በመንገዱ … ቀደምቷ የእንጨት ጀልባ ! (ነቢዩ ሲራክ)

በደማሙ የቀይ ባህር ዳርቻ ያለችውን ጀልባ መልኳ ቡናማ ነው … በእንጨት ተገጣጥማ ከተሰራች ከእኔ እድሜ በላይ አስቆጥራለች ፣ አሁን አሁን ግን እርጅታለች ፣ የእንጨት ጀልባዋ ጓዟን በጫንቃዋ ተሸክማም ባይሆን በሆዷ እያቀፈች የደማምን የባህር ጫፍ ጫፍ እየታከከች ታዳሚውን በማንሸራሸር ከእለት ጉረስ ባለፈ የጌታዋ የጀርባ አጥንት ጭምር ናት … በእንጨት ተቀፍቅፋ አምራ ከተሰራች ጀምሮ ከባህር ሉል እስከ ባህር ውስጥ አሳ ማጥመጃ አገልግላለች ፣ የባህሩ ጀልባ መጓጓዣ በዘመነ ስነ ጥበብ ሲተካም የእንጨቷ ጀልባ ከባህሩ ዳርና ዳር አልተወገደችም … ለባለቤቶቿ እንደ ቀደመው ብቸኛ አገልጋይ ሆና መረብ ተዘርግቶባት አሳው ከማጥመዱ ይለቅ የቀደምት አሰራር ጥበቡ የሚስባቸው የስልጡኑ ትውልዶችን ቀልብ እየሳች የባህረ ዳር ዳር ይጎበኝባታል !

የባህር ሉልና የአሳ ብቸኛ ማጥመጃና መሰብሰቢያ ሆና የገፋችው ያ የቀደመው ጊዜ አክትሞ ቀን ወጥቶላት ደረቷን ገልብጣ ወደ ሰው መጫኛ ስትሸጋገር ያመጣቸው ሲሳይ በወጣትነቷ ካስገባችው የተሻለ እንጅ ያነሰ አይደለም ። ለባለቤቶቿ ደግሞ በረቀቀው ስነ ጥበብ ከተሰሩት ዘመናዊ ጀልባዎች ይበልጥ የእሷ ነገር አይሆንላቸውም ። እሷም ለእነሱ አትታልትምና ፣ ይወዷታል… !

ዛሬ ዛሬ በምክንያት በምክንያቱ ከሚወዷት ባለቤቶቿ በተጨማሪ የሚወዷት ጎብኝዎች አሏት ፣ የሚወዷት ሰራተኞችም ጭምር አሏት ! የደላቸው ጎብኝዎች ሩቁን ዘመን ያዩባታል ፣ የቅድመ አያቶቻቸውን ብርታትና ትጋት የህይዎት መሰናክልና እዚህ የደረሰውን ስኬት በእንጨቷ ጀልባ በምናብም ቢሆን ታሪኳ እየተነገራቸው ከአዘመነኞች ዳጎስ ያለ ገንዘብ እየከፈሉ በኩራት ይመለከቷታል …

የእንጨት ጀልባዋ ከልጅነት እስከ እውቀት አገልግላ ባለቤቶቿን የናጠጡ ሃብታሞች አድርጋ እዚህ ያደረሰችው የእንጨት ጀልባ ለእኔ ቢጤ መጤ አፍሪካውያን ከአምስት ያላነሱ ስደተኞችም ከእለት ጉርስ ባለፈ ትደጉማቸው ፣ ትጠቅማቸዋለችና ለጀልባዋ ያላቸው ፍቅር ወደር የለውም … ከእለት ጉርስ አልፎ ሀገር ቤት ያሉ ወገኖቻቸውን ይደግፉባታልና ከባለቤቱ በተሻለ መንገድ ይንከባከቧታል …

እኔም የተፍረገረገው እንጨት ሳያስፈራኝ ፣ ተሳፍሬባታለሁ …ሞልቶ ሳይጎድል እየሆነ ባለው ያልረካች ነፍሴን ለስለስ ያለው ማዕበል ወዲህና ወዲያ ውሃው ሲንጣት ትፍስህትን አግኝቻለሁ ! … በስራ ደክሞ የዋለ አዕምሮየ የሚፈልገው አንዳች ነገር አለ … ሰላምና ፍቅር … ሰላምና ፍቅር ደግሞ ያለው ምነም ከማያውቁት ልጆች ሳቅና ጨዋታ ውስጥ ነው ፣ ልጆች ደግሞ ለሰአታት ቢሆን ሩቅ ነው ያሉ …

በምናብ ከራሴ ጋር አንዱን አንዱን ሳወጣ ሳወርድ በአካል ብኖርም መንፈሴን ወደ ባህሩ አሸግሬ ልኬ መስጠሜ የታወቀኝ ዘግይቶ ነበር …. የሆነውን ረስቸ በአዲስና በሌለ መንፈስ ራሴን ላዝናና እታገላለሁ … ከተንጣለለው ጸጥ ረጭ ላለው ቀይ ባህር ላይ ደጋግሜ ራሴን ጥየለታለሁ … የእንጨቷ ጀልባ በተረጋገው ለስላሳ ማዕብል ወዲህና ወዲህ ዘንበል ፣ ቀና እያደረገ ነፍሴን ሲንጣት እናቴ ብላቴና ልጇን በጀርባዋ በአንቀልባዋ አድርጋ ጀርባውን እየተጠበጠበች የምታባብለኝ ያህል ስሜት ተሰማኝ … በእናቴ መንፈስ ነጉጀ ነቃሁ ! ተስፋና ጽናት አንገቴን ቀና አደረገው … የእንጨቷ ጀልባ እናቴን አስታውሳ ነፍሴን አስደስታዋለችና እኔም የደማሟን ቀደምት ባለታሪክ ፣ የቀድሞ ደሃ የዛሬ ባለጸጋ ንብረት የሆነችውን የእንጨት ጀልባ ወድጃታለሁ … ከጥቂት ሰአታት በኋላም ተጓዥ ነኝ ፣ ባህር እወዳለሁና ለባህሩ ስተነፋፍስና ስብተከተክ ጠያራው እንዳያመልጠኝ ብፈራም ዛሬም መንገዴን ለእሱ ሰጥቸ በመንገዱ እጓዛለሁ …

ከባህሩ ዳርቻ ፣ ደማም …

ሰላም

ነቢዩ ሲራክ
ህዳር 8 ቀን 2008 ዓም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.