ለቴዎድሮስ ካሳሁን ወይም ለጎሳዬ ተስፋዬ!

teddy &Gosayeቴዎድሮስ ካሳሁንና ጎሳዬ ተስፋዬ አልበሞቻቸውን (የዘፈን ጥራዞቻቸውን) ሊያወጡ ሥራዎቻቸውን እንዳጠናቀቁ እየተናገሩ ነው፡፡ ግሩም ግሩም ሥራዎችን እንደሚያደርሱን ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ቴዎድሮስ ወይም ጎሳዬ ይህችን ግጥም ጥዑመ ዜማ ይፈልጉላትና አንደኛቸው በአልበማቸው አካተው እንዲያወጡት በመሻት እንካቹህ ብያለሁ፡፡ የምትቀርቧቸው አድርሱልኝ፡፡

ከሁለቱ ውጭ ግን ሌላ ሰው ይሄንን የዜማ ግጥም ድርሰት በሙል ወይም በከፊል እንዲጠቀም አልፈቅድምና ከያኔያን ስሕተት እንዳይፈጽሙ ማሳሰብ እወዳለሁ፡፡

ቴዎድሮስ ወይም ጎሳዬ ዕድሉን ካልተጠቀሙበት ይህ ዕድል ለወጣቶቹ ጎሳዬ ቀለሙ ወይም ዳዊት ጽጌ የሚሰጥ ይሆናል፡፡

 

-ዖፈ ብርጋና-

የወፏን ሕይዎት ፤ ታሪክ ለመጻፍ

ብዕር አድርጎ ፤ የላባዋን ጫፍ

ላባ ለማግኘት ፤ ብራና የሚቀዝፍ

የግድ ነው ወይ? ፤ የወፏ ማለፍ ፡፡

 

ዕድሜ ነበራት ፤ ገና የምትኖረው

ሕልም ነበራት ፤ ብዙ የምትፈታው

ለጓጓችለት ፤ ለታላቅ ሕልሟ

ባትሞት ምን አለ? ፤ ተብሎ ለስሟ ፡፡

 

መብረርሽ ይቅር ፤ ላባን አርግፊ

ሰበብ ከሆነሽ ፤ እንድትጠፊ

ምግብሽ ያለው ፤ ከሆነ በዓለም

ሰማዩን ተይው ፤ ያለሽ ይረገም፡፡

 

ወፊቱ ስትበር ፤ ወይ ስታራጋፍ

ይወድቅ የለም ወይ? ፤ ላባዋ ከክንፍ

እንዴት ታሰበ ፤ የወፏ ማለፍ?

እስኪ እንጠይቅ ፤ ምንድን ነው ይሄ ጽንፍ? ፡፡

 

በኅብረ ቀለም ፤ ያሸበረቀው

ዖፈ ብርጋና ፤ ላባዋ ውብ ነው

ውበት ብርታቱ ፤ እያስቀናባት

ሞቷን ይሻሉ ፤ ማን ይታደጋት? ፡፡

 

እንደ ብርጋና ፤ የበረረ ወፍ

በአራቱ አቅጣጫ ፤ ከአጽናፍ እስከ አጽናፍ

ቢፈለግ የለም ፤ በሷ ያልታቃኘ

ግዙፉ እረቂቅ ፤ በሷው ተገኘ ፡፡

 

ስንቱ አበደ ፤ በፍቅሯ ማቅቆ

ስንቱ ተሠዋ ፤ ስለ እሷ ወድቆ

ዕንቆችን ወልዳ፤ በድንግልና

ለየሎስ ቀለብ ፤ አይተርፍ ናሙና ፡፡

 

ሊጻፍ ያልተሻው ፤ በደንብ ታሪኳ

አቅሙ አስገድዶ ፤ ተገልጿል ልኳ

አለመጻፉ ፤ በመቸት ጎልቶ

ፈጠራ መስሏል ፤ ገድሏ እምነት አጥቶ ፡፡

 

አሳሹ እና ፤ ታሪክ ጸሐፊው

ካላቹህ ግድ ነው ፤ ሞት ልትሆን ሕያው

ለታሪክ ድምቀት ፤ ለማኅተሙ

በደሟ ይጻፍ ፤ ይቅር ቀለሙ ፡፡

 

 

ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው

መስከረም 2006ዓ.ም.

amsalugkidan@gmail.com

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.