ለክቡር አቶ አባዱላ ገመዳ ዳጎ (ግርማ ሠይፉ ማሩ)

ሀብታሙ አያሌው በጠና ታሞ በሆስፒታል
ሀብታሙ አያሌው በጠና ታሞ በሆስፒታል

ለክቡር አቶ አባዱላ ገመዳ ዳጎ

የኢፌዲሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ

አዲሰ አበባ

 

ጉዳዩ፤ አቶ ሀብታሙ አያሌው ህክምና እንዲያገኝ የበኩሎን እንዲያደርጉ ስለመጠየቅ

ሀብታሙ አያሌው የቀድሞ አንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ የነበረ ሲሆን ከሐምሌ 1/2006 ጀምር ለአስራ ሰምንት ወራት በአሸባሪነት ድርጊት ተሳትፏል በሚል ክስ ተመስርቶበት በእስር ቆይቷል፡፡ በአሁኑ ወቅት በሃሰት ከቀረበበት ውንጀለ በፍርድ ቤት ውሳኔ በነፃ ተሰናብቷል፡፡ ነገር ግን ዓቃቢ ህግ ይግባኝ በመጠየቁ ከእስር ውጭ ሆኖ እንዲከታተል በሰበር ውሳኔ በተሰጠው ትዕዛዝ መሰረት በውጭ ሆኖ ጉዳዮን በመከታተል ላይ ይገኛል፡፡ በይግባኙ ምክንያት ወደ ውጭ እንዳይወጣ በፍርድ ቤት እግድ ተደርጎበታል፡፡ በአሁኑ ወቅት በእስር በነበረበት ወቅት በደረሰበት ኢ-ሰብዓዊ አያያዝ የተነሳ በከፍተኛ ህመም እየተሰቃየ ሲሆን ለህይወቱ አሰጊ በሆነ ደረጃ ላይም ይገኛል፡፡ የጤናውን ሁኔታ ለማሻሻል ወደ ውጭ ሄዶ ተገቢውን ህክምና ማግኘትም አልቻለም፡፡

ክቡር አፈጉባዔ በዚህ ደብዳቤ እኔም ሆንኩ ሌሎች የሀብታሙ አድናቂዎች እና ቤተሰቦቹ በማክበር የምንጠይቀው ተጠሪነታቸው እርሶ በበላይነት ለሚመሩት ምክር ቤት የሆኑ የፍትህ አካላት ይህን ጉዳይ ትኩረት ሰጥተው እግዱ እንዲነሳ ግፊት እንዲያደርጉ እና ይህ ወጣት ልጅ ተገቢወን የህክምና ድጋፍ እንዲያገኝ የበኩሎን እንዲያደርጉ ነው፡፡

የደህንነትም ሆነ የፍትህ አካላት ሀብታሙ አያሌው ከሀገር ወጥቶ ይቀራል የሚል ጥቂትም ቢሆን ስጋት ካላቸው ተገቢውን ዋስትና ለመስጠት ዝግጁ መሆናችንን፣ በተለይ በግሌ አቶ ሀብታሙ አያሌው ታክሞ እስከሚመለስ ድረስ በማነኛውም ሁኔታ ከሀገር እንዳልወጣ የዋስትና እግድ ሊደረግብኝ ፈቃደኛ መሆኔን አስታውቃለሁ፡፡

ክቡር አፈጉባዔ ይህን ጥያቄ የማቀርበው የፖለቲካ ልዮነታቸን ለስብዓዊነት ሚዛን ምንም ፋይዳ የሌለው መሆኑን ያስመሰክራሉ በሚል ግምት ሲሆን፣ ይህን በጎ ድርጊት ለማድረግ እንደማይቸገሩም ስለማምን ነው፡፡

 

ከማክበር ሠላምታ ጋር

ግርማ ሠይፉ ማሩ

 

 

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.