በሲኖዶስ የጳጳሳት ሹመት ላይ የተነሡ ተቃውሞዎች ሲፈተሹ! (ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው)

ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው
ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው

ሲኖዶስ ብየ ስል “የትኛውን?” የሚል አይጠፋም፡፡ በአንድ ሀገር ቤተክርስቲያን ውስጥ ሊኖር የሚችለው አንድ ሲኖዶስ ነው ሁለት ሲኖዶስ የለም፡፡ ሲኖዶስ ይሰደዳል ወይ?፣ እዚህ ሀገር ቤት ያሉትም ሲኖዶስ ነን ይላሉና የትኛው ነው ትክክለኛና እግዚአብሔር የሚቀበለው? ፣ ፓትርያርኩና ጳጳሳቱ መሰደድ ነበረባቸው ወይ? ስደታቸው ከወንጌልና ከሕገ ቤተክርስቲያን አኳያ ትክክልና የሚገባ ነው ወይ? ለሚሉ ጥያቄዎች ከተፈጠሩ ነባራዊ ሁኔታዎች አኳያ ወንጌልንና ሕገ ቤተክርስቲያን እየጠቀስኩ ትክክል መሆኑን ከዚህ ቀደም በሚገባ መልስ ሰጥቸበታለሁና አሁን ወደዚያው አልመለስም፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ በስደት አሜሪካን ሀገር ያለው ነው፡፡ እዚህ ያሉት በእሱ ስር ሆነው በቤተክርስቲያንን የሚያገለግሉ (እያገለገሉ ከሆነ) አሜሪካ ያለው ሲኖዶስ አካል ናቸው እንጅ በራሳቸው ሲኖዶስ አይደሉም፡፡

ሰሞኑን ይህ በስደት የሚገኘው የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ 6 ጳጳሳትን ከመሾሙ ጋር ተያይዞ ከያቅጣጫው ተቃውሞዎች ሲነሡ ነበር፡፡ እጅግ የገረመኝ ነገር ብዙዎቹ የዚህ የሲኖዶሱ ሹመት ተቺ ተቃዋሚዎች እዚህ ሀገር ቤት ያለአግባብና ያለ ቀኖና ቤተክርስቲያን ሲኖዶስ ነን ያሉት በወያኔ ታንቆ የተያዘው የጳጳሳት ቡድን የተጣለበትን ኃላፊነትና አደራ ባለመወጣት ቤተክርስቲያንን ለወያኔ ሸጦ የወያኔ መጫዎቻ መቀለጃ ሲያደርጋት፣ ዳግም ልታገኛው የማትችላቸውን በርካታ ጥቅሞቿን እንድታጣ ስትደረግ፣ መንጋዋ በገፍ ተበልቶባት ባዶዋን ስትቀር፣ ሥርዓቷ ቀኖናዋ ሕግጋቷ አልፎም ዶግማዋ ሲጣስ ሲሻር ሲፈርስባት በዝምታ ከመመልከት ውጭ ምንም ማድረግ ያልቻለ መሆኑን እያየ ትንፍሽ ብሎ የማያውቀው ሁሉ እየተነሣ በንዴት ጦፎ የማይገባ የነገር ዱላውን እየመዘዘ ምንም ባልገባው ጉዳይ ላይ የጳጳሳቱን ሹመት ሲቃወምና ሲያወግዝ ሳይ እጅግ ነው የገረመኝ፡፡ ብዙዎቹን ከሁኔታቸው እንደታዘብኳቸው ከወያኔ ቅጥረኝነታቸው የተነሣ ነው ያሉትን ሁሉ ሲሉ የነበረው፡፡ ስለሚናገሩት ነገር ሳያውቁ አግባብነት የሌለው ልፍለፋ ለመለፍለፍ አደባባይ ሲወጡ ሰው ይታዘበናል አለማለታቸው ግን በእጅጉ ገርሞኛል፡፡

እነኝህ ግለሰቦች ከጠቃቀሷቸው የተቃውሞ ምክንያቶቻቸው ዋናዎቹም፡-

  1. ሹመቱ ተገቢ አይደለም
  2. መናፍቅ ተሹሟል
  3. ካንድ መንደርና ቤተሰብ ብቻ የተውጣጡ ናቸው፡፡ የሚሉ ናቸው፡፡ እነኝህ ተቃውሞ ትችቶች ስላላቸው ተጨባጭነት እያንዳንዳቸውን እንመልከት፡-

ሹመቱ ተገቢ አይደለም፡- ይሄንን የሚሉ ሰዎች ለዚህ ተቃውሞ ምክንያት ሲጠየቁ የሚመልሱት “በቤተክርስቲያን ላይ ያለውን መከፈል ዘላቂ እንዲሆን ያደርገዋልና እርቅ ነው እንጅ መፈጠር ያለበት ክፍፍሉን ቋሚ ሊያደርግ የሚችል ተግባር አይደለም” የሚል ነው፡፡ ይሁንና እነኝህ ወገኖች ያለውን ነባራዊ ሁኔታ ግን አጢነው መረዳት ያለባቸውን ነገር መረዳት አልቻሉም፡፡ ዝምብሎ በምኞት የሚሆን ነገር የለም፡፡ ይሄንን ለማድረግ የሚያስችል ሁኔታ አለ ወይ? ተብሎ መጠየቅ ይኖርበታል፡፡

ምክንያቱም እዚህ ሀገር ቤት ያሉቱ ሊቃነ ጳጳሳት ይሄንን የእርቅ ሒደት ለመፈጸም በሚደክሙበት ጊዜ በወያኔ ከጥተኛ ጣልቃ ገብነት እርቁ እንዲቋረጥ በመደረጉና አሁን ደግሞ ወደፊት እንዳያስኬዱት በወያኔ ስለተከለከሉ ስለታገዱና “ይሄንን እርቅ ለማስፈጸም የሚንቀሳቀሱ ቄሶችን እንሰቅላለን!” የሚል ከባድ ማስፈራሪያና ማስጠንቀቂያ ከወያኔ ባለሥልጣናት ዘንድ ስለተሰነዘረባቸው እነኝህ ጳጳሳት ድፍረት አግኝተው እውነትንና ቀኖና ቤተክርስቲያንን መሠረት ባደረገና በጠበቀ መልኩ እርቁ እንዲፈጸም ማድረግ የሚችሉበትን ዕድል ባላገኙበት ቁርጠኝነቱም በታጣበት ሁኔታና ወያኔ እስካለ ጊዜ ድረስም ይህ ጉዳይ ሊፈጸም የማይችል በሆነበት ሁኔታ የሚፈለገው እርቅ እንዲፈጸም መጠየቅ ነባራዊ ሁኔታዎችን ግምት ውስጥ ያላስገባ ባዶ የየዋሀን ምኞት ከመሆን የሚዘል አይሆንም፡፡

“ሲኖዶስ ወያኔ እስኪወድቅ ድረስ ዝም ብሎ ይጠብቅ” እንዳይባልም የቤተክርስቲያን አገልግሎት የሚጎዳ ሆነ፡፡ ቤተክርስቲያን አገልግሎቷን ለማስፋት፣ ለማጠናከር፣ ለማሟላትና ለማሳለጥ የኤጲስ ቆጶሳቱና የጳጳሳቱ ሹመት የግድ አስፈላጊ ሆነ፡፡ በመሆኑም ሹመቱ መፈጸም ነበረበትና ሊፈጸም ቻለ፡፡ ስለዚህም ይሄንን ነጥብ በማንሣት በዚህ ጉዳይ ላይ የተነሣው ተቃውሞ ብስለት ቅንነትና ሙሉ ግንዛቤ የጎደለው ሆኖ እናገኘዋለን፡፡

ሁለተኛው የተቃውሞ ነጥብ “በዚህ ሹመት ላይ መናፍቅ ተሸመዋል” የሚለው ነው፡፡ በእርግጥ ግን መናፍቅ ተካቷል ወይ? ብለን ስንጠይቅ መናፍቅ በተባሉ መነኩሴ ላይ የቀረቡ መረጃዎች በእጅጉ የዕውቀትና የግንዛቤ ማነስ ጎልቶ የሚታይባቸው በተሳሳተ ግንዛቤ ላይ የተመሠረቱ ሆነው እናገኛቸዋለን፡፡ መናፍቅ በተባሉት በአባ ወልደትንሣኤ ላይ ቀረቡ የተባሉትን ክሶች እንይ፡-

አባ ወልደ ትንሣኤ አሳማ ይበላል ብለው ይሰብካሉ፣ በኦርጋን ያስጨፍራሉ፣ ሰንበቴን በቢራና በውስኪ እንዲወጣ ፈቅደዋል የሚሉ ናቸው፡፡ እስኪ እያንዳንዳቸውን ክሶች ከቤተክርስቲያን አስተምህሮ አንጻር እንያቸው፡-

በእርግጥ ግን አሳማ ይበላል? ይሄንንስ አባ ወልደትንሣኤ ብለዋል ወይ? ከተባለ አባ ወልደትንሣኤ አሳማን ብቻ ሳይሆን አይጡንም ጉርጡንም እባቡንም ፈረሱንም ውሻውንም ሁሉንም ነገር ይበላል እንደሚሉ እገምታለሁ፡፡ ይሄንን በማለታቸው ግን መናፍቅ የሚሏቸው ሰዎች ካሉ በአብነት ትምህርትቤቶች በመጽሐፍ ቤትና በቅኔ ቤት የሚሰጠውን የቤተክርስቲያንን አስተምህሮ ጨርሶ የማያውቁ እንደሆኑ ማረጋገጥ ይቻላል፡፡ ይሄ ማለት ግን የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን እነኝህን እርኩስ ነገሮች እንዲበሉ ትሰብካለች ታበረታታለች ማለት አይደለም፡፡ የመልእክታተ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስን ትምህርት ስታስተምር ይሄንን ትምህርት የግድ ማስተማር ስላለባት እንጅ፡፡

ከገማልያል ስር የተማረው ሳውል (ጳውሎስ) እነኝህ እንስሳት በእግዚአብሔር ትዕዛዝ እርኩስና የማይበሉ መሆናቸውን እያወቀ ዘሌ. 11፤1-47 ዘዳ. 14፤4-21 እንዴት “በሥጋ ገበያ የሚሸጠውን ሁሉ ከሕሊና የተነሣ ሳትመራመሩ ብሉ፤ ምድርና በእርስዋ የሞላባት ሁሉ የጌታ ነውና” 1ኛ. ቆሮ. 10፤25 በማለት ያስተምራል? ከተባለ “…እንግዲህ የምትበሉ ወይም የምትጠጡ ብትሆኑ ወይም ማናቸውን ነገር ብታደርጉ ሁሉን ለእግዚአብሔር ክብር አድርጉት። እኔ ደግሞ ብዙዎቹ ይድኑ ዘንድ ለጥቅማቸው እንጂ የራሴን ጥቅም ሳልፈልግ በሁሉ ነገር ሰውን ሁሉ ደስ እንደማሰኝ፥ ለአይሁድም ለግሪክም ሰዎች ለእግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያንም ማሰናከያ አትሁኑ” 1ኛ. ቆሮ. 10፤31-33 በማለት ይሄንን የሚያደርገው ክርስትና የሚሰበክላቸው አሕዛብ፣ አረማውያንና ኢአማንያን የለመዱትንና የሚወዱትን ነገር ሲከለከሉ ወንጌልን ከመቀበል ወደ ኋላ እንዳይሉ፣ ሁሉም እንዲድን ካለው ጉጉትና ስስት የተነሣ እንደሆነ ይነግረናል፡፡  ልብ በሉ ይህ የተደረገው ትምህርቱና ባሕሉ ስለሌላቸው፤ እንግዶች ስለሆኑት ስለ አሕዛብ አረማዊያንና ኢአማንያን ሲባል ነው፡፡

ቅዱስ ጳውሎስ ሁሉም በክርስቶስ አምኖ ይድን ዘንድ ከመሻቱ የተነሣ “በሥጋ ገበያ የሚሸጠውን ሁሉ ከሕሊና የተነሣ ሳትመራመሩ ብሉ፤ ምድርና በእርስዋ የሞላባት ሁሉ የጌታ ነውና” ሲል ግን “አትብሏቸው ያረክሳሉ” ብሎ የከለከለው እሱ እራሱ እግዚአብሔር መሆኑን ዘሌ. 11፤1-47 ዘዳ. 14፤4-21 አውቆ ዘንግቷል፡፡ ምን ያድርግ? ቢቸግረው ነው፡፡ ነገር ግን “የጌታ ነውና” በሚለውማ ከሔድን ሰይጣንስ ቢሆን የሱ አይደል? ሌላ ፈጣሪ የለ!

እንግዲህ ጳውሎስን ከሐዋርያቱ ሁሉ ለየት የሚያደርገውም ይሄ ድፍረት የተሞላበት አኪያሔዱ ነው፡፡ በዚህ አኪያሔዱ የተነሣ ከሐዋርያት ጋር እስከመጣላት የደረሰበት ወቅትም ነበር፡፡ ይሁን እንጅ ቅዱስ ጳውሎስ ይጠቅማሉ ይበጃሉ ከሚል ቀና አስተሳሰብ አንዳንድ ወጣ ያሉና የተለዩ ትምህርቶችን ሰጥቶ ሲያበቃ ግን “…እኔ እላለሁ፥ ጌታም አይደለም!” 1ኛ ቆሮ. 7፤12 “…የጌታ ትእዛዝ የለኝም፥ ነገር ግን የታመንሁ እሆን ዘንድ ከጌታ ምሕረትን የተቀበልሁ እንደ መሆኔ ምክር እመክራለሁ፡፡ እንግዲህ ስለ አሁኑ ችግር ይህ መልካም ይመስለኛል፤ ሰው እንዲህ ሆኖ ቢኖር መልካም ነው” 1ኛ ቆሮ. 7፤25 በማለት መደናገር እንዳይፈጠር ያስጠነቅቃል፡፡ ይሄንን ሲያደርግ በጎ አስቦ ነውና በእግዚአብሔር ዘንድ በደል እንደማይሆንበት ጠንቅቆ ያውቃል፡፡

ይሄ ድርጊቱ የሚያሳየን ዐቢይ ጉዳይ ቢኖር ምንድን ነው? ለካህናት የተሰጣቸው ሥልጣን ከፍተኛ መሆኑን ነው፡፡“እውነት እላችኋለሁ በምድር የምታስሩት ሁሉ በሰማይ የታሰረ ይሆናል፥ በምድርም የምትፈቱት ሁሉ በሰማይ የተፈታ ይሆናል” ማቴ. 18፤18 ይላልና፡፡ ኃጢአት ስለሠራ ኃጢአተኛ የሆነንና እንደ የእግዚአብሔር ቃልም ለኩነኔ ሊዳረግ የነበረ ሰው ካህኑ ስለፈታው ብቻ በሰማይም የተፈታ ወይም የጸደቀ ይሆናል፡፡ ይሄንን ያህል ነው ሥልጣናቸው፡፡ ቅዱስ ጳውሎስም የተጠቀመው ይሄንን ሥልጣን ነው፡፡

አባ ወልደትንሣኤ የአሁኑ አቡነ በርናባስ የሐዋርያው ጳውሎስን መንገድ የተከተሉ እየመሰላቸው የሚያደርጉትን ነገር እንደሚያደርጉ ከሚያደርጓቸው ነገሮች መረዳት ይቻላል፡፡ ያልተረዱት ነገር ቢኖር ቅዱስ ጳውሎስ ያንን ያደረገው ጥቅም ቀርቶባቸው፣ ቁስልን ተሰቅቀው ወንጌልን ከመቀበል በክርስቶስ ከማመን ወደ ኋላ እንዳይሉ ባሕሉ ላልነበራቸው፣ አስተምህሮው ለሌላቸው ለአሕዛብ ለአረማዊያንና ለኢአማንያን እንጅ ይሄንን በማስተማሩ ለተቃወሙት አስተምህሮው ባሕሉ ለነበራቸው አይሁዶች ወይም ኦሪትን ለተቀበሉ አለመሆኑን ነው፡፡ ሁሉቱ ሰፊ መሠረታዊ ልዩነቶች አሏቸው፡፡

በየትኛውም መንገድ፣ ባሕል፣ አስተሳሰብና አስተምህሮ ቢሆን በኩርና ተከታይ፣ ብዙ የደከመ ባለመቶና በመጠኑ የደከመ ባለ ሠላሳ ወይም ምንም የሌለው እኩል ሊታዩ ሊመዘኑ ሊገመቱ የሚችሉበት አግባብና አሠራር የለም፡፡ አባ ወልደትንሣኤ ወይም አቡነ በርናባስ የሳቱት ይሄንን ነው፡፡

አባ ወልደትንሣኤ የቅዱስ ጳውሎስን አስተምህሮ ለነማን መስበክ እንዳለባቸው አላወቁም፡፡ ለነማን? መቸ? ለምንና እንዴት? ሳይሉ ዝም ብለው እንደወረደ ነው እያስተማሩት ያለው፡፡ ይሄ ደግሞ ስሕተት ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ እንኳንስ አማኙ አረማዊውና አሕዛቡ እንኳ አሳማውን ፈረሱን፣ አይጡን ጉርጡን፣ እባቡን ውሻውን የመብላት ባሕል የለውም፡፡ ይሄ ባሕል ለሌለውና ለሚጸየፈው ብሉ ብሎ ማስተማር ቅዱስ ጳውሎስ ጌታ የሞተለትን ከማሰናክል በማለት“…ስለዚህም መብል ወንድሜን የሚያሰናክለው ከሆነ፥ ወንድሜን እንዳላሰናክለው ለዘላለም ከቶ ሥጋ አልበላም” 1ኛ ቆሮ. 8፤13 በማለት እጅግ የተጠነቀቀለትን ምስጢር አለማወቅ ነው፡፡ አባ ወልደትንሣኤ በዚህ አስተምህሯቸው ምክንያት ለተሰናከሉባቸው ነፍሳት የሚጠየቁ መሆናቸውን የማያውቁ ከሆነ ምንም የገባቸው ነገር የለም፡፡

ወደ ተከታዩ ክሳቸው ስንሔድ “በኦርጋን ያስጨፍራሉ” የሚለው ነው፡፡ አዎ በእርግጥ እሳቸው ይሄንን ያደርጋሉ፡፡ ይሄንን የሚያደርጉት ደግሞ “እስትንፋስ ያለው ሁሉ እግዚአብሔርን ያመስግን!” የሚለውን ቃል አሳስተው ተርጉመው በመረዳታቸው ነው፡፡ “እስትንፋስ ያለው ሁሉ” ማለት ድምፅ የሚሰጥ ነገር ሁሉ ማለት መስሏቸዋል፡፡ እስትንፋስ ያለው ሁሉ ማለት ሕይዎት ያለው ነገር ሁሉ ማለት እንጅ ሲመታ ድምፅ የሚሰጥ ግኡዝ ነገር ሁሉ ማለት አይደለም፡፡ እሳቸው ያልተባለውን በተሳሳተ አረዳድ እንደተባለ ቆጥረው ሥጋዊ የዘፈን ፈቃድንና ስሜትን ለማርካት የዘፈን መሣሪያዎችን ሁሉ እያንጫጩ ለመጠቀም መሞከር በእውነት እግዚአብሔርን አለመፍራትና አለማፈር ነው፡፡

ይሁንና አባ ወልደትንሳኤ ይሄንን በማድረጋቸው የምእራቡ ዓለም የዜማ ባሕል ምርኮኛ ወይም ዳንኪረኛ ናቸው ሊያሰኛቸው ቢችል እንጅ መናፍቅ ሊያሰኛቸው አይገባም፡፡ ምክንያቱም የአኃት (እኅቶች) አብያተክርስቲያናት የመዝሙር መሣሪያም ይሄው ነውና፡፡ ኦርጋን የአኃት አብያተክርስቲያናት የመዝሙር መሣሪያ ነው ስል ግን እኛም ኦርጋንን በመዝሙር መሣሪያነት እንቀበለው እንጠቀምበት እያልኩ አይደለም፡፡ መሆንም የለበትም፡፡ ከአኃት (ከግብጽ፣ ከአርመን፣ ከሶሪያ፣ ከህንድ) አብያተክርስቲያናት ጋር በዚህ ጉዳይ ላይ ብቻ ሳይሆን ባጠቃላይ በሥርዓትና ቀኖና ጉዳዮች ላይም እንኳ ሰፊ ልዩነቶች እንዳሉን መገንዘብ ይገባል፡፡

እነሱ የሐዲስ ኪዳን ልጆች እንደመሆናቸውና በኦሪቱ ዘመን እግዚአብሔርን አለማወቃቸው በኦሪት ሥርዓት እግዚአብሔርን አለማምለካቸው ለልዩነቱ መፈጠር ዐቢይ ምክንያት ነው፡፡ በመሆኑም አኃት አብያተክርስቲያናት እኛ በብሉይ ኪዳንም እግዚአብሔርን አምላኪዎች በመሆናችን ያሉን ጠቃሚና አስፈላጊ አገልግሎቶች፣ ሥርዓትና ሃይማኖታዊ ባሕሎች እነሱ የሏቸውም፡፡ ጉዳዩ እንዲያውም ከዚህም አልፎ እኛ ነባር እግዚአብሔርን አማኝ አምላኪ እነሱ አዲስ እንግዶች ከመሆናቸው የተነሣ ዶግማዊ ሊባል የሚችል ልዩነት የሚታይበት ሁኔታም አለ፡፡ ለምሳሌ እኛ ጽላትና ታቦት አለን፡፡ የጽላትና የታቦት አገልግሎት ለእኛ ቤተክርስቲያን ሊቀር ሊለወጥ ሊሻሻል የማይችል ዶግማ (አምደ እምነት) ነው፡፡ እነሱ ግን በስውራን ቅዱሳኖቻቸው ዘንድ ካልሆነ በስተቀር ጽላትና ታቦት የላቸውም፡፡

ከዚህም የተነሣ “ከስሩ ከመሠረቱ እንዴት ነው?” የሚያሰኝ ሥርዓት ወይም ጥያቄ በሚያስነሡ ጉዳዮች ላይ ያላቸውና የሚከተሉት ሥርዓት አስተምህሮና ሃይማኖታዊ ባሕል እንደመሰላቸው በዘፈቀደ የሚደረግ ከመሆኑ የተነሣ ብዙ ጊዜ የተሳሳተ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ በዚህም ምክንያት “እነሱ ዘንድ እንዲህ ይደረጋልና እኛም ዘንድ እንዲህ ብናደርግ ችግር የለውም! ወይም ማድረግ ይኖርብናል!” ልንል የምንችልበት አግባብ አይኖርም፡፡ እነ አባ ወልደትንሣኤ ይሄንን ቁምነገር ነው የሳቱት፡፡

እናም የዚህ ኦርጋን የተባለው የዜማ መሣሪያ ጉዳይ እንዲያ ነው፡፡ በኦርጋን ዙሪያ ስላለው ጉዳይ ከቤተክርስቲያናችን ባሕልና አስተምህሮ አንጻር ያለውን አጠቃላይ ጉዳይ “እውን ኦርጋን የመዝሙር መሣሪያ ነውን?” በሚል ርእስ ከጻፍኩት ጽሑፍ መረዳት ይቻላልና ይሄንን ይዝ (ሊንክ) ተጭነው ይረዱ፡፡

https://www.satenaw.com/amharic/archives/13054

ሌላኛው ክስ ደግሞ “አባ ወልደትንሣኤ ሰንበቴን በቢራና በውስኪ እንዲወጣ ፈቅደዋል” የሚለው ነው፡፡ እንደ ይሄንን ክስ ያቀረቡ ምእመናን ግንዛቤ ሰንበቴም ሆነ ማኅበር የሚወጣው በጠላና በእንጀራ ብቻ ነው፡፡ ከዚህ ውጪ ባለ መጠጥና ምግብ እንዳይደረግ በሕግ የተደነገገ ይመስላቸዋል፡፡ ይሄ ብቻ ሳይሆን ሕግና ድንጋጌ የሌለውና በተገኘው ነገር ሊፈጸም የሚችለው ብዙው ነገር ሁሉ እነሱ ከሚያውቁት በተለየ መንገድ ሲደረግ ሲያዩ ያ ለእነሱ ኑፋቄ ወይም ክህደት ነው፡፡

እንግዲህ እነዚህን ወገኖች ለዚህ የተሳሳተ ድምዳሜና ፍረጃ የሚዳርጋቸው አለማወቃቸው ነውና ተቆርቋሪነታቸውን ልናደንቅ የሚገባ ቢሆንም ይሄንን ተቆርቋሪነት ከቤተክርስቲያናችን ቀኖና ሥርዓት ሕግና ድንጋጌ አኳያ እያዩ እንዲያደርጉት እየመከርኩ ስሕተታቸውን በክፋት ሳንመለከት ማለፍ ይኖርብናል፡፡ ነገር ግን እንዲህ በቀላል በተሳሳተ ግንዛቤ የሰው ስም መጥፋቱና መሰበሩ ለእነሱም ቢሆን ዕዳ በደል ነውና የሚሆንባቸው በዚህ ስሕተታቸው ሊሰማቸውና ሊጠነቀቁም ይገባል፡፡ ንስሐም መቀበል ይኖርባቸዋል፡፡

እና እንግዲህ አባ ወ/ትንሣኤን በመናፍቅነት ያስከሰሷቸውና የማውቃቸው እነኝህና ክሶቹም ተገቢ ያልሆኑ ናቸው፡፡ አባ ወ/ትንሣኤ ሌላ ዶግማን በተመለከተ ኑፋቄ እንዳለባቸው ወይም እንዲህ ብለው የተሳሳተና ኑፋቄ ሲያስተምሩ ሰምቻለሁ የሚል ሰው አጋጥሞኝ አያውቅም፡፡ እናም አባ ወልደትንሳኤ ከላይ የጠቀስኳቸው ሊያስተካክሏቸው የሚገቡ ጉዳዮች እንዳሉ ሆነው ሥልጣኑ ይገባቸዋል ስም ማጥፋቱ ተገቢ አይደለም እላለሁ፡፡

የኑፋቄ ጉዳይ ከተነሣ ግን አሁን ላይ በጵጵስና እንዳሉና እራሴን ምስክር አድርጌ በልጅነቴ ያየሁትንና የሰማሁትን በመጥቀስ በመናፍቅነት የከሰስኳቸው አቡነ ዮሐንስ ጉዳይ ቢጣራ መልካም ነው፡፡ ከኑፋቄያቸው ተመልሰው ከሆነ ለጵጵስና የበቁት እሰየው ነው፡፡ በእርግጥ አንድ ያጠፋ የተሳሳተ ሰው ንስሐ ገብቶ ሊመለስ የሚችልበት ሁኔታ ስላለ ያን ስሕተቱን አሁንም እየፈጸመ መሆኑ ካልታወቀና ካልታየ በስተቀር ቀድሞ በፈጸመው ስሕተት አሁንም መውቀስ መክሰስ ስሕተት ነው፡፡ ከዚህ የተነሣ ነው እንዲጣራ መጠየቄ፡፡

እንዲያው ልዑል እግዚአብሔር የማይመከሩ የማይገሰጹ የማይመለሱ እንደሆን እኒያን ሽማግሌ የዓለም ስማቸውን ባውቀው በዚያው ብጠራቸው ምንኛ ደስ ባለኝ ነበር አቡነ መልከጸዴቅ የሚባሉትን ማለቴ ነው በቶሎ ንቅል አድርጎ ይውሰድልን እንጅ እሳቸው የሚሠሩት ሥራ ቤተክርስቲያንን እጅግ እያወከ ነው፡፡

ወደ ሦስተኛው ነጥብ ማለትም “ካንድ መንደርና ቤተሰብ ብቻ የተውጣጡ ናቸው” ወደሚለው ስናልፍ፡- መቸም ነገሮችን ማጋነንና ፈጥሮ ማውራት የሐሰተኛ ሰው ልማድ ነውና ልማድ ሆኖባቸው ካንድ ቤተሰብና መንደር የወጡ አደረጓቸው እንጅ እነሱስ አይደሉም፡፡ ከአንድ ክፍለ ሀገር ናቸው ቢሉ ግን ትክክል ናቸው፡፡ እሱም ቢሆን እንዲህ ሊሆን የቻለው ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ጎንደሬ ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ ወገንተኝነት እየተሰማቸው ከእሳቸው ጋር ማበር መሰለፍ በወያኔ ዘንድ በጠላትነት ማስፈረጁን ሳይፈሩና ሳያፍሩ እየተቀላቀሏቸው ያሉት ካህናት ጎንደሬዎች በመሆናቸው ነው፡፡ ሌሎቹ ወያኔን እየፈሩ የማይቀላቀሏቸው ሆነ እንዴት ይደረግ ታዲያ?

ምናልባት ግን ሲኖዶሱ የወያኔ ቅጥረኛ ያልሆነ፣ አሳልፎ የማይሰጣቸውንና የሚታመንን ሰው ሲፈልጉ የግድ የሚያውቁትንና የሚቀርቡትን ሰው ለመሾም ተገደው ከሆነና በዚህም ምክንያት የአንድ አካባቢ ሰዎችን የሚሰበስቡ ዘረኞች መስለው ታይተው ከሆነ ለዚህ ችግር ተጠያቂው የዘረኝነትን ከል ቤተክርስቲያን ላይ የጫነባት የመረዛት ወያኔ እንጅ ሲኖዶስ ሊሆን አይችልምና በዚህ ጉዳይ ላይ ሲኖዶስን እየከሰሳቹህ ያላቹህት ወገኖች ልብ ግዙ እላለሁ፡፡

ልዑል እግዚአብሔር የቤተክርስቲያንን ጋኔን ወያኔን አጥፍቶ፣ የቤተክርስቲያናችንን ሰላምና ደኅንነት መልሶ፣ ቤተክርስቲያን ወያኔ ካመጣባት ደዌ ተፈውሳ ለማየት ያብቃን አሜን!!!

ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው

amsalugkidan@gmail.com

 

 

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.