ለኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ ጥብቅና! (አንዱዓለም ተፈራ) – የእስከመቼ አዘጋጅ

ረቡዕ ሐምሌ ፳ ፯ ቀን ፳ ፻ ፰ ዓመተ ምህረት ( 08/03/2016 )

ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ
ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ

ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱን በግሌ አላውቀውም፤ ነገር ግን እስከሚበቃኝ ድረስ አውቀዋለሁ። ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ እኔን አያውቀኝም፤ ነገር ግን እኔና በሚሊዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያን ጠበቆቹ እንዳለን ያውቃል። ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ ጎንደር ውስጥ አንገረብ እስር ቤት ባሁኗ ሰዓት – ምሽት፣ ረቡዕ ሐምሌ ፳ ፯ ቀን ፳ ፻ ፰ ዓመተ ምህረት – ለጊዜው አለ። እዚያ እንዲቆይ ያደረገው ወገኑ ነው። ሁላችንም እንደምናውቀው፤ በእስር ቤት ያለ ግለሰብ፤ በትክክል ይሁን በድፍረት በመታሰሩ ብቻ፤ ጠበቃ ያስፈልገዋል። እናም ጠበቃው ነኝ።

የጠበቃ ሀ፣ ሁ ው፤ ሠርተሃል ከተባለበት ወንጀል በፊት፤ ፍርድ ቤቱን መመዘን ነው። እናም ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ የሚቀርብበትን ፍርድ ቤት እንመርምር። እንደማንኛውም ፍርድ ቤት ቆጥረን ይሄን ፍርድ ቤት ብንመለከተው፤ ሕግ አለ፣ ፖሊስ አለ፣ ዳኛ አለ፣ ከሁሉም በላይ ደግሞ፤ ፍርድ ቤቱን ያቋቋመው መንግሥት አለ። ፍርድ ቤቱን ስንመረምር፤ ያቋቋመውን መንግሥትም ማጤን አለብን። ከላይ ያነጠብኳቸውን እያንዳንዳቸውን ነጣጥሎ መመልከቱ ችግር ይፈጥራልና፤ እስኪ ጠቅለል አድርጌ በአንድነት ላቅርበው። በርግጥ አንድነት ባሁኑ ዘመን አስቸጋሪ ከመሆኑ በላይ፤ ራሱ አንድነት የሚለው ቃል ወንጀል ሆኗል። ነገር ግን፤ የማያመልጡትን መረብ፤ በተስፋ ቃኝተው፤ መውጪያ በመፈለግ መጣር ያለ ነውና፤ በዚያው ላምራ።

ፍርድ ቤቱን ያቋቋመው መንግሥት፤ የኅብረተሰብን ብሶት አንገብኩ ብሎ፤ ትጥቅ አንስቶ፤ በጉልበቱ ሥልጣን ላይ የወጣ አካል ነው። እናም ከተፈጥሮው ምንነት የተነሳ፤ ማንንም የኅብረተሰብ ብሶት አንስቶ የሚታገልን ግልሰብ ሆነ ቡድን፤ ፍርድ ቤት ሊያቀርብ፤ ሕጋዊ ፈቃድም ሆነ የሞራል ብቃት የለውም። የዚህ አካል መሪዎች፤ የሥልጣን ንጥቂያ ግብግባቸው ባይሳካላቸው ኖሮ፤ ራሳቸው ፀረ-ሕዝብ፣ ፀረ-ሀገር፣ ፀረ-መንግሥት ተብለው በዚሁ ፍርድ ቤት ይቀርቡ ነበርና!

በሌላ በኩል ደግሞ፤ አሁን በሀገራችን ሕግ የለም። አሁን በሀገራችን ደንብ የለም። አሁን በሀገራችን የአስተዳደር መመሪያ የለም። ያለው የጉልበት ግዛት ነው። ያለው፤ ባለጉልበቱ የሚፈልገው፣ በፈለገው መንገድ፣ በፈለገው ጊዜና በፈለገው ቦታ፤ ባሻው መንገድ መፈጸሙ ብቻ ነው። ቋሚ የሆነ ሕግ የለም። እንዲያውም እንደ ዕውነቱ ከሆነ፤ ሕግ ቦታ የለውም። ቦታ ያለው፤ ገዥው የሚፈልገው ጉዳይ ብቻ ነው። ከዚህ ተነስተን፤ ዳኛው፣ ፖሊሱ፣ ሕጉ፣ ጠበቃዎቹ፣ ሁሉ የገዥውን ፍላጎት አስፈጻሚ አካል ለመሆናቸው ጥርጣሬ ሊኖረን አይገባም። ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱን በመከላከል ሊቀርብ የሚፈልግ ጠበቃ ሁሉ፤ ከኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ የበለጠ ወንጀለኛ ሆኖ እስር ቤት ይገባል። ለዚህ ነው፤ አንድ ብቻዬን ሳልሆን፤ በሚሊዮን የምንቆጠር ኢትዮጵያዊያን ለሱ ጥብቅና የቆምነው፤ አንዳችን ስንታሰር ሌላችን በየተራ ለመታሰር ተዘጋጅተን።

ቀረብ ብለን ስንመለከት፤ ፍርድ ቤቱ በተግባር የገዥው ክፍል መሣሪያ ከመሆኑ አልፎ፤ ከላይ እስከታች የተሰገሰጉት፤ የዚሁ ገዥ ፓርቲ አባላት ናቸው። የገዥው ፓርቲ አባላት ሙሉ በሙሉ ትግሬዎችና ትግሬዎች ብቻ ናቸው። በወሳኝነት ያሉት የዚሁ ፍርድ ቤት አባላት ደግሞ፤ ሁሉም በአባልነታቸው ትግሬዎች ናቸው። እና አንድ አማራ ወልቃይቴን፤ ለዚያውም በጥቅማቸው በወልቃይት ላይ ለመጣ ወኪል፤ በደሉን ሆነ ወንጀሉን ያዳምጣሉ ማለት፤ ከሰማይ መና ይወርዳል ብሎ ነጠላ መዘርጋት ይሆናል። ወልቃይት እኮ የታሪክ ወይንም የሕግ ጉዳይ ሳይሆን፤ የትግሬዎች ክልል የጥቅም ጉዳይ ነው! እናም የወልቃይትን ጉዳይ የትግሬዎች መንግሥትና ክልል መዋቅርና ዳኞች ይመልከቱት ማለት፤ ወይንም በዚያ ቀርቦ ትክክለኛ ፍርድ ለማግኘት መሞከር፤ ትርጉም የማይሠጥ ሂደት ነው። በጎንደሩ ሰላማዊ ሰልፍ አንድ መፈክር ከሁሉ ደምቆ ታይቶኛል፤ “ትግሬ እንጂ ትግራይ ተከዜን ተሻግሮ አያውቅም!” የሚለው።

በመጀመሪያ ነገር ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ የመጀመሪያው ወይንም የመጨረሻው እስረኛ አይደለም። ፕሮፌሰር አስራት ወልደየስ ታስረው፤ በዚያው ዕድሜያቸውን ጨርሰዋል። እስክንድር ነጋ፣ አንዱዓለም አራጌ፣ የእስልምና ተከታይ አቤቱታ አቅራቢዎች፣ በብዙ ሺ የሚቆጠሩ የኦሮሞ ተወላጆች፤ አሁንም በስር ቤቶች እየማቀቁ ይገኛሉ። ኢትዮጵያዊ የሆኑ ተቋማትና መሪዎቻቸው በሙሉ ተባረዋል፣ ተደምስሰዋል፣ ተገድለዋል፤ – የኢትዮጵያ መምህራን ማኅበር፣ የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች ማኅበር፣ የኢትዮጵያ ሠራተኞች ማኅበር፣ ወ. ዘ. ተ. ።

ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ ለምንድን ነው ለእስር የተዳረገው? ተመልከቱ፤ በሌሊት ሊያፍኑት የመጡትን የትግራይ መሪ የአባይ ወልዱ ታጣቂዎች፤ “በሕግ የምትፈልጉኝ ከሆነ፤ ሲነጋ፤ መጥታችሁ ልትወስዱኝ ትችላላችሁ። እኔ በሕግ የሰፈረልኝን መብት ጠንቅቄ የማውቅ ግለሰብ ነኝ።” ቢላቸው፤ በግድ ገብተው እጁን ሊይዙት ሞከሩ፡ ራሱን እንደሚከላከል ሲገልጽላቸው፤ ተኩሰው ዘው ብለው ገብተው ሊያፈኑት ጣሩ።  ራሱን ለመከላከል እሱም ሞከረ። በዚህ የተኩስ ልውውጥ አመለጠ። ሕዝቡ ከጎኑ ቆመ። ለሕዝቡና ለሕዝቡ ድምጽ ደንታ የማይሠጠው የትግራይ ክልል ገዥና የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር ዋና መሪ ብሎም የኢትዮጵያ መሪ፤ ጉልበት እንጂ ራሱ ያወጣውን ሕግም ስለማያከብር፤ ሕዝቡን ጥሶ ሰዎችን ገደለ። ቀደም ብሎ አፍኖ የያዛቸውን የወልቃይት ሕዝብ አቤቱታ ወኪሊችን ሰወረ። አሁንም የውሸት ውርጅብኝ በማከታተል፤ ሕዝቡን ወንጀለኛ ራሱ ግን ሕግን አክባሪ አድርጎ አስቀመጠ። መቼም ማን ሕግን አክባሪ፤ ማን ሕግን ጣሽ እንደሆነ የኢትዮጵያ ሕዝብ ያውቀዋል።

ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ ወልቃይትን ለዘለዓለም ታድጓታል። ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ ጎንደርን በሕይወቱ ጠመንጃውን አንስቶ ታድጓታል። ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ አማራውን በማንነቱ እንዲኮራ ታድጎታል። ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ ኢትዮጵያን ከትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር ነፃ እንድትሆን ክንፉን ዘርግቶ ታድጓታል። ነገ ዛሬ የተጫረው እሳት ምን ሊያስከትል እንደሚችልና ምን መሆን እንዳለበት በጃችን ነው። አሁን በዚች ሰዓት ግዴታችን ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱን መታደግ ነው። ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ በዚህ ሕገ-ወጥ በሆነ መንግሥት ፍርድ ቤት ትክክለኛ ፍርድ አያገኝም። ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ ነፃ የሚሆነው በቆመለት ሕዝብ ብቻ ነው። ምንም ያጠፋው ነገር እንደሌለ ሁላችን እናውቃለን። ያደረገው ቢኖር፤ አማራ ነኝ እንጂ ትግሬ አይደለሁም። በጎንደሬነቴ የመጣ ሕይወቴን እሠጣለሁ። ነፃነቴን እፈልጋለሁ፤ ማለቱ ብቻ ነው። ነፃነቱን ለሚሻ አብረን መቆም አለብን። በአንድነት እንሰለፍ።

ከታላቅ አክብሮታ ጋር

አክባሪያችሁ አንዱዓለም ተፈራ

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.