ጎንደር የጦር ቀጠና እንደሆነች ነው፤ ዐማሮች ዛሬም ለተጋድሎ ወጥተዋል (ሙሉቀን ተስፋው)

r1
• ደብረታቦር ሰላማዊ ሊባል በሚችል መልኩ ተጋድሎው እየተከናወነ ነው
• በጋይንት ሕዝብና ፖሊስ ተፋጧል
ጎንደር፡ በጎንደር ከተማ የተለያዩ አካባቢዎች ከፍተኛ የተኩስ ልውውጥ አለ፡፡ 18 መስጊድ፣ አራዳና ፒያሳ ከፍተኛ የተኩስ ድምጽ የሚሰማባቸው አካባቢዎች ናቸው፡፡ የጎንደር ከተማ ወጣቶች ዛሬም ገንፍለው ለተጋድሎ ሰልፍ ወጥተዋል፡፡ የወያኔ መከላከያ ሠራዊት በንጹሐን ዜጎች ላይ ጥይት እየተኮሰ ነው፡፡ የዐማራ ወጣቶች የጥይትና የአስለቃሽ ጪሱ ብዛት ሳይበግራቸው ተጋድሏቸውን እያሰሙ ነው፡፡ በጎንደር ከተማ እጅግ ብዛት ያለው የመከላከያና የፌደራል ፖሊስ እንደፈሰሰ ነው ከቦታው ያገኘነው መረጃ የሚያመለክተው፡፡

ደብረታቦር፡ በደብረ ታቦር ከተማ በታሪኳ ታይቶ የማይታወቅ የዐማራ ተጋድሎ ሰልፍ እየተካሔደ ነው፡፡ ምን ያክል ሕዝብ ተጋድሎውን እንደተቀላቀለ ለአቀረብንላቸው ጥያቄ ‹‹እስካሁን በደብረ ታቦር እንዲህ ያለ የተጋድሎ ሰልፍ አይቼ አላውቅም፤ የከተማውም የፋርጣም ገበሬ የቀረ አይመስለኝም›› ሲሉ አንድ ተሳታፊ መልስ ሰጥተዋል፡፡ የወያኔ የፌደራል ፖሊስ አስለቃሽ ጪስ ወደ ወጣቶች ሲተኩስ ወደያውኑ ተበትነው እልፍ ብለው ተጋድሏቸውን እንደሚጀምሩ ነው የተገለጸው፡፡ በጠዋት 12 ሰአት በትንሽ ወጣቶች የተጀመረው የተቃውሞ ሰልፍ አሁን ላይ ከሕጻን እስካ አዋቂ፣ ሴት፣ ወንድ፣ ደካማ አዛውንት ሳይል ሰልፉን ሁሉም ተቀላቅሏል፡፡ የጋሳይ እና የክምር ድንጋይ ከተማ ነዋሪዎች የደብረ ታቦሩን ተጋድሎ ለመቀላቀል ቢሞክሩም በወያኔ ታጣቂዎች ታግደዋል፡፡ ሆኖም ባሉበት ሆነው ተጋድሏቸውን እያሰሙ ነው፡፡ ከሞክሼ የመጡት የታጠቁ ገበሬዎች የወያኔን ወታደር ጥሰው ደብረ ታቦር መግባታቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡ በደብረ ታቦር እስካሁን በሰውና በንብረት ላይ የደረሰ ጉዳት የለም፡፡

ነፋስ መውጫ፡ የጋይንት ሕዝብ ዛሬ በማለዳው ነው የተጋድሎ ሰልፉን የተቀላቀለው፡፡ የጋይንት ዐማሮች ትናንት ሰልፍ ያስተባብራሉ ተብለው የታሰቡትን በወያኔ ቅጥረኞች የታሰሩ ወጣቶችን ማስፈታታቸው ታውቋል፡፡ የአየር ንብረቱ ዝናባማ ቢሆንም የጋይንትን የተቆጣ ዐማራ ሊያስቆም የሚችል አልነበረም፡፡ የጋይንት ዐማሮች ድምጽ ጨጭሆን አልፎ ወደ መቄትና ዋድላ ደላንታ መድረሱን ነው የምንሰማው፡፡ በነፋስ መውጫ የቅጥረኛ ፖሊሶች እርምጃ ሕዝቡን የበለጠ አስቆጥቶ ወደ ማይመለስ ግጭት እንዳይገባ ስጋት አለ፡፡
ይህ ሁሉ የመጨረሻው መጀመሪያ ነው!!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.