ልቤ በጣም አዘነ – መልእከት አለኝ ለትግራይ ልሂቃን ‪- ግርማ ካሳ‬

Ethiopia

“የሥርዓቱ አገልጋይ የሆኑ የትግራይ ተወላጆችን መንግሥታቸው በአየር መንገድ በኩል ሲያጓጉዝ መዋሉን ለማወቅ ተችሏል፡፡ ዛሬ ከጎንደር አጼ ቴዎድሮስ አየር ማረፊያ ወደ መቀሌና አዲስ አበባ በርካታ የትግራይ ተወላጆች መውጣታቸውን ለማረጋገጥ ችለናል” ሲል ጋዜጠኛ ሙሉቀን የጦመረዉን አነበብኩ። ስናስጠነቅቅ፣ ስንመክር፣ ፍቅርን፣ እርቅን፣ ሰላምን እያስተጋባን ስንጮህ የነበረው ይህ አይነቱ ክስተት እንዳይፈጠር በመስጋት ነበር።
እዚህ ደረጃ መዳረሳችንን ሳሳሰብ ልቤ በጣም አዘነ። እኛ ኢትዮጵያዉያን በሰላም በፍቅር በዘር ሳንከፋፈል ነበር የኖርነው። ኦሮሞው ከአማራዉ ከሶማሌው ከጉራጌው ..ጋር ተዋልዷል። ተዛምዷል። ሆኖም ግን ብዙዎች “አማራ ከአገራችን ይውጣ” በሚል ከኖሩበት ቦታ ተፈናቀለው የዘር ማጽዳት ወንጀል ተፈጸመባቸው። ህወሃት በረጨው መርዝ በኦሮሞዎች እና በሌሎች መካከል አለመተማመን እና በጎሪጥ መተያየት ተጀመረ። አንድ የነበርን አሁን “እነርሱ እና እኛ” መባባል ጀመርን። ሕወሃት እና ኦነግ ያመጡት ቁሻሻ የዘር ፖለቲካ !!!

በሰሜን ጎንደር እና በሰሜን ወሎ አማራው (ወሎዬው እና ጎንደሬው) ከትግሬው ጋር ተዋልዶ ተዛምዶ ነው የኖረው። በወልቃይት ጠገዴ የሚኖረው ህዝብ ትግሪኛ ያውቃል፣ አማርኛ ያውቃል። ሲያሻው ሽሬ ሄዱ ይነግዳል፣ ሲያሻው ጎንደር ይሄዳል። በጎንደር ምናልባት ከትግራይ እና ከአዲስ አበባ ቀጥሎ እጅግ በጣም ብዙ የትግራይ ተወላጆች የሚኖሩበት አካባቢ ነው። ለዘመናት ተከባብሮና ተፋቅሮ በጋራ የዉጭ ወራሪዎችን የመከቱ ናቸው። ትግሬውና ጀግናው አጼ ዩሐንስ ጎንደር ተቃጠለች ብለው ጎንደርን ለመመከት ሲሉ ነው መተማ ላይ የወደቁት።

አሁን ግን ትግሬ አማራ እየተባባለን ከአገር ልጅነት ይልቅ፣ ከስብእና ይልቅ ጎጣችን ላይ እያተኮርን ትናንሾች እየሆንን ነው። የሕወሃት ዘረኛ ፖለቲካ ሰለባ ሆነን። በወልቃይት በግድ ያልሆኑትን ሁኑ እየተባሉ ቁም ፍዳቸውን እያዩ ነው። ኢትዮጵያዊ መሆን አይበቃም እንዴ ? ሰው መሆን አይበቃም እንዴ ? ወልቃይቴ መሆን አይበቃም እንዴ ? ትግሬ መሆን ለምን አስፈለገ ? ለምንስ በግድ ትግሬ ናችሁ ተብለው ዜጎች ትግሪኛ ተናጋሪ ስለሆኑ ያልሆኑትን እንዲሆኑ ይገደዳሉ?

በሌላ በኩል ደግሞ ሕወሃት ከትግራይ ሕዝብ የወጣ በመሆኑ አብዛኞቹ ህወሃት የሚደግፉት ደግሞ በብዛት የትግራይ ተወላጆች በመሆናቸው፣ ደም መፋሰስ በበዛ ቁጥር ነገሮች ከቁጥጥር ዉጭ እየሆኑ የትግራይ ወገኖቻችን ሕይወት አስጊ ሁኔታ ላይ የወደቀበት ሁኔታ ነው ያለው። በጎንደር አሁን በትግራይ ተወላጆች ያለው የተፈጠረው ፍርሃት በታሪክ ተፈጥሮ የሚያውቅ አይመስለኝም። የሕወሃት የዘር ፖለቲካ ያመጣው መዘዝ ነው።
አሁን ባለው ሁኔታ በዘር ላይ ወደ ተመሰረተ ግጭትና እልቂት እያመራን መሰለኝ። ለዚህ ተጠያቂው 200% ህወሃት ነው። የሕወሃት የኋላ ቀር አጥፊና ከፋፋይ የዘር ፖለቲካ ነው።

ሕወሃት ነገሮች እንዲወጠሩ በማድረግ እዚህ ደረጃ አድርሶናል። ነገ ተያይዘን ገደል ዉስጥ እንድነገባ ከማድረጉ በፊት ሕወሃትን ማስቆም አለብን። በትግራይ ያላችሁ ወገኖቼ ከመቼዉም ጊዜ በላይ በሕወሃት ላይ መነሳት አለባችሁ። ህወሃት በተቀረው የኢትዮጵያ ክፍል እንደትጠሉ እያደረገ ነው። እናንተ ያልሆናችሁትን ሰው እንደሆናችሁ አድርጎ እያሰበ ነው። የጎንደር ሕዝብ ሆነ ሌላው በናንተ ላይ ጥላቻ ኖሮት አያውቅም። አይኖረዉምም። ስለሌላውስ አይደለም እንዴ ያለ ምንም ችግር ይኸው ለዘመናት ተፋቅራችሁ ተዋልዳችሁ ከሌላው ጋር በሰላም የኖራችሁት። አሁን ግን በሕወሃት ምክንያት ነገሮች በጣም እየተበላሹ ነው። እነዚህ ሰዎች በቃችሁ ሊባሉ ይገባል። የትግራይ ልሂቃን ጠንካር መልእክት ማስተላለፍ አለባችሁ።አሁን አስቸኳይ ብሄራዊ እርቅ ነው የሚያስፈልገን። አሁንስ በቃ ማለት አለባችሁ !!!!!!!!!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.