በአክሱም ዩኒቨርስቲ መምህር የሆነው የአንድነት ፓርቲ አባል ዩኒቨርስቲው ውስጥ ባሉ ካድሬዎች በደል እየተፈጸመብኝ ነው አለ

መምህር ብርሃነመስቀል ንጉሤ ዘውዴ በአክሱም ዩኒቨርስቲ መምህር ሲሆን በአዳማ የአንድነት ፓርቲ አባል ነው የመጀመሪያ ዲግሪውን በ2001 ዓ.ም ከአዳማ ዩኒቨርስቲ በፔዳጎጂካል ሳይንስ ሁለተኛ ዲግሪውን በ2004 ዓ.ም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በሂዩማን ሪሶርስ ኤንድ ኦርጋናይዜሽናል ዴቨሎፐመንት ኢን ኢዱኬሽን አግኝቷል፡፡ አስከፊውን የኢህአዴግ ሥርዓት በሰላማዊ መንገድ ለመታገል የተቀላቀልኩት የ11ኛ ክፍል ተማሪ ሳለሁ ነው:: በ1997 ዓ.ም በምስራቅ ሸዋ ናዝሬት የመኢአድ አባል ነበርኩ፣ በ1998 ዓ.ም በሰላማዊ የተቃዋሚ ፓርቲ አባሎች የደረሰው ድብደባና አስራት በእኔም ደርሷል በማለት የገለጸው መምህር ብርሃነመስቀል፣ አሁን በአዳማ የአንድነት ፓርቲ አባል ሆኜ ዓመታትን አስቆጥሬያለሁ፡፡ በ1999 ዓ.ም አዳማ ዩኒቨርስቲ እንደገባሁ ተማሪውን የኢህአዴግ አባል ለማድረግ በየክፍሉ ባላቸው የሴል አመራር አባላት ተስፋ የቆረጡ ተማሪዎችን ወደኔ በመላክ እንዲጣሉኝ፣ በሃሰት እንዲወነጅሉኝ በማድረግ ከዩኒቨርስቲው እንድባረር የተለያዩ ሙከራዎች ቢደረግብኝም ፈጣሪ በሰጠኝ ብርታት በፔዳጎጂካል ሳይንስ ትምህርት ዘርፍ በከፍተኛ ማዕረግ ለመመረቅ በቃሁ፡፡

brhane Meskel Nigussiie
መምህር ብርሃነመስቀል ንጉሤ ዘውዴ

በአዳማ ዩኒቨርስቲ አብረን ለ3 ዓመታት አንድ ክፍል ስንማር የነበረ የብአዴን የተማሪዎች የሴል አመራር የሆነ በመረጃ (ጆሮ ጠቢነት) ሥራ ተጠምዶ የነበረ ለከፍተኛ ተቋም መምህርነት ስንማር ያልነበረውን ውጤት ይዞ አክሱም ዩኒቨርስቲ ለመቀጠር የበቃው መምህር ስለሺ ጎሹ ገና ግቢውን እንደረገጠ ወደተሰጠው ሚሽን በመግባት እኔን የአካባቢው ተወላጅ ከሆኑት ጋር በማጋጨት እንድባረር ለማድረግ ከፍተኛ ጥረት እያደረገ ይገኛል፡፡ ዛሬ በመምህርነቱ ሳይሆን በመረጃ አቀባይነቱን ተጠቅሞ ከፖለቲካ ጋር በማያያዝና በመክሰስ ህልውናዬ አደጋ ውስጥ ወድቋል፡፡

አንድ መምህር እንደ መምህር ሊገመገም የሚገባው በቂ ዝግጅት አድርጎ መግባት፣ ኮርሱን በተመደበለት (በታለመለት) ጊዜ ገደብ መጀመርና መጨረስ፣ ተማሪውን ሊመዝን የሚችል አግባብነት ያለው ቴስት፣ ፈተና አሳይመንት በማዘጋጀት ተማሪውን መመዘን፣ ከሃይማኖት፣ ከፖለቲካ፣ ከአድልዎ የፀዳ ውጤት መስጠት እና የመሳሰሉት ናቸው፡፡ እስካሁን ድረስ መማርና ማስተማርን አስመልክቶ በመደበኛ፣ኤክስቴንሽንና በክረምት መርሃ ግብር በሰጠኋቸው ኮርሶች ዙሪያ ምንም አይነት የፅሑፍና የቃል ቅሬታ በተማሪ ቀርቦብኝ አያውቅም፡፡

ከአዳማ ዩኒቨርስቲ ጀምሮ አብረን ስንማር የነበረውን አሁንም በማስተማር ላይ ያለውን መምህር ስለሺ ጎሹን በግምገማ ጎድተኸዋል በሚል ቂም በመያዝ የተቃዋሚ ፓርቲ አባል በመሆኔ ብቻ የሳይኮሎጂ ት/ት ስልጠና ሳይኖረኝ (ባልተቀጠርኩበት) ኮርስ በግድ እንዳስተምር መደረጉን በመቃወሜ ለማስተማር ፈቃደኛ አይደለህም በሚል ተወንጅያለሁ፡፡

መቼም ቢሆን እኔ በአቋሜ የፀናሁ ነኝ ኢህአዴግ አይደለሁም ብለሃል እና የመሳሰሉትን ምክንያቶች በመፍጠር እንዲሁም ከታች እስከ ላይ ያሉ የግቢው የአመራር እርከን ላይ ካሉ አካላት ጋር በመተባበር በግቢው ውስጥ እኔን ከፖለቲካ ጉዳይ ጋር አገኛኝቶ ጥላሸት በመቀባት እንድገለል ተደርጌያለሁ፡፡

የህወሓት አባል ከሆነው መምህር ሰለሞን ብርሃነ ጋር በመሆን ከምመራው የፕሮግራም መሪነት ምንም ቅሬታ ሳይኖር በህገወጥ መንገድ እንድነሳ አድርገው ከእኔ ጋር ቅሬታ ውስጥ ያለውን የብአዴን አባል መምህር ስለሺ ጎሹን የፕሮግራሙ መሪ አደረጉ፡፡ እነዚህን በደሎች ጠቅሼ ለሶሻል ሳይንስ ቋንቋዎች ኮሌጅ ክስ ሳስገባ ክሴን ሳያዩት ለተከሳሾች ከለላና ሽፋን በመስጠት ክሴን ውድቅ አድርገው በተገላቢጦሽ ኦፊሺያል የመጨረሻ የፅሑፍ ማስጠንቀቂያ በግቢው በሚገኝ የማስታወቂያ ቦርድ ላይ በመለጠፍ የስም ማጥፋት ዘመቻ አድርገውብኛል፡፡ እነሱ ለሚፈፅሙትና እየፈፀሙ ላሉት Acadamic Crime or acadamic Corruption ክስ አስገብቼ ቢያንስ በ15 ቀን ውስጥ ውሳኔ ይሰጠው ቢልም እኔ ግንቦት 25 ቀን 2006 ዓ.ም ያስገባሁት ማመልከቻ እስከ ዛሬ ድረስ ሳይታይ ቆይቷል፡፡

ለምን ይግባኝና ክስ አስገባህ በሚል ሰበብም በአንድ ወር ከአሥር ቀን እንደገና ሁለተኛ የመጨረሻ የጽሑፍ ማስጠንቀቂያና የአንድ ወር ደሞዝ ተቀጣሁኝ፡፡ ይህ ሳያንስ የመጨረሻ የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ ስለጻፍንብህ በዚህ ዓመት ክረምት ላይ ስፔሻላይዝ ያደረኩበትን ሙያዬን ማለትም EpDM ኮርስ እንዳላስተምር አግደንሃል ብለው ስለከለከሉኝ ማግኘት የሚገባኝን 32 ክሬዲት ሃወር በብር ሲሰላ 32,000 (ሰላሳ ሁለት ሺህ) ብር እንዳጣ ተደርጌያለሁ፡፡ የሚደረግብኝን ተጽዕኖና በደል በዩኒቨርስቲ ውስጥ ለሚመለከታቸው የተቋሙ ቢሮዎችና እስከ ትምህርት ሚኒስቴር ድረስ ባመለክትም ምላሽ የሚሰጠኝ አካል አጥቼ የሞራል ውድቀት እንዲደርስብኝ ተደርጌያለሁ፡፡ ከእንግዲህም በኔ ላይ ምን ለማድረግ እንዳሰቡ ለማወቅ ተቸግሬያለሁ፡፡ እኔ ለዚህች አገር ዜጋ ነኝ እንደ መምህርነቴ የት/ት ጥራት ጉዳይ ያሳስበኛል፡፡ ይህ የፖለቲካ ጉዳይ ብቻ ተደርጎ መወሰድ የለበትም፡፡ ሁላችንም እንደ አገር ማሰብ አለብን፣ በማለቴ እንደ ወንጀለኛ አስቆጥሮኛል፡፡ አሁንም ምን እንዳዘጋጁልኝ አላውቅም፡፡ የተቃዋሚ ፓርቲ አባል መሆን አገር እንደመክዳት እየተቆጠረ ሰዎች አቅም እንዳይኖራቸው ከማህበረሰቡ እንዲገለሉ እየተደረገ፣ በካድሬዎች በደል እየደረሰበት፣ ከስራ እንዲሰናበት፣ በረሃብ ልመና ውስጥ እንዲገባ ተደርጎ የማያምንበትና የማይደግፈውን እንዲደግፍ እየተደረገ ነው በማለት መምህር ብርሃነመስቀል ንጉሤ ዘውዴ በምሬት ለፍኖተ ነፃነት ዝግጅት ክፍል ገልጾዋል፡

ምንጭ፥   Millions of voices for freedom – UDJ

1 COMMENT

  1. First, learn how to spell your master’s name correctly. It’s Isaias Afwerki not “Isasias Afewerki” as you put it. Now he will be mad that you spelt it wrong and continue to sell more “Adgitat” (donkeys) from Ginbot 7. I blame you for that!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.