ሐሳብ፡-ማንነታችንን ያዋረደንን ፖለቲካ በሽማግሌዎች እናዳኘው (ሰርጸ ደስታ)

ethio-ertriaሰሞኑን በኢትዮጵያና ኤርትራ የተፈጠረው ግጭት ከአገርኛነትም በላይ ከዋና ዓለም ዓቀፍ ዜናዎች አንዱ ሆኖ ሰንብቷል፡፡ ግጭቱ ብዙም የተለየ ሆኖ አስደመመኝም፡፡ ከግጭቱ በኋላ ግን በሁለቱ አገራት ባለስልጣናት መካከል የሚደረገው የቃላት ጦርነት አመድ በዱቄት ይስቃል አይነት ሆነብኝ፡፡ ማነው አመድ ማነው ዱቄት አትበሉኝ፡፡ ከሁሉም ያሳዘነኝ ግን በኬንያ አንድ ቴሌቪዥን ላይ የሁለቱ አገራት በአንድ ቦታ ተገኝተው የተለዋወጡት እንካ ሲላንታ ነው፡፡ አነጋግራቸው የነበረቸው ጋዘጠኛ ሁለቱንም አንድ ላይ አምጥታ ማናገሯ የሚያስመሰግናት ነው፡፡ እኔን እጅግ ያሳዘኝ ግን የአምባሳደሮቹ ሁኔታ ነው፡፡ ያዘንኩትም ለእራሳቸው ለአንባሳደሮቹ እንጂ በተናገሯቸው ቃላቶች አይደለም፡፡ የሄ እንግድህ የዘመኑ ፖለቲካ ምን ያህል አዋራጅና የራስን ክብር መቅ አውርዶ ለሌሎች ሐሳብ ባሪያ መሆን እንደሆነ ማሳያ እንጂ እነዚህ ሁለት አምባሳደሮችን ብቻ የሚመለከት አይደለም፡፡

በኬኒያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ እና የኤርትራው አቻቸው በየነ ርዕሶም በግል ሕየወታቸው ጓደኛሞች እንደሆኑ እዛው ከቃለምልልሳቸው መረዳት ይቻላል፡፡ ሆኖም ጓደኝነታቸውና እርስ በእርስ በግል ሊኖራቸው የሚችለው መከባበር እዚህ ቃለምልልስ ላይ ከውርደት አላዳናቸውም፡፡ ሁለቱም ጋር ያለው ጭንቀት በጌቶቻቸው የታዘዙትን መፈጸም እንጂ በአምባሳደርነትም ይሁን በአሳለፉት እድሜያቸው ያካበቱትን ክብርና ልምድ የሚያስከብር ሐሳብን ማስተላለፍ አልነበረም፡፡ የየአገራቸውን ፖለቲካ በመነጠል መወጋገዝና እርስ በእርስ ፕሮቶኮላቸውን ጠብቆ ሐሳብ ለመስጠት የሚያስችልና ዲፕሎማሲያዊ ልምድ እንዳላቸው አምናለሁ፡፡ ሆኖም የየራሳቸውን ሓሳብ ቢጠቀሙ በጌቶቻቸው ምን ሊደርስባቸው እንደሚችል በማሰብ ይመስላል እርስ በእርስ እንኳን አንዱ ሌላውን በማክበር ዲፕሎማሲያዊ አቅማቸውን መጠቀም አልቻሉም፡፡ እውንም ፖለቲካ እጅግ አዋራጅ የሆነ ሥራ ልበለው፡፡ እኔን ይመስለኝ የነበረው ፖለቲካ በአብዛኛው ውሸት ሊሆን እንደሚችል እንጂ እንዲ ፉጹም እውነት ተሳስቶ እንኳን እንዳይነገረበት የተሰላ ክስረት እንደሆነ አላውቅም፡፡ ምን አልባት የኢትዮጵያና የኤርትራ ፖለቲከኞች ይሆኑ በዚህ ደረጃ የተዋረዱት ብዬም አሰብኩ፡፡ ብዙ ሓሳብም ወደ አእምሮዬ መጣ፡፡ በ50ዎቹና 60ዎቹ የተለከፈው ትውልድ እስከዛሬም እንደቀጠለ አስተዋልሁ፡፡ ማንነቱን የጣለ ለሌሎች ሐሳቦች ራሱን ባሪያ ያደረገው ይሔው ትውልድ በየትኛው ጸበል እንደሚድን የምርም አሳሰበኝ፡፡ ነጭና ቀይ ብሎ እርስ በእርሱ የተባላባቸው እነዚያ በሰውኛ የሓሰብ ልዩነቶች ምን አጠፉ ራሱ ትውልዱ አእምሮው ለባርነት የተሸጠ እንደሰው ማሰብ የተሳነው መሆኑ እንጂ የሚል ሐሳብም መጣብኝ፡፡ ዛሬም የአለም አቀፉ ሁኔታ ስላላመቸ እንጂ ምንም  እንደ ሰው አእምሮ የሚሻውን ሰውኛ አስተሳሰብን ማሰብ ቢችሉ እንኳን ብዙዎች በሌሎች ሀሳብ ባርነት ሥር ወድቀው ይኖራሉና ነጭና ቀይ ብለን የተባላንበት ሁኔታ እንዳለ አለ፡፡ እንዲያ ባይሆንና እንደሰው ማሰብ ቢቻል የሐበሻ ምድር በዓለምም ዝናን ያተረፈ መንግስት ሊኖረን በቻለ፡፡ ማን ወደ አእምሮአችን ይመልሰን፡፡

ወገኖቼ አስተውሉ፡፡ የኢትዮጵያና ኤርትራ ሕዝብ በአሁኑ ወቅት ከሁሉም አገራት ይልቅ ተሰዳጅ ሕዝብ ሆኗል፡፡ ሰሞኑን በሆነ አካል የወጣው ሪፖረት የኤርትራን መንግስት ዜጎችን ለስደት የዳረገ በሚል በወር በሺዎች የሚቆጠሩ እንደሚሰደዱ ተናገረ፡፡ የኢትዮጵያ ባለስልጣናት ይሄ እንደ ትልቅ ብስራት ሆኖላቸው በየሚዲያው ጮቤ ሲረግጡ ትንሽ እንኳን አላሳፈራቸውም፡፡ እውንም እንደተባለው በኤርትራውያን ሥም የሚሰደድ ብዙ ኢትዮጵያዊ ሊኖር እንደሚችል እገምታለሁ፡፡ በመሆኑም የኤርትራ ሥደተኛ ቁጥር መብዛት የኤርትራ ባለስልጣናት እንደሚሉት ከዚህ ጋር ሊገኛኝ ይችላል፡፡ ያም ባይሆን ሥደት አለ በተባለበትና የስደት የሞት ጎዳናዎችን ሁሉ ሳይቀር አጨናንቆ ያለውን ኢትዮጵያዊ ብዛት ሳስብ የኢትዮጵያ ባለስልጣናት የእኛን ደግሞ መቼ ትነግሩን ይሆን የሚል መሸማቀቅ በተሰማቸው፡፡ ሊያውም አኮ አሁን ራሱ በሌላ አካል ኢትዮጵያ ራሷ በዜጎች ላይ ግፍ እፈጸመች ነው የሚል ክስ እየቀረበባት ነው፡፡ በአንድ ወቅት በሊቢያ የታረዱ 30 ወንድሞቻችንን በአየን ወቅት እጅግ አዘንን፡፡ እንደዛ ባለ ሁኔታ የሚያልቁ በሺዎች የሚቆጠሩ እህት ወንድሞቻችን እንዳሉ ማሰብ አልቻልንም፡፡ በዚያው የሊቢያው መርዶአችን ሰሞን በባሕር ሰጥመው መርዷቸው ዘግይቶ የደረሰን ዜጎቻችን ቁጠር በ30ዎቹ የተጣጣ ነው ብለን አልፈንዋል፡፡ በደቡብ አፍሪካም የተቃጠሉ ወገኖች እንዲሁ፡፡ በየቀኑ ይህ ኢትዮጵያውያና ኤርትራውያን ሰቆቃ ነው፡፡ ግን አይሰማም፡፡ የዜጎች በደል ሊቆጨን አልቻለም፣ የማንነት መጎደፍ ለባርነት ለተሸጠ አእምሮ የሚገባው አይደለም፡፡ አይሲሰ ወይም ሌላ አረመኔ ዜጎቻችንን አረደ አቃጠለ ብለን ለምን እንደምናዝንም ግራ ይገባኛል፡፡ ሲጀምር አይሲስና ሌሎቹ አረመኔዎች ከሚያደርሱት ጭካኔ ያላነሰ በዜጎች ላይ የሚጨክኑ ባለስልጣናት ናቸው አገራቱን የሚያስተዳድሩት፡፡ እነሲ የገዛ ዜጎቻቸውን ሲገድሉና ሲያሰቃዩ ሕግ አይሲስ ሲያደርገው አረመኔያዊ ድርጊት ነው አስተሳሰባችን፡፡

የኢትዮጵያ ባለስልጣናት አገሪቱ በኢኮኖሚ እየተመነደገች ነው ብለው ሲያወሩ አእምሮ ላለው ስለየትኛዋ አገር እንደሚያወሩ ግር ይላል፡፡ ሁሌም እንደምለው እድገት የተመዘገበባቸው ሂደቶች እንዳሉ አይካድም፡፡ የአገሪቱ ባለስልጣናት የሚያወሩት እድገት ግን ምን ያህል አገሪቱን አደጋ ላይ እየጣላት እንደሆነ መረዳት የተሳነን ይመስላል፡፡ ከላይ የጠቀስኩትን ስደትን ጨምሮ የአገሪቱ ዜጎች ድህነትና የኑሮ ውድነት ከአምባገነንነት ስርዓት ዓልበኝነት፣ የአስተዳደር በደልና  ሌብነት (ሙስና) ጋር ሆነው አገሪቱን ወደ አልታሰበ ውድቀት ምን አልባትም መመሰቃቀል እያመሯት ሊሆን እንደሚችል ሊታሰብ አልተፈለገም፡፡ ተቃዋሚዎችም እንዲሁ በስልጣን ላይ ያሉትን ከመኮነን ያለፈ ፋይዳ ያለው ቁርጠኝነትን የተላበሰ አካሄድ የላቸውም፡፡ እርስ በእርስም (ተቃዋሚ ለተቃዋሚ) ለመጠፋፋት እንጂ በአንድ አላማ እንሻልሀለን የሚሉትን ሕዝብ ሊታደጉት የሚያስችላቸው አሰራር የላቸውም፡፡ መሐል ላይ ሆኖ የሚዳኝ የሚገስጽም ጠፋ፡፡ በአንድ ወቅት በታዋቂው አሸማጋይ ፕሮፌሰር ኤፍሬም ይሳቅና ሌሎች ወገኖች ተመስርቶ ሲንቀሳቀስ የነበረው አገርኛው አሸማጋይ አካልም ቀስ በቀስ  ከገጽታ ጠፋ፡፡ አሁን ሁሉም የራሱን ጽንፍ ይዞ ተወጣጥሮ የሚገኝ በሆነ ወቅት ሊፈነዳ የሚችልን አደጋ ለአገሪቱ ያቆየ አሰላለፍ ነው ያለው፡፡ እንደኔ ዜጎች እነዚህ ጽንፍ ያላቸውን አካላት መከተል ይበጃቸዋል የሚል እምነት የለኝም፡፡ የሚከተል እንደገባው ይከተል፡፡ ግን አሁንም እነዚህን የየራሳቸውን ፅንፍ ይዘው ስለ ኢትዮጵያና ሕዝቦቿ እንሻላለን የሚሉ አካላት (ገዥውን ፓርቲ ጨምሮ) በኢትዮጵያዊነት ጽዱ ስሜት ሊያደራድርና ሁላችንንም ወደ አእምሮአችን የሚመልሰን አካል ያስፈልገናል ብዬ አምናለሁ፡፡ ከላይ እንደጠቆምኩትም ችግሩ በየግላችን ላይሆን ይችላል፡፡ በየግላችን ሁላችንም ጥሩ ልንሆን እንችላለን፡፡ ድርጅታዊ ስንሆን ግን እያሰብን ያለንው በባርነት በተያዘ አእምሮ ነው ባይ ነኝ፡፡ አሁን አገሪቱን አደጋ ሆኖባት ያለውም ይሄው አይነት አስተሳሰብ ነው፡፡ የሰው ልጅ ላመነበት ጉዳይ ሲናገር ነው ጉልበት ያለው፡፡  ድርጅት ብለን ለአቋቋምንው ጣዖት እንጂ ለራሳችን የአእምሮ ችሎታ እየተመራን አይደለም፡፡ በዚህም ምክነያት አንድን ሕዝብ፣ ብሔር እንወክላለን በሚሉ ድርጅቶች እንኳን መካከል ያለው ክፍተት ከልዩነት አልፎ የባለአንጣነት ነው፡፡ ቀድሞ የነበሩት ዛሬ የተሳሳቱባቸውን ሂደቶች ለተከታዮቻቸው በማስረዳት ሌላ ስህተት እንዳይደገም አይመክሩም፡፡ ብዙም ጊዜ ለቃለመጠይቅ ሲቀርቡ የአለፉ ሂደቶችን ከማውራት የዘለለ ይሄ ክፍተት ነበር እንዲህ ሊስተካል ይገባዋል አይሉም፡፡ የድርጅቶች መብዛት ሌላው ውዥንብር ነው፡፡

ታዋቂው አሸማጋይ ፕሮፌሰር ኤፍሬም ይስሐቅ በቡድኖች መካከል፣ እንዲሁም በዘረኝነት የተለከፈው መሪ ሊሆን የሚችለው የተማረው አካል እርስ በእርሱ ባለአንጣ መሆን እጅግ ያሳስባቸዋል፡፡ ኤፍሬም በሌሎች አገራት መካከል ሳይቀር በማሸማገል የተሳተፉና የተሳካላቸው ቢሆንም እወዳታለሁ የሚሏት አገራቸው ጉዳይ ግን እንደከበዳቸው ይታያል፡፡ ዋነኛው ችግራቸው ደግሞ ተማርኩ በሚለውና የፖለቲካ ድርጅቶችንም እየመራ በሚገኘው በዘር መንፈስ የተበከለው ወገናቸውን አንድ ላይ አምጥቶ በወንድማማችነት እህትማማችነት (በአንድ አገሬ ልጅነት) ማወያየት ማወቃቀስ አለመቻላቸው ነው፡፡ እንደውም ቆይቶ የገዥው ፓርቲ ደጋፊ በሚል ተቃዋሚ ተብዬዎች ጆሮ ሊሰጧቸው እንኳን አልቻሉም፡፡ ኤፍሬም ከገዥው ፓርቲ ባለስልጣናት በተለይም ከቀድሞው ሟቹ ጠ/ሚኒስቴር ጋር የጠበቀ ወዳጀነት እንዳላቸው አይካድም፡፡ ይህ በሌሎች ዘንድ እንደ በጎ ነገር አልታሰበላቸውም ይመስላል፡፡ ኤፍሬም ካላቸው ፍልስፍናና የሽምጋይነት ሚናቸው አንጻር ግን ከገዥው ፓርቲ ባለስልጣናት ጋር ወዳጅና ተቀባይ መሆናቸው በሌሎችም የጠላቴ ወዳጅ በሚል ሳይሆን መሠረታዊ አላማቸውን በማየት ተቀባይነት ቢኖራቸው ብዙ ተጽዕኖ ሊፈጥሩ እንደሚችሉ ይታሰባል፡፡ በእርግጥም ሽማግሌ ሁሉም ወዳጁ ሆኖ በጠላትነት በሚተያዩ ወገኖች መካከል የሚቆም እንጂ ለአንዱ ወግኖ አይሆንም፡፡ ኤፍሬም ብዙዎች የልቻሉትን በቀድሞውን ጠ/ሚኒስቴር ላይ ሌሎችን የሚጠቅሙ በወሳኝ ጉዳዮች  ተጽኖ ማሳደር የቻሉት ከጠ/ሚኒስቴሩ ጋር በነበራቸው ቅርበት እንደሆነ እናውቃለን፡፡ በአንድ ወቅት የታሰሩ የፖለቲካ ቡድን መሪዎችን ማስፈታት ጨምሮ በተለያየ ወቅት የተለያዩ ግለሰቦችን እንዳስፈቱ ይታወቃል፡፡ እንደውም በሂደት የአገሪቱን እስር ቤቶች ሙሉ በሙሉ ከፖለቲካ እስረኞች ነጻ ለማድረግ የሚያስችላቸውን ሐሳብ ወዳጃቸው ለሆኑት መለስ አንስተው መለስም ይህን ሐሳብ ሊያስቡበት እንደሚችሉ ቃል እደገቡላቸው ኤፍሬም ይናገራሉ፡፡ ይህ የሆነው ኤፍሬም ከመለስ ጋር በነበራቸው ቅርበት ነው፡፡ ቅርበታቸውን ደግሞ ያዋሉት ለአገርና ሕዝብ በሚጠቅም በጎ ተጽኖ በማሳደር እንጂ ለግላቸው አልነበረም፡፡

አሁንም ኤፍሬምና የኤፍሬምን ሐሳብ የሚደግፉ ተጀምሮ የነበረውን ተግባር ቢያጠናክሩት እላለሁ፡፡ ይህ ሙሉ ለሙሉ ለእውነት፣ ለፍትህና ለሕሊና የሚንቀሳቀስ ስለሚሆን ሁሉንም አካል በአንድ አምጥቶ ማደራደር፣ ማወያየት መወቃወስ (ማካሰስ ግን አይደለም) የሚያስችል አቅም ይኖረዋል ባይ ነኝ፡፡ ለዚህ እንደ ሐሰባ በሕሊናቸው በጎ የሆኑ የእምነት አባቶች፣ ታዋቂ ግለሰቦች፣ በሕዝብ ዘንድ ትልቅ ስፍራ ያላቸው የባሕል መሪዎች (ለምሳሌ አባገዳዎች) ቢሳተፉበት መልካም ነው፡፡ እዚህ ላይ ጥንቃቄ ሊደረግበት የሚገባው እንዲሁ ስለተባለ ብቻ ከላይ ከጠቀስኳቸው አካላት በተወካይነት ማሰባሰብ ሳይሆን ለዚህ ተግባር ተሳታፊ የሚሆኑ ግለሰቦች ራሳቸው ሙሉ ፍቃደኛና በሕዝብ ዘንድ የተመሰከረለት በጎነት ያላቸው መሆን ይገባዋል፡፡ አገርና ሕዝብ እንጂ ለማንም ፖለቲካ ድርጅት አድሎ የሌላቸው፣ የመገሰጽ ኃይል ያላቸው ማንንም የማይፈሩ ግን የሚያከብሩ ሊሆኑ ይገባል፡፡ ከዚህ ውጭ ዝም ብሎ ተወካ ከሙሲሊሙ፣ ከክርስትናው፣ ወዘተ በሚል የሚሰባሰቡ ከሆነ ያው የተለከፍንበት የውሸት ፖለቲካ ይሆናል፡፡  ፖለቲከኞችም ወደራሳቸው እንዲመለሱ በየግል የሚያስቡትን በድርጅታቸውም እንዲያንጸባርቁትና የፖለቲካ ድርጅቶች ፍጹም እውነት የሌለባቸው ሀሳቦችና አመለካከቶች የሚንጸባረቁባቸው ሳይሆን ቢያንስ በከፊል ከእውነት የተዛመዱ እንዲሆኑ ያስፈልጋል ባይ ነኝ፡፡

 

አመሰግናለሁ

 

እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርከ!

 

ሰርጸ ደስታ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.