ቀይ መስቀል በጋምቤላው ጥቃት የተጎዱ 39 ኢትዮጵያዊያንን ለማከም መቸገሩን አስታወቀ

maiwut_county_hospital

ኢትዮጵያዊያኑ እየታከሙ የሚገኙት በደቡብ ሱዳን ነው

(ሳተናው) የደቡብ ሱዳን ሙርሌ ታጣቂዎች በኢትዮጵያ ጋምቤላ ክልል ባደረሱት በመሳሪያ የታገዘ ጥቃት ጉዳት የደረሰባቸው ከ30 የሚበልጡ ኢትዮጵያዊያን በአለም አቀፉ የቀይ መስቀል ኮሚቴ በሚታገዘው የህክምና ጣቢያ እርዳታ ደቡብ ሱዳን ውስጥ የህክምና እገዛ እየተደረገላቸው እንደሚገኝ ቀይ መስቀል ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡

በጥቃቱ 208 ንጹሐን (ሴቶችና ህጻናት ይበዙበታል)መገደላቸውና ከ100 የሚልቁ ህጻናት ታፍነው ከተወሰዱበት እስካሁን አለመመለሳቸውና በህይወት ይኑሩ ወይም ይገደሉ ሊታወቅ አልተቻለም፡፡

ከሁለት ሳምንታት በፊት ሙርሊዎች በፈጸሙት የጭካኔ ተግባር በጥይት ተመትተው ክፉኛ ከቆሰሉ ሰዎች መካከል 39 ያህሉ በቀይ መስቀል እገዛ ወደ ደቡብ ሱዳን ተወስደው ህክምና እየተደረገላቸው የሚገኝ ቢሆንም ሆስፒታሉ ችግሮች እንዳሉበት ይፋ አድርጓል፡፡

የህክምና ክሊኒኩ ማናጀር የሆኑት ቺዩኪ ዮሺዳ ‹‹ያሉን ባለሞያዎች በሙሉ ያለማቋረጥ የሚመጡ ህመምተኞችን በመቀበል ለመርዳት በመስራት ላይ ይገኛሉ፡፡ሆስፒታላችን በምግብ እጦት የተጎዱ፣በወባ የተያዙና በደቡብ ሱዳን ከየትኛውም አካባቢ ከአመጽ ጋር በተያያዘ ጉዳት የሚደርስባቸውን የሚቀበል በመሆኑም ዋነኛ ችግራችን ከአቅማችን በላይ በእርዳታ ፈላጊዎችን መጨናነቃችን ነው››ብለዋል፡፡

ከጋምቤላ 20 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በላይኛው ናይል አካባቢ የሚገኘው የህክምና ጣቢያው የሚገኝበት ልዩ ቦታው ማዉት ይባላል፡፡ሆስፒታሉ በአካባቢው ለሚገኙ 80.000 ያህል ሰዎች የህክምና እገዛ የሚሰጥ ብቸኛው ስለመሆኑም ተነግሮለታል፡፡

ማናጀሩ በያዝነው ዓመት ብቻ ለ1.600 ጉዳተኞች የቀዶ ህክምና አገልገሎት መስጠቱን አስታውቀዋል፡፡

ምንጭ ኢንተርናሽናል የቀይ መስቀል ኮሚቴ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.