ገጣሚ ፋሲል ተካልኝ መሳሪያ በታጠቁ ሲቪሎች መደብደቡን ገለጸ

getami

(ሳተናው) ደራሲ ገጣሚና ኮሜዲያን ፋሲል ተካልኝ አደሬ በማህበራዊ ገጽ (ፌስ ቡክ) ባቀረበው ጽሁፉ በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አቅራቢያ መሳሪያ በታጠቁ አምስት ሰዎች መደብደቡን ይፋ በማድረግ ለዜጎቹ ደህንነት የሚጨነቅ መንግስት የሌለኝ በመሆኑም ማንንም አልከስም በማለት ምሬቱን አስቀምጧል፡፡

ከታች የሰፈረው ፋሲል በፌስ ቡክ ገጹ ሁኔታውን ለመግለጽ የተጠቀመበት ጽሁፍ ነው፡፡

ሚያዚያ 6 ቀን 2008 ዓ/ም በግምት ከምሽቱ 4 ሰዓት (ከአዲስ አበባ ሬስቱራንት ጀርባ) አዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አቅራቢያ አካባቢ መሣሪያ ያነገቱ አምስት ሰዎች ተረባርበው ደበደቡኝ፡፡ራሴን ሳትኩ፡፡ከዚህ በኋላ የሆነውንና የተደረገውን አላውቅም፡፡ ስነቃና ራሴን ሳውቅ ሆስፒታል ውስጥ ድንክ አልጋ በመሰለና ቁመቱ በረዘመ ስትሬቸር ላይ ተኝቼያለሁ፡፡ በግራ እጄ አይበሉባ ግሉኮስ ተሰክቷል፡፡ ማን አመጣኝ? ፣ እንዴት መጣሁ? ለማስታወስ ሞከርኩ፡፡ ዳሩ ግን ማስታወስ የቻልኩት ራሴን እስክስት የነበረውን ብቻ ነው፡።

በነጋታው ሆስፒታል የተኛሁበት ተኝቼ ካለሁበት ድንገተኛ ክፍል ድረስ በመምጣት ሲናገር እንዳደመጥሁት የፖሊስ ቃል ከሆነ ሸራተን ምግብ ቤት አካባቢ መንገድ ላይ ወድቄ እንዳገኙኘኝና ወደ ራስ ደስታ ዳምጠው ሆስፒታል ይዘውኝ እንደመጡ ነው፡፡ ማለዳ ላይ የተለያዩ ወጣት ሐኪሞች የተካተቱበትና በአንድ አንጋፋ ሐኪም በሚመራ ቡድን ተጎበኘሁ፡፡ በጉብኝቱ መሪ ሐኪም ምን እንደሚሰማኝ ተጠየቅሁ፡፡ምላሽ ሰጠሁ፡፡ ጉሉኮሱ እንዲነቀልልኝና ወደ ጥርስ ህክምና ክፍል እንድሄድ ትዕዛዝ ሰጡ፡፡ወጡ፡፡እንደወጡ ወደ ጥርስ ህክምና ተወስጄ ተመረመርኩ፡፡ ተመርምሬም መድኃኒት ታዘዘልኝ፡፡ በመጨረሻም በሕይወት ወደ ቤቴ ለመግባት ችያለሁ፡፡

ይሁን እንጂ በጎድን አጥንቴና በጀርባዬ ላይ ከባድ ጉዳት ደርሷል፡፡ ሆስፒታል እስክወሰድ ድረስ መንገድ ላይ ወድቄ በነበርኩበት ሰዓት ብዙ ደም ፈሶኛል፡፡በዚህም ምክንያት እስካሁን ያዞረኛል፡፡ሁለት የግራና የቀኝ የላይኛው መንጋጋ ጥርሶቼ ተነቃንቀዋል፡፡ የላይኛውና የፊት ለፊቱ አራት ሰው ሰራሽና ከታች የሚገኙ ሁለት የፊት ለፊት በድምሩ ስድስት ጥርሶቼ ሙሉ ለሙሉ ወልቀዋል፡፡

በተጨማሪም በወቅቱ አድርጌ የነበረውን ሸራ ጫማን ጨምሮ ለጡዘት ቁጥር 2 የግጥም መድበል የተሰናዱ የተለያዩ ግጥሞችና ሌሎች ጽሑፎችን የያዘውን ተንቀሳቃሽ ስልኬን በሺዎች የሚቆጠር ገንዘብ ( ጥቂት የተለያዩ ውጭ ሀገራት የገንዘብ ኖቶች ያሉበት) የተለያዩ መታወቂያዎችንና የኤ.ቲ.ኤም ካርድ ይዞ የነበር ቦርሳዬ ተወስዷል፡፡

የሆነው ሆኖ በሀገራችን የዜግነት ክብር ይሉት ሐረግ ያለው በብሔራዊ መዝሙር ውስጥ ነው እንጂ በገሐድ እንደሌለ በተለያዩ አጋጣሚዎች ከማረጋገጥ ባሻገር መንግስት ተብዬውም ለሥልጣኑና ለሥርዓቱ እንጂ

ለዜጎቹ ጥበቃ እንደማያደርግ እንደዚሁም ደንታ ቢስና ግድ የለሽ መሆኑን አውቃለሁ፡፡ስለዚህ ፍትህ አገኛለሁ ብዬ ማንንም አልከስም፡፡ከማንም መፍትሔ አልጠብቅምም፡፡በዚህ አጋጣሚ ከዚህ ከሰፊው መንደር መጥፋቴን ተከትላችሁ፣አለመኖሬ አሳስቧችሁ፣በስልክም ሆነ በውስጥ መስመር ለጠየቃችሁኝ በሙሉ ልባዊ ምሥጋናዬን አቀርባለሁ፡፡

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.