የዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ የአዲሱ ዓመት ምኞት “የኩረጃና የግልበጣ ዘመን ማብቃት አለበት”

ያለፈውን ዓመት ከሁለት አኳያ ነው የምመለከተው፡፡ አንደኛው ከግል አኳያ ሲሆን ሁለተኛው ከሃገራችን ሁኔታ በተለይም ከፖለቲካው አኳያ ነው፡፡ በግል ደረጃ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እያስተማርኩ ነው የከረምኩት፡፡ ቤተሰቦቼ ቦስተን አሜሪካን ይኖራሉ፤ እነሱ ናፍቀውኛል፣ሄጄ ማየት እፈልጋለሁ፡፡

Dagnachewበሀገር ደረጃ የዲሞክራሲ ሂደቱ በጣም አስቸጋሪ ሆኗል፡፡ በተለይ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ካለፉ በኋላ ትንሽ የመደናበር እና የመደናገጥ ሁኔታ በገዢው ፓርቲ ላይ ይስተዋላሉ፡፡ በመሆኑም በአንድ በኩል በአቶ መለስ አለመኖር፣ በሌላ በኩል በምርጫው መቃረብ የተነሳ እቺን ጨቅላና ሙከራ ላይ ያለች “ዲሞክራሲ” ገዥው ፓርቲ መሸከም ያቃተው ይመስላል፡፡ አሁን ደግሞ ወጣት ጦማሪያንን እንዳደረገው የሚዲያ ፀሃፊዎችን ማዋከብ ይዟል፡፡ ከ3 ወር በፊት ጦማሪያን ሲታሰሩ በጋዜጠኞች ላይም ሊቀጥል ይችላል ብዬ ነበር፡፡ ይሄም እየሆነ ነው፡፡

አሁን የተፈለገው አንድ ዓይነት ሃሳብ ብቻ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ለሃገር ጥሩ አይደለም፡፡ ኢህአዴጎች ከ20 ዓመት በላይ ሃገሪቱን ካስተዳደሩ በኋላም ራሳቸውን የመተቸት ልማድ አላካበቱም፡፡ አንድ አመራር ደግሞ ራሱን የመተቸትና ሌሎችም እንዲተቹት የመፈቀድ ባህሉን ካላጠናከረ ችግር አለው ማለት ነው፡፡

የአዲስ ዓመት ምኞት ሲባል ብዙ ጊዜ እየተደጋገመ የሚባለው ሰላም ብልፅግና… ነው፡፡ ሰላምና ብልፅግና ዘመን በተቀያየረ ቁጥር ብቻ አይደለም የሚያስፈልገው፡፡ እኔ በአዲሱ ዓመት ወደ ራሳችን ቀልብ እንድንመለስ፣ ኢትዮጵያ ኮራጅና ገልባጭ መሆኗን እንድታቆም ነው የምመኘው፡፡ አሁን ለምሳሌ “EBC” ብሎ መሰየም ምን ማለት ነው? የአማርኛ፤ የኦሮምኛ ወይም ሌላ የአገራችን ቋንቋ ቃል ጠፍቶ ነው? አማርኛን ጠላነው ካሉ ለምን መናገሩን አይተውትም ?! ይሄ የግልበጣና በራስ ያለመተማመን ችግራችንን ፈትሸን ወደአዲሱ ዘመን እንድንሻገር ነው የምፈልገው፡፡ ቲያትሩ፣ ሲኒማው፣ሬዲዮ ፕሮግራሙ ኩረጃ ነው፡፡ ይህ የግልበጣ ዘመን ይቁምና ኢትዮጵያ “ኢትዮጵያ” ትሁን ነው የምለው፡፡ እንግዳ ተቀባይ ነን፣ እንደኛ የሚያምር የለም..ወዘተ እያልን ለራሳችን የተለየ ግምት የምንሰጥባቸውን አባባሎች ማቆም አለብን የትኛውም ሃገር እንግዳ ተቀባይ ነው፡፡ ጥሩ ሃገር፣ ትልቅ ሃገር አለን፣ በዚህ ደረጃ እናስብ፡፡

(አዲስ አድማስ ጋዜጣ፣ መስከረም 10 2007 ዓ.ም)

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.