ውርደት! – መለስ ፣ ስብሃት፣ የኢህአዴግ ኤምባሲ ከዚያስ?

በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ

አገርና መሪ ላላቸው ኤምባሲ አገር ነው

eagle-flag-620x310

ሰሞኑን ኢህአዴግ በፈለፈላቸው ድርጅቶች ታጅቦ የ”ባንዲራ ቀን” በሚል የመለስን ፈረጀ ብዙ ዝክር ሊደግስ ከወዲያ ወዲህ እያለ ነው። አቶ መለስ “ጨርቅ” ብለው ሲያነሱና ሲጥሉት የነበረውን ያገር መለያ ለፈጠራና ከጀርባው ተንኮል ያዘለ ዓላማቸው ሲሉ ቀኑ እንዲዘከር አድርገዋል፤ የምዕራባውያን ጉዳይ አስፈጻሚ እንደመሆናቸውም የታዘዙትን በሠንደቅ ዓላማው ላይ ጨምረዋል። በዚሁ የ”ባንዲራ ክብር” ሳይሆን በሌላ አህጉራዊ ክስተት ራሳቸው ያሰፉትን ጨርቅ ገልብጠው ባደባባይ ሰቅለውት ነበር። በወቅቱ ራሳቸው ያሰሩትን ባንዲራ አናትና ግርጌ መለየት ባለመቻላቸው ተወግዘውበታል፤ የትግራይን ቢሆን እንዲህ ያደርጉት ነበር ተብሎም ተጠይቋል።

ባድመ ስትወረር “ደርግ ኢሰፓ” ተብለው ጎዳና ላይ የተጣሉት የቀድሞው ሰራዊት አባላት ለዳግም ዘመቻ “እናት አገር ጥሪ” ሲተም በገጸ በረከትነት የተሰጠው ያደራ ቃል ኪዳን ይኸው “አታስፈልግም ጨርቅ ነህ” የተባለው መለያ ነበር። ሲፈልጉ የሚጥሉት፣ ሲጨንቃቸው የሚያነሱት መከረኛ ባንዲራ ዳግም አጀንዳ ሆኖ ሰሞኑንን ቀርቦልናል።

wedi1-174x300በአሜሪካ በሚገኘውና ኢህአዴግ “ኤምባሲ” በሚለው ቅጥር ግቢ ውስጥ ወዲ ወይኒ የሚባሉ ታጋይ የፈጸሙት ድርጊት ነው የባንዲራን ጉዳይ ዳግም አጀንዳ ያደረገው። የወዲ ወይኒ ገድለ ዜና አስገራሚ የሆነባቸው፣ ያሳዘናቸው፣ ያናደዳቸው፣ የተደፈርን ስሜት የፈጠረባቸው፣ ክስተቱን በመቃወም ኢህአዴግን በመወከል መግለጫ ያወጡ፣ እስከመቼ ኢህአዴግ “ሆደ ሰፊ ይሆናል” ብለው የጠየቁ፣ አሜሪካንን የወነጀሉ፣ ውጭ ጉዳይ ሚ/ር ጆን ኬሪ ለፍርድ እንዲቀርቡ የጠየቁ፣ … በተለይም የሳይበር ሚዲያውን አጣበውት ከርመዋል። በሌላ በኩል ዜናውን እንደዜና ብቻ ወስደው ሚዲያ በዘነጋቸው ኢትዮጵያዊያን ላይ ለሚደርሰው ግፍ ያዘኑ ስፍር ቁጥር የላቸውም።

ዋሽንግተን በሚገኘው የኢህአዴግ ጽ/ቤት ውስጥ የመዋቅሩ “መሪ” ተብለው የተቀመጡትን ግርማ ብሩን ለማነጋገር እንደመጡ የሚናገሩ ኢትዮጵያዊያን ላይ ወዲ ወይኒ ጥይት ሲተኩሱ ተሰምቷል። ታይቷል። ተረጋግጧል! በኢትዮጵያ ስም የተሰቀለው የህወሃት/ኢህአዴግ ዓርማ ወርዷል! በዚሁ በፊልም ተደግፎ በቀረበው ዜናና የማህበራዊ ገጽ ዓምዶች ላይ ዋሽንግቶን ከተማ ከዋይት ሃውስ 4 ማይል ርቀት ላይ በሚገኘው የኢህአዴግ ግቢ ውስጥ ተሰቅሎ የነበረው “ጨርቅ” ወርዶ ተጥሏል። “የጨርቁ ፍቅር ያቃጠለው” የጽህፈት ቤቱ ሰራተኛ የተጣለውን “ጨርቅ” ሰብስቦ ወደ ቢሮ ሲያስገባም ከካሜራ እይታ አላመለጠም። እንግዲህ ይህንን እውነት ነው ለመካድና “ከዓይናችሁ ጆሯችሁን እምኑ” እየተባልን ያለነው።

በሌላ በኩል የህዝብ ቀልብ ለመሳብ “ባንዲራ ያዋረዱ” በሚል “ኢህአዴግ በፈቃዱ ያሰራውን ጨርቅ” አውርደው የጣሉትን ለመክሰስና ከሃዲ አድርጎ ለመሳል ተሞክሯል፤ ሙከራውም ቀጥሏል። ሁኔታውን የሚከታተሉ እንደሚሉት “ይህ የኢትዮጵያ ባንዲራ ነው” በማለት የሚጠሩትን ጨርቅ “ይህ የእኔ ባንዲራ አይደለም” በማለት ቀዳደው የሚጥሉ ዜጎች በምን ሂሳብ ተቃውሞ ይሰነዘርባቸዋል የሚል ጥያቄ እያነሱ ነው።

ህወሃት ትግራይን ነጻ ለማውጣት ትግል ጀምሮ፣ በወቅቱ ደርግ በነበረው የአመራር ጥበብ እጥረትና ሌሎች ተጽዕኖዎች ከአገዛዝ መንበር ተነስቶ ህወሃት/ኢህአዴግ አገር ገዢ ለመሆን ሲታደል የአገሪቱን ባንዲራ “ጨርቅ” ብሎ አዋርዶታል። የቀለብ መቋጠሪያው እራፊ አድርጎ ክብሩን ገፎታል። ባደባባይ አገርና ህዝብ እየተቃወመ በጠብ መንጃ ሃይል አስወግዶታል፤ አቃጥሎታል። ራሱ ባሰፋው ሌላ “ጨርቅ” ተክቶበታል። ይህ የሸፍጥ ታሪክና ተግባር የተረሳ ተደርጎ ዛሬ ህወሃት/ኢህአዴግ ደርሶ ለሠንደቅ ዓላማ ክብር ሰጪ ሆኖ ሙግት መግጠሙ ጥያቄውን የሚያነሱ ክፍሎች ተግባሩ “ያቅለሸልሻል” ባይ ናቸው።

“አገር የነሱ መፈንጫና ሃብት ማግበስበሻ የሆነችላቸው የድጋፍ ቀረርቶ ለማሰማት ቅድሚያ ቢይዙ፣ አገር የላችሁም፣ ባንዲራ አልባ ናችሁ፣ የተባልን የነሱ የሆነውን ጨርቅ አንፈልግም ብንል ምን ይገርማል?” የሚሉት ክፍሎች፣ “በሎንደን የኤርትራ ኤምባሲን ዘልቀው ለሰዓታት የተቆጣጠሩት አምባገነን በሚባሉት የፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ “ዲፕሎማቶች” ጥይት አልተተኮሰባቸውም። ኢሳያስን አምባገነን በማለት የኤርትራን ህዝብ “ነጻ” አወጣለሁ የሚለው ህወሃት ግን በወዲ ወይኒ አማካይነት ህግ ባለበት አገር የህወሃትን ማንነት ባደባባይ አሳይቷል። “እዛው ህወሃት በሚነዳት አገር ውስጥ ቢሆን ኖሮ ስንቱን ይረሽን ነበር” ሲሉም የሚጠይቁ አሉ። እነዚህ ክፍሎች “አገር ቤት የተረሸኑትንና ታስረው የሚሰቃዩትን ቤት ይቁጠራቸው” ሲሉ ተደፈርን በሚል ስሜታቸውን የሚያንጸባርቁትን ወገኖች “ወዮልኝ ቀን ያጋደለ እለት” በሚል ምጸት ጥርሳቸውን ይነክሱባቸዋል።

ወዲ ወይኒ በጠራራ ጸሃይ፣ በካሜራ ታጅበው፣ እንደ ፊልም አክተር ሽጉጥ ወጥረው ሲያስፈራሩ፣ “ተኩስ፣ ግደለኝ፣ ተኩሰው” እያሉ ሲጠጉዋቸው የነበሩት ወገኖች ግርማ ብሩን እንደሚፈልጉ ገልጸዋል። “የብሄር ብሄረሰብ መብት በገፍ ተሸክሜ ልገዛ መጣሁ” የሚለው ኢህአዴግ የወከላቸው አቶ ግርማ ሰዎቹን ወጥተው ለምን አያነጋግሩም? ችግራችሁ ምንድነው? ምን እንርዳችሁ? የማይሉበት ምክንያትስ ምንድነው? ይህ የእኛም አቋም meles-sibhat-embassy1-300x148ነው። ላደላቸው ኤምባሲ አገራቸው ነው። አምባሳደር መሪና ተከራካሪ ጠበቃቸው ነው። ለታደሉ ኤምባሲ በሄዱበት የባዕድ ምድር የሚሰበሰቡበት ቤታቸው ነው፤ ትንሽዋ አገራቸው ነው። መሪውም የቤቱ አስተዳዳሪ ነው። አገር በቤት፣ ህዝቦቿም በቤተሰብ ከተሰየሙ፣ የቤተሰቡ መሪና ረዳቶቹ ልጅና እንግዴ ልጅ ለይተው ላንዱ ወርቅ፣ ለሌላው ጥይት አያቀርቡም። በዚህ እሳቤ “የኢህአዴግ የመዋቅር ቅርንጫፍ ጽ/ቤት” ብለን በጠራነው ቅጥር ውስጥ ወዲ ወይኒ የፈጸሙት ተግባር ከህወሃት ማንነት የተቀዳ ስለመሆኑ አንጠራጠርም።

በሰለጠነ አለም ውስጥ እንዳሻቸው እየበሉና እየጠጡ የሚኖሩ ሰዎች “ግደለኝ፣ ተኩስብኝ፣ ግደለኝ” በማለት ሞትን ለመጋፈጥ ሲወስኑ ምልክቱ “ብሶት ከልክ ማለፉን የሚያሳይ ነው” የሚሉ ክፍሎች “ይህ ድርጊት ነገ መልኩን ቀይሮ አገር ቤትም ሆነ ሌላ ቦታ ዋሽንግቶንን ጨምሮ ላለመከናወኑ ማረጋገጫ የለም” ይላሉ። ተበልቶና ተጠጥቶ በሚታደርበት አገር ውስጥ ዜጎች ሞትን ከናቁት፣ የኑሮ ጠኔ የሚለበልባቸው የበይ ተመልካቾች ያመረሩ ቀን አቶ ኦባንግ ሜቶ እንዳሉት “የከፋ ቀውስ” ይከተላል። ህግና ስርዓት ባለበት አገር ጥይት እያንባረቁ አካኪ ዘራፍ ማለት፣ በዚያው ስሜት ተመልሶ “ተደፈርን” ብሎ መጮህ የሚያመለክተው “ከልክ ያለፈ ጥጋብ ተራራ ማከሉን ነው” ሲሉ በድርጊቱ የተበሳጩ ይናገራሉ።

የአገር ቤቱ አልበቃ ብሎ ህግና ስርዓት ባለበት አገር “በጫካ ማንነት አምባገነን ለመሆን መሞከር በጥጋብ መወጠር ያመጣው የትዕቢት ድምር ነው” በማለት አምርረው የሚናገሩት ክፍሎች “በጥጋብ የተወጠሩና ጥጋባቸው ያሳወራቸው ጥቂቶች፣ ርሃብ እንቅልፍ በነሳቸው፣ ግፍ ባንገፈገፋቸው፣ አገር ላይ የሚፈጸመው ዝርፊያ ተስፋ ባስቆረጣቸው ህዝብ መካከል እንደሚኖሩ መዘንጋታቸው” የወደፊቱን ሲያስቡ ሃዘን እንደሚገባቸው ይጠቁማሉ።

ይህንኑ ከልክ ያለፈ ጥጋብ መተንፈስ እንዳለበት ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ ዋና ዳይሬክተር ኦባንግ ሜቶ ለህወሃት አመራሮች በቅርቡ በላኩት ደብዳቤ እንዲህ ብለው ነበር፤ “ከእናንተ ጋር ሚቃወመውን ሁሉ “አሸባሪ” በማለት ማሰራችሁን አቁሙ! ኃይልን ወይም ጉልበትን በመጠቀም እስከመጨረሻው በሥልጣን አትቆዩም! በዓለም ታሪክ ያልተከሰ ስለሆነ እናንተ ልትከውኑት አትችሉም። እናንተ አለን ከምትሉት ጉልበት በብዙ እጥፍ የሚበልጥ የነበራቸውም ተንኮታኩተዋል። ስለዚህ ከትዕቢታችሁ ተንፍሱ፤ ትህትና አሳዩ፤ ከፍ ብላችሁ የተሰቀላችሁበት ከመሰላችሁ “ፎቅ” ውረዱ! ለለውጥ ያላችሁን ግልጽነት አሳዩ! ለዓመታት ሳታቋርጡ ስታወሩ የነበራችሁትን ውሸት አቁሙ፤ እውነትን መናገር ተለማመዱ። የሃሰትን መንገድ ሳይሆን ትክክለኛውን በመከተል በዜጎች መካከል መተማመን እንዲፈጠር የሚያስችል ሥራ ማከናወን ጀምሩ!”

“ውርደት ቀለቡ” የሚባለው ህወሃትና ሟቹ መሪው ተጠልተዋል። ጥላቻው ልክ አልፏል። መለስ ስድብና ርግማን ጠግበው እንደ ክዳን ቆርኪ ተስፈነጠሩ። ከህልፈታቸው በፊት ውግዘትና ርግማንን ጠግበው የነበሩት መለስ “ሲሰው” ስብሃት ነጋ ስታርባክስ ቡና ሊጠጡ ገብተው ሃፍረትን በሲኒማ ተከናነቡ፣ “የህወሃት ቁስ” ከሚባሉት አንዱ ሬድዋን ሁሴን የልብስ ሱቅ ውስጥ ልጆችና ቤተሰባቸው አጥንት ስር ዘልቆ የሚገባ የውግዘት መርዝ ተጋቱ፣ አሁን ደግሞ ዋሽንግቶን የተተከለው ቅጥር ግቢያቸው ትዕቢታቸውን አሟሟው። እንደ እነዚህ ክፍሎች ገለጻ በስምምነትም ሆነ በግዴታ ወዲ ወይኒ 24 ሰዓት ሳይሞላ እንዳሻቸው መግደልና ማሰር ወደሚችሉባት የህወሃት ኢትዮጵያ መላካቸው አድሮ የህግ ጥያቄ ያስነሳል። ለዚሁ ይመስላል ህወሃቶች ግድያ ሊፈጽም የነበረው ሰው ትግሬ በመሆኑና የተነካውም ክብር የትግሬ ህወሃቶች በመሆኑ የስምምነት መግለጫ እንዲወጣ ይፈልጋሉ። አሜሪካ ይህንኑ እንድትፈጽም ጥረት ስለመኖሩ አቶ ግርማ ብሩ ፍንጭ መስጠታቸውን ያመለክታሉ።

ለኢህአዴግ ልሳን ቃላቸውን የሰጡት አቶ ግርማ፣ ከስቴት ዲፓርትመንትና ከሌሎች አካላት ጋር በዲፕሎማሲያዊ ቋንቋ ተነጋግረናል” ሲሉ መናገራቸውን የሚጠቁሙ እንደሚሉት” ወዲ ወይኒ ወደ ህወሃት የግዛት አገር እንዲሄዱ የተደረገው ለፖሊስ የምርመራ ቃል ከሰጡ በኋላ በሁለትዮሽ ንግግር ነው። “ንግግሩ ምንም ይሁን ምን አሜሪካ ወንጀለኛውን የምትፈልግ ቢሆን “ኤምባሲ” ከሚባለው ቅጥር ግቢ ሲወጡ ፖሊስ ሊያስራቸው ይችል ነበር።

የስቴት ዲፓርትመንት ቃል አቀባይ ጉዳዩ እንደተፈጸመ “ከጦር መሳሪያ ጋር የተያያዘ ጉዳይ በጥንቃቄ ይታያል” ማለታቸው አይዘነጋም።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.