አዲስ አመራር በአዲስ አመት ለአንድነት – አማኑኤል ዘሰላም (ክፍል 1)

መስከረም 2 ቀን 2007

UDJ-300x296«እኔ በአጭር ጊዜ ዉስጥ ወደ እረፍቱ ብሄድ የምመኘው ነው ነገር ስለሆነ፣ አሁንም ለወጣቶቹ አቅማችሁን ባካችሁ ባካችሁ አዳብሩ፤ እኔንን በአስቸኳይ፣ በአስቸኳይ ተኩ ነው የምለው»

ይህን የተናገሩት የአንድነት ሊቀመንበር ኢንጂነር ግዛቸው ሽፈራው ነበሩ፣ ከሰባት ወራት በፊት። ወጣቶችን ወደ አመራሩ በማምጣት ዙሪያ ከአንድነት ራዲዮ ጋር ያደረጉት ቃለ ምልልስን ለማዳመጥ ከዚህ በታች ያለውን ሊንክ ይጫኑ።

ከአንድነት ራዲዮ ጋር የተደረገ ቃለ ምልልስ

ኢንጂነር ግዛቸው ሽፈራው ለትግሉ ብዙ ያበረከቱ መሪ መሆናቸው እንደተጠበቀ፣ የአሁኑ ትውልድ የሚጠብቀዉን የፖለቲካ አመራር መስጠት ግን የከበዳቸው ይመስላል። ከበርካታ ወጣት አመራሮች ጋር ተስማምቶ የመስራት ችግር እያጋጠማቸው ነው። በቅርቡ ከሥራ አስፈጻሚው ኮሚቴ ራሳቸዉን ባገለሉ ከአምስት በላይ በሚሆኑ ወጣት አመራር አባላት ዙሪያ በጀርመን ድምጽ ራዲዮ ተጠይቀው «ከኔ ጋር መስራት አልቻሉም» የሚል ምላሽ ነበር የሰጡት። ወጣት የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ብቻ ሳይሆኑ፣ ሌሎች በርካታ አባላት፣ እንዲሁም ዉጭ ያለው የአንድነት ደጋፊዎች፣ ኢንጂነሩ ትግሉን እንደሚገባው መምራት እንዳልቻሉ እየገለጹ ነው።

ለኢንጂነር ግዛቸው ያለኝ መልእክት፣ ከሰባት ወራት በፊት ለሕዝብ የገቡትን ቃል እንዲያከብሩ ነው። «ለወጣቶቹ አቅማችሁን ባካችሁ ባካችሁ አዳብሩ፤ እኔንን በአስቸኳይ፣ በአስቸኳይ ተኩ ነው የምለው» ብለው በሕዝብ ፊት የገቡትን ቃል የማያከብሩ ከሆነ፣ ከዚህ በኋላ የሚናገሩትን፣ አባላት፣ ደግፊዎች እንዲሁም ሕዝቡ እንዴት ሊቀበላቸው ይቻላል ? ቃላቸውን በማይጠብቁ መሪዎች ነው የሚመራው በሚልስ አንድነት አይጎዳም ወይ ? አንድ በሉ።

ኢንጂነር ግዛቸው ከሰባት ወራት በፊት ቃል ስለገቡ ብቻ አይደለም። ለትግሉ አስፈላጊ በመሆኑም ነው፣ በ2007 የአንድነት መሪ መሆን የሌለባቸው። አንድነት የጀመረዉን ሕዝባዊ እንቅስቃሴ ከግብ ለማድረስ ትልቅ ሕዝባዊ ድጋፍ ያስፈልገዋል። ጠንካራ የፋይናንስ አቅም ሊኖረው ይገባል። አሁን ካሉት የበለጠ ደጋፊዎቹን ማብዛት የግድ ይኖርበታል። ኮንትሮቨርሻል የሆኑ፣ በብዙዎች ዘንድ ድጋፍ ላይኖራቸው የሚችሉ መሪዎችን ማሰቀመጡ ትልቅ ችግር አለው። አንድ ነገር መርሳት የሌለብን ባለፉት ስድስት ሳምንታት ብቻ አባላትና ደጋፊዎች በኢንጂነር ግዛቸው አመራር ቅር ተሰኝተው፣ የመሸሽ አዝማሚያ እየታየባቸው ነው። ይሄ በአስቸኳይ መስተካከል ያለበት ይመስለኛል። ሁለት በሉ።

ኢንጂነር ግዛቸው ከብዙ የድርጅት መሪዎች ጋር ችግር እንዳለባቸው ይነገራል። በተለይም ከሰማያዊ ፓርቲ አመራሮች ጋር ተደዋዉለው፣ ወይንም ተነጋግረው ማወቃቸውንም እጠራጠራለሁ። እንደ ሰማያዊ ያሉ ድርጅቶችን ወደ ዉህደት ወይንም ትብብር ለማምጣት፣ የተበታተነዉን ትግል ለማሰባብሰ፣ በጣም ያስቸግራል፣ የአንድነት መሪ ኢንጂነር ግዛቸው ሆነው ከቀጠሉ።

ዶር አክሎ ቢራራ «ስርዓቱ የሚሰራውን ያውቃል ። የሚሰራውን የማያውቀው ተቃዋሚው ሆኗል» እንዳሉት፣ ስርዓቱ ተቃዋሚዎች መከፋፈልና መበታተን ዋና ስትራቴጂ አድርጎ እየሰራበት እንደሆነ፣ ተቃዋሚዎች ደግሞ የአገዛዙን ተንኮል ተረድተው፣ ተሰባስቦ የአገዛዙን ተንኮል ለማምከን እንዳልቻሉ ነው የሚነግሩን። የሰማያዊ፣ የአንድነት የመኢአድ በዋናነት ከተቻለም ሌሎችን ማሰባሰብ፣ ለትግሉ በጣም ቁልፍ ነው። እነዚህ ድርጅቶች እንዳይሰባሰቡ የሚፈልገው አገዛዙ ብቻ ነው። በመሆኑም እነዚህ ድርጅቶች እንዳይሰባሰቡ መሰናክል የሆኑ ጉዳዮች በቶሎ መፍትሄ ያስፈልጋቸዋል። ከነዚህ መሰናክሎች አንዱ ደግሞ የኢንጂነር ግዛቸው አመራር ነው። በመሆኑም ትግሉን ለማስተባበር ሲባል የኢንጂነር ግዛቸው መልቀቅ በጣም ቁልፍ ጉዳይ ነው። ሶስት በሉ።

ሌሎች ምክንያቶችን መደርደር ይቻላል። ለአሁን ይበቃኛል። ለአዲሱ አመት ኢንጂነር ግዛቸው ለአገር፣ ለሕዝብና ለትግሉ የሚያበረክቱት ትልቅ አስተዋጾ አለ። እርሱም የዶር ኃይሉ አርዓያን ፈልግ ተከትለው፣ አንድነትን በመሪነት ሳይሆን በሌላ ካፓሲቲ መርዳት ነው።

በ2006 አንድነት የጀመረዉ የሚሊዮኖችን ንቅናቄ ትልቅ ዉጤት አሰመዝግቧል። ከአዲስ አበባ ጀምሮ በአራቱም ማእዘናት በየክልሎቹ ሕዝቡ ለመብቱና ለነጻነቱ እንዲነሳ ከማድረግ የበለጠ ህዝባዊ እንቅሳሴ የለም። ይሄንን በደሴ፣ በባህር ዳር፣ በአዳማ፣ በጊዶሌ፣ በደብር ማርቆስ፣ በአዲስ አበባ አይተናል። ይሄ ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ መቀጠል አለበት። የአንድነት አባላትን ደጋፊዎች እንዲሁም ሕዝቡ ኢነርጃይዝድ መሆናን አለባቸው። አንድነት በአዲስ አመት አዲስ አመራር ያስፈልገዋል። አዲስ አመት ከአዲስ አመራር ጋር !

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.