ደቡብ ሱዳናዊያን ስደተኞች 14 ኢትዮጵያዊያንን በጭካኔ ገደሉ

ደሱ

(ሳተናው) ከጋምቤላ ከተማ በስተምስራቅ 17 ኪ.ሜ ርቀት ላይ በሚገኘው ጃዊ የስደተኞች ካምፕ አቅራቢያ ኢትዮጵያዊው ሹፌር በደቡብ ሱዳናዊው ስደተኛ ላይ ላደረሰው የመኪና አደጋ የደቡብ ሱዳን ስደተኞች በሰጡት ምላሽ 14 ኢትዮጵያዊያን የጭካኔ ድርጊት ተፈጽሞባቸው ለሞት መብቃታቸውን ከአካባቢው የተገኙ መረጃዎች ጠቁመዋል፡፡

በስደተኞቹ ካምፑ ለሚገኙ ደቡብ ሱዳናዊያን አገልግሎት የሚሰጡ የእርዳታ ሰራተኞች ለማመላለስ በሹፍርና ስራ የተቀጠረው ኢትዮጵያዊ አንድን ደቡብ ሱዳናዊ በሚያሽከረክራት መኪናው በመግጨት ጉዳት ቢያደርስበትም ሹፌሩ የተገጨውን ግለሰብ ወደ ህክምና ጣቢያ ለመውሰድ ሙከራ ሲያደርግ በአካባቢው የነበሩ ደቡብ ሱዳናዊያን ስደተኞች ሹፌሩን ጨምሮ ያገኙትን ኢትዮጵያዊ እጃቸው ላይ ባገኙት ድንጋይ፣ገጀራና ቢላዋ በመጨፍጨፍ ለሞትና ለከፍተኛ ጉዳት ይዳርጓቸዋል፡፡

በደቡብ ሱዳናዊያኑ ተፈንክተው፣በገጀራው ተከትፈውና በቢላ ተወግተው የተገደሉትን ሰዎች ማንነት ለመለየት ማስቸገሩንም የአካባቢው ሰዎች ይናገራሉ፡፡የአሜሪካው ድምጽ የአማርኛ የሬዲዩ ፕሮግራም እንደዘገበው ከሆነም የ12 ሰዎችን ማንነት መለየት አልተቻለም፡፡

የስደተኞቹ መጠልያ ካምፕ ከጋምቤላ ከተማ ወጣ በመቱ መውጫ ላይ የሚገኝ ሲሆን ከ10 ሺህ በላይ ደቡብ ሱዳናውያን ተጠልለውበታል፡፡ደቡብ ሱዳናዊያኑ በኢትዮጵያዊያኑ ላይ የጭካኔ ተግባራቸውን ሲፈጽሙም የጸጥታ ሰራተኞች በስፍራው አለመገኘታቸው ብዙዎችን አስገርሟል፡፡

ባሳለፍነው ሳምንት አርብ የደቡብ ሱዳን ሙርሌ ተወላጆች መሆናቸው የተነገረላቸው ታጣቂዎች ከ250 በላይ ንጹሐን ኢትዮጵያዊያንን በመግደል ከአንድ መቶ የሚልቁ ህጻናትን አፍነው መውሰዳቸው አይዘነጋም፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.