የሆላንዱ ሼር ኩባንያ በኢትዮጵያ ውስጥ ትልቁ የአበባ አምራጭ ኩባንያ ነው

kenyaflorists -satenaw ድርጅቱ በፈርንጆች አቆጣጠር በ2004 ከኬንያ ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት 1 ሺ የእግር ኳስ ሜዳ በሚያክል መሬት ላይ የአበባ እርሻ ልማት ስራ ጀምሯል። ድርጅቱ በአመት 1 ቢሊዮን 200 ሚሊዮን የጽጌረዳ አበባ ወደ ሆላንድ ይልካል። አበባዎቹን ለማሳደግ ደግሞ በእያመቱ 2 ሺ የኦሎምፒክ የመዋኛ ገንዳ የሚሞላ ውሃ ይጠቀማል። በሊትር ሲሰላ ደግሞ 5 ቢሊዮን ሊትር ውሃ ይደርሳል።

ሼር የአበባ አምራች ኩባንያ በኢትዮጵያ ውስጥ እየፈጸመ ያለውን ድርጊት ያጋለጠው በሆላንድ ታዋቂ የሆነው ዜምብላ የተባለው ዝግጅት ነው። ዝግጅቱ በኔዘርላንድ የቴሌቪዥን ጣቢያ በቀጥታ የተላለፈ ሲሆን፣ ጋዜጠኛ ዮስ ቫነ ዶንጀን ወደ ኢትዮጵያ ተጉዞ የተለያዩ ሰዎችን አነጋግሯል።

በሚስተር ፒተር ባርን ሆርን የተቋቋመው ሼር ኩባንያ 10 ሺ የሚሆኑ ሰራተኞች አሉት። የሰራተኞቹ አማካኝ ወርሃዊ ክፍያ 30 ዩሮ ወይም 750 ብር ገደማ ቢሆንም፣ ሰራተኞች ለምግብ እና ለቤት ኪራይ ከፍለው ኑሮአቸውን መግፋት እንዳልቻሉ በፊልሙ ላይ ይናገራሉ። 200 ሚሊዮን ዩሮ የሚጠጋ ሃብት ያለው ኩባንያ ለሰራተኞቹ የሚከፍለው ገንዘብ አነስተኛ መሆኑ ብቻ ሳይሆን፣ ለሆላንድ ዜጎችና ለኢትዮጵያውያን የሚከፍለው ገንዘብ ልዩነት እጅግ አስደንጋጭ መሆኑ በዘገባው ላይ ተመልክቷል። በድርጅቱ ውስጥ የሚሰሩ 42 የሆላንድ ዜጎች ወይም በመደበኛ አጠራራቸው ደቾች በአመት የሚከፈላቸው ክፍያ 9 ሺ 664 ኢትዮጵያውያን ከሚያገኙት ክፍያ በ800 ሺ ዩሮ ይበልጣል። ኩባንያው ለ42ቱ የሆላንድ ዜጎች በአመት 3 ሚሊዮን 300 ሺ ዩሮ ደሞዝ የከፈላቸው ሲሆን፣ ለቀሪዎቹ 9 ሺ 664 ት ኢትዮጵያውያን ሰራተኞች ደግሞ 2 ሚሊዮን 500 ሺ ዩሮ ከፍሏል።

በዘገባው ላይ የቀረበው ሌላው አስደንጋጭ ዜና፣ ኩባንያው የሚጠቀምበት የተባይ ማጥፊያ ኬሚካል ለጤና አደገኛ መሆኑ ነው። በርካታ የድርጅቱ ሰራተኞች በኬሚካሉ የተነሳ ከፍተኛ ጉዳት እየደረሰባቸው መሆኑን የተናገሩ ሲሆን፣ በድብቅ ካሜራ የተቀዳው ፊልምም የድርጅቱ ሰራተኞች ለአደጋ መጋለጣቸውን የሚያረጋግጥ ነው።

ኩባንያው በሚጠቀመው ውሃ ምክንያት በአካባቢው ያሉ የውሃ ምንጮች እየደረቁ መምጣታቸውን ነዋሪዎች በምሬት የሚናገሩ ሲሆን፣ ከዚህም አልፎ ድርጅቱ ወደ ዝዋይ ሃይቅ በሚልከው ፍሳሽ የተጠራቀመው ኬሚካል አሳዎችን እየገደላበቸው መሆኑን ኢትዮጵያውያን ለጋዜጠኛው ተናግረዋል።

በዘገባ ፊልሙ የተጋለጠው ሌላው መረጃ ደግሞ ከታክስ ጋር የተያያዘ ሰሆን፣ ይህ ግዝፉ ኩባንያ በፈረንጆች አቆጣጠር በ2011፣ 402 ዩሮ ወይም 7 ሺ 280 ብር፣ በ2012 ፣ 20 ሺ 201 ብር ፣ በ2013 3ሚሊዮን 137 ሺ 942 ብቻ ለመንግስት ታክስ የከፈለ ሲሆን አምናና ታች አምና ታክስ አለመክፈሉ ተጋልጧል። በብዙ መቶዎች የሚቆጠሩ አርሶአደሮች ተፈናቅለው የተቋቋመው የአበባ ኩባንያ፣ ለኢትዮጵያ እያስገኘ ያለው ጥቅም አነስተኛ መሆኑ በዘገባው የተመለከተ ሲሆን፣ ይህንንም ለማሳየት በኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ረሃብ፣ የውሃ እጥረት፣ በልመና የሚተዳደሩ ዜጎችን ሁኔታ የባለሙያዎችን አስተያየት በማከል አቅርቧል።

ዘጋቢ ፊልሙ እንደወጣ ሼር ኩባንያ አፋጣኝ መግለጫ ያወጣ ሲሆን፣ በመግለጫው የቀረበው ዘገባ የተሳሳተ እና ኩባንያውን የማይወክል ነው ብሎአል። ከ6 ሺ ላላነሱ የሰራተኞች ልጆች ትምህርትና ህክምና በነጻ እየሰጠ መሆኑ የገለጸው ሼር፣ የዝዋይን ሃይቅ አለመበከሉንና የውሃ እጥረት እንዲፈጠር አለማድረጉን ገልጿል።
የዚህን ዘገባ ፈልም ተርጉመን የምናቀርብ መሆኑን እንዲሁም ዘገባውን የሰራውን ጋዜጠኛም ለኢሳት ቃለመልልስ ለመስጠት ፈቃደኛ በመሆኑ በቅርቡ እንደምናቀርብ ለመግልጽ እንወዳለን።

ምንጭ፦ ኢሳት

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.