ረዳት አብራሪ ኃይለመድህን አበራ የአብራሪነት ፈቃዱ ቢሰረዝም በነጻ ተሰናበተ

Hailemedehin-Abera

(ሳተናው) በዛሬው ዕለት በስዊዘርላንድ ፍርድ ቤት ለውሳኔ ተቀጥሮ በነበረው በረዳት አብራሪ ኃይለመድህን አበራ ጉዳይ ችሎት የተገኙት የአብራሪው ህጋዊ ጠበቆች ነበሩ፡፡ኃይለመድህን ቀደም ብሎ ፍርድ ቤቱ በጄኔቫ ካንቶን ጥበቃ ስር እንዳለ የቴራፒ ህክምና እንዲከታተል በማዘዙ አብራሪው ሳይገኝ መቅረቱ ተነግሯል፡፡

የኢትዮጵያዊው አብራሪ ጠበቆች ፍርድ ቤቱን የህግ ደምበኛቸው በነጻ እንዲሰናበት በመጠየቅ እንደምክንያትም ኃይለመድህን በአውሮፕላኑ ተሳፍረው የነበሩትን መንገደኞችንም ሆነ ሰራተኞች የመጉዳት ፍላጎት ያልነበረው መሆኑንና ማንም ጉዳት ሳይደርስበት የመንገደኞቹን አውሮፕላን በሰላም በማሳረፍ እጁን ለመንግስት መስጠቱን አብራርተዋል፡፡

የ40 ዓመቱ ረዳት አብራሪ ጠበቆች ከፍርድ ቤቱ የጠየቁትን ፍትህ በማግኘት ከችሎቱ በድል ወጥተዋል፡፡የኃይለመድህንን ጉዳይ ሲመረምር የቆየው ፍርድ ቤት አብራሪው የፋይናንስ አቅሙ ሲስተካከል ለችሎቱ 3.092 ዶላርና የጠበቆቹን ወጪ መሸፈን እንደሚገባው በማዘዝ የአብራሪነት ፈቃዱ ግን መሰረዙን አስታውቀዋል፡፡

ከሁለት ዓመት በፊት 2006 የካቲት ወር ከአዲስ አበባ ወደ ሮም ይበር በነበረው አውሮፕላን ዋና አብራሪው ወደ መጸዳጃ ቤት እንደገቡ የአብራሪ ክፍሉን በመቆለፍ አውሮፕላኑን መጥለፉን ያስታወቀው ኃይለመድህን ወደ አውሮፓ  የአየር ክልል እንደገባ በሁለት የጣልያንና የፈረንሳይ ጄቶች ተከብቦ ጄኔቭ ላይ ለማረፍ መብቃቱ አይዘነጋም፡፡

202 ሰዎችን አሳፍሮ የነበረው አውሮፕላን በሰላም ካረፈ በኋላ አብራሪው እጁን በመስጠት የፖለቲካ ጥገኝነት ጠይቋል፡፡በስዊዘርላንድ ህግ አብራሪው አውሮፕላን በመጥለፍ ወንጀል እስከ 20 ዓመት በሚደርስ የእስር ቅጣት ሊጣልበት በሚችል ክስ ሊጠየቅ ይችል የነበረ ቢሆንም ዋና አቃቤ ህግ አብራሪው በወቅቱ የአእምሮው ሁኔታ ትክክለኛ ውሳኔ ለማሳለፍ የሚያስችለው አልነበረም በማለቱ በመወሰኑ የስነ አእምሮ ድጋፍ እንዲያገኝ አድርጓል፡፡

ኃይለመድህን በሌለበት በኢትዮጵያ ክስ የተከፈተበት ሲሆንም ጉዳዩን ሲመለከት የቆየው ፍርድ ቤት ባለፈው ዓመት የመጋቢት ወር 19 ዓመት ከስድስት ወር የእስር ቅጣት ያስተላለፈበት መሆኑን ማስታወቁ አይዘነጋም፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.