ሃይማኖተኛን ሰው ፖለቲከኛ እንዳይሆን የሚከለክለው ሕግ አለን?

አንዳንዶቻቹህ የዚህን ጽሑፍ ከፊል ከዓመታት በፊት ማስነበቤን ታስታውሱ ይሆናል፡፡ ሌሎች መልስ የሚፈልጉ ተጓዳኝ ዐበይት ጉዳዮች በመኖራቸው የእነሱም ምላሽ ጨምሬበት እንዲህ አቅርቤላቹሀለሁ መልካም ንባብ፡-

ፖለቲካ የሚለው ቃል የባዕድ ቃል ነው ትርጉሙ እምነተ-አሥተዳደር ማለት ነው:: አንድ መንግሥት ይበጀኛል ሕዝቡን ሀገሩን አሥተዳድርበታለሁ ብሎ የሚያምንበት የአሥተዳደር ስልት፣ አስተሳሰብ፣ መንገድ፣ ዘይቤ ማለት ነው፡፡

ይህ ፖለቲካ የሚለው ቃል ከባዕድ ከመምጣቱም ቃሉንና አስተሳሰቡን በመልካም ጎኑ ቀምሰን ሳናጣጥመው ወዲያውኑ ምሬቱን ስላሳየን ለቃሉና ለተግባሩ መልካም ስሜት የለንም፡፡ አንድ አባባልም ፈጥረንለት ከሥነ-ቃሎቻችን ቀላቅለንለታል “ፖለቲካንና ኮረንቲን በሩቁ!” የሚል፡፡ በእርግጥ ግን ፖለቲካን ርቆ መራቅ ይቻላል?

ለዚህ ቃልና ለተግባሩ ባለን ጥሩ ያልሆነ አመለካከት የተነሣ ፖለቲካ ያለውን የሀገርንና የሕዝብን እጣ ፈንታ የመወሰንን ያህል ግዙፍ አቅምና ሚና ዘንግተን ለፖለቲካና ለፖለቲከኛነት ጭንቅላታችን ውስጥ የጭራቅ ምሥል ሥለን በመፍራት በመጥላትና በመሸሽ በዜግነታችን ለሀገራችን ልናበረክተው የሚገባንን ተግባርና አገልግሎት እንዳናበረክት፣ እንደ ሰው ለራሳችን ለግላችንም ልናስገኝ የሚገባንን መብትና ጥቅም እንዳናገኝ፣ ሀገሪቱም በፖለቲካ ምክንያት ከሚከሰቱ ትብትብ ችግሮች እንዳትወጣ አድርጓል፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ ይህ ሁኔታ ማለትም ሕዝቡ ፖለቲካን መጥላቱ ከፖለቲካ መራቁ መገለሉ ገዥዎች በመድረኩ ላይ ያለጠያቂ እንደፈለጉ እንዲፋንኑ ምቹ ሁኔታን ፈጥሮላቸዋል፡፡ ይህ ሁኔታ ሕዝቡን ለፖለቲካ በሚሰጠው የተሳሳተ ግንዛቤ ሊያስጨብጠው ከሚችሉት ልፈፋዎች (propaganda) ከሚፈጠር ፍርሐት የተነሣ በርከት ያሉ የመገለያ ሰበቦችን እንዲፈጥር አስገድዶታል፡፡

ሕዝባችን አሁን ያለበትን አስቸጋሪ ሁኔታ ማየት ለዚህ በቂ ምሥክር ነው፡፡ ሕዝቡ ሀብታም ከድሀ ሳይለይ የግፍ አገዛዙ ከልክ በላይ ያንገፈገፈው ቢሆንም ሊከፍለው የሚገባውን ዋጋ ከፍሎ የተነጠቀውን ነጻነት በእጁ ለመጨበጥ ያለው ቁርጠኝነት እጅግ ደካማ ሆኗል፡፡ ከዚያ ይልቅ በዝምታ ግፍን ተንጋሎ መጋት የመረጠ አስመስሎታል፡፡  ይህ ትዝብት የተጋነነ መስሎ የሚታየው ዜጋ ይኖራል ብየ አልገምትም፡፡ ነገር ግን ሁሉም ሊባል በሚችል ደረጃ ይህ ሁኔታ እንዳለ ያምንና ለድካማችን፣ ለስንፍናችን፣ ለፍርሐታችን፣ ለዳተኝነታችን ምክንያት የእናታችንን ቀሚስ የምንጠቅስ ነን፡፡ ይሄንን ጉዳይ ተጨባጭነት ባለው ምሳሌ ለማስረዳት ልሞክር፡፡

እኔ ለአቅመ አዳም ከመድረሴ በፊት ጀምሮ ማለትም ገና የ2ኛ ደረጃ ተማሪ እያለሁ ጀምሮ ባቅሜ ግፍና በደልን በመቃወም ትግል አሳልፌአለሁ፡፡ በዚህ ጊዜ ውስጥ ብዙ የታዘብኳቸው ነገሮች አሉ እንደኔና እኔን እንደመሰሉ ሁሉ የሚፈጸሙ ግፍና በደሎችን እነሱም ይቃወሙ ዘንድ ከምንጠይቃቸው ወገኖች ከፊሎቹ “አይ እኔ ፈሪ ነኝ፣ ራስ ወዳድ ነኝ፣ የግል ጥቅሜን አሳዳጅ ነኝ የሌላው አይገደኝም!” ላለማለት ዘወትር የሚናገሩት ነገር ነበር አለም፡፡ “አይ ይሄ ፖለቲካ ነው አያገባኝም!” የሚል በተለይ ቤተክርስቲያን አካባቢ ያሉትና ሃይማኖተኛነትን በተሳሳተ መንገድ የተረዱ ሰዎች፡፡

እነኝህ ሰዎች በደሉን ያደረሱት ፖለቲከኞች እንደሆኑና በደሉም የደረሰውም በቤተክርስቲያን ላይ ሆኖም እያለ እንኳ ያንን የደረሰ ጥቃት በደል መቃወም ለእነሱ በአማኝነታቸው ሊወጡት የሚገባ መብትን ማስከበር ሳይሆን ፖለቲካ (እምነተ አሥተዳደር) ነው፡፡ የግንዛቤያቸው መወለጋገድ እጅግ አስገራሚ ነው፡፡

እንግዲህ ይህ ችግር የሚፈጠረው አንደኛው ከላይ እንዳልኩት ራስን ከኃላፊነት ለማሸሽ፣ ግዴታንና ኃላፊነትን ላለመወጣት ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ በእርግጥም ፖለቲካ ማለት ምን ማለት እንደሆነ ካላመረዳትም ነው፡፡ እንደ እውነቱ ከሆነ ማንኛውም ዜጋ ወዶም ይሁን ተገዶ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ፖለቲካዊ ጉዳይ ይመለከተዋል ይገደዋል፡፡ ይመስለናል እንጅ የእያንዳንዱ ዜጋ ሕይዎት ለደቂቃም ቢሆን ከፖለቲካ ውጪ ሆኖ አያውቅም፡፡

ፖለቲካ ነው አያገባኝም ብሎ ማለት በሌላ አማርኛ እኔ ዜጋ አይደለሁም ሀገርንም ሆነ ሕዝብን እራሱን ግለሰቡን ጨምሮ እንደፈለጉ እንዳሻቸው ቢያደርጉ አይመለከተኝም እንደማለት ነው፡፡ እንዲህ ብሎ የሚል ሰው ደግሞ በዜግነቱ ሊያገኛቸው የሚችላቸውን ወይም የሚገባውን ማለትም የመሥራት፣ የመማር፣ የመኖር ወዘተረፈ. መብቶችና ጥቅሞች ለእኔ አይገቡኝም አልጠይቅም አልፈልግም ማለቱ እንደሆነ ያለመረዳትን ያህል ድንቁርና የተጫነው አባባልና አስተሳሰብም ነው፡፡

አንድ ሃይማኖተኛ ወይም መንፈሳዊ ሰው ሃይማኖተኛ ወይም መንፈሳዊ ቢሆንም በሌላ በኩል ደግሞ ዜጋም ነው፡፡ ሃይማኖተኛነቱ ዜጋነቱን አይከለክለውም ዜጋነቱም ሃይማኖተኛነቱን አይቃወመውም፡፡ እነዚህ ጉዳዮች በተለይ በኢትዮጵያ ሲሆን ደግሞ (ምክንያቱም ኢትዮጵያ በመጽሐፍ ቅዱስና በፍልስፍና መጸሐፍትም ጭምር ሀገረ እግዚአብሔርነቷ እንደመመስከሩ ተጣጥመው ያሉ እንጅ የሚቃረኑ ባለመሆናቸው ነው) ስለሆነም ለኢትዮጵያ የሚከፈል ዋጋ ሁሉ ለእግዚአብሔር የተከፈለ ዋጋ ማለት ነው፡፡ ለኢትዮጵያ መጋደል ለእግዚአብሔር መጋደል ማለት ነው፡፡ በነፍስም ዋጋ ያሰጣል፡፡

እንግዲህ አንድ የሃይማኖት ሰው ሊወጣቸው የሚገባቸው ሁለት የማንነት መገለጫዎች አሉት ማለት ነው፡፡ የሃይማኖት ሰው ቢሆንም እንደዜጋነቱ ደግሞ ሀገሪቱ እንዲያደርግላትና እንዲወጣላት ከሱ የምትጠብቀው ብዙ ግዴታዎች ደግሞ አሉ፡፡ ይሄም ስለገባቸው ነው አባቶቻችን ለሀገራቸው ታቦት ተሸክመው ጦርነት ይወጡ ይዋደቁ ይሞቱላትም የነበሩትና የሀገራችንን ነጻነት ሉዓላዊነትና ክብር አስጠብቀው ሊቆዩ የቻሉት፡፡

እንደምታስታውሱት ከሁለት ሦስት ዓመታት በፊት ጀምሮ (2006ዓ.ም. መነሻ በማድረግ ወደኋላ) ስደተኛውን ሲኖዶስ ለመመለስ ወይም ሀገር ቤት ካሉ አባቶች ጋር ለማስታረቅ ሰፊ እንቅስቃሴ እየተደረገ በነበረበት ጊዜ በመሀሉ አባ ጳውሎስ ዐረፉ፡፡ “አይ አግዚአብሔር እሱ ባወቀ ነገሩን አስተካከለው!” ተብሎ ሲታሰብ አጋጣሚው ወይም ፈጣሪ የፈጠረው ምቹ ሁኔታ ለወያኔዎቹ አልተመቻቸው ኖሮ ወያኔ ጣልቃ ገብቶ ሽምግልናውን አሰናከለና የእርቅ ድርድሩ ለማሰናከሉ አንድ ሰበብ ፈጥሮ አባቶች እንዲናገሩት አደረገ፡፡ መግለጫ አወጡና ስደተኞቹን አባቶች “ከቤተክርስቲያን ጋር ግንኙነት የሌለውን ፖለቲካዊ ጉዳይ ያነሣሉ ስለሆነም የእርቅ ድርድሩ መሰናክል ገጥሞታል ወይም ወደፊት ማስቀጠል አልቻልንም!” አሉ ፡፡

በወቅቱ ይህ መግለጫ እጅግ ካስቆጣቸውና ካሳዘናቸው ወገኖች አንዱ ነበርኩና ወዲያውኑ በመጽሔት፣ በመካነ ድሮች ይሄንን የተሳሳተና ሸፍጥ ያዘለ ፍረጃ የሀገር ቤቶቹ አባቶች የዘነጉትን የታሪክ እማኝነት በማንሣት መግለጫቸውን እርቃኑን ያስቀረ ጽሑፍ ለንባብ አበቃሁ፡፡

ለራሳቸው ለስደተኛው ሲኖዶስም በመካነ ድራቸው በኩል እንዲደርሳቸው በማድረግ እነዚህ የዛሬዎቹ ‹‹አባቶች›› ፖለቲካ ብለው ያሉት ነገር የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ባለባት ታሪካዊ ኃላፊነት ወይም ባለ አደራነት ከኦሪት ጀምራ ከዚያም በፊት ከሕገ ልቡና ጀምራ ስትወጣው ስትከውነው የኖረችው ከአምላክ የተጣለባት ኃላፊነትና የተቀደሰ ተግባር መሆኑን፣ ነገሥታትን በዕውቀትና በጥበብ በሥነ-ምግባር አሳድጋ ቀብታ ስታነግሥ የኖረች መሆኗን ወደ ኋላ ደግሞ ማለትም በ13ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ሲሦ መንግሥት ተሰጥቷት እስከ ቅርብ ጊዜ 20ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ቆይቶ ሀገራችን ለየት ባለ መልኩ እንዳለባት የጠላት ብዛት ሁሉ በፈተናዎች የተዋጠች ብትሆንም ይህች ሀገር ፈተናዎቿን ተቋቁማ ህልውናዋን በማስቀጠል እረገድ ቤተክርስቲያን ከሀገሪቱ ነጻነት እስከ ሥልጣኔዋ የማይተካ ቁልፍ ሚና የተጫወተችና ኃላፊነቷን በሚገባ የተወጣች መሆኗን፤ አሁን በስደት ላይ ያሉ አባቶችን የሀገርንና የሕዝብን ጉዳይ በማንሣታቸው ፖለቲከኞች ብለው የሚነቅፏቸው የሚኮንኗቸው ከሆነ እየነቀፉ ያሉት እነሱን ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ብለው “ድሀ ተበደለ ፍርድ ተጓደለ” እያሉ የተጋደሉትንና መከራ የተቀበሉትን በስንክሳሩ የሚዘከሩ ቅዱሳን አባቶቻችንን፤ ባጠቃላይ የቤተክርስቲያኗን ተጋድሎ እና ታሪክ መሆኑን “ድሀ ተበደለ ፍርድ ተጓደለ” ብሎ ስለ ተበደሉ ፍትሕ ስለተነፈጉ ወገኖች ስለ እውነት መጮህ መሟገት ጌታ በእያንዳንዱ ክርስቲያን ጫንቃ ላይ የጫነውን አምላካዊ ኃላፊነትን መወጣትና ሐዋርያዊ ግዴታም መሆኑን፣ ከሐዋርያት ሕይዎትና ከክርስቶስ ቃል ጋር በማመሳከር ለዚያ የደነቆረ ፍረጃና ነቀፋ አጥጋቢ ምላሽ እንደሰጠሁ ብዙ ሳይቆዩ ማለትም ከሁለት ሳምንታት በኋላ እስከዚያ ጊዜ ድረስ ፖለቲከኛ ሲሏቸው ይሸማቀቁና በዜግነታቸው የሚሰማቸውን ሁሉ አፋቸውን ሞልተው በሀገራዊ ጉዳይ ላይ ለመናገር ይሳቀቁ የነበሩ ስደተኞቹ አባቶች የጽሑፌን ሐሳብ ሙሉ ለሙሉ በማካተት “እንዲህ እንዲህ በማለታችን ፖለቲከኞች ተባልን፣ እንዲህ እንዲህ ማለት ፖለቲከኛነት ሳይሆን ሐዋርያነት ነው!” የሚል መግለጫ አወጡና ለብዙኃን መገናኛዎች ለቀቁ፡፡

እኔም በእውነት እንዲያ ብዙ ስደክምለት የኖርኩትን አስተሳሰብ ያውም በሲኖዶስ ደረጃ ሲንጸባረቅ የተሰማኝ ደስታ የላቀ ነበር፡፡ ከዚያ በኋላማ እንዲያውም በተለይ ከሀገር ውጭ ያሉ ሰባክያን ይሄንን አስተሳሰብ በደንብ እያንጸባረቁት እንደሆነ በመገናኛ ብዙኃን ሳይቀር እየሰማናቸው ነው፡፡ ጎሽ! እንዲያ ነው ከዚህ በኋላ ፈሪውና ራስ ወዳዱ ለዳተኝነቱ፣ የዜግነት ኃላፊነቱን ላለመወጣቱ የሚጠቅሰው ሌላ ምክንያት ምን እንደሆነ እንግዲህ ደሞ እንሰማለን፡፡

እዚህ ላይ በፊትም ቢሆን እነኝህ ስደተኞቹ አባቶች ይሄንን እውነታ አተውት ወይም ሳያውቁት ቀርተው ነው ማለቴ አይደለም፡፡ ልቦናቸው ይሄንን ሀቅ ስለሚያውቅማ ነው በቂም ባይሆን አምነውበት ለመተግበር ሲሞክሩ የቆዩት፡፡ ነገር ግን በሀገራችን ፖለቲካን ወይም ሀገራዊ ጉዳይን ከዜግነት ግዴታና ከቤተክርስቲያን ለመነጠል ከፋሽስት ጣሊያን ጀምሮ በደርግ በተለይም ደግሞ በወያኔ የተሰበከው ማወናበጃና ማምታቻ በሁሉም ኢትዮጵያዊያን አስተሳሰብ ላይ የተሳሳተ ግንዛቤ እንዳጠላ ሁሉ ይህ ሁኔታ ከባድ ጫና ፈጥሮባቸው “በዜግነታቸው ለሀገራችን ልናበረክት ይገባል!” ብለው የያዙትን ቀናና ትክክለኛ አስተሳሰባቸው ከልብ ወጥቶ ወደ አንደበት ስላልደረሰ ነበር በሀገራዊ ወይም በፖለቲካዊ ጉዳይ ላይ በሚጠሩና በሚከወኑ መድረኮች ተገኝተው ያለ ሀፍረትና መሸማቀቅ እንደ ቀድሞዎቹ ሁሉ የቅርብ የሆኑትንም ማንሣት እንችላለን እንደ አርበኞቹ አቡነ ጴጥሮስ፣ አቡነ ሚካኤል ሁሉ በግንባር ቀደምትነት በወኔና በስሜት ምላት መናገር ያለባቸውን ለመናገር ተሳትፏቸውንም ለማበርከት ይቸገሩ የነበሩት፡፡

አሁንም ቢሆን ገና ይቀራል ይቀራል፡፡ እንደ ሐዋርያትና ሠማዕታት ሁሉ ባለ 30,60,100 ፍሬ ባለ አዝመራ መሆን የፈለገ አባት ወይም የሃይማኖት ሰው ወይም ክርስቲያን ቢኖር መንገዱ ይሄው ነው ሌላ የለምና ያለ ማመንታት በልበ ሙሉነትና በወኔ ስለ እውነት፣ ስለ ፍትሕ፣ ስለ ቤተክርስቲያን፣ ስለ ሕዝብ ተጋደሉ ውጡ በየመድረኩ ተሳተፉ፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ፣ በስንክሳሩና በገድላ ገድሉ የምናስባቸውን የምንዘክራቸውን አባቶችና እናቶችን አስቡ፤ ለዚያ የሠማዕትነት ክብር ሲበቁም ያንን ግፍ በምን ምክንያት እነማን እንዳደረሱባቸው መለስ በሉና ልብ ብላቹህ አጢኑ፡፡

ሃይማኖተኛ ነን ከሚሉ ሰዎች አካባቢ ከሕዝቡም ቢሆን የሚነሣው ሌላኛው ሰበብ ደግሞ “እግዚአብሔር ያመጣውን ምን ማድረግ ይቻላል እሱ ያመጣውን እሱ እስኪመልሰው ዝም ብለን መቀበል ነው እንጅ!” የሚል ነው፡፡

ለአሁኑ ባጭሩ ለመመለስ አንደኛ ነገር “ማንም ሲፈተን  በእግዚአብሔር እፈተናለሁ አይበል እግዚአብሔር በክፉ አይፈትንምና፤ እርሱ ራሱስ ማንንም አይፈትንም፡፡ ነገር ግን እያንዳንዱ በራሱ ምኞት ሲሳብና ሲታለል ይፈተናል፡፡ ከዚህ በኋላ ምኞት ፀንሳ ኃጢአትን ትወልዳለች ኃጢአትም ካደገች በኋላ ሞትን ትወልዳለች” ያዕ. 1÷13-15 ተብሎ መጻፉን ልብ ይሏል፡፡

ሁለተኛ ስኬት የሚገኘው ከጥረት ከግረት ከልፋት መሆኑን አዳምን “ጥረህ ግረህ በግንባርህ ወዝ ብላ እደር” ዘፍ. 3÷19 ባለውና “ሊሠራ የማይወድ አይብላ!”  2ኛተሰ. 3÷8-13 ባለው ቃል እጅና እግርን አጣምሮ ቁጭ ብሎ በማየት የሚገኝ ነገር እንደሌለ እንቅጩን ተናግሯል፡፡ በዚህም ላይ የሚሠሩ እጆችና እግሮች የሚያስብ ጭንቅላት የሰጠን የሚበጀንን ነገር እንደወደድን እንድናደርግበት መሆኑ ይታወቃል፡፡ እስከዛሬም ድረስ በዓለም ታሪክ የሆነውን ብንመለከት ሰዎች በጥረታቸው አንዱ አንዱን ይጥልና ፍላጎቱን ያሳካል አንዱ አንዱን ያነሣል እንጅ እግዚአብሔር እራሱ ወርዶ “እናንተ ይበቃቹሀል ወግዱ! ኑ እናንተ ተቀመጡ!” ብሎ አንዱን ሸኝቶ ሌላውን አምጥቶ አያውቅም፡፡

ነገር ግን በእያንዳንዱ ነገር ላይ የእርሱ ፈቃድ እንዳለበትና አድራጊውም ሥራውን በርትቶ እየሠራ በሚሠራው ነገር ሁሉ የእግዚአብሔር ፈቃድና እረድኤት እንዲኖርበት ወደ ፈጣሪ መለመን መጠየቅ ማሳሰብ እንዳለበት እሙንም ግድም ነው፡፡ ስለተጣረ ብቻ የትም አይደረስምና፡፡

የሀገራችንንም የቅርብ ጊዜ ታሪክ ብናይ ያለው እውነታ ይሄው ነው፡፡ ደርግን የሸኘው እግዚአብሔር መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ ይሁን እንጅ እግዚአብሔር እራሱ ወርዶ ደርግን ከመንበሩ አውርዶ ወያኔን ደግሞ “ና ተቀመጥ!” ብሎ አስቀምጦ አይደለም፡፡ ወያኔን ምክንያት አድርጎ “እግዚአብሔርን አላውቅም አላምንም!” ብሎ በኃይሉ በጉልበት ሲታመን ሲታበይ ሲመካ የነበረውን ደርግ ከዐሥሩ ወታደሮቹ አንዱ ብቻ ታጣቂ ባለመሣሪያ የተቀረው ጀሌ በሆነ ተራ የወያኔ ሠራዊት ደርግን ሸኘው እንጅ፡፡

ለስኬት የበቁበት መንገድ አስነዋሪና የሀገር ክህደት የተሞላበት ቢሆንም ቅሉ በደርግ የተማረሩ ወያኔዎች ወተው ባይታገሉ ኖሮ “አይ እግዚአብሔር ያመጣውን እኛ ምን ማድረግ እንችላለን? እሱ ያመጣውን እሱ ይመልሰው እንጅ!” ብለው እጅ እግራቸውን አጣምረው ቁጭ ቢሉ ኖሮ ደርግን ታግለው ለመጣልና ሥልጣን ለመጨበጥ ለመቆናጠጥ መቻላቸው የሚቻል ይሆን ነበር ወይ? ወይ ደግሞ በይነ-ሕዝባዊ (ዲሞክራሲያዊ) ሥርዓት ኖሮ ተመርጠው ለሥልጣን ካልበቁ በስተቀር ዕድሉን ሊያገኙ አይችሉም ነበር፡፡ በመሆኑም ሰው ማግኘት የፈለገውን ነገር የእግዚአብሔር ፍቃድና ረድኤት ታክሎበት በልፋት በጥረት በትግል ያገኛል እንጅ እጅና እግርን አጣምሮ ቁጭ ካሉበት ከሰማይ ዱብ የሚል ነገር ጨርሶ ምንም ነገር የለም ኖሮም አያውቅም፡፡ እያንዳንድህ በቁምህ ስትቃዥ ኖረህ እንደቃዥህ አፈር ትገባታለህ እንጅ፡፡

ይህ ዑደት እስካሁን እንደነበረ ሁሉ ወደፊትም ይቀጥላል፡፡ በወያኔ የተማረረ ሕዝብ ወያኔ እንዲወገድና ነጻነቱን በእጅ መጨበጥ ማስገባት ከፈለገ ከላይ እንደገለጽኩት ሁሉ ያለው አማራጭ አንድና አንድ ብቻ ነው ተራ ሰበብና ምክንያትን ነቅሎ ጥሎ፣ የፍርሐትንና የራስ ወዳድነትን ማቅ አውልቆ፣ ዋጋ ለመክፈል ተዘጋጅቶ፣ ቆረጥ ቆፍጠን ጨከን ብለህ እከሌስ ለምን? እከሌ… ሳትልና ሳትተያይ በዜግነትህ ማድረግ ስላለብህ እንደምታደርገው ብቻ አምነህና ዐውቀህ መታገል ብቻ!!

ሦስተኛው የሰበበኞች ሰበብ ደግሞ በመሠረተ ሐሳብ ደረጃ ከሁለተኛው ጋራ ተመሳሳይ ሆኖ ነገር ግን ብልጠት አይሉት ድንቁርና የተሞላበት አስገራሚ ሰበብ ነው፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስ በሮሜ መልእክቱ 13÷1-7 ያለውን ይጠቅሱና “ለተሾመው ሁሉ ሰጥ ለበጥ ብለን የመገዛት አምላካዊ ግዴታ አለብን!” ይላሉ፡፡ እጅግ አሳፋሪ ድንቁርናና ነውረኛነትም ነው፡፡ ቃሉን እንይ “ነፍስ ሁሉ በበላይ ላሉ ባለ ሥልጣኖች ይገዛ፡፡ ከእግዚአብሔር ካልተገኘ በቀር ሥልጣን የለምና፤ ያሉትም ባለሥልጣኖች በእግዚአብሔር የተሾሙ ናቸው፡፡ ስለዚህ ባለ ሥልጣንን  የሚቃወም የእግዚአብሔርን ሥርዓት ይቃወማል የሚቃወሙትንም በራሳቸው ላይ ፍርድን ይቀበላሉ፡፡ ገዥዎች ለክፉ አድራጊዎች እንጅ መልካም ለሚደርጉት የሚያስፈሩ አይደሉምና፡፡ ባለ ሥልጣንን እንዳትፈራ ትወዳለህን? መልካሙን አድርግ ከእርሱም ምስጋና ይሆንልሀል፡፡ ለመልካም ነገር ለአንተ የእግዚአብሔር አገልጋይ ነውና፡፡ በከንቱ ግን ሰይፍ አይታጠቅምና ክፉ ብታደርግ ፍራ ቁጣውን ለማሳየት ክፉ አድራጊውን የሚበቀል የእግዚአብሔር አገልጋይ ነውና፡፡ ….ለሁሉም የሚገባውን አስረክቡ ግብር ለሚገባው ግብርን፣ቀረጥ ለሚገባው ቀረጥን፣ መፈራት ለሚገባው መፈራትን፣ ክብር ለሚገባው ክብርን ስጡ” ይላል ቃሉ፡፡

እንግዲህ ይሄንን ቅዱስ ቃል እንዴት ለፍላጎታቸው አጣመው እንደተጠቀሙበት አያቹህ? ቃሉ ምንም በማያሻማና ጥርት ባለ መልኩ ነው የቀረበው፡፡ ቁጥር 3-4 ያለውን ቃል ልብ ብለው ቢመለከቱት ቅዱስ ጳውሎስ ስለ የትኞቹ ባለ ሥልጣኖች ወይም ገዥዎች እየተናገረ እንደሆነ በተረዱ ነበር፡፡ “ገዥዎች ለክፉ አድራጊዎች እንጅ መልካም ለሚያደርጉ የሚያስፈሩ አይደሉምና፡፡ ባለ ሥልጣንን እንዳትፈራ ትወዳለህን? መልካሙን አድርግ ከእርሱም ምስጋና ይሆንልሀል” ቃሉ እንዳለው “ገዥዎች ለክፉ አድራጊዎች እንጅ መልካም ለሚያደርጉ የሚያስፈሩ አይደሉምና” በሚለው ቃል ግልጽ ባለ መልኩ የተናገረው ስለ ቅን ፈራጅና መልካም ምስጉን ነገሥታት ወይም ገዥዎች እንደተናገረ አሳይቷል፡፡

በዘመንኛ አገላለጽ ለፍትሕ ለቆሙ፣ ድሀ ለማይበድሉ ፍርድ ለማያጓድሉ፣ ግፍ ለማይፈጽሙ፣ ለሕዝብ ሁለንተናዊ ጥቅም ለቆሙ ማለቱ እንጅ እጃቸውን በንጹሐን ደም ለሚያጥቡ ግፈኞች ማለቱ እንዳልሆነ ግልጽ ነው ምክንያቱም “መልካም ለሚያደርጉ የሚያስፈሩ አይደሉምና፣ ለመልካም ነገር ለአንተ የእግዚአብሔር አገልጋይ ነውና” ብሏልና ለፍትሕ የቆሙና ወይም ዲሞክራት ለሆኑ መሪዎች መልካም ለሚያደርጉት ማለትም ለሕግ የበላይነት ለሚታገሉት፣ ለሰብአዊ መብቶች ለሚጮሁት፣ ፍርድ ተጓደለ ደሀ ተበደለ እያሉ ስለተበደሉትና መብታቸውን ስለተነፈጉት ለሚጮሁት፣ ግፉና ጭቆናን ለሚቃወሙት ለሚሟገቱት የሚያስፈሩ አይደሉምና ማለት ነው፡፡ እንኳን ሊያስፈሩ ይቅርና ይሄንን በማድረጋቸው ማለትም መልካም ሥራ በመሥራታቸው ፍትሕ እንዲሰፍን በመታገላቸው እንዲያውም “ከእነሱም ምስጋና ይሆንልሀል” በማለት እያወራላቸው ያላቸው ባልሥልጣናት ወይም መንግሥታት ስለ የትኞቹ ዓይነቶች እንደሆነ ግልጽ አድርጓል፡፡

ይሄንን ጉዳይ በሚገባ ለመረዳት በሀገራችን ላይ ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ብናየው ነገሩ ግልጽ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ምክንያቱም በግልጽ እንደምናየው የኛ ባለሥልጣናት ወይም አገዛዙ የሚያስፈሩት ለሕግ የበላይነት ለሚታገሉት፣ የፍትሕ ያለሕ!፣ የመንግሥት ያለህ!፣ የዳኛ ያለህ!፣ የሕግ ያለህ! ለሚሉት፣ ለተጨቆኑት፣ የሰብአዊ መብት እረገጣ ለደረሰባቸው ወገኖች ለሚጮሁት፣ ፍርድ ተጓደለ ድሀ ተበደለ ለሚሉት፣ ግፉና በደል ስለ ደረሰባቸው ምስኪኖች ለሚጮሁት፣ ለሕዝብ ሁለንተናዊ ነጻነት ለሚታገሉት፣ እውነት ለሚናገሩት እንጅ ክፉ ለሚያደርጉት ማለትም ሰብአዊ መብትን ለሚረግጡት፣ ፍርድ ለሚያጓድሉት፣ ለሚጨቁኑት፣ ግፍ ጭቆና ለሚፈጽሙት፣ ለሚመዘብሩት፣ በደል ለሚያደርሱት፣ ፍትሕ ለሚነፍጉት፣ ለሚያንገላቱት እንዳልሆነ የምናውቀው ሀቅ ነው እነኝህ ዓይነቶቹ እንዲያውም የአገዛዙ ጭንቅላት፣ እጅ እግር፣ ሕዋሶች ናቸው፡፡

በመሆኑም እራሳቸው ክፉ አድራጊዎችና መልካም የሚያደርጉትንም የሚያመሰግኑ የሚሸልሙ ሳይሆኑ የሚሳድዱ፣ የሚያስሩ፣ የሚገሉ፣ የገቡበትም ገብተው ድራሻቸውን የሚያጠፉ፣ በንጹሐን ደም የታጠቡና የሚታጠቡ ግፈኞችና በደለኞች የእግዚአብሔር ነፍስ የተጸየፈቻቸው እኩያን ናቸው እንጅ ቃሉ እንዳለው ለእኛ የተሰጡ የእግዚአብሔር አገልጋዮች አይደሉም፡፡

በመሆኑም ይህ የአገዛዝ ሥርዓት የእግዚአብሔር ቃል ከሚልላቸው ባለሥልጣናት ወይም መንግሥታት ዓይነቶቹ በተቃራኒ ያለ መሆኑ ግልጽ ነውና ይሄንን ቃል ለሚጠቅሱ አባዮችና እራሳቸውን ለሚያታልሉ የዋሀን በቃሉ የሚያምኑ ከሆነ ጥቅሱ ላይ በቁጥር 4 ላይ ያለውን ማለትም “ቁጣውን ለማሳየት ክፉ አድራጊውን የሚበቀል የእግዚአብሔር አገልጋይ ነውና” እንዳለ ሁሉ በሀገርና በሕዝብ በቤተክርስቲያንም ላይ ክፉ የሚያደርገውን ወያኔን በመበቀል የእግዚአብሔር አገልጋይ ለመባል እንዲተጉ ማሳሰብ እወዳለሁ፡፡

እናም ቃሉ ምንም የሚያምታታ ነገር የሌለበት ጥርት ባለ መልኩ እንዳስቀመጠው ቅን ፈራጅ ለሆኑት ለሕዝብ ልብ በሉ “ለሕዝብ” ሁለንተናዊ ደኅንነት ሰላምና ጤና ለቆሙት፣ ለሀገር ለሚያስቡት ለሚቆረቆሩት ባለሥልጣናት ማለቱ እንጅ እንደነ ዲዮቅልጥያኖስ፣ መክስምያኖስ በሀገራችን ደግሞ ዮዲት ጉዲት፣ ግራኝ አሕመድ፣ በወረራ መጥቶ ለነበረው ለፋሺስት ጣሊያን ዓይነቶች ሁሉ “ተገዙ እንዳሏቹህ ሁኑ!” ማለቱ አይደለም፡፡ ለእንደነዚህ ዓይነቶቹ እንኳን ልንገዛላቸውና ክብር ልንሰጣቸው የእግዚአብሔር ሰላምታ እንኳን እንዳንሰጣቸው ሐዋርያት ከላይ ያለውን ጥቅስ ጨምሮ በበርካታ ቦታዎች ላይ እያለቀሱም ጭምር አበክረው አስጠንቅቀዋል፡፡ ምክንያቱም ለእነዚህ ዓይነቶቹ አሜን ብለን ብንገዛ፣ አድርጉ ያሉንን ብናደርግ ጣዖት አምላኪያን ወይም አሕዛብ እንሆናለን እንጅ ሃይማኖታችንን ጠብቀን እግዚአብሔርን አምላኪያን ልንሆን አንችልምና፡፡

ከዚሁ ጋር በተያያዘ በክርስቶስ ያመኑ አይሁዶችን ጨምሮ አሁን በዘመናችን እስካሉ ክርስቲያኖች ነን የሚሉ ዘመኑ የወለዳቸው ቡድኖች (መናፍቃን) ድረስ ምን ይላሉ “ክርስቶስ በዚህች ምድር በእግረ ሥጋ 33ዓመት ከ3 ወራት እየተመላለሰ በነበረበት ዘመን በፖለቲካ (በእምነተ አሥተዳደር) ጉዳይ አልገባም ነበርና እኛም የእሱ ተከታይ ክርስቲያኖች በፖለቲካ (በእምነተ አስተዳደር) ጉዳይ መግባት አይገባንም፡፡ ጌታ በወቅቱ በሮማዊያን የቅኝ ግዛት ስር የነበረችውን የተወለደባቸውን የወገኖቹን የአይሁዶች ሀገር እስራኤልን ነጻ ለማውጣት አንዳችም ያደረደው ነገር አልነበረምና” ይላሉ፡፡

አይሁዶች በትንቢት እስራኤልን የሚያድን ንጉሥ እንደሚነግሥ ሲነገርና ሲጠብቁት የነበረ ስለነበር “አዳኝ መሲሕ ክርስቶስ ይመጣል ከባርነት ከግዞት ነጻ ያወጣቹሀል” ኢሳ. 32፤1, 33፤17, ኤር.23፤5 ሲባሉ ስለነበር እነሱን ይመስላቸው የነበረው ከሮማዊያን ቅኝ ግዛት እንጅ ከኃጢአት ባርነት ከዲያብሎስ ግዞት መሆኑን ስላላወቁ ስላልገባቸው መሲሑ መጥቶ ከቅኝ ግዛቱ ነጻ እንዲወጡ የሚያደርጋቸው ይመስላቸው ነበር ዮሐ.6፤15, ማቴ.21፤4-9፡፡

ክርስቶስ ግን ሰማያዊ ንጉሥ እንጅ ምድራዊ ንጉሥ አልነበረም፡፡ መንግሥቱ ሰማያዊ እንጅ ከዚህ ዓለም አልነበረችም ዮሐ.18፤36, 1ቆሮ. 15፤24-28, 2ኛ ጴጥ.1፤11፡፡ በመሆኑም አይሁዶች መሲሑ ክርስቶስ በትንቢት ሲነገራቸውና መስሏቸው ይጠብቁት እንደነበረው ሁሉ በወቅቱ ከነበሩበት ከሮማዊያን ቅኝ አገዛዝ ነጻ እንዲወጡ ለነጻነታቸው ያደረገው ምንም ነገር አልነበረምና ክርስቶስን ያ በትንቢት ይመጣል ተብሎ የተነገራቸው መሲሕ እሱ መሆኑን አምነው ለመቀበል ቸገራቸው፡፡ ይሄንን ዓይተውም በተሳሳተ መረዳት “በእሱ ያመንን ነን የእሱ ተከታይ ነን!” የሚሉ ቡድኖች “በፖለቲካ ጉዳይ መግባት የለብንም!” በማለት በየአዳራሻቸው ይሰብካሉ፡፡

ከዚሁም ጋራም አያይዘው “ሀገር የሚለው ሐሳብ የሰዎች እንጅ የእግዚአብሔር አይደለምና የኛ ሀገር የእነሱ ሀገር ምናምን እያልን መካለልና የጥቅም ግጭት መፍጠር አይገባም! የእግዚአብሔር ሐሳብ ይሄ የእከሌ ሀገር ያ የእከሌ ሀገር ሳይባል የሰው ልጅ ወደፈለገው ቦታ ሔዶ የመኖር መብት ሰጥቶታልና” ይላሉ፡፡ አስቀድሜ ያነሣሁትን “በእሱ ያመንን ነን የእሱ ተከታይ ነን! በፖለቲካ ጉዳይ መግባት የለብንም!” ያሉትን ልቋጭና ወደዚህኛው እመለሳለሁ፡፡

መቸስ በጣም ይገርማል እንዲህ የሚሉ ሰዎች አማኝ ነን ይበሉ እንጅ የክርስቶስን ማንነት ጨርሶ አያውቁትም፡፡ ለመሆኑ እስራኤልን ዐመፅ ቀስቅሶም ምንም አድርጎ ከቅኝ ግዛት ነፃ እንዲያወጣቸው ይጠብቁት የነበረው ሲጀመር በዐመፃቸው ምክንያት በነቢያቱ ቢመክር ቢያስመክር “እምቢ!” በማለታቸው “እሽ!” ባለማለታቸው ባለመታዘዛቸው ምክንያት ለቅጣት ወደ ፋርስ ባቢሎን ከመጋዝ አንሥቶ በባቢሎናዊያን በሮማዊያን ወዘተረፈ. ለብዙ ምዕት ዓመታት በቅኝ ግዛት ስር እንዲወድቁ ያደረጋቸው ማን ሆነና ነው አዝማች ፊታውራሪ ሆኖ ተዋግቶ ወይም ዐመፅ አስነሥቶ ነጻ እንዲያደርጋቸው ክርስቶስን የሚጠብቁት?

በዓመፃቸው ምክንያት በእስራኤል ልጆች ላይ ያንን ሁሉ ቅጣት ያመጣ እሱ እራሱ ክርስቶስ እንደሆነ አያውቁም እንዴ? ክርስቶስ እግዚአብሔር መሆኑንና ያንን ያደረገውም እሱ መሆኑን ካወቁ እንዴት ነው ታዲያ “ክርስቶስ በወቅቱ ስለነበረው ቅኝ አገዛዝ አግባብ አለመሆን ያለው የተናገረው ነገር ለምን አልኖረም? ይሄ የሚያመለክተው በፖለቲካ ጉዳይ ላይ መግባት የሚገባ አለመሆኑን ነው” ሊሉ የቻሉት? ይሄንን ጥያቄ የሚያነሡ ሰዎች የክርስቶስን እግዚአብሔርነት በአፋቸው እንጅ በልባቸው የሚያምኑ ወይም የሚያውቁ አለመሆናቸውን አነጋገራቸው ያረጋግጣል፡፡ በእስራኤል ልጆች ላይ ያንን ሁሉ ቅጣት ያመጣ ያደረገ እግዚአብሔር (ክርስቶስ) እንደሆነ ቢያምኑ ቢያውቁ ኖሮ ክርስቶስ ዓውቆና ይሁን ብሎ ያደረገውን ነገር ለራሱ ሥራ እራሱ ተቃዋሚ ተቃራኒ ሆኖ እስራኤልን ነጻ እንዲያወጣ ወይም ቅኝ ገዥዎችን ሮማዊያንን እየተቃወመ እንዲናገር ወይም እንዲያስተምር ባልጠበቁ ነበር፡፡

እናም እስራኤልን በቅኝ እንዲያዙ ያደረገው እሱ ራሱ ስለሆነ ነው ክርስቶስ ስለ ቅኝ ገዣቸው ሮማዊያን በስብከቱ ለአይሁዶች ምንም ነገር ሳይል የሔደው፡፡ የሱ ተከታዮች ሐዋርያትም ሰጥ ለበጥ ብለው እንዲገዙ ከማስተማር ውጪ ሮሜ. 13፤1-7 ዐምፁ እንቢ አሻፈረኝ በሉ ብለው ያላስተማሩት በዚህ ምክንያት ነው፡፡ እንደ ክርስቶስ ሁሉ ስለ ቅኝ ግዛቱ አግባብ አለመሆን ወይም በመቃወም ምንም ነገር ሳይሉ የቀሩት፡፡ ያንን ያደረገው ክርስቶስ መሆኑን ስለሚያውቁና የእስራኤል ልጆች ወደ እግዚአብሔር በተመለሱ ወይም እሱ በቃ! ባለ ጊዜም በራሱ መንገድ ነጻ እንደሚያወጣቸው ስለሚያውቁ፡፡ ካልተመለሱና በዐመፃቸው ከቀጠሉ ወይም በቃ! ሊላቸው ካልፈቀደ ደግሞ እንደጨው ዘር በመላው ዓለም የሚበትናቸውና መልሶም የሚሰበስባቸው እሱ እንደሆነ ስለሚያውቁ፡፡

በስብከታቸውም ገዥዎች ጨካኝም ሆነ ደግ ከእግዚአብሔር እንደሚሾሙ የተናገሩት ለዐመፀኛ ሕዝብ ይቀጣ ዘንድ ክፉና ጨካኝ ገዥ፤ ለቅንና እግዚአብሔርን ለሚፈራ ሕዝብ ደግሞ ቅንና ደግ መሪ የሚሾመው እሱ ራሱ እግዚአብሔር እንደሆነ ስለሚያውቁና የእግዚአብሔርን ሥራ መቃወም እንደሆነ ስለሚያውቁ ዐምፁ ገልብጡ ብለው አልሰበኩም፡፡ “ታዲያ አንተ ምነው በወያኔ ላይ ዓምፁ! ወያኔን ገልብጡ! ትላለህ?” የሚለኝ ቢኖር እኔ “እግዚአብሔርን እሽ ብለን ረድኤተ እግዚአብሔርን አጋዥ አድርገን” አልኩ እንጅ በእግዚአብሔር ላይ እንዳመፅን ሆነን አላልኩምና ክሱ አይመለከተኝም፡፡

እስራኤሎች የልባቸው መሻት እንዲፈጸምላቸው መልካም መልካሙ ነገር እንዲደረግላቸው ከባርነት ነጻ እንዲያወጣቸው ከፈለጉ መፍትሔው በእግዚአብሔር ላይ ካደረጉት ዐመፃቸው ተመልሰው ፊታቸውን በንስሐ ወደ እግዚአብሔር መመለስ እንደሆነ ሐዋርያቱ አስተምረዋል፡፡ በወቅቱ እሽ ብለው እንዲህ ቢያደርጉ ኖሮ እግዚአብሔር ወይ የገዣቸውን ኃይል አድክሞ በማክሰም ነጻ ያወጣቸው ነበር ወይ ደግሞ የእነሱን ኃይል አበርትቶ ወኔ ሰጥቶ ዐመፅ እንዲያነሡ በማድረግ ገዣቸውን አሽቀንጥረው እንዲጥሉ እንዲያስወግዱ በማድረግ ነጻ ያወጣቸው ነበር፡፡ ምክንያቱም እስከዛሬ ድረስ እግዚአብሔር ሥራውን ሲሠራ አንዱን ሲሸኝና ሌላውን ሲያመጣ በእነዚህ በጠቀስኳቸው በሁለቱ መንገዶች ነው እንጅ እሱ እራሱ ወርዶ ሒድ አንተ ይበቃሀል ውረድ አንተ ደሞ ና ባለ ተራ ነህ ተቀበጥ ብሎ ሹም ሽር አድርጎ አያውቅምና ነው፡፡ እግዚአብሔር አንዱን መንግሥት ሲሸኝና ሌላውንም ሲያመጣ እራሱ ወርዶ ካልሆነና በሰዎች ላይ አድሮ ከሆነ እንበል ለምሳሌ ደርግን በወያኔ እንደሸኘው ሁሉ ማለት ነው፡፡ ዐመፅ ማመፅ እንቢ አሻፈረኝ ማለት ኃጢአት በደል ኩነኔ አይደለም ማለት ነው፡፡ ቁልፉ ነገር እግዚአብሔርን መያዙ ላይ ነው፡፡ እግዚአብሔርን ሳይዙ የሚመጣ ለውጥ “ጉልቻ ቢለዋወጥ” ሆኖ አንዱ ጨካኝ ሲሔድ ሌላው አውሬ እየመጣ መቀጣት መረገጥ ነው እንጅ የሚሆነው አስደሳች ለውጥ ሊመጣ አይችልም፡፡

አዲስ መጪው እሱም በተራው ሥልጣን ይዞ ሊጨቁን ሊረግጥ ነው ወይስ በደግነት ሊያስተዳድር? የሚለውን ጥያቄ ማጤን ያስፈልጋል፡፡ ይሄንን ጥያቄ የሚመልሰው የዚያ ሕዝብ ሥራ ተግባር ማንነት ነው፡፡ እኛ ከዐመፃችን ባለመመለሳችን ንስሐ ባለመግባታችን ይቅር በለን ባለማለታችን ነው ከደርግ የከፋ ጭራሽም የሀገርና የሕዝብ አንድነት፣ የብሔረሰብ እርስ በእርስ ትስስርና ፍቅር የማያውቀውን ጭራሽ እንዲያውም እነኝህ እሴቶች እንዳይኖሩ እንዲጠፉ የሚያሴረውን፣ ዘር እየለየ በጠላትነት በመፈረጅ “ጠላቴ መጥፋት ያለበት ዘር” በማለት ለማጥፋት ሌት ተቀን የሚደክመውን፣ የራሱን ዘር ብቻ ተጠቃሚ ለማድረግ ሌት ተቀን የሚጥረውን የከፋ የጉግ ማንጉግ አገዛዝ አምጥቶ ቁጭ ያደረገብንና ይበልጥ እንድንቀጣ እንድንሰቃይ ሀገር እንዳይኖረን፣ በገዛ ሀገራችን ባይተዋር እንድንሆን፣ ተሰደን በማለቅ እንድንቀጣ ያደረገን ወዘተረፈ፡፡

እናም እኛ ካልተመለስን እግዚአብሔር የነበረውን ሸኝቶ በአዲስ ጉልበት እኛን ዓመፀኞችን ቀጥቅጦ የሚገዛንን ከወትሮው የከፋ አገዛዝ አመጣ እንጅ የተሻለ አላመጣም፡፡ ስለሆነም ቀጣዩን የተሻለ መልካም ቅን ደግ እንዲያደርግልን አስቀድመን የቤት ሥራችንን እንሥራ፡፡ ንስሐ በመግባት “ይቅር በለን! ማረን!” እንበልና እንታገል፡፡ ንስሐ ከገባን ወደ እርሱ ከተመለስን ነገሩን እጅግ ያቀናልናል ያቀልልናል፡፡

ወያኔንም ወይ በራሱ ጊዜ ማንም ሳይነካው ከመቅጽበት ተዳክሞ ከስሞ እንዲወድቅ እንዲበተን ያደርገዋል ወይ ደግሞ ፍርሐታችንን አስወግዶና አነሣሥቶ በቀላሉ ነቅለን እንድናስወግደው ያደርግና ነጻ ያወጣናል፡፡ ስለሆነም በክፉ መንግሥት ላይ ዐምፆ መነሣት እግዚአብሔርን ማገልገል የእግዚአብሔር መገልገያ መጠቀሚያ መሆን ማለት ነው እንጅ በማያገባን በማይመለከተን ፖለቲካ (እምነተ አሥተዳደር) መግባትና የማይገባ ተግባር መፈጸም አይደለም፡፡

በመንግሥት ጉዳይ ወይም በፖለቲካ ጉዳይ አትግቡ የሚል ቃል አንድም የለምና፡፡ “የቄሣርን ለቄሳር የእግዚአብሔርን ለእግዚአብሔር አስረክቡ” ማቴ. 22፤21 አለ እንጅ የእኔ የእግዚአብሔር ናቹህና የቄሳር ነገር አይመለከታቹህም አላለም፡፡ ክርስቲያኖች እንደ ሰው እንደ ዜጋ በአንድ ሀገር ሲኖሩ በዜግነታቸው መብትና ግዴታ ተጥሎባቸው መንግሥት የሚጠብቅባቸውና ለሀገር ሊያበረክቱት የሚገባ ብዙ ግዴታዎችና ኃላፊነቶች አሉና፡፡

አሁን “ሀገር የሚለው ሐሳብ የሰዎች እንጅ የእግዚአብሔር አይደለምና የኛ ሀገር የእነሱ ሀገር ምናምን እያልን መካለልና የጥቅም ግጭት መፍጠር አይገባም! የእግዚአብሔር ሐሳብ ይሄ የእከሌ ሀገር ያ የእከሌ ሀገር ሳይባል የሰው ልጅ ወደፈለገው ቦታ ሔዶ የመኖር መብት ሰጥቶታልና” ስላሉት ጉዳይ ስንመለስ፡፡ አባባሉ ፍጹም የተሳሳተና ሸፍጠኛ ዓላማ ያለው አባባል ነው፡፡

እግዚአብሔር ይጠብቁት ይኖሩበትም ዘንድ ለሰው ልጆች ከሰጣቸው ሕግጋት ከዐሥርቱ ትዕዛዛት አንዱ “የባልንጀራህን ቤት አትመኝ፤ የባልንጀራህን ሚስት ሎሌውንም ገረዱንም በሬውንም አህያውንም ከባልንጀራህ ገንዘብ ሁሉ ማናቸውንም አትመኝ” ዘጸ. 20፤1 ከዚህ ጥቅስ የምንረዳው እግዚአብሔር የንብረት ባለቤትነት መብትን ለሰው ልጆች መስጠቱንና ያንንም መጋፋት መንጠቅ መቀማት የማይቻል የማይገባ ተግባር መሆኑን መደንገጉን ነው፡፡ ቤተሰብ መሬትን ጨምሮ ሌሎች ንብረቶች የኖሩታል፣ ዘመድ አዝማድ መሬትን ጨምሮ ሌሎች ንብረቶች ይኖሯቸዋል፣ ጎሳ ነገድ ብሔረሰብ መሬትን ጨምሮ ሌሎች ንብረቶች ይኖረዋል፡፡ ሀገር የሚባለው እንግዲህ የግለሰቦች የወል ስብስብ የሆኑ የተወሰኑ ጎሳዎች ነገዶች ብሔረሰቦች የኛ የሚሉት ከልለው የያዙት መሬትና በውስጡ ያሉት ነገሮቹ ሁሉ ማለት ነው እንጅ ሌላ አይደለም፡፡ አንደኛው የሌላኛውን በኃይል እንዳይነጥቅ እንዳይመኝ ከልክሏልና ሀገር የሚል ክልላ የሰው ሐሳብ እንጅ የእግዚአብሔር አይደለም ሊባል አይቻልም፡፡

መጽሐፍ ቅዱስን በምናነብበት ጊዜ የምንረዳውን ይሄንን ሀቅ ቢኖር እስራኤላዊያን በባዕዳን ወራሪዎች ሲወረሩ ሲመዘበሩ ሲወጉ ወራሪዎቹ የእነሱ ያልሆነን ሀገርና ንብረት ለራሳቸው ተመኝተው ወረራውን አድርገዋልና እግዚአባሔር አዝማቻቸው ሆኖ ሀገራቸውን ከጠላቶቻቸው እንዲጠብቁ እንዲከላከሉ ኃይል ብርታት ጽንእ መከታ ሆኖ ሀገራቸውን እንዲያስከብሩ ሲያደርጋቸው ሲያስችላቸው በበርካታ ቦታዎች እንመለከታለን፡፡

ይህ የሚያረጋግጠው “ሀገር” የሚለው ሐሳብ ሕልውና በእግዚአብሔርም እውቅና ያለው መሆኑን ነው፡፡ እግዚአብሔር በመጽሐፍ ቅዱስ በበርካታ ቦታዎች ለምሳሌ፡- …የሁለተኛውም ወንዝ ስም ግዮን ነው፣ …እርሱም የኢትዮጵያን ምድር ሁሉ ይከብባል ዘፍ. 2፤13 ፣ …ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች መዝ. 67/68፤31፣ …ለኢትዮጵያ ሰዎች ምግባቸውን ሰጥተሀቸዋልና መዝ. 73/74፤14፣ …በፊቱም ኢትዮጵያ ይሰግዳሉ መዝ. 71/72፤9፣ … የኢትዮጵያም ሕዝብ መዝ. 86/87፤4፣ …የእስራኤል ልጆች ሆይ እናንተ ለእኔ እንደ ኢትዮጵያ ልጆች አይደላቹህምን? አሞ. 9፤7 ወዘተረፈ. ሲል ኢትዮጵያ የምትባል ሀገር መኖሯንና ለእሷም እውቅና ሰጥቶ እንጅ ኢትዮጵያ ስለሚባል ሌላ ዓለምና በዚያ ዓለም ላይ ስለሚኖሩ ሰዎች እያወራ አይደለም፡፡

ስለሆነም ባዕዳን ሀገራችንን ቅኝ ለመግዛት አስበው ይዶልቱ ከነበሩበት ዘመን ጀምረው ሰብከው የወሰዷቸውን መናፍቃን ወገኖቻችንን ሲሰብኳቸው ሀገራቸውን እንዳይወዱ፣ ለሀገራቸው እንዳይሞቱ ወይም የዜግነት ግዴታዎቻቸውን እንዳይወጡ፣ የሀገርፍቅር ስሜት አልባ እንዲሆኑ ለማድረግ አስበው በዚሁ መልኩ ስለሚቀርጹዋቸው ነው እንጅ አባባሉስ ከላይ ለማየት እንደሞከርነው ፍጹም መጽሐፍ ቅዱሳዊ አይደለም ወይም ደግሞ መጽሐፍ ቅዱሳዊ የሆነውን አስተሳሰብ የሚጻረር ነው፡፡እንግዲህ ያለው ነገር ይሄው ነው፡፡ ተስፋ አደርጋለሁ ይሄንን ጉዳይ ግልጽ እንዳደረኩላቹህ፡፡ ቸር ይግጠመን፡፡

ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!! ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!!!

ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው

amsalugkidan@gmail.com

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.