በጣም የሚያም ነገር ነው – ግርማ ካሳ

“ሽንቴን እንድጠጣ በኃይል ተደርጊያለሁ” ባህሩ ደጉ

“መርማሪዎቻችን ሽንታቸውን በላያች ላይ ሸንተዉብናል”፤ መዉለድ እንዳችል ተደርገናል፤ “ እነ መቶ አለቅ ጌታቸው መኮንን

“ሙሉ ልብሴን እንዳወልቅ ተገድጄ ራቁቴን በወንድ መርማሪዎች ፊቱ ስፖርት እንድሰራ እገደድ ነበር “ የዞን ዘጠኝ ጦማሪ. ማህሌት ፋንታሁን

ኢትዮጵያ የጄኔቫ ኮንቬሽን ፈራሚ ናት ። በኮንቬሽኑ ያሉትን አለም አቀፍ ሕግጋቶች የማክበር ግዴታ አለባት። “መረጃዎች ለማግኘት ሲባል ሆን ተብሎ በሰው ላይ የሚፈጸም፣ በአካልና በስነ ልቦና ላይ የሚደርስ፣ ማናቸውም አይነት ጉዳት እና ስቃይ ቶርቸር ይባላል” ሲል የጄኔቫ ኮንቬንሽን አንቀጽ አንድ በግልፅ ያሰቀምጣል። በአንቀጽ አራት ደግሞ ኮንቬሽኑን የፈረሙ አገራት ቶርቸርን የሚከለከል፣ ቶርቸር የፈጸሙና እንዲፈጸም መመሪያ የሰጡትን የሚቀጣ ጠንካራ ሕግ እንዲያወጡም ያዛል። በአጭሩ ቶርቸር በአለም አቀፍ ሕግ የሚያስጠይቅ ወንጀል ነው።

PPየኢትዮጵያ ሕገ መንግስት አንቀጽ አሥራ ስምንት ንኡስ አንቀስ አንድ “ ማንኛውም ዜጋ ጭካኔ የተሞላበት፣ ስብእናዉን የሚደፍር፣ ኢሰብአዊ ተግባር (cruel, inhuman or degrading treatment) አይፈጸምበትም” ይላል። አንቀጽ አሥር ንኡስ አንቀጽ አምስት ደግሞ “ ማንኛው ዜጋ በኃይል ጥፋተኛነቱን እንዲያምን (forced confessions or admissions ) ማድረግ የተከለከለ ነው። በዚህ ሁኔታ የሚቀርብ ማንኛዉም መረጃ በሕግ ፊት ተቀባይነት አይኖረውም” ይላል። አንቀጽ ሃያ አንድ ንኡስ አንቀጽ አንድ “ በእሥር የሚገኝ ማንኛውም ዜጋ ሰብአዊ መብቱን ባልተዳፈረ መልኩ ሰብአዊ መብቱ ይጠብቃል “ ይላል።

እንግዲህ የአለም አቀፍም ሆነ የኢትዮጵያ ህግ የሚለው ይሄ ነው። ሆኖም በተግባር ግን በአገራችን ኢትዮጵያ እየተፈጸመ ያለው ፈጽሞ የተለየ ነው። “ሕገ መንግስቱ ወረቀት ብቻ” እያሉ የአዲስ አበባ ሰልፈኞች እንደተናገሩት።

ገዢዎቻችን ሰዎች ሳይሆኑ ሰሞኑን አንድ የአሜሪካ የቀድሞ አፈጉባዬ የተናገሩትን አባባል ልዋስና “ ስይጣን ስጋ ለብሶ “ ( Lucifer in a flesh) ናቸው።

ባህሩ ደጉ ይባላል። “ሽብርተኛ” ተብሎ በነዘላለም ወርቅአገኘው መዝግብ ዉስጥ የተከሰሰ ነው። ፍርድ ቤት ቀርቦ የደረሰበትን ተናገረ። ለጆሮ፣ ለሰሚ የሚሰቀጥጥ። “ራቁቴን እንድሆን ተገድጄ ራሴን መቆጣጠር እስኪያቅተኝ ድረስ ተደብድቢያለሁ። ሽንቴን እንድጠጣ በኃይል ተደርጊያለሁ” ነበር ያለው።

መቶ አለቃ ጌታቸው መኮንን ፣ እንዲሁም በርሳቸው ስም ባለ መዝገብ ዉስጥ የታሰሩ ፣ እንደ አቶ ተስፋዬ ታሪኩ፣ አግባው ሰጠኝ ..ያሉ ከጎንደር እና ከጎጃም የመጡ፣ የመኢአድ፣ የሰማያዊ እና የአንድነት እስረኞች ለፍርድ ቤት ተመሳሳይ ብሶት ነው ያቀረቡት። መርማሪዎች በላያቸው ላይ ሽንት እንደሚሸኑባቸው። ያ ብች አይደለም፤ ራቁታቸውን እንዲሆኑ ተደርገው፣ የወንድ ብልቶታቸው ላይ የሁለት ሊትር ዉሃ ጠርሙስ አስረው እያንጠለጠሉ ያሰቃዩዋቸው ነበር። የብዙዎች በዚህ መልኩ ስለተጎዱ መዉለድ እንደማይችሉ ነው እስረኞቹ ለፍርድ ቤት የተናገሩት።

“ሙሉ ልብሴን እንዳወልቅ ተገድጄ ራቁቴን በወንድ መርማሪዎች ፊቱ ስፖርት እንድሰራ እገደድ ነበር። ሴትነተሽ እንዲህ ከሚዋረድ አመጽ እንዳስነሳሽ እመኚ ተብያለሁ” ሥትል የዞን ዘጠኝ ጦማሪ ማህሌት ፋንትሁን፣ ለሰብአዊ መብት ጉብዬ ገልጻለች።

ጓደኛው ኤዶም ካሳዬ ከርሷ የተለየ ነገር አላለችም። “በተለምዶው ከምመረመርበት ቢሮ ዉጭ አንደኛ ፎቅ አዳራሽ ዉስጥ ለምርመራ ተወስጄ ልብሴን እንዳወልቅ እና የተለያዩ ለመናገር የሚከብዱ ስፖራትዊ እንቅስቃሴዎች እንድሰራ ተገድጃለሁ። እንዲህ ከምትዋረጂ አምጽ ልናስነሳ ነበር ብለሽ አታምኚም እያለ ይመታኝ ነበር” ስትል ነው የደረሰባት ኢሰብአዊ፣ ኢሞራል እና ሰይጣናዊ ተግባራት ያጋለጠቸው።

እንግዲህ በኢትዮጵያ እሥር ቤቶች እየሆነ ያለው ይሄ ነው። መርማሪዎቹ በቀጥታ በአቶ ጌታቸው አስፋ የደህነት ሃላፊ መመሪያ እየተቀበሉ፣የአለም አቀፍም ሆነ የአገሪቷን ሕግ እየጣሱ በወገኖቻችን ላይ ለሰሚ፣ ለተመልካች አስደንጋጭ የሆነ፣ ለባህላችንን በጣም እንግዳ የሆነና ፈጽሞ የራቀ የለየለት የጭራቅ ሥራ ነው እየሠሩ ያሉት። እንግዲህ የዛሬይቱ የወያኔዎች ኢትዮጵያ ይሄንን ነው የምትመስለው። በጣም ያሳዝናል፤ በጣም ያበሳጫል።በጣምም ያማል።

ግን የበለጠ የሚያሳዝነው ሌላ ነገር ነው። እንደ ሕዝብ እንደ አገር ፣ እንዲህ አይነት ለመስማት የሚከብድ ወንጀል አይደለም ከወንጀል በላይ የሆነ ጭካኔ እየተፈጸመ የምንታገስ ደካማዎች መሆናችን።

ከዚህ የበለጠ ዉርድት ከየት ነው የሚመጣው ? ከዚህ የበለጠ ሞት ምን አለ ? እነዚህ ሰዎች እኮ ከእንስሳት ሁሉ በታች እየቆጠሩን እኮ የሚቀልዱብን ? እነዚህ ሰዎች እኮ እንደ ኳስ ነው እየተጫወቱብን ያሉት ? እነዚህ ሰዎች እኮ ከማርስ ወይንም ከጁፒተር የመጡ ከኛ በላይ ኃይል ያላቸው (supermen) የተለዩ ፍጥረታት አይደሉም። እንደኛው ሁለት እጆች፣ ሁለት እግሮች, ሁለት ጆሮዎች ..ያሏቸው ናቸው። ታዲይ ለምንድን ነው የምንፈራቸው ? ለምንድን ነው በነርሱ ፊት ራሳችንን እንደ ትንሽ እና አቅም እንደሌለው የምንቆጠረው ? ለምንድነው ነው በአይምሮዋችን እና በሳይኮሎጂ እያታለሉን እንዲጫወቱበን ፣ ፈርተናቸው አንገት ደፍተን እንድንኖር የምንፈቅድላቸው?

እንግዲህ ከልባችን ይሄ መሆን የለበትም፤ ይሄ መቆም አለበት የምንል ብስጭታችንን እና ንዴታችችን ወደ ተግባር እንለዉጠው። መደራጀትና በጋራ በአንድነት የዲያብሎስን ዘዉድ እናፍርስ ።

እንችላለን። ከአሜሪካኖች አንጠብቅ። ከሻእቢያ አንጠበቅ፤ ለምን ከሻእቢያ ጀርባ ያለው ዲያብሎስ ነውና። ባሩዳ ሳናሸት በሰላም ለውጥ ማምጣት እንችላለን። እነሩስ ጥቂቶች ናቸው። እኛ ሚሊዮኖች ነን።

አንዳንድ አፍቃሪ ወያኔዎች ይኖራሉ፤ ከዚህ በላይ ያስቀመጥኳቸውን ለማመን የሚከብዳቸው። አዎን እዉነት ታማለች። ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች በይፋ በፍርድ ቤት የተናገሩትን ነው የጻፍኩት። እነዚህ ወያኔን የሚደግፉ፣ ትንሽም ቢሆን ሕሊና ካላቸው፣ የአቋም መሽጋሽሸግ ያደርጋሉ ብዬ አስባለሁ። ካላደረጉ ግን እነርሱም ራሳቸው ዲያብሎስ በስጋ (Lucifer in a flesh ) ናቸው።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.