዛኞቹ ያው ናቸው።  ከነዚህ ውስጥ ግን ሁሌም በሚናገረው መሳጭ የነበረው ሰለሞን ኃይለማርያም የተባለ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሄደ ነበረ። የፈለገውን ያህል ሰዓት ወስዶ ረጅም ንግግር አድርጎ  ቢቀመጥም ሁለት ሶስት ሰዎች ከተናገሩ በኋላ ተማሪው/ሰልጣኙ ሰለሞን ይናገር እያለ በመጮህ፣ በድጋሜ እየወጣ ይናገር ነበር። እኔም የሰለሞን ንግግር ከሚመስጣቸው ውስጥ አንዱ ነበርኩ። ሶስተኛው ገጠመኝ፣ ይህ የአሰፋን ስራ ሳነብ የተሰማኝ ነው። አንብቤ ከጨረስኩ በኋላ አነበብኩ ብዬ አልረካሁም። ደጋግሜ እያነበብኩ እመሰጥበታለሁ። መላልሼ ካነበብኳቸው ውስጥ “ትዝታ ነው የሚርበኝ” በሚለው ርዕስ ስለ ትውልድ ሀገሩ ጨንቻ የገለፀበትንና “ዶሮ ራስ አንበል” በሚል ስለአንዲት ዶሮውና በግ የተረከበት መጣጥፍ ዋናዎቹ ናቸው። ይዘታቸው ጠጥሮ አይደለም። ማርኮኝም ነው ለማለት ይከብደኛል። አብዛኛው አዲስ ነገር አይደለምና። እንደዚያች አይነት ዶሮ እኔም አውቃለሁ። በጨንቻ የታየውም ለውጥ በብዙ የሀገራችን ክፍሎች ባሉት የታየ ነው። እኔን የሳበኝ ቋንቋቸው መሆን አለበት። አሰፋ እጁ ሳያቋርጥ ስለሁሉም ነገር በፃፈ ተሰኘሁ። ይህ መታደል ነው።

የአሰፋ ትውልድ ይገርመኛል። የአሰፋ ትውልድ የምለው ከ60 ዓመት በላይ ያለውን ሁሉ ነው። አሰፋ “ከ50 ዓመት በላይ ያለ ሁሉ ለኔ ወጣት ነው” ይላል (ገፅ 1)። ከሱ መስማማቴ ወይ መለየቴ አይደለም። በሀገራችን ታሪክ ላይ ከፍተኛ አሻራ የተወ ትውልድ ስለሆነ ነው። በተለይ ፊደል ቀመስ የሆነውን የሚመለከት ነው። ይህን ትውልድ ወደፊት ታሪክ አንድም በጥሩ፣ አብዛኛው በክፋት የሚዘክረው ይመስለኛል።

ምንም እንኳ የምዕራባዊያን አይነት አለማዊ ትምህርት በመንግስት ደረጃ በምኒልክ ግዜ ቢጀመርም፣ በጣም የተስፋፋውና ከፍተኛ ትምህርት ተቋማትም የተከፈቱት በኃይለሥላሴ ወቅት ነበር። የዘመናዊ ትምህርቱ ከሀገራችን ነባር የትምህርት እድገት የተገኘ አለመሆኑና ከህብረተሰቡ ባህልና ልማዳዊ እውቀት ላይ አለመመስረቱ ወይም ለማዛማድ መንገድ ሳይፈልግ መካሄዱ የዚህ ዘመን አመጣሽ ትምህርት ቀማሽ የሆኑት እድሜያቸው ሰላሳን ያልዘለለ ከእኛ ወዲያ አዋቂ ማን አለ ባይ እንዲሆኑ መንገድ ከፈተ። አባቶቻቸው በዚያ ያለፉ አልነበሩምና እነሱን መስማት ኋላቀርነት ሆነ። የአባቶቻቸው አስተሳሰብ ብቻ ሳይሆን፣ አባቶች እራሳቸው ኋላቀር ተደርገው ተወሰዱ። ማን ከእድሜ ባለፀጋ አባቶች ምክር ይሰማል! የወቅቱ የአለማችን ፖለቲካ ተጨምሮ፣ ሀገሪቱ ከማትወጣበት አዘቅት ውስጥ ከተቷት። ነጭሽብር-ቀይሽብር፣ ከዚያም በላይ በጎጥ እና በመንደር ተቧድኖ እርስ በእርስ መጋደላቸው አንሶ በእድሜ ጠግበው ይማራሉ በሚባልበት ሰዓት፣ ወንድም ወንድሙን ገድሎ ኃውልት የሚሰሩ አሳፋሪዎች የወጡበት ትውልድ ለመሆን በቃ። ከታሪካዊ የጥቅም ጠላቶቻችን ጋር አብብሮ[ii] ወንድሙን የሚገድል፣ በዚህም የሚኮራ ትውልድ ሆነ። ጥራዝ ነጠቅ እውቀት ሁሌም አደገኛ ነው።

በምኒሊክ አድዋ ድል ማግስት አንድ የአሜሪካ ልዑካን ቡድን ወደኢትዮጵያ መጥቶ ነበር። የዚህ ቡድን መሪ የነበረው፣ ሮበርት ፒ. ስኪነር የተባለ ዲፕሎማት ነበር። ይህ ሰው ጉዞውን መዝግቦ በኋላ መፅሀፍ አድርጎ አሳትሞታል። ስኪነር በዚህ ላይ የታዘበውን እንዲህ ብሎ ነበር፤ “የተባበረች ኢትዮጵያ ነፃነቷን ለመድፈር የሚመጣባትን እስከመቼውም ልትቋቋም ትችላለች—ከዚህ በፊት እያንዳንዱን ወረራ በተሳካ ሁኔታ መክታ እንደመለሰችው። ኢትዮጵያ ልትሸነፍ የምትችለው፣ ህዝቦቿን አንዱ በአንዱ ላይ እንዲነሳ በማድረግ/ከተነሳ ብቻ ነው”።[iii] ጣልያን ከ30 ዓመት በኋላ ከሞላ ጎደል ይህንን ለመጠቀም ሞክራ ነበር። የጣልያን ባይሳካም ሀገር በቀል ወራሽ ግን አልጠፋም።

የአሰፋን ትውልድ በጅምላው እንዳንወቅስ የሚያደርገን በጣት ቢቆጠሩም የሚያስደንቁ ስብዕናዎችም መኖራቸው ነው። ከእነዚህ ውስጥ አንዱ ኃይሌ ገሪማ[iv] ነው። በብዕራቸው ብቻ የማይሞት ስም የተከሉና ለቀጣይ ትውልድ መኩሪያ ከሆኑት ውስጥ ደግሞ እነፀጋዬ ገብረመድህን እና በዓሉ ግርማን መጥቀስ ይቻላል። እነዚህ ሰዎች ብዕራቸውን ለሰብዓዊነትና እውነት ለመሰላቸው አውለውታል። አሰፋ ከእነዚህ (እና ሌሎች ስማቸውን ካልጠቀስኳቸው ጥቂት) ሰዎች ተርታ የሚገባ ይመስለኛል።[v]

አሰፋ፣ በዚህ መፅሀፉ በብዕሩ ያነሳቸው ጉዳዮች አንዳንዴ ይገርሙኛል። ለምሳሌ፣ “የኔይቱን ጀግና” ይመልከቱ። በቤት ሰራተኝነት የገባች ሴት እንዴት የቤት አስተዳዳሪና የቤቱ አርዓያ እንደሆነች የሚተርክበት ነው። ጀግና ፍለጋ ሩቅ አልሄደም። ስም ያለውንም አልፈለገም። እራሱ ስም አበጀ እንጂ። በዚያ ፅሁፍ ከሴትዮዋ ሰናይ ምግባርና አርአያነት በላይ እኔ ያየሁት ደራሲውን ነው—ለሰው ልጅ ያለውን ክብር።

በፖለቲካ አቋማቸው ቀናኢ ሆነው ለሚያምኑበት ሽንጣቸውን ገትረው በመሟገት የሚገርሙኝና የማደንቃቸው ሁለት ሰዎች ቢኖሩ ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያምና አሰፋ ጫቦ ናቸው። ሁለቱም ፍርሀት ማለት ምን እንደሆነ የሚያውቁ አይመስለኝም። ምሁር ተብዬ ስብዕና ቢስ ከበዛበት ትውልድ ቢወጡም፣ ለሆድ ብሎ ማደር እነሱ ጋ የለም። ይህ የአሰፋ ስብስብ ስራ የሚያመለክተን ይህንኑ ነው። ዛሬ፣ በሀገር ቤት ያለውን በጎሳ ከፋፈለ ብሎ የሚወቅስ በውጭ፣ በተለይ በምዕራባውያን ሀገሮች፣ የሚኖረው ዜጋ ፖለቲከኛው ቀርቶ  የሀይማኖት ሰው ነኝ ባዩ ሳይቀር እራሱ (በጎሳ-ፖለቲካ) ተከፋፍሎ (ከሀገር ቤት በባሰ ሁኔታ) ሲናቆር ይታያል። አሰፋ በዚህ አብሮት በሚኖረው ስደተኛ ላይም ቢሆን፣  ብዕሩን አልመለሰም። ምዕራፍ 24 ማርከሻው ጠበሉ! እንደጠፋ ቀረ…? እንደተሰወረ??! በሚለው ርዕስ ላይ የሚከተለውን ይላል፤ “በዚህ ላይ ትንሽ እዚህ አሜሪካ ቆየት ያልነው በሃብት (Material) ድህነትና በአእምሮ ድህነት መካከል ያለው ልዩነት የጠፋብን ይመስለኛል። ከኢትዮጵያ የሚመጣ ሰው የፈለገውን ያክል የተማረ የተመራመረ ቢሆን እንደ አላዋቂ የመውሰድ አዝማሚያ ሰፍኗል። ከዚህም የተነሳ ዛሬ ጧት ከኢትዮጵያ ለመውጣት [sic ለወጣ] ምሁር ‘የኢትዮጵያን ተጨባጭ ሁኔታ’ ‘ተንትኖ ለማስረዳት ለማስተማር’ እንሞክራለን። ነገሩ ያሳዝነኛል!!” (ገፅ 267)። እውነትም ያሳዝናል። የሚያሳዝነው የፖለቲካችን ነገር ብዙ ነው። እዚያ ውስጥ አልገባም—ለዚህ ከበቂ በላይ ፖለቲከኞችና ተንታኞች አሉና።[vi]

ግርማ አውግቸው ደመቀ

ትሪንተን፣ ኒውጀርሲ

ቀን: 4/10/2016 እግአ

[i]               እንደ ግሪጎሪያን አቆጣጠር

[ii]              በዚህ ቃል ላይ የ ‘ብ’ መደገም ጥብቀትን ለማመልከት ነው።

[iii]     ትርጉሙ ቃል በቃል አይደለምና የእንግሊዝኛውን ቃል ልስጥ፤ “A united Abyssinia would be able to resist indefinitely any ordinary attempt to break down an independence which has withstood assault successfully from every invasion […]. If independent Abyssinia falls, that contingency is most likely to result from dissensions among the Abyssinians themselves” (Skinner, Robert P. 1906. Abyssinia of To-Day: An Account of the First Mission Sent by the American Government to the Court of the King of Kings (1903-1904). London, New York: Longman, Green & Co., p. 178.)

[iv]     ኢትዮጵያም ሰፍታባቸው የመንደር ፖለቲካን ከጠነሰሱ ትውልድ መሀል ወጥቶ፣ ኃይሌ በተቃራኒው በሙያው የመላው ጥቁር ህዝብ ጉዳይ፣ ጉዳዩ አድርጎ በአለም ስሙን የተከለ የአፍሪካዊ መብት ተሟጋች ነው። ለዚህ “ሳንኮፋ” የተሰኘ ፊልሙን ብቻ መመልከት ይበቃል።

[v]      የእነዚህ ሰዎችን የታሪክ ቦታ ለመገንዘብ ከፀጋዬ “እሳት ወይ አበባ”ን (ወይም ከዚያ ውስጥ አንዲቷን ግጥም፣ “ሰቆቃወ ጴጥሮስ”ን)፣ ከበዓሉ “ከአድማስ ባሻገር”ን፣ እና ከአሰፋ ይህን መፅሀፉን ብቻ መመልከቱ በቂ ይመስለኛል።

[vi]     የፖለቲካው ችግር በቀጥታ የሚመለከታቸው ሀላፊዎች ግን፣ ለመፍትሄው (ቅንነቱ ካለ) ከመስፍንና ከአሰፋ ስራዎች በተጨማሪ ከሌሎች መሰል በሳልና ቅን አሳቢዎች ስራ ብዙ መማር የሚችሉ ይመስለኛል።

1 COMMENT

  1. Professor Messay:

    Thank you for a visionary and forward looking article. Hope the Woyane and the back-up singers in diaspora heed the warning that you beautifully captured.

    Ignore your detractors and keep up the good work!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.