ኤርሚያስ አመልጋ ‹‹በማይገናኝና ሊሆን በማይችል ነገር መታሰሬ ያሳፍራል››አሉ

ermias_tekle

(ሳተናው)  ፖሊስ የአቶ ኤርሚያስ አመልጋን ጉዳይ በሚመረምርበት ወቅት ተጨማሪ የምርመራ ጊዜን የሚጠይቅ ሐሰተኛ ሰነድ ማግኘቱን በመግለጽ በዋስትና እንዳይለቀቁ በመጠየቁ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ተሰጥቶት የተጠርጣሪው የዋስትና መብት ለጊዜው እንዲታገድ መደረጉ አይዘነጋም፡፡

ለፖሊስ የተሰጠው ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ በመጠናቀቁና የፍርድ ቤት ቀጠሮ በመድረሱ ፖሊስ አርብ ዕለት ኤርሚያስን በመያዝ ችሎት ተገኝቶ ነበር፡፡ፖሊስ በድጋሚ ምርመራውን ባለማጠናቀቁና ሌሎች ግብረ አበሮቻቸውን ለመያዝ ባለመቻሉ ፍርድ ቤቱን ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ቢጠይቅም ተከልክሏል፡፡

ፖሊስ ጉዳዩን ሲያብራራም  የአቶ ኤርሚያስ አመልጋ ስም የሠፈረበት ሐሰተኛ ሊብሬ ማግኝቱን ሲያስረዳም ዳኛው ‹‹ አዲስ የሠራህውንና በቀጣይ የምትሠራውን አስረዳ፤›› በማለት  አቋርጠውታል፡፡ ፖሊስ  የመኪናው ሊብሬ ሐሰተኛ ሆኖ መገኘት  ከሐሰተኛ የኮንስትራክሽን ሥራ ፈቃድ ጋርም እንደሚገናኝ መጠርጠሩን አስታውቋል፡፡ በመሆኑም ለሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ደብዳቤ መላኩን፣ሐሰተኛ ሊብሬውን በሚመለከትም ለትራንስፖርት ባለሥልጣን ደብዳቤ መጻፉን በማስረዳት  ሥራው ከሌሎች ግብረ አበሮች ጋር የተሠራ በመሆኑ ግብረ አበሮችን መያዝ፣ የምስክርነት ቃል መቀበልና  የአቶ ኤርሚያስን አሻራ ማስነሳት እንደሚቀረው በመግለጽ ተጨማሪ የ14 ቀናት ጊዜ እንዲሰጠው  ጠይቆ ነበር፡፡

ተጠርጣሪው አቶ ኤርሚያስ አመልጋ በበኩላቸው ‹‹ተገኘ የተባለው ሐሰተኛ ሊብሬ ላይ የእኔ ፎቶ የለም፡፡ እሱስ ፎርጂድ ቢሆን? በሆነ ባልሆነው፣ በማይገናኝና ሊሆን በማይችል ነገር መታሰሬ ያሳፍራል›› ብለዋል፡፡ የኮንስትራክሽን ሥራ ፈቃድ ለማውጣት አንዱ መሥፈርት ገልባጭ ተሽከርካሪዎችን ማቅረብ ከመሆኑ ጋር ተገናኝቶ መጠራጠራቸውን ባይቃወሙም፣ በተጠረጠሩበት ሊብሬ የተገኘው ተሽከርካሪ ፒካፕ አይሱዙ ከመሆኑ አንፃርና ፎርጅድ የተባለው ሊብሬ የሳቸው መሆን አለመሆኑ ሳይረጋገጥ በእስር ላይ እንዲቆዩ መደረጋቸው ተገቢ አለመሆኑን ገልጸዋል፡፡ ተሽከርካሪውም ከአምስት ዓመታት በፊት በ2002 ዓ.ም. መሸጡን ለማሳየት ‹‹ይኸው ሰነዱ›› በማለት ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል፡፡

ፍርድ ቤቱ የግራ ቀኙን ክርክር ከሰማና ለአሥር ደቂቃ ረፍት ወስዶ በጽሕፈት ቤት ከተወያየ በኋላ በሰጠው ብይን እንደገለጸው፣ ተጠርጣሪው ሐሰተኛ ሊብሬ በማከራየት ከ30,000 እስከ 50,000 ብር አግኝተዋል፡፡ ይኼ ደግሞ ድርጊቱ እውነት ሆኖ ቢገኝ ከ100,000 ብር ያነሰ በመሆኑ ከአሥር ዓመት በላይ አያስቀጣም፡፡ በመሆኑም ዋስትና ሊያስከለክል ስለማይችል በአሥር ሺሕ ብር ዋስ እንዲፈቱ መፍቀዱን አሳውቋል፡፡

 

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.