ለብአዴኖች ማስጠንቀቂያ አዘል ምክር አለኝ – ግርማ ካሳ

BADNበሕዝቡና ህዝቡ መብቱን ለማስከበር በሚያደርገው እንቅስቅሴ መሃል አትግቡ። ይልቅ የሕዝቡን እንቅስቃሴ ተቀላቀሉ። የእንቅስቃሴው አካል ሁኑ። ሕወሃት የበሰበሰ፣ እንኳን በአማራው ክልል፣ እንኳን በሌሎች ክልሎች፣ በትግራይ ክልል ራሱ የተተፋ ዘረኛ ድርጅት ነው። አታዩም እንዴ በኦሮሚያ የተነሳዉን ተቃዉሞ ? አታዩም እንዴ በድፍን ሰሜን ጎንደር ዞን ምን ያል የህወሃት ነገር ሰውን እንዳንገፈገፈው ? አታዩም እንዴ እንደ ጄነራል ጻድቃን ገብረትንሳኤ፣ እንደ ጀነራል አበበ ተክለ ሃያማኖት ያሉ ቱባ ቱባ የቀድሞ ሕወሃት አመራሮች የሚጽፉትን እና የሚናገሩትን ? ሕወሃት ራሷ እርስ በርስ እየተከፋፈለችና እየተበጣበጠች ነው። ታዲያ ሞኝ ሆናችሁ ስለምን በስብሶና ደርቆ ተቀንጥሶ ሊወድቅ ትንሽ የቀረው ቅርንጫፍ ላይ መንጠልጠሉን መረጣችሁ ?

አብዛኛው የብአዴን መካከለኛው እና ታችኛው አመራር አባል የሆናችሁ ሕወሃት በብአዴን ላይ የጫነዉን ቀንበር አራግፋችሁ ለመጣል የቆረጣችሁ እንደሆነ እንሰማለን። ባለፈው የባህር ዳሩ የብአዴን ጠቅላላ ጉባኤ ላይ፣ ህወሃትን በተመለከተ ምን ትሉ እንደነበረ ይታወቃል። “”እነርሱ ባለ ፎቅ እየሆኑ እኛ ከነርሱ ጋር በመስራታችን የተረፈልን ሎተሪ መሸጥ ነው” ስትሉ እንደነበረ።

እንግዲህ የብአዴን አባላት በየቀበሌው በወረዳና ዞን ደረጃ ብተወያዩና ከታች ወደ ላይ የሆነ ድርጅታዊ እንቅስቃሴዎችን ብታደርጉ ጥሩ ሊሆን ይችላል። ከሕዝቡ ጋር ያላችሁት እናንተ ናችሁ። በሕወሃት ታዘው ከህዝብ ስሜትና ጥይቄ ጋር የሚቃረን መመሪያ የሚልኩ ከፍተኛ የብአዴን አመራር አባላትን ካሉ (ይኖራሉም) እነርሱን አንታዘዘም ማለት መጄምር አለባችሁ። በዚህ ወቅት ለሕዝቡ ያሳያችሁት ታሪካዊ አጋርነት በሕዝብ ልብ ዉስጥ የሚመዘገብ ነው የሚሆነው።

በፓርላማ ወደ 138 የምትሆኑ የብአዴን አባላት በአማራው ክልል የሚኖረዉን ህዝብ እንወክላለን የምትሉ አላችሁ። ምናልባት ሕወሃት በአዲስ አበባ ዘመናዊ ቤት ስለሰጣችሁ ወይንም ደሞዝ ስለምትቀበሉ፣ በፓርላማ በሕወሃት ረቆ የሚቀርቡትን አፋኝ ህጎች ለማጽደቅ ታጎበድዱ ይሆናል። ሆኖም ነገ ሕወሃቶች ከተጠቀሙባችሁ በኋላ እንደ ሸንኮራ አገዳ መጠው እንደሚተፏችሁ መርሳት የለባችሁም። ወክሎናል ከምትሉት ሕዝብ ጎን መቆሙ ይሻላቹሃል። ፓርላማው የሕወሃት መፈንጫ ሳይሆን የሕዝብን ጥያቄ የምታነሱበት ቦታ ይሁን። ፓርላማው ጌታቸው አሰፋ፣ ሶሞራ የነሱን እና ሌሎች በጸረ-ሽብርተኝኘት ስም ሕዝቡን የሚያሸብሩት ጠርቶ ማነጋገር መቻል አለበት ? እነ ሶሞራ የኑስ ምንድን ናቸዉና በፓርላማው ፊት የማይቀርቡት ? ጌታቸው ረዳ የተባለዉ የሕወሃቱ ግለሰብ እና የኢቢሲ ሃላፊዎች በሰሜን ጎንደር ሕዝብ ላይ ለከፈቱት የስም ማጥፋትና ዘረኛ ፕሮፖጋንዳ ለምንድን ነው በፓርላማ ቀርበው ተጠያቂ የማይሆኑት ? በዚህ ረገድ ጡንቻችሁን አፈርጥማችሁ በፓርላማ ዉስጥ መንቀሳቀስ አለባችሁ። ያንን ባታደርጉ ማን እንደሆናችሁ ህዝብ ያውቃል። በዚህ ወቅት ሕዝብን ወክለናል ብላችሁ ዝምታን ከመረጣችሁ ህዝብን እንደ ካዳችሁ ተደረጎ ነው የሚቆጠረው። ለዚህ ለክህደታችሁም ትልቅ ዋጋ እንደምትከፍሉ መረዳት አለባችሁ። ከዚህ በፊት የደነዛችሁና የሞታችሁ ነበራችሁ። ቢያንስ አሁን እንኳን ነቃ በሉ። ያን ካደረጋችሁ ሕዝብ የከዚህ በፊት ድንዛዜያችሁን ይቅር ብሎ በወሳኝ ወቅት ለወሰዳችሁት ወሳኝ አቋም አክብሮቱን ይለግሳቹሃል። ።

1 COMMENT

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.