መጨዋወት መልካም–እንጨዋወት (ግርማ በቀለ)

ለሰሞኑ — ህወኃት እና የግንቦት ሃያ ቱርፋቶች ከሃያ አምስት ዓመታት በኋላ

Woyane 788-0መነሻው አንድ ወዳጄ ‹አንተን ከማውቅህና ካደግክበት የመቻቻል ልምድ በተለየ በዚህ መንግስት ላይ እንደዚህ ያማረረህና ያመረርከው፣ የአገሪቱን ለውጥ ለማየት የጋረደብህ ምንድን ነው አጫውተን ›› በሚል ያቀረበው ተደጋጋሚ ጥያቄ ነው፡፡ ጥያቄው መጽሃፍ የሚወታው መልስ ሊጻፍበት ቢችልም ለጨዋታ/ ለማሰላሰያና መተከዢያ ያህል ይህቺን ጫርኩ፡፡

(ክፍል አንድ)
ህወኃት ይዞልን የመጣውን ራዕይ በኢኮኖሚ ልማት፣ ፖለቲካ ፣ እና ማኅበራዊ ጉዳይ ዘርፎች ጠቅለል አድርገን ስንመለከት ብዙ ነገሮች በየዘርፉ ተረት-ተረት እንዲሆኑ የተያዘ እቅድ እንደሆነ እንመለከታለን፡፡ ዘርዘር ስናደርገው፡-
በኢኮኖሚው — ዜጎች በቀን ሶስት ጊዜ ተመግበው ፣ረሃብ ተረት ሆኖ በፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል ዜጎች ወደ መካከለኛ ገቢ የሚመነደጉበት አገራችንም በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ ኢኮኖሚ ባለቤት የምትሆንበት ፣

በፖለቲካው— ጦርነት ተረት የሚሆንባት የዜጎች መብት የተከበረባት፣ በልዩነት ላይ በተመሰረተ ጠንካራ አንድነት በዜጎች መካከል እና ከጎረቤት አገሮች ያለው ግኝኑነት የተጠናከረ አገር የምንገነባበት አሳታፊ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት የሰፈነበት፣
በማኅበራዊ— በብሄር ብሄረሰቦች መካከል ያለው ልዩነት እና ያለመተማመን/የጥርጣሬና ጥላቻ ስሜት ከስሩ ተነቅሎ የሚጣልበት፣ መቻቻልና አብሮነት ተጠናክሮ የገዢ/ተገዢ ግንኑነት የሚያከትምበትና ተረት ተረት የሚሆንበት፤ እንደሆነ እንረዳለን ፡፡
በዚህ ከተስማማን የግንቦት ሃያ ቱርፋቶችን ከዚህ አንጻር ስንፈትሽና ስንመዝን — በፀረ-ልማትና ጸረ-ሰላም ጦርነት ናፋቂዎችና ቀናተኞች ዕይታ ካልሆነ በቀር የሚከተሉትን መካድ የማይቻሉ ለውጦች መጨበጣችን እርግጥ ነው፡፡

1. በኢኮኖሚ
ራዕዩ–በኢኮኖሚው — አገራችን ዜጎች በቀን ሶስት ጊዜ ተመግበው ፣ረሃብ ተረት ሆኖ በፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል ዜጎች ወደ መካከለኛ ገቢ የሚመነደጉበት አገራችንም በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ ኢኮኖሚ ባለቤት የምትሆንበት ፣
አዎን — ባዶ እጃቸውን ወደ ከተማዋ የዘለቁ ፣ ከገቡም በኋላ የተቀላቀሉ የህወኃት ባለስልጣናትና የጥቅም ተጋሪዎቻቸውና የኢህአዴግ እና አጋር ድርጅቶች ባለሥልጣናት እርግጥ ነው በቀን ሦስት ጊዜ ከመብላት አልፈው መለኪያው 3 ሺህ ብር በሚያወጣ አልኮል በቀን ሦስት ጊዜ መስከር ከሚችሉበት ደረጃ ደርሰዋል፡፡ በተጨማሪም የአገሪቱን ከተሞች በተለይ አዲስ አበባና ዙሪያዋን ባለሰማይ ጠቀስ ፎቅ በማድረግ ከውጪ የሚመጡ ኢንቨስተሮችን ቀርቶ የእኛን ምስክርነት አግኝተዋል፡፡ በዚህ ሂደት ትናንት የማይታወቁ ከሜዳ የተነሱ ሚሊየኔር ኢንቨስተሮች ተፈጥረው አገራችን ከሶስት ሺህ በላይ ሚሊየኔሮች እንዳሏት ተመዝግቦላታል፡፡ በተጨማሪም በዓመቱ ቤተሰባቸውን የማይመግቡ ሚሊየነር የልማት አርበኛ ገበሬዎችና አርብቶ አደሮች ተፈጥረው በየዓመቱ ኒሻን ተሸልመዋል፡፡ አልፎ ተርፎም በውጪ አገር በሚሊየን ዶላር ሃብት የሚያጠራቅሙ ባለስልጣናትና ነጋዴዎች መኖራቸው የአደባባይ ምስጢር ሲሆን የመንግስት ባለሥልጣናት ‹ጥረው ግረው› በላባቸው ጭማቂ ያገኟትን ጥቂት ጥሪት/ከአንዳንዶች በቀር ከመቶ ሚሊዮኖች የማታልፍ/ ዶላር ባህር በማሻገር ቀዳሚ መሆናቸው የሚካድ አይደለም፡፡ ይህን የኢኮኖሚ ዕድገት በጥቅል ካነሳን በኋላ አንዳንድ ዋና ዋና ማሳያዎችን ብቻ ወደመመልከት እንሻገር፡፡
1.1. በቴክኖሎጂው ዘርፍ በኣለም አቀፍ መድረክ ተወዳዳሪ ሆነናል//
1.1.1. አሜሪካ አርባምንጭ ላይ ያኖረቺውን ድሮን/ሰው አልባ አይሮፕላን/ ከኮንትራት ጊዜው በፊት ይዛ ውልቅ በማለቷ የተበሳጨው ሜቴክ ድሮን የሰራበትን፤
1.1.2. አንድ ወጣት በአገሪቱ በተስፋፋው ጥራቱን የጠበቀ ትምህርት ( በጤናው ዘርፍ) በገበየው ዕውቀት እና በተፈጠረው የምርምር የተመቻቸ ሁኔታ ሰንዳፋ ላይ አይሮፕላን –በግል ያመረበትን፤
1.1.3. አሁን በቅርቡ በደምቢዶሎ የአሜሪካን ጄት ባህር ላይ ማረፉን ለመወዳደር የሚበቃ በጭቃ ላይ የሚያርፍ አይሮፕላንና አብራሪ ይህንም መራቂ ዶክተር ባለሥልጣናት ያገኘንበንት፣
1.1.4. አገሪቱን በባቡር ለማገናኘት አቅደን አዲስአበባን በሁሉም አቅጣጫ ያገናኘንበትን፤
1.2. ኤክስፖርት
1.2.1. ኤለክትሪክ ወደ ጎረቤት አገሮች የላክንበትና ዜጋው በኤሌክትሪክ እጥረት የሚሰቃይበት፣ የአገሪቱ ኢንዱስትሪዎች በኃይል እጥረት ለኪሳራ የተዳረጉበትን፤
1.2.2. ስኳር ከራሳችን አልፈን ለውጪ ገበያ ለማቅረብ አቅደን አስር ፋብሪካዎች አልመን ከተነሳንበት እንዱም ሳይሳካልን ለ 77 ቢሊዮን ብር ክስረት የተዳረግንበትንና ከውጪ እያስገባን ያለንበትን፣
1.2.3. ከምንም በላይ የተሳካልን ወታደር ልጆቻችንን ኤክስፖርት አድርገንሞታቸውንና አካላቸውን ለሰራዊቱና ቤተሰብ የማናሳውቅበት ነገር ግን ከፍተኛ የውጪ ምንዛሪ ገቢ ያገኘንበትን፣
1.2.4. ከየቱም አገር በተለየ ውሃ ከምድራችን ለጎረቤት ጂቡቲ በነጻ ያቀረብንበትን፣
1.2.5. ልጆቻችንን ለጎረቤት አረብ አገራት ኤክስፖርት በማድረግ ከፎቅ ላይ ያስወረወርንበት፣ ሥቃይና ሞታቸውን ሳንከታተል መከታ ሳንሆን ከዳረጎታቸው ከፍተኛ የውጪ ምንዛሪ ገቢ የሰበሰብንበትን፣
1.2.6. ከሌላው ዓለም ሁሉ በተለየ የውጪ ምንዛሪ ኤክስፖርት ስናደርግ በተደጋጋሚ በውጪ አገር ኤርፖርቶች የተያዝንበትን፤
ሁኔታዎችን ስንመለከት ህወኃት ይዞልን የመጣው ዕቅድ አልተሳካም ማለት በፀረ-ምናምንና ቀናተኛ ዓይኖች ካልተመለከትነው በቀር የኢኮኖሚ ልማቱንና ዕድገቱን በሺ የሚቆጠሩ ሚሊዬኔሮች ባፈራንበት አስር ሚሊዮን ወገን ተራበ ፣ ሃያ ሚሊዮን ህዝብ ለረሃብ ተጋለጠ ፣ ስደት በረከተ፣ የተማረ ኮብል ፈለጠ፣ … በሚል ብቻ እንደምን መካድ ይቻላል፡፡
እናንተ ካላላችሁ ዛሬ ላይ ትርፍ እንካፈልበታለን ተባለውን ‹‹የህዳው ግድብ›› ያለበትን አንስቼ ሆድ ኣስብሳችሁምና በእኔ በኩል እነዚህ በኢኮኖሚው ዘርፍ የታየውን ምጥቀትና ዕድገት ለመግለጽ ለማሳያነት ይበቃሉ፡፡ ከተመቻቸን ወደ ሌሎቹ ዘርፎች እዘልቃለሁ፡፡ እናንተም የራሳችሁን ‹ምርምር› ግኝቶች አክሉባቸው፡፡
እስከዚያው ከጸረ- ልማትና ሰላም ኃይሎችና ከቀናተኞች ጠብቆን ልማታችንን በያዝነው መንገድ ለማስቀጠል በቸር ያገናኘን፡፡ ሰኔ 20/2008. UNITE.

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.