የሰሜኑ ጦርነት እንደገና ሊጀመር ነው! (የዳዊት ከበደ ወየሳ ሪፖርታዥ – ኢ.ኤ.ኤፍ)

tsorena_war-ethiopiaበሰሜን የኢትዮጵያ ክፍል… በኤርትራ እና በትግራይ ድንበር አካባቢ ጦርነት መቀስቀሱ እየተሰማ ነው። ጦርነቱ በተለይ የተቀሰቀሰው በኤርትራ እና በትግራይ ክልል፤ በጾረና ግንባር መሆኑን ለማወቅ ተችሏል። እሁድ ንጋት ላይ የተጀመረው አዲስ ጦርነት አሁንም ድረስ እንደቀጠለ መሆኑን ነው የአካባቢው ነዋሪዎች የሚገልጹት።

ነዋሪዎቹ እንደሚሉት ከሆነ፤ ከባድ የተኩስ ልውውጥ መሰማት የጀመረው ንጋት ላይ ነው። የከፍተኛ ተኩሱ ድምጽ እስከ ምስራቅ ዛላ’ምበሳ ድረስ ተሰምቷል። የጦርነቱን መነሻ በተመለከተ የተለያዩ ወሬዎች በአካባቢው ሰዎች ዘንድ ይናፈሳል። ከትላንት በስትያ የተሰማው ወሬ፤ “የመከላከያ ሰዎች ኳስ እየተጫዌቱ ሳለ፤ የሽምቅ ተዋጊዎች በከፈቱት ተኩስ የተወሰኑት ሲሞቱ ቀሪዎቹ ደግሞ መቁሰላቸው የጸቡ መነሻ ነው።” ይላሉ።
ሌሎች ደግሞ የሚሉት፤ “ጦርነቱ ከመጀመሩ በፊት የህወሃት ትግራይ ወታደሮች የኤርትራን ድንበር አልፈው ሰላማዊ ሰዎችን በመያዝ፤ ወደ ድንበር ከተማዋ ገሩ-ሰርማይ አምጥተው ማሰር ከጀመሩ በኋላ ነው” ይላሉ ሌሎቹ ምንጮች። በዚያም ተባለ በዚህ ግን ጦርነቱ የተጀመረ ይመስላል። ለዚህም መረጃ የሚሆነው፤ ዛሬ ከሰአት በኋላ በትግራይ የጦር ካምፖች የሚገኙ ወታደሮች በተጠንቀቅ ላይ እንዲሆኑ ትእዛዝ መሰጠቱና በመቀሌ የሚገኘው ሜካናይዝድ ጦርም ወደ ሥፍራው እንዲንቀሳቀስ መደረጉ ነው።
የዛሬ 18 አመት በስፍራው ጦርነት ሲነሳ የኢትዮጵያ ህዝብ ከዳር እስከዳር “ሆ” ብሎ መነሳቱ ይታወሳል። በወቅቱ ህዝቡ ከዳር እስከዳር የተነሳው በተለይ የሻዕቢያ ወታደሮች በኤርትራ ውስጥ የነበሩ ኢትዮጵያውያንን ንብረት ወርሰው በማባረራቸው እና ሌሎች ተመሳሳይ ቁጭቶች ምክንያት መሆኑ ይታወሳል። ኢትዮጵያውያኑ ከተባረሩ በኋላ ወያኔ በሰጠው መግለጫ፤ “ያለአግባብ የተባረረ አንድም ኢትዮጵያዊ የለም” ነበር ያለው። ይሄ ሁሉ ሆኖ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ ኤርትራውያን ደግሞ እንደአንደኛ ዜጋ መታየታቸው በህዝቡ ውስጥ ቁጭትን ፈጥሮ ቆይቶ ነበር። እናም ጦርነቱ ባድመ ላይ መጀመሩ ሲሰማ፤ የቀድሞ ወታደሮች ጭምር ዘመቻውን ተቀላቀሉ። አብዛኛዎቹ ወታደሮች ከአዲስ አበባ ሲነሱ፤ “ከባድመ መልስ… ወደ መለስ!” እያሉ በመጨፈር ወደ ኤርትራ ድንበር ተጋዙ።
በባድመ፣ በዛላምበሳ እና በጾረና ከፍተኛ ውጊያ ሲካሄድ እነዚህ “ከባድመ መልስ… ወደ መለስ!” ያሉት ሃይሎች በግንባር ቀደም ተሠልፈው እንዲያልቁ ተደረገ። በየሰራዊቱ ውስጥ ጥያቄ ያነሱ የነበሩ በተለይም የኢህዴን (በኋላ ብአዴን) የቀድሞ ሰራዊት አባላት ጭምር በግንበር ቀደምትነት እንዲዘምቱ ተደረጉና ደብዛቸው በዚያው ጠፋ። በውጤቱም ከ80 ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያን አለቁ (ብዛቱን እስካሁን ያስተባበለ የለም)። የሚገርመው ነገር… ይህን ያህል ብዛት ያለው ሰራዊት ደርግ በ17 አመቱ ጦርነት እንኳን አላለቀበትም ነበር።
ይህም ሁሉ ሆኖ… ከብዙ መስዋእትነት በኋላ ጦሩ የኤርትራን ድንበር አልፎ ወደ አስመራ ለመገስገስ ሲዘጋጅ፤ በባለ ራዕዩ የቀድሞ ጠቅላይ ሚንስትር መለስ ዜናዊ ትእዛዝ ጦሩ እንዲያፈገፍግ ተደረገ። በኋላ ላይ ይህ ጉዳይ በነስዬ አብርሃ በኩል ተነስቶ ሟች መለስ ዜናዊን በራሳቸው ሸንጎ መክሰሳቸውና ጭቅጭቁ ይይፋ ሆኖ በህወሃት
ውስጥ ክፍፍል መፈጠሩ የሚታወስ ነው። ያንን ጦርነት ከኳስ ጨዋታ ጋር በማመሳሰል፤ “የወዳጅነት ጦርነት” ይሉታል። የሆኖ ሆኖ ግን ድንበር አልፈው የሄዱት መመለሳቸው ላይቀር፤ ባድመም ለኤርትራ መሰጠቱ ላይቀር በአጭር ግዜ ጦርነት ብዙ   የተሰዉበት ጦርነት ነበር።
እንግዲህ ይሄ ሁሉ አልፎ፤ ለነዚያ ለሞቱት ሠማንያ ሺህ ወታደሮች መታሰቢያ ሃውልት ሳይቆምላቸው፤ ወላጆቻቸው እስካሁን ድረስ በወታደራዊ ደንብ መርዶ ሳይነገራቸው 18 አመታት አለፉ። እናም ሌላ ጦርነት ሊጀመር ነው። ይህ ጦርነት የተጀመረው መከላከያ ሚንስትር ከሁሉም መስሪያ ቤቶች በላቀ ደረጃ በሙስና ውስጥ መዘፈቁ በፓርላማው ጭምር ከተነገረ በኋላ ነው። ዋናው ጥያቄ የሚሆነው ግን… “ጦርነቱ ቢጀመር የኢትዮጵያ ህዝብ እንደኬዚህ ቀደሙ ከዳር እስከዳር ‘ሆ’ ብሎ ይነሳል ወይ?” የሚለው ይሆናል። የህዝቡን ምላሽ… በጦርነቱ ዋዜማ ላይ ሆነን አብረን የምናየው ይሆናል።