አያ አዳነና አቶ ጋሰለ ለምን ተጣሉ? (በላይነህ አባተ)

(abatebelai@yahoo.com)

Commentአያ አዳነና አቶ ጋሰለ ወርቅ አምባ በምትባል መንደር በ፲፱፷ዎቹ መጀመሪያ ይኖሩ ነበር፡፡ አያ አዳነ እንደ ችፍርግ ያጠረች፤ እንደ ጭራም የቀጠነች ነገር ግን በብልኻትና በዘዴ የምትታወቅ ጎበዝ ነበረች፡፡ ባገሩ ባህል ሰው ከአካሉ ቀለል ከአእምሮው ግን ረቀቅ ሲልና በጥበብ ወይም በጀግንነት ሲታወቅ አንቺ እየተባለ በሴትኛ ስለሚጠራ አያ አዳነም ባካሏ ችፍርግነት፣ በብልኻቷና በዘዴዎቿ አንቺ እየተባለች ትጠራ ነበር፡፡ አቶ ጋሰለ በተቃራኒው ቁመቱ እንደ ተመቸው ግራር የወጣ፤ አካሉም በሙስና ኬክ ተዝፈጠፈጠ እንደሚባለው መቶ አለቃ ግርማ ባይሆንም በሕዝብ ደም ጠበደለ እንደሚባለው አባ ዱላ ግድንግድ ነበር፡፡ አቶ ጋሰለ እንደ አባ ዱላ ከአካሉ የገዘፈውን ያህል ከአእምሮው ቀጭጮ ሐሳብ እሚያጥረው፤ ብልኻትና ዘዴ ሲያልፉም እማይነኩት እንደ ባቄላ ንክር እየተባለ ይታማ ነበር፡፡ ይህ ብልኻትና ዘዴ ያልነካኩት አቶ ጋሰለ ተከራክሮ ማሸነፍ ስለማይችል በምዕራባውያን ለሎሌነት ከወንበር እንደተጎለቱት ያፍሪካ አምባገነኖች ስሜቱን እሚገልጠው በጡንቻ ነበር፡፡

ላቶ ጋሰለ እናቱ እማማ ወለቴ ያወጡለት ስም አረሩ ነበር፡፡ እማማ ወለቴ አረሩ ለምን እንዳሉት ባይታወቅም አቶ ጋሰለ በቅባት እንደሚወለወለው አቶ ሙጋቤ የተወቀጠ ኑግ ስለሚመስል መልኩን ለመግለጽ እንደነበር ማህበረሰቡ ይገመታል፡፡ እንደ አጋጣሚ በዚሁ አቶ ጋሰለና አያ አዳነ በሚኖሩባት ዘመን አረሩ እሚባል አለሌ አህያም በወርቅ አምባ ይኖር ነበር፡፡ አህያው አረሩ በቆዳው ቀለም እንደ አቶ ጋሰለ የተወቀጠ ኑግ ቢመስልም ቁመቱ እንደ አያ አዳነ አጭር ነበር፡፡ አህያው አረሩ ቁመቱ እንደ አያ አዳነ ቢያጥርም የአካሉ ጥንካሬ ግን እንደ አቶ ጋሰለ የደነደነ ነበር፡፡ አካለ ደንዳናው አህያው አረሩ እንኳን ተራ አህዮችን የጠነጠኑ አለሌዎችን በእንክሻና በእርግጫ ልክ እሚያስገባ ወቢ የተፋው አምባ ገነን አለሌ ነበር፡፡

አለሌው አረሩ በአካል ጥንካሬው ካቶ ጋሰለ ቢመሳሰልም ከእንሰሳነቱ በተጨማሪ በሁለት ነገሮች ከአቶ ጋሰለ ይለይ ነበር፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ አቶ ጋሰለ እንደ ድንጋይ ዝም ያለ ሲሆን አህያው አረሩ ግን እንደ ፍየል ለፍልፎ እማይደክም አለሌ ነበር፡፡ እንዲያውም አህያው አረሩ የሚታወቀው በማክላላት ችሎታው ነበር፡፡ አረሩ “ሃ! ሃ!! ሃ! ሁም!” እያለ ድምፁን አንዴ ከፍ ሌላ ግዜ ዝቅ መልሶ ከፍ እንደገና ዝቅ እያደረገ ምንግጭሉን ወደ ሰማይ ቀስሮ በመረዋ ድምጹ ሲያክላላ የጎጃምን፣ የቤጌምድርንና የወሎን ገዳማት አዳርሰው የዜማ መምህር የሆኑትን መሪጌታ ዲበኩሉን ያስንቅ ነበር፡፡ ይህ መረዋው የአረሩ ድምጽ ሳይሰማ ውሎ ካደረ የመንደሩ አድባርና ቆሌዎች እንደሚቆጡ ይገመት ነበር፡፡ በሁለተኛ ደረጃ አቶ ጋሰለ ለሚስቱ ያለው ታማኝነት በቁርባን ኖረው በቁርባን ያለፉትን  የክቡር ሀዲስ አለማየሁን ያህል ባይሆንም በመንደሩ በምሳሌነት እሚጠቀስ ነበር፡፡ አህያው አረሩ በተቃራኒው ከቢል ክሊንተን፣ ከቄስ ታደሰና “አባ ጳውሎስ” ተቀቧቸው አንዳንድ ጳጳሳት የባሰ ራሱን መቆጣጠር እማይችል ሐጅ ነበር፡፡ በዚህ ለሰው የተደነገጉትን አስርቱ ቃላትን ብቻ ሳይሆን ለአለሌዎች የተወሰኑትን ገደቦች በሚጥስ ባህሪውም አረሩ እንኳን በወረቅ አምባ ባጎራባች መንደሮችም ይታወቅ ነበር፡፡ በሰፈር በመንደሩ ጥቁር አህያ በተወለደ ቁጥር “የአረሩ ሥራ ውጤት” እየተባለ ይወራ ነበር፡፡

በሰፈር በመንደሩ ዝናን ካተረፈው አህያው አረሩ ለመለየት ይሁን ወይም ለሌላ ጉዳይ አቶ ጋሰለ ለአርባ ዓመታት ሲጠራበት የኖረውን  አረሩ የተባለውን ስሙን በጋሰለ ቀየረው፡፡ የአረሩ ወደ ጋሰለ መቀየር ዛሬ በስማቸው እየተሸማቀቁ “ለመጥራት እንዲቀል፣ ላማሳጠር፣ ለመሰልጠን፣ ለቁልምጫ ወዘተርፈ” በሚል ሰበብ ፈረንጅ ለመምሰል አትጠገብን ቲጂ፣ ሚካኤልን ማይክ፣ ዮሐንስን ጆን፣ ቢልልኝን ቢል፣ ሉሊትን ሊሊ ወዘተርፈ እያሉ ምንነታቸውን ከሚገድሉት ግብዞች ጋር እሚወዳደር አልነበረም፡፡ ከእነዚህ ግብዞች በተለየ መንገድ የድሮው አቶ አረሩ ያሁኑ አቶ ጋሰለ የቀየረው አንዱን ያበሻ ስም በሌላ ነበር፡፡ ይህም ቢሆን ብዙው የሰፈሩ ሕዝብ የእማማ ወለቴ ልጅ አረሩ ስሙን በመቀየሩ ደስተኛ አልነበረም፡። ደስተኛ ባይሆንም አብዛኛው የሰፈሩ ሕዝብ ያቶ ጋሰለን መብት ለመጠበቅ ጋሰለ እያለ ይጠራው ነበር፡፡ አብዛኛው ሕዝብ አዲሱን ስም ቢለምደውም ኢትዮጵያ እሚለው ቃል ላንቃውን እንደሚጠረቅመው ለገሰ ዜናዊ ሁሉ ጋሰለ እሚለው ስም “ስምን መላክ ያዋጣል!” እያለች የምትከራከረውን ያያ አዳነን ጉረሮ ያንቀው ጀመር፡፡ አያ አዳነ “ደሞ አረሩ ብሎ እሚገሰላ ጀግና! ለዚህ ቆሞ ለሚሄድ ግንድ አረሩም ሲበዛበት ነው!” እያለች አቶ ጋሰለን አረሩ ብላ መጥራቱን ቀጠለች፡፡ ባያ አዳነ እምቢተኝነት ያልተደሰተው የድሮው አረሩ ያሁኑ አቶ ጋሰለ “አዳነ ጋሰለ ብሎ ታልጠራኝ ምላሱን እቆርጠዋለሁ” እያለ ማስፈራራት ጀመረ፡፡ ይህንን ማስፈራራት የሰሙ የሰፈሩ ሰዎችም አቶ ጋሰለን “ብልኻተኛዋ አዳነ በብልኻት ትጥልሃለች!” ሲሉትም “ተነብልኻቷ እንደ ኳስ ጠቅልዬ ተጣልኳት ብልሃቷ ተየት ይመጣል” እያለ መዛት ቀጠለ፡፡ አቶ ጋሰለ ከዛቻውም በተጨማሪ አያ አዳነን ባገኛት ቁጥር የግርማ ቸሩን የመሰለውን ክንዱንና ቡጢውን እያሳዬ ሊያስፈራርት ቢሞክርም አያ አዳነ አረሩ ብላ ከመጥራት አልቆጠብ አለች ፡፡

አያ አዳነ የንብረት ድሃ ነገር ግን ባበሻነቷ የምትኮሯ ተጀንና መሬቱን ስትረግጠው ዝሆን ያሓከለች እሚመስላት ጎምላላ ዜጋ ነበረች፡፡ የታህሳስ ገብርኤል ለት አያ አዳነ በእንዶድ ፍትው ብሎ የታጠበውን ሙታንታዋንና ጥቢቆዋን ግጥም አድርጋ፤ በአመድ እሽት ተደርጎ የታጠበውን ኩታዋን ከአፍንጫዋ ጣል አርጋ፤ ቅቤ የጠጣ ጅንፋም ከዘራዋን ከመሬት ችክል፣ ንቅል እያደረገች እየተጀነነች ማበር ልትጠጣ ስታልፍ አቶ ጋሰለ አህያው አረሩ ከሚግጥበት መስክ ጋቢውን አንሰርፎ ድንኳን መስሎ ተቀምጦ አየችው፡፡ አያ አዳነ አቶ ጋሰለንና አረሩን እልፍ እንዳለች አለቃ ገብረ ሃና አሉ እንደሚባለው “ደህና ዋላችሁ?” ስትል ሰላምታ ሰጠችና “ዘመድ ተዘመዱ፤ አህያም ታመዱ!” እሚለውን ተረት ተረተች፡፡ አህያው አረሩ ሰላምታውና ተረቱ ገብቶት ይሁን የሚያክላላበት ሰዓት ደርሶ “ሃ!..ሃ!! ..ሃ!!!” እያለ በኃይል ሲጮህ ሽብርተኛው አሻንጉሊት አገዛዝ መርካቶ ያፈነዳውን ቦንብ ያህል በታች አነጠሰው፡፡ ንጥሻውን የሰማችው አያ አዳነም “የትኛው አረሩ እንዳነጠሰው ባለውቅም ይማርህ!” ብላ ሳትጨርስ  ባያ አዳነ ንግግር የተበሳጨው አቶ ጋሰለ እንደ ግስላ ተገስልቶና ዓይኑን አጉረጥጦ ከንፈሩን እያንቀጠቀጠ አያ አዳነን ገፈተራት፡፡ አያ አዳነም “እኔ ግፊያ አላውቅም ለግፊያም አልተፈጠርኩም” ስትል ያቶ ጋሰለ ብስጭት እንደ ጋስ ምድጃ ተንቦገቦገ፡፡ ብስጭት ያንቦገቦገው አቶ ጋሰለ ያያ አዳነን ማጅራት ወተት እንደ ደፋች ድመት ይዞ ከነብልኻቷ ከመሬት አነጠፈና ትንፋሿን እያዳመጠ ቀጠቀጣት፡፡ ይህንን ቅጥቀጣ የተመለከቱ ገላጋዮች ተጋግዘው አቶ ጋሰለን እንደ ወደቀ ዛፍ ካያ አዳነ ገላ አነሱላት፡፡ ፊቷ የሰርግ ደጋሿን የወይዘሮ ጠጅቱን ድልህ፤ አይኖቿ ደግሞ የስልክ መጥለፊያ ሽቦ እሚቀጥል ቻይናዊ አይኖችን የመሰሉት አያ አዳነ በአልሞት ባይ ተጋድይነት “ያኛው አረሩ ቦንብ ሲያፈነዳ ይኸኛው አረሩ ደንብሮ እኔ ላይ ወደቀ” እያለች ለገላጋዮች ሰበብ ስትደረድር አቶ ጋሰለ ስሩ እንደ ነገለ ግራር እንደገና ሊወድቅባት ተገለገለ፡፡ ነገር ግን ገላጋዮች መከታ ሆነው አያ አዳነን አዳኑና ሁለቱንም ወደ እየቤታቸው አደረሷቸው፡፡

ይህ ያያ አዳነና ያቶ ጋሰለ ጠብ በድፍን መንደሩ ተወራ፡፡ የመንደሩ ሕዝብም እንዲታረቁ ባያ አዳነና ባቶ ጋሰለ ተጽእኖ አሳደረና ወዲያው ሶስት ሽማግሌዎች መረጠ፡፡ የተመረጡት ሽማግሌዎች ተበዳይን ከበዳይ እግር በማንበርከክ ሽምግልና ከገደሉት ከአታላዩ ጠምጣሚ ኤፍሬም ይስሀቅና፤ በእግሩ ሊገዛን ካቀደውና ዲሞክራሲ ቅንጦት እሚል ጠረን ከሰፊ አፉ ከወጣው ኃይሌ ገብረስላሴ ፍጹም የተለዩ ነበሩ፡፡ አያ አዳነና አቶ ጋሰለን ለማስታረቅ የተመረጡት ሽማግሌዎች ህሊናቸውን ከአድሎና ከሆዳቸው አላቀው መለኮትን እያስታወሱ በተቻላቸው መጠን ሚዛናዊ ፍርድን የሚሰጡ ነበሩ፡፡ እነዚህ ብቁ ሽማግሌዎችም አያ አዳነንና አቶ ጋሰለን ለየብቻ ደጋግመው ካነጋገሩ በኋላ የታህሳስ ማርያም ለት ፊት ለፊት እንዲገናኙ አደረጉ፡፡ አያ አዳነ ግራሶ የተቀባ የመሰለውን ፊቷን በእራፊ ሸፍና በግራ ገጥ ከሽማግሌዎች ፊት ቁጭ አለች፡፡ አቶ ጋሰለ ደግሞ በልሃ ልበልሃ እንደሚከራከር ጋቢውን መስቀልኛ አጣፍቶ በቀኝ ገጥ ሊቆም ሲል ሽማግሎቹ “ያለኸው ፍርድ ቤት አደለም” ብለው እንዲቀመጥ ጋበዙት፡፡

የመኸል ሽማግሌው በሰላም አስጀምሮ በሰላም እንዲያስጨርሳቸው ጸሎት ካደረሱ በኋላ አያ አዳነና አቶ ጋሰለን ለየብቻ ካነጋገሯቸው በላይ እሚጨምሩት ካለ በለሆስታ እንዲናገሩ ጋበዟቸው፡፡ አያ አዳነ “እህ ..እህ” ብላ ጉረሮዋን ጠራረገችና “እኔ አሁንም ስምን መላክና ወላጅ ያወጣል” ብዬ እማምን ሰው ነኝ አለች፡፡ “አዳነ ስምን መላክ ያዋጣዋልን ስታስብ ስም አይወድቅበት የለውንም አስተውል” አሉ በተነፋነፈ ድምፅ በተለምዶ “የትግሬ ዘመቻ” በሚባለው ሁለተኛው የጣሊያን ወረራ ዘምተው አፍንጫቸውን በፋሽሽት ጥይት ያጡት የቀኝ ሽማግሌው ብላታ ተገኘ፡፡ ብላታ ተገኝ በመቀጠልም “በዘመትኩበት በትግሬ ዘመቻ ወቅት ኃይለስላሴ ጉግሳ እሚባሉ የጦር መሪ ነበሩ፡፡ ጦርነቱ ሲፋፋም እኒህ ሰው አገራቸውንና ሕዝባቸውን ከዱና ጦራቸውን ይዘው ለወራሪው ጥሊያን አድረው እኛን ወገኖቻቸውን አስፈጁ፡፡ እንደምታውቁት ኃይለስላሴ ማለት የስላሶች፣ የክርስቶስ፣ የእግዚአብሔር ኃይል ማለት ነው፡፡ እና አዳነ የእኒህን ከሐዲ ስምም መላክ አውጥቶታል ልትለን ነው?” ብለው ሲያፋጥጡት “እማማ ወለቴ ግን እንኳን አገራቸውንና ሕዝባቸውን ጌቶቻቸውን እንኳ ክደው ስለማያውቁ ያወጡት ስም ይጸድቃል” ሲል መለሰ አያ አዳነ ላለመሸነፍ፡፡

አቶ ጋሰለ ጠበኛው አያ አዳነ ሳይቀር “እማማ ወለቴ ከድተው አያውቁም” በማለቱና እንደ ኃይለስላሴ ጉግሳ ልጆች የከሀዲ ልጅ ባለመሆኑ ቢደሰትም “እማማ ወለቴ ያወጡት ስም ይጸድቃል” በሚለው በመከፋቱ በስጨት ብሎ “ለመሆኑ እሱ አዳነ ተብሎ እንኳን ሌላውን ራሱንስ መቼ አዳነ!” ሲል ካቶ ጋሰለ አእምሮ ይህ ሐሳብ ይወጣል ተብሎ ስለማይጠበቅ እንኳን ሽማግሌዎች አያ አዳነም ተገርሞ በፍንጭት ጥርሶቹ ፈርጠም አለ፡፡ ቀጥሎም “በፊትም በጡንቻው ሳይሆን  በአይምሮው እንደዚህ ቢያስብ ጠብ አይኖርም ነበር” አለ፡፡ ባቶ ጋሰለ ያልተጠበቀ መልስ የተፈጠረው ፈገግታ ሰፍኖ የነበረውን የጠብ ደመና ገፈፈውና ሽማግሌዎቹ “ያለፈውን ተውና ለየብቻ ባነጋገርናችሁ መሰረት ወደፊት አቶ አዳነ ያቶ ጋሰለን የስም መብት አክብሮ በፈለገው ስም እንዲጠራው፤ አቶ ጋሰለም ለቁስል ማሳከሚያ ላቶ አዳነ አምሳ ብር እንዲሰጠው” ሲሉ የሽምግልና ፍርዳቸውን ሰጡ፡፡

በሽማግሌዎች አስቀድሞ በተነገረው መሰረት አቶ ጋሰለ ተበድሮ ያመጣውን አምሳ ብር ላያ አዳነ ሰጠ፡፡ አያ አዳነና አቶ ጋሰለ የሽማግሌዎችን ጉልበት ሳሙ፤ እርሰ በርሳቸውም ጉንጭ ለጉንጭ ተሳሳሙ፡፡ ጉንጭ ለጉንጭ በሚሳሳሙበት ሰዓትም አያ አዳነ በሹክሹክታ “ቢሻህ ግደለኝ፤ አሁንም አረሩ እንጅ ጋሰለ አልልህም” አለው፡፡ ሰላም የሰፈነ መስሎት የተደሰተው አቶ ጋሰለ ባያ አዳነ ያቋም ጥናትና እምቢተኝነት ተረብሾ እንደገና ሊገሰላ ሲያስብ አያ አዳነ “”በፊትም በጡንቻው ሳይሆን  በአይምሮው እንደዚህ ቢያስብ ጠብ አይኖርም” ያለው ትዝ አለውና  ወደ አእምሮው ተመልሶ አረሩ የተባለበትን ምክንያት መሬት መሬቱን እያዬ እንዲህ አስረዳው፡፡ “ወንድሜ አዳነ! እናቴ የሰየመችኝ ጋሰለ ብላ ነበር፡፡ አረሩ እንድትለኝ የወሰነ እድሜ ልኳን በገረድነት ያገለገለችው ጌታዋ ነው፡፡ እኔም የፈለኩት እናቴ ያወጣችልኝን ስም ነው፤ ጋሰለ ያለችኝም በጌትነትና በሎሌነት ግፋዊ ትስስር እንድገሰላ ነው፡፡ ስለዚህ ያመጥኩት ጉልበቷን ሲመጠምጥ ኖሮ ስታረጅ ባልጦራት ጌታዋና በግፍ ላይ ነው” ብሎ ሳይጨርስ አያ አዳነ ድንጋይ ተሸከመና ከእግሩ ወድቆ እያነባ “ጋሰለ ይቅርታ አድርግልኝ!’ ብሎ ይቅርታ ጠየቀው፡፡ አቶ ጋሰለም እንባ እየተናነቀው ድንጋዩን ካያ አዳነ ትከሻ አንስቶ ራሱ ተሸከመና “አዳነ አንተም ይቅርታ አድርግልኝ!” አለው፡፡ አያ አዳነ ድንጋዩን ከአቶ ጋሰለ ትከሻ አንስቶ መሬት አስቀመጠና ላርባ ዓመታት ተለያይተው እንደተገናኙ እናትና ልጅ እንባ እያወረዱ ተቃቅፈው ተሳሳሙ፡፡

 

ግንቦት ሁለት ሺ ስምንት ዓ.ም.

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.