የወያኔ “ የመረጃና ማስረጃ” ድንፋታ፣ ይገረም አለሙ (ይገረም አለሙ)

የወያኔው ብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎትና የፌዴራል ፖሊስ የጋራ ፀረ ሽብር ግብረኃይል ያስራጨው የፕሮፓጋንዳ ወሬወያኔ የሙያ ማህበርም ይሁን የፖለቲካ ፓርቲ መሪ ለሥልጣኑ አስጊ ሆኖ ሲታየው ( ፕ/ር ዓሥራት ወ/የስ፤ ዶ/ር ታየ ወልደሰማያት) በምርጫ ሲሸነፍ ወይንም ልሸነፍ እችላለሁ ብሎ ሲሰጋ (ምርጫ 97) የዜጎችን የመብት ጥያቄ ተከራክሮ መርታት ወይንም ተገቢውን ምላሽ መስጠት ሲያቅተው፡ ( የሙስሊም ችግሮች መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ፤ የወልቃይት ኮሚቴ ) ሀሳብን በሀሳብ መሞገት፣ ብዕርን በብዕር መርታት ሲሳነው (በየእስር ቤቱ ያሉ ጋዜጠኞች ) ምን እንደሚያደርግ ትናንትን የመርሳት ችግራችን አሰረስቶን ካልሆነ በስተቀር የሚታወቅ ነው፡፡

ያለ ስማቸው ስም ሰጥቶ፣ ባልዋሉበት አውሎ፣ ያልሆኑትን አይደለም ፈጽሞ ሊሆኑ የማይችሉትን ናቸው ብሎ ማሰር ለሥልጣኑ ማረዘሚያ የሚጠቀምበት ዋንኛው ተግባሩ ነው፡፡ ታዲያ ሰዎቹ ተይዘው ከአዲስ አበባው ባዶ ስድስት ማዕከላዊ ከመድረሳቸው አስቀድሞ የተፈበረከው ወንጀል እየተዘረዘረ በቁጥጥር ሥር ያዋልናቸው ይህን በማድረጋቸው ነው ለዚህም ከበቂ በላይ መረጃም ማስረጃም አለን እየተባለ ይፎከራል፡፡

ነገር ግን የተባለው ወንጀል ሁሉ በአሳሪዎቹ ጭንቅላት ውስጥ ያለ እንጂ በመሬት ላይ ያልተፈጸመ በመሆኑ ሰዎቹን አስረው የሀሰት ማስረጃ ከማዘጋጀት በትዕዛዝ የሚፈርድ ችሎት እስከማቋቋም ይደርሳሉ፡፡ ከዛም ለረዥም ግዜ የማሰመሰያ ክርክር ይካሄድና የቀረባበቸውን ማስረጃ ማስተባበል ባለመቻላቸው ተብሎ የፖለቲከኞቹ ውሳኔ በዳኞች አፍ ይነገራል፡፡

በዚህ እኩይ ተግባር የተካኑት የተንኮል አባቱ አቶ መለስ ነበሩ፡፡ የእኔ የምለው የምሰራውም ሆነ የምናገረው የለኝም ብለው የአቶ መለስን ንግግር ብቻ ሳይሆን አነጋገራቸውን ሳይቀር ለመውረስ የሚቸገሩት አቶ ኃለማሪያምም ተያይዘውታል፤ሰሞኑን የወልቃይት ኮሚቴ አባላትን ለማፈን ጎንደር ዘምቶ ችግር የገጠመው ሁለተኛው መንግስትም ባወጣው መግለጫ ይህንኑ ፉከራ አሰምቶናል፡፡ በየግዜው የሰማነው ፉከራ ባዶ ክሶቹም የውሸት ለመሆናቸው ችሎቶችን የተከታተለ ዜጋ ሁሉ የሚመሰክረው ነው፡፡ እኔ የአይን እማኝ ከሆንኩባቸው መካከል የአንድን ሰው ምስክርነት በማስረጃነት ላቅርብ፡፡

ምርጫ 97 ሁሉንም ኢትዮጵያዊ ፖለቲከኛ አድርጎት ነበር ለማለት ባልደፍርም ሁሉም ሰው የእለት ተእለት የሀገሩን ሁኔታ እንዲከታተል አብቅቶት ነበር ማለት ግን ማጋነን አይሆንም፡፡ ማንበብ መጻፍ የማይችሉ አናቶች ሳይቀሩ ከቤተክርስቲያን ሲመለሱ አለያም ወደ ገበያ ወጣ ሲሉ ጋዜጣ እየገዙ ቤት ሲደርሱ አንብቡልኝ ይሉ እንደነበር የሚዘነጋ አይመስለኝም፡፡

ይህን የፖለቲካ ተነሳሽነት የፈጠሩት ሰዎች ሲታሰሩ ደግሞ የሁሉንም ትኩረት ሳበው ፡፡ ከሀገር ክህደት እስከ ዘር ማጥፋት የከበደ ወንጀል ተለጥፎባቸው አቶ መለስ እንደለመዱት በቂ መረጃና ማሰረጃ ይዘን ነው ያሰርናቸው እያሉ መፎከራቸው ደግሞ የችሎቱን ሂደት አጉዋጊ አድርጎት ነበር፡፡

ችሎቱ ቃሊቲ ወርዶ ቢርቅም፣ የውርጋጥ ደህንነት ተብየዎች ግልምጫ ስድብና ዛቻ ቢፈታተንም፤ ችሎት ሲገባ የነበረው ፍተሻ ቢያስመርርም፣የሚፈቀደው ለጥቂት የታሳሪ ቤተሰቦች ብቻ ቢሆንም ሁሉን ችለው ችሎቱን ከተከታትሉት አንዱ ነበርኩ፡፡ በቀዳሚነት የቀረቡት የአቃቤ ህግ የምስል (ቪዲዮ) ማስረጃዎች ሲሆኑ አይደለም አቶ መለስ የፎከሩበትን አቃቤ ህጉ ማስረጃዎቹ የሚያስረዱልኝ በማለት ለችሎቱ ከሚናገረው ጭብጥ ጋር የሚዛመዱ አልነበሩም፡፡ የድምጽም የሰነድም ማስረጃዎቹም እንደዚሁ፡፡ በዚህ አጀኢብ እያልን አየተገረምን ከሰው ምስክሮች ደግሞ ምን እንሰማ ይሆን በማለት ስንጠብቅ አብዛኛዎቹ ሰልጥነው የመጡ አባይ ምስክር መሆናቸውን እንጂ የሰዎቹን ወንጀለኛነት የሚያሳዩ አልሆኑም፡፡

ከእነዚህ ምስክሮች የአንዱን ነው በአስረጅነት የማቀርበው፡፡ እኝህ ሰው 367 ምስክሮች አሉኝ ያለው አቃቤ ህግ 59 አሰምቶ ቀሪዎቹ የተለየ አይመሰክሩም ሰርዣለሁ ተጨማሬ 15 ምስክሮች አቅርቤ ላሰማ ብሎ ተፈቅዶለት የመጀመሪያ ሆነው የቀረቡ ናቸው፡፡ አቶ ኑር ሁሴን ይባላሉ፣ ትግረኛ ተናጋሪ ሲሆኑ የሚኖሩት ሽሮ ሜዳ አካባቢ፣ የሚተዳደሩት በሀገር ባህል ልብስ ንግድ ነበር፡፡ ነብሳቸውን ይማረውና አሁን በህይወት የሉም፡፡ ጥቅምት 23/98 በመደብደባቸው መጀመሪያ ዘር ማጥፋት ኋላ ሙከራ ለተባለው ክስ ማስረጃ ሆነው ነው የተፈለጉት፡፡ አቃቤ ህግ መጀመሪያ ርሳቸውን ባለማግኘቱ ሁለት የቀበሌ ጆሮ ጠቢዎችን አሰልጥኖ ሽሮ ሜዳ አካባቢ ተደብድበው ወድቀው ሲያጣጥሩ አግኝተናቸው ማነው የመታዎት ብለን ሰንጠይቃቸው በግድ እየታገሉ ፍቃዱ እዮብ ቻይና (ብዙ ስም ጠርተዋል ) ናቸው፤ሽጉጤንም ወስደውብኛል ብለው ነግረውናል ብለው አንዲመሰክሩ አድርጓል፡፡ከዚህ በኋላ ነው አዴግራት ተገኝተው ሊመሰክሩ የመጡት፡፡

እንደ እምነታቸው መሀላ ፈጽመው ቃላቸውን ሲሰጡ አነጋገራቸው የሚያነቡ እንጂ በቃላቸው የሚናገሩ አይመስልም ነበርና ማጉረምረም ተሰማ፡፡ የመሀል ዳኛውም የምታመለክቱት ነገር ካለ ተናገሩና እናስፈትሻለን ከዛ ውጪ ማጉረምረም አይቻልም በማለት ቆጣ አሉ፡፡ እናስፈትሻለንን ምን አመጣው ዳኞቹም ተጠራጥረዋል ማለት ነው አልን፡፡ የጠየቀ ግን አልነበረምና ምስክሩ መናገራቸውን ቀጠሉ፡፡ የሚፈልጉት የተናገረላቸው አቃቤ ህጎች ለዘር ማጥፋት ሙከራ ክሳቸው አስተማማኝ ማስረጃ እንዳቀረቡ ተሰምቶአቸው ፊታቸው በደስታ ፈካ፡፡

ዳኛው ስማቸውን የጠሩዋቸውን ሰዎች እዚህ ካሉት መካከል ማሳየት ይችላሉ በማለት ምሥክሩን ሲጠየቋቸው አዎ በማለት ከመቀመጫቸው ተነስተው ከፊሎቹን በትክክል ከፊሎቹን ደግሞ ስማቸውን እያቀያየሩ ጠቆሙ፡፡

ከዛም መስቀለኛ ጥያቄ ካላ ሲባል አንድ መልከ መልካም ወጣት ከበስተኋላ በኩል እጁን አወጣ፡፡ ዳኛው ወደ ፊት ናና መነጋገሪያውን ተጠቅመህ ጥያቄህን አቅርብ አሉት፡፡ መነጋገሪያውን ተቀብሎ አንገቱን ሰብሮ በተቅለሰለሰ አነጋገር አቶ ኑር ሁሴን እንተዋወቃለን አይደል አላቸው ፤ ምስክሩም ወደ ቀኝ ዞር ብለው አተኩረው እያዩት ሳቅ አሉና አንተ ልጄ ፍቃዱ በደንብ እንተዋወቃለን እንጂ እኔን ልጆቼን ጸጉራችንን የምታስተካክለን አይደለህም እንዴ ሲሉት ፈጠን ብሎ ታዲያ እኔ ምን አደረኩዎት አላቸው፣ ማ አንተ እኔን አረ ምንም አላደረከኝም በማለት ሲመልሱለት እግዜር ይስጥልኝ ብሎ በፍጥነት ወደ መቀመጫው ተመለሰ፡፡

በዚህ የተደፋፈረ ሌላ ስሙን የጠቀሱት ወጣት እጁን አውጥቶ ሲፈቀድለት መነጋገሪያውን ተቀብሎ እኔ አልመታሁዎትም እግዚአብሔር ምስክሬ ነው፣ ሕዝብ ምሥክሬ ነው ሲል ዳኛው ጥያቄ ጠይቅ አሉት፤ እሱ ግን አልጠይቃቸውም እግዚአብሄር ይፍረድ በማለት ወደ ቦታው ተመለሰ፡፡

ሌላው ዕዮብ በቀለ በማለት የጠቆሙት ወጣት ቀጠለና እኔስ ምን አደረኩዎት አላቸው ፤ ምስክሩም ምንም አላደረከኝም፣ ሁላችሁም ምንም አላደረጋችሁኝም ዐቃቤ ሕግ ስላለኝ እንጂ፣ እኔ ተደብድቤ ተጥዬ ፍቃዱንስ ዕዮብንስ ሌላችሁንስ መች አየሁና አሉ፡፡ በዚህ ግዜ በደስታ ተምነሽንሸው ፊታቸው ፈክቶ የነበሩት ሶስቱም ዐቃቢያነ ሕጎች በድንጋጤ ፊታቸው ከሰለ ከንፈራቸው ደረቀ፤ ዳኞቹ አግራሞት ታየባቸው ፣ታዳሚው በደስታ ስሜት አጉረመረመ፡፡

ጓደኞቹን እንኳን አላናግር እያለ ለብቻው ይፏልል የነበረው ዐቃቤ ህግ ሽመልሽ ከማል መደበቂያ ያጣ መሰለ፡፡ ነገሩ ደግሞ በዝምታ የሚታለፍ አይደለም፣ በፍርድ ሂደቱ ላይ የሚያመጣው ለውጥ ባይኖርም ዝም ብሎ ማለፉ ያስገመግማል፡፡ በመሆኑም ሁለተኛው ዐቃቤ ህግ አብርሀ ተጠምቀ የሞት ሞቱን ከመቀመጫው ተነስቶ እየተርበተበ እንኳን ለምስክሩ ለራሱም ግራ በተጋባ ሁኔታ ጥያቄ ሲያቀርብላቸው ሰምቻለሁ፣ አላየሁም እያሉ አስተካላለሁ ያለውን ጨርሶ ሲያበላሹበት ክቡር ፍርድ ቤቱ የጤንነታቸውን ሁኔታ ግምት ውስጥ ያስገባልን በማለት አመለከተ፡

አንዳንዴ ነሸጥ እያደረጋቸው አንዳንዴም እውነት እየተፈታተነቻቸው ለደቂቃዎች እውነተኛ ዳኛ የሚሆኑት የመሀል ዳኛው አዲል አህመድ በቁጣ ቃል ችሎቱን ማሳሰብ አትችልም፤ጥያቄ ካለህ ጠይቅ ሲሉት ድንግጤው ብሶበት ጨርሻለሁ በማለት ተቀመጠ፡፡ ዳኞች የማጥሪያ ጥያቄ ቀጠሉ፤.
ጥ-ቅደም ደበደቡኝ አላሉም ነበር
መ-በል ተብዬ ነው
ጥ-ማነው ያለዎት
መ- ወደ ዐቃቢያነ ሕጎቹ እያመለከቱ እነርሱና ፖሊስ
ጥ- ማን እንደመታዎት በትክክል ያውቃሉ፡
መ-አላውቅም
ጥ- ሰማሁ ያሉት ማን ነው የነገረዎት
መ- መንግሥት
ጥ-መንግሥት ሲሉ ማንን ነው
መ-የደበደቡህ ተይዘዋል በማለት ማእከላዊ ጠሩኝ፣እዛ ስሄድ ስማቸውን ነግረውኝ እነዚህ ናቸው የደበደቡህ ፍርድ ቤት ቀርበህ ትናገራለህ አሉኝ ፤ምስክርነታቸው በዚሁ አበቃ፡፡ ይሄ ነው አንግዲህ የወያኔዎች መረጃም ማስረጃም አለን ፉከራ፡፡