በኮሉምበስ ኦሃዮ የወልቃይት ጠገዴና ጠለምት የአማራ ብሔር የማንነት ጥያቄን አስመልክቶ የተካሄደውን ስብሰባ በሚመለከት የተሰጠ መግለጫ፦

July 17 20016(ሐምሌ 10 ቀን 2008)

13731624_10209705498504977_3247603340161467476_n

በዚህ ኮሚቴው በጠራው የአስቸኳይ ጊዜ ስብሰባ በርካታ የጎንደር ክፍለ ሀገር ተወላጆች የተገኙ ሲሆን በኢትዮጵያ በተለይ በጐንደር ክፍለ ሀገር እና አካባቢው ስለአለው ወቅታዊ ሁኔታ በስፋት ከተወያየ በኋላ ስለተገደሉት፤ስለታፈኑት የወልቃይት ጠገዴና ጠለምት አስተባባሪ የኮሚቴ አባላት እና ደጋፊዎቻቸው እንዲሁም የቀሩት የኮሚቴ አባላት ላይ እየተደረገ ያለው የማሳደድ ዘመቻ ምን ማድረግ አለብን በሚል ርእስ ቀርቦ በርእሱ ላይ ሰፋ ያለ ውይይት ተደርጎ የሚከተለውን የአቋም መግለጫ አውጥቷል።

1/ ሐምሌ 5ቀን 2008 ዓ/ም(July 12 2016) የህ.ወ.ሃ.ት አፋኝና ከሃዲ ቡድን የፈፀመውና እንደልማዱ በጨለማ የወልቃይት ጠገዴና ጠለምት ተወላጆችን በማፈን የገቡበት እንዳይታወቅ እንዳደረጋቸው ሁሉ አሁንም ይህንን ስልት በመጠቀም በማን አለብኝነት ከራሱ ክልል አልፎ በአማራ ክልል ጐንደር ከተማ በመግባት የወልቃይት ጠገዴና ጠለምት አስተባባሪ ኮሚቴ አባላት ላይ ያደረገውን አፈና  ግድያና እስራት እናወግዛለን።

2/ ህዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ (ህ.ወ.ሃ.ት) +-ከ25 ዓመት በፊት በርሃ በትግል እያለ ይጠቀምበት የነበረውን የግድያና የአፈና ስልት አሁንም በመንግስት ደረጃ ተቀምጦ መፈፀሙ ያለውን ህዝብን የመምራት አቅምና ብቃት ደካማ መሆኑን በግልጽ ያሳያል።መንግሥት ህዝብን ከአፋኞችና ከአሸባሪዎች ይከላከላል እንጅ መንግሥት ራሱ አሸባሪና አፋኝ ሆኖ በንፁሃን ዜጎች ላይ በሌሊት የጥይት እሩምታ ማውረዱ በጣም አሳዛኝ ለህሊና የሚሰቀጥጥና ለወደፊቱም የሰላማዊ ህዝባችን ህይወት ጉዳይ ያሳሰበን መሆኑን እንገልፃለን።

3/ ሁላችንም እንደምናውቀው የተገደሉትና የታፈኑት የወልቃይት ጠገዴና ጠለምት አስተባባሪ ኮሚቴ አባላት ህጋዊ በሆነ መንገድ ራሱ የኢትዮጵያ መንግሥት ባወጣው ህገ-መንግሥት መሠረት መብታቸውን ለመጠቀምና ማንነታቸውን ለማስከበር ከተቋቋሙበት ቀን ጀምሮ በየቀኑ ወደ የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ጥያቄያቸውን በፁሑፍ በማቅረብ የመንግሥት አካላትን በማነጋገር ህጋዊ ፈቃድ ተሰጥቷቸው የሚንቀሳቀሱ አካላት መሆናቸው የታወቀ ሆኖ እያለ እነኝህ ህጋዊ ሰውነትና ፈቃድ ያላቸው የወልቃይት ጠገዴና ጠለምት አስተባባሪ የኮሚቴ አባላት አሸባሪ ናቸው በማለት የሀሰት ክስ መስርቶ ለመወንጀል መሞከር በህወሃት የወልቃይት ጠገዴና ጠለምትን የአማራ የማንነት ጥያቄ ለማዳፈን የተጠነጠነ ሴራ ከመሆን አልፎ እውነት መሆን እንደማይችል መላው የኢትዮጵያ ሕዝብና በተለይም የጐንደር ሕዝብ ያውቀዋል።ስለሆነም የወልቃይት ጠገዴና ጠለምት ሕዝቦች የማንነት ጥያቄ ግለሰቦችን በመግደል፤በማፈንና በማሳደድ የማይቆም የህዝብ ትግል መሆኑን ህወሃት ጠንቅቆ ማወቅ የሚገባው መሆኑን እያሳሰብን በግፍ ያለምንም ወንጀል በእስር ቤት እየማቀቁ ያሉትን የወልቃይት ጠገዴና ጠለምት አስተባባሪ ኮሚቴ አባላትና ደጋፊዎቻቸው በአስቸኳይ እንዲፈቱልን እንጠይቃለን።

4/ የትግራይ ወያኔዎች እንደሚያውቁት መብቱ የተነፈገ ህዝብ ለመብቱ ከመታገል ወደ ኋላ እንደማይልና የመብትና የማንነት ጥያቄ የመኖርና የአለመኖር ጥያቄ መሆኑን በመረዳት የህዝብን ጥያቄ ሰላማዊና ፍትሃዊ በሆነ መንገድ መልስ ከመስጠት ይልቅ በአፈናና በግድያ ህዝብን ጨርሰን ፍላጎታችንን እናሟላለን የሚለው ጽንሰ ሀሳብ ሌሎች መንግሥታት ሞክረው ያልተሳካላቸውና ጊዜው ያለፈበት ጠባብ አስተሳሰብ መሆኑን ተረድተው የወልቃይት ጠገዴና ጠለምትን ሕዝብ የአማራ ብሔር የማንነት ጥያቄያችንን በአስቸኳይ ፍትሃዊ መልስ እንዲሰጠን እንጠይቃለን።

5/ በዚህ በወልቃይት ጠገዴና ጠለምት አስተባባሪ ኮሚቴ ላይ በጐንደር ከተማ የተደረገውን አፈና እና ግድያ አፋኞቹ እንዳሰቡት ድምጽ አልባ ሆኖ እንዳይቀርና አፋኞቹ ራቁታቸውን እንዲወጡ በማድረግ ትልቅ አስተዋፅኦ ላደረገው የጐንደር ህዝብ ለሠሩት የጀግንነት ሥራ ተሰብሳቢው አክብሮቱንና አድናቆቱን እየገለጸ ታሪክ ሠሪው ህዝብ መሆኑንና አሁንም የጎንደር ሕዝብ የሠራው ታሪካዊ ገድል የወያኔዎችን የአፈና ሙከራ በማክሸፉ ያሳየው  ጀግንነት ያኮራው መሆኑን  ምስጋናውን በአድናቆት አቅርቧል።

6/ ተሰብሳቢው ይህንን የወልቃይት ጠገዴና ጠለምት የአማራ ብሔር የማንነት ጥያቄ ምላሽ እስከሚያገኝ እና የታሰሩት የኮሚቴ አባላት እስኪፈቱ ድረስ የጀመረውን ትግል አጠናክሮ እንደሚቀጥልና በአገር ቤት ጉዳዩን ለማስፈጸም እየተንቀሳቀሰ ለሚገኘው ሕጋዊ አስተባባሪ ኮሚቴ አስፈላጊውን የሞራልና የማቴሪያል ድጋፉን እንደሚያደርግ በመወሰን ተፈጽሟል።

7/ በመጨረሻም በዚህ አጋጣሚ ለትግራይ ሕዝብ ማሳሰብ የምንወደው የጥቂት ቱጃር ባለሥልጣናትን ጥቅምና ፍላጎት ለማስጠበቅ ብለህ የችግርህ ቀን ደራሽ ከሆነው በታሪክና በአብሮነት ከማትለያየው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር ከመቃቃርና ከመጋጨት ይልቅ ከጎናችን ተሰለፈህ እነዚህን የእናት ጡት ነካሾችና ከሃዲዎች ኢትዮጵያን ለመበታተን እያደረጉት ያለውን ታሪካዊ ውንድብድና በጋራ እናከሽፈው ዘንድ ጥሪያችን እናቀርባለን።

ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!

በሰሜን አሜሪካ የሚገኘው የወልቃይት ጠገዴና ጠለምት የአማራ ብሔር የማንነት ጥያቄ አስተባባሪ ኮሚቴ።

ኮሉምበስ ኦሃዮ