ፍትህ የሌለባት የተጨማለቀች አገር – ግርማ ካሳ

Habtamu- satenaw

በየትኛውም ሕግ ባለበት አገር ክስ በሚቀርብበት ጊዜ ፍርድ ቤቱ አጠር ያለ ጊዜ ወስዶ የአቃቢ ሕግን ክስ ይመረምራል። Preliminary hearing ይሉታል ፈረንጆች። ይህ የሚሆንበት ዋና ምክንያት አቃቢ ሕግ መሰረት የሌለዉና የማይረባ ክስ አቅርቦ ዜጎችን እንዳያንገላታና የፍርድ ቤትን ጊዜ ላለማቃጣል ነው። ክሱን መርምሮ ተከሳሹ ይከላከል ወይንም መከላከል ሳያስፈልገው በነጻ ይለቀቅ ይላል። ይህ ሂደት ቢበዛ በሶስት ወራት ባነሰ ጊዜ ዉስጥ፣ ወይንም በሁለት ወይንም ሶስት የፍርድ ቤት ቀጠሮ የሚጠናቀቅ ሂደት ነው።

ሃብታሙ አያሌውን ጨመሮ አስር ሰላማዊ ዜጎች “ሽብርተኞች ናችሁ” በሚል ክስ ሐምሌ 1 ቀን 2006 ነበር የታሰሩት። ከአንድ አመት ከአንድ ወር እና 14 ቀናት እና ከ22 ጊዜ በላይ የፍርድ ቤት መመላሰ በኋላ፣ ከአስሩ አምስቱ (ሃብታሙ አያሌው፣ አብራሃም ሰለሞን፣ የሺዋስ አሰፋ፣ ዳንኤል ሺበሺ እና አብርሃ ደስታ) ነሐሴ 14 ቀን መከላከል አያስፈልጋቸው ብሎ ፍርድ ቤቱ ይወስናል።

አቃቢ ሕግ ይግባኝ ይላል።ዉጭ ሆነ ሆነው መከላከል ሲገባቸው ሃብታሙ እና አብርሃም ለስድስት ወራት ፣ እንዳይፈቱ ተደርጎ የካቲት 9 ቀን 2007 ዓ.ም ተፈቱ። የሺዋስ እና ዳንኤል ሁለት ከወራትታ በኋላ፣ አብርሃ ደስታ ደግሞ ከአራት ወራት በኋላ ተፈቱ። ወደ ዉጭ እንዳይወጡ እገዳ ተደርጎባቸው ፣ የአቃቢ ሕግ ይግባኝ ሂደት በከፍተኛው ፍርድ ቤት ቀጠለ።

አቃቢ ሕግ እነ ሃብታሙን ሽብርተኛ ናቸው ብሎ ሲከስ ማስረጃዎች ዉሃ እንደማይቋጥሩ በመግለጽ ነበር የታችኛው ፍርድ ቤት መከላከል ሳያስፈልጋቸው እንዲለቀቁ የወሰነው። የከፍተኛ ፍርድ ቤት፣ አቃቢ ሕግ በታችኛው ፍርድ ቤት ያልቀረበ ሌላ ማስረጃ ካለ እንዲቀርብ ጠይቆ፣ ማስረጃ ካልቀረበ ግን፣ የታችኛው ፍርድ ቤት ዉሳኔ መርምሮ ዉሳኔ በአጭር ጊዜ ዉስጥ ዉሳኔ ማሳለፍ ነበረበት።

ግን አቃቢ ሕግ ይግባኝ ከጠየቀ ጀምሮ የከፍተኛው ፍርድ ቢያንስ 25 ጊዜ እነ ሃብታሙን እያመላለሰ ነው። መስከረም 21፣ ጥቅምት 3፣ ጥቅምት 17፣ ጥቅምት 22፣ ጥቅምት 30፣ ሕዳር 6፣ ሕዳር 29 ፣ ታህሳስ 8፣ ታህሳስ 15፣ ታህሳስ 19፣ ታህሳስ 22፣ ታህሳስ 29፣ ጥር 10፣ ጥር 24፣ የካቲት 1፣ የካቲት 3፣ የካቲት 7፣ የካቲት 9፣ የካቲት 18፣ የካቲት 22፣ መጋቢት 30፣ ግንቦት 30፣ ሰኔ 28፣ ሐምሌ 11፣ ሐምሌ 19 ….

በዚህ ሂደት ሃብታሙ አያሌው በሥር ቤት በደረሰበት ቶርቸር ምክንያት በጸና በመታመሙ ዉጭ አገር ሄዶ እንዲታከምና ፍርድ ቤቱ ሃብታሙ ወደ ዉጭ እንዳይወጣ ያደረገበትን እገዳ እንዲያስነሳ ተማጽኖ ቢቀርብለትም፣ ፍርድ ቤቱ መጀመሪያ የሃኪም ማስረጃ አምጡ አለ። ዉጭ መዉጣት እንዳለበት የሃኪም ማስረጃ ሲመጣ ደግሞ፣ አንድ ሐኪም ብቻ ሳይሆን የሕክምና ቦርዱ ነው መወሰን ያለበት አለ። የሕክምና ቦርዱ የፈረመበት ደብዳቤ ሲደርሰው ዳኛው የሉም ተባለ። ለአራተኛ ጊዜ ደግሞ አቃቢ ሕግ ቀርቦ ሃብታሙ ወደ ዉጭ ሄዶ ቢታከም ቅሬታ ካለው በቃል ያሰማ ተባለ። በቀጠሮ ቀን ደግሞ አቃቢ ሕግ ቀርቦ ሳለ፣ በቃል አቃቢ ሕግ አስተያየቱን ማረብ የለበትም በጽሑፍ ይቅረብልኝ በሚል ሌላ ቀጠሮ ተሰጠ። የሃብታሙ የሕክምና ጉዳይ በጣም አጣዳፊና ለሕይወቱ አስጊ እንደሆነ እየታወቀም፣ ፍርድ ቤቱ ቢያንስ ከስድስት ጊዜ በላይ የሃብታሙን ቤተሰቦችን አመላልሷል። ፍርድ ቤቱ እስከ አሁን ድረስ ዉሳኔ ያልወሰነ ሲሆን ሌላ ቀጠሮ ለፊታችን ዓርብ ሐምሌ 22 ቀን ሰጥቷል።

በይግባኙ ዙሪያ በሃባታሙ እና ሌሎች ላይ ዉሳኔ ለማሳለፍ ደግሞ ለሚቀጥለው አመት ለጥቅምት 11 ቀን 2009 ዓ.ም ነው ቀጠሮ የተሰጠው።

የነሃብታሙን ጉዳይ እንደ ምሳሌ አቀረብኩት እንጅ በሌሎች እስረኞችም ላይ ተመሳሳይ ሁኔታ ነው ያለው። በዛሬይቷ የሕወሃት ኢትዮጵያ ሕግ የለም። ፍትህ የለም። ያለው የጫካ አገዛዝ ነው።

እንግዲህ ሰው ነህ፣ በሕግ መተዳደር አለብን የምንል ካለን፣ እነዚህ የጫካ አስተሳሰብ ያላቸውን ፍርድ ቤቶችን የጥጋባቸዉን የአንባገነንነታቸው መፈንጫ ያደረጉትን ፣ በወገኖቻችን ሕይወት ላይ የሚቀልዱት ማስወግድ የግድ ነው። በዚህ መልኩ አገራችን እና ሕዝባችንን እንዲያምሱት መፍቀድ የለብንም።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.