ጎንደር፥ የህዝቡ ትግል ሲግል-የኢህኣዴግ ውድቀት ሲቀላጠፍ !!! – ትዴት / ታንድ

Aregawi Berhe
Aregawi Berhe

ህዝብን በወታደርና በፖሊስ ሃይል ኣፍኖ መግዛት ጊዜው ያለፈበት የማያዛልቅ ፈሊጥ መሆኑ ያልገባቸው የኢህኣዴግ ኣምባገነን ቱጃሮች በኦሮሞ ምድር ላይ ያፈሰሱትን ደም ሳይደርቅ ሰሞኑን ደግሞ ፍትህ በጠማው የጎንደር ወገኖቻችን ላይ ተመሳሳይ ኣበሳ እያወረዱ ይገኛሉ። የህዝብ ብሶትና የኣበሳ ክምር መቀመቅ እንደሚከታቸው ለማየት ተስኖኣቸው፥ የህዝቡ ትግል ሲግል በሻእቢያ ሲያላክኩ መደመጣቸው የመሰሪነታቸው መለኪያ እንጂ ማንም ሊሞኝ እንደማይችል ልናረጋግጥላቸው እንወዳለን። ወቅታዊ ትግሉ ግፍ ያማረረው ህዝብ የቀሰቀሰው እምቢታ መሆኑና እንደሚቀጥልም ቢያውቁት ይበጃቸዋል።

በጎንደር ሰላማዊ ህዝባችን ላይ እየደረሰ ያለው የግድያና የኣፈና ሰቆቃ፣ የመርሳት ችግር እስካልተጠናወተን ድረስ፣ ኣዲስ ነገር ኣይደለም። ኢህኣዴግ ገና ከጅምሩ ስልጣን ላይ ጉብ እንዳለ በ1983 ዓ/ም የህዝብ ጥያቄ ኣንግበው ሰላማዊ ሰልፍ በወጡ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ላይ ያካሄደው ግድያ ላንዳፍታም ቢሆን የማይዘነጋ ግፍ ነው። እዛም ሳያቆም የግፉ መጠን፥ በስፋትም እየጨመረ ሄዶ በጋምቤላ፣ በሲዳማ፣ በኣዲስ ኣበባ፣ በኦጋዴን፣ ባጭሩ ህዝባዊ ጥያቄ በተነሳበት የኢትዮጵያ ኣካባቢ ሁሉ ተዳርሰዋል። ኣምባገነኖቹ ኣያሌ የንጹሃን ደም ያለገደብ እንዲፈስ ኣድርግዋል። ኣሁንም በጎንደር ይህንኑ ኣረመኒያዊ ተግባራቸው ቀጥለውብታል።

ከቅርብ ኣመታት ወዲህ ጀምሮ የኣዲስ ኣበባና የመቀሌ ከተሞችን እናሰፋለን በሚል ሰበብ የሰርቶ/ኣርሶ ኣደሩን መሬት ነጥቀው ብለውም ተከፋፍልው ለመሸጥ የጀመሩትን መሰሪና ስግብግብ ውጥን ህዝቡ በሰላም ሲቃወም – መቃወም መብት መሆኑ የማይገባቸውና ያለ ጥይት መልስ የማያውቁ ኣምባገነኖች – በህዝቡ ላይ ያወረዱት ግፍ ይህ ነው የማይባል መሆኑ ኣይዘነጋም። ከጥይት የተረፈው ህዝብም ኣብዛኛው ያለመጠወርያና ያለመጠጊያ ለማኝ ሆኖ እንዲኖር ሲገደድ፥ በስፋት ያልተዘገበው የመቀሌውን ብንወስድ፥ በዙርያ እግሪ-ሓሪባ መንደር ነዋሪ የነበሩት እንደነ ወይዘሮ ኣልጋነሽ ገብሩ (የ3 ህጻናት ብቸኛ ኣሳዳጊ) የመሰሉ እናቶች ጨምሮ ‘በሽብርተኛነት’ ተከሰው፥ ሌሎቹም ‘ኣድመኞች’ ተብለው እስርቤት ውስጥ ድርብርብ ስቃይ እያሳለፉ ናቸው።

የኣምባገነኖቹ ‘ህገ-መንግስት’ (ፕሮግራም ቢባል ይመጥነዋል) የመዘገበው መብት ተማምነው ሕጋዊ ኣቤቱታ ያቀረቡ፣ ሰላማዊ ሰልፍ የወጡ፣ ያመኑበትን ሓሳብ የገለጹ፣ ለሰብኣዊ መብት መከበር የቆሙ የተለያዩ ወገኖች በጠራራ ጸሓይ ተረሽነዋል፣ ታፍነው ተወስደው ደብዛቸው ጠፍተዋል፣ እስር-ቤት የሚማቅቁት እንደነ እስክንድር ነጋ፥ በቀለ ገርባ . . . ቆጥረን ኣንጨርሰውም። እንደ ኣሸል የፈሉት የኢህኣዴግ እስርቤቶች የጠባይ ማረሚያ መሆኑ ቀርቶ የበሳል ሓሳብ ኣፍላቂዎች መደፍጠጫ ወፍጮ ቤት ሆኖዋል።

ይህ የኣምባገነን ቱጃሮች መደብ በስልጣን እየኖረ፥ ጥቅሙን ለማራመድ ሲል የኣንዲት ሃገር ህዝብን በተለያዩ ፈሊጦች ከፋፍሎ፣ እየበዘበዘ፣ ተቃውሞ ሲነሳበትም በየተራ እየጨፈጨፈ ይሀውና 25 ኣመታት ሊዘልቅ ችለዋል። በኣንድ ህግ-ኣልባ ስርኣት ስር የሚማቅቅ ህዝብ ሁሉ ተቃውሞውን በተበታተነ መልኩ በማካሄድ ኣንድባንድ እየተመታ የመከራ ጊዜው ማራዘሙና እጅግም ኣሳሳቢ ጉዳት መጋበዙ ፈጦ የሚታይ ሃገራዊ ችግር ለመሆኑ ባያጠያይቅም፣ ከዚህ ኣደገኛ ኣዙሪት ለመውጣት በሚፈለግበት ጊዜ ኣንድ ጎልቶ የወጣ ትልቅ ችግር እንዳለ ከወዲሁ ለመጠቆም እንወዳለን። ይህም ለጋራው ትግል ኣሰላለፋችንና ኣደረጃጀታችንን ይመለከታል። ትግል የሚሳካው በዘፈቀደ ኣካሄድ ሳይሆን ስልቱና ስትራቴጂው ተጠንቶ ኣላማው ወለል ብሎ ሲታይና ለዚህ የሚያበቃ ኣደረጃጀትም ሲኖር ነው።

ኣሁንም ተበታትኖ እየታገለ – ኣንድባንድ እየተመታ ያለው ህዝባችን በኣንድነት እንዲነሳና የሚበጀው ስርኣተ-መንግስት እንዲያቆም ከተፈለገ ኢትዮጵያዊው የፖለቲካ ሊሂቅ የጋራ ኣመራር መስጠት መቻል ይኖርበታል።  የጋራ ኣመራር መስጠት ስንል ደግሞ ህዝቡን ኣስተባብሮ፥ ኣታግሎ ሃገራዊ የጋራ ስርኣት እስከመመስረት ላለው የጋራ ትግል ማቀናጀት ማለታችን እንጂ የፓርቲዎች የስልጣን ቅብብሎሽ እንዳልሆነ ግልጽ ማድረግ እንወዳለን።

የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ትብብር (ትዴት/ታንድ) በኣሁኑ ወቅት በጎንደር ሰላማዊ ህዝባችን ላይና ባጠቃላይ ደግሞ በመላው ኢትዮጵያ ህዝብ ላይ እየደረሰ ያለው ግድያና ኣፈና በምሬት እያወገዘ፣ ማውገዝ ብቻውን ግን ህዝቡ የሚጠብቀው ለውጥ ያመጣል ብሎ ኣያምንም። ይህ የኣምባገነን ቱጃሮች ስብስብ ስልጣን ላይ እስከተቀመጠ ድረስ በመላው ህዝባችን ላይ እየደረሰ ያለው ግፍ በውግዘት ሊቆም ስለማይችል፥ ኢህኣዴግን የማስወገዱና በሕግ የተገራ ስርኣት የመመስረቱ ትግል እንደቆየው በተበታተነ መልኩ ሳይሆን በተቀናጀና በተማእከለ መዋቅር ኣሁንኑ መካሄድ ኣለበት ይላል።

ትዴት/ታንድ ከዚህ በፊት ቀደም ሲል በኢተፖድህ፥ ከዛም በኢዴሃሕ ስም የትግል ኣንድንት ፈጥሮ ኣሁን ደግም በኢትዮጵያ ህዝብ የጋራ ትግል ሸንጎ (ሸንጎ) ስር ተደራጅቶ ኢህኣዴግን ለማስወገድና የጋራ ዴሞክራሲያዊ ስርኣት ለመመስረት እየታገለ ይገኛል። በዚሁም ሳይወስን ሸንጎው ያቀረበው ሰፊ ሃገር-ኣቀፍ የሕብረት ምስረታ ጥሪ እውን ለማድረግ ኣበክሮ ይታገላል።

ጭቁን የትግራይ ህዝብ እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ በኣምባገነን ቱጃሮቹ ግፍ እየማቀቀ እንደመሆኑ ሁሉ የተናጠል ትግሉ ጭቆናውን ከጫንቃው እንዳላወረደለት ጠንቅቆ ያውቃል። ለዚህም ነው ትዴት/ታንድ ትግሉ በሃገር ደረጃ መቀናጀት እንዳለበት በማመን በዚህ ረገድ ላቅ ያለ እንቅስቃሴም በማድረግ ላይ የሚገኘው። ለዚህም ነው ከየትም ይወርወር ከፋፋይ ቅስቀሳዎች ኣጥብቆ የሚቃወመው። የትግራይ ህዝብን የኣምባገነኑ መደብ ኣጋር ኣድርጎ የሚያይ ሽባ ኣመለካክት ከሽባነቱ ኣልፎ የጋራ ትግሉን ኣደናቃፊ በመሆኑ ኣጥበቆ ይቃወመዋል። የኢህኣዴግ ገዥ ቱጃሮችን በማንበርከክ የሥልጣን ባለቤት ለመሆን የኢትዮጰያ ህዝብ የሚያደርገውን ትንቅንቅ ለመበረዝና የሚካሄደው ትግልን ተራ የብሔሮች ቅራኔ በማስመሰል አንዳንድ ቡድኖች ለፕሮፓጋንዳ፥ ለፖለቲካና ለንብረት ፍጆታ ሲሉ ትግሉን ጥላሸት ሊቀቡት የሚዳዱ አደናቃፊዎችም በጊዜ ሃይ ሊባሉ ይገባል።

በሌላ በኩልም ጥቅማቸው የተነካባቸው ወይም ከገዢው መደብ ጋር የተሳሰሩ የህወሓት ካድሬዎች ህዝቡ ከጭቆና ስለሚላቀቅበት መንገድ ከቁምነገር ሳይቆጥሩና ላንዳፍታም ቢሆን የህዝቡን መከራ ሳይመለከቱ፥ ህወሓት እንደ ድርጅት ስለሚሻሻልብት ዘዴ ሲመክሩ ይደመጣሉ። ‘በስብሰናል’ ያለ ድርጅት ለመጠገን መሞከር ውጤቱ ኣብሮ መበስበስ እንደሆነ ልንነግራቸው እንወዳለን። የበሰበሰ ነገር ተወግዶ ለተኪው ኣዲስ ሁኔታ ስፍራው መልቀቅ ደግሞ ባህሪያዊ ነውና ከለውጥ ፈላጊው ሰፊው ህዝብ ጋር ቢራመዱ ለሁሉም ይበጃል። ከዚህም ይነሳ ከዛ ሁለቱም ጽንፈኛ ኣመለካከቶች ትግሉን የሚከፋፍሉ፥ ኣንድነታችንን የሚሸረሽሩ ለኢህኣዴግ ከፋፋይ ሴራ የሚያገለግሉ በመሆናችው ኣበክረን ልንቃወማቸው ይገባል።

የጎንደር ህዝብ ይሁን መላው ኢትዮጵያዊ የተነሳሳበትን የፍትህ፥ የኣንድነት፥ የሰላም ፍለጋ ትግል ማንም ሊያግደው የማይችል ማእበል ነውና፥ ጊዜ ሳይፈጅ ግቡ እንዲምታ በኣንድ ሃገራዊ ራእይ ስር ተሰባስበን እንታገል እንላለን።

 

የጋራ ጭቆና በጋራ ትግል ይወገዳል!!! የጋራ ሃገር በጋራ ጥረት ይለመልማል!!!

የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ትብብር (ትዴት/ታንድ) ፣ 18-7-2016

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.