Unity-satenaw-700x437

ነሃሴ ፭ ( አምስት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም

ኢሳት ዜና :- ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የሚደርሱን መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ገዢው ፓርቲ በአማራ እና በኦሮምያ ክልሎች የተነሳውን ህዝባዊ ተቃውሞ ለማስቆም የጸጥታ ሃይሉን በብዛት በማሰማራት ውጥረቱን አባብሶታል። የፌታችን ቅዳሜ እና እሁድ ተቃውሞ ይካሄድባቸዋል በሚባሉት በርካታ የ አማራ ክልል ወረዳዎች ብዛት ያላቸው የመከላከያ ሰራዊት አባላት እና የፌደራል ፖሊሶች እየገቡ ሲሆን፣ ተቃውሞውን ሊያስተባብሩ ይችላሉ የተባሉት ደግሞ እየታፈሱ ወደ እስር ቤት እየተጋዙ ነው። በተለይ በደብረማርቆስ ውጥረቱ ከፍተኛ ደረጃ ላይ መደርሱን የከተማዋ ነዋሪዎች ለኢሳት ተናግረዋል። በክልሉ ዋና ከተማ ባህርዳርም እንዲሁ የፊታችን እሁድ የተቃውሞ ሰልፍ በድጋሜ ሊጀመር ይችላል ተብሎ እየተነገረ መሆኑን ተከትሎ ወታደሮች ጥበቃቸውን አጠናክረዋል።

በዛሬው እለት አንዳንድ ንግድ ድርጅቶችና የትራንሰፖርት መኪኖች እንቅስቃሴ ቢጀምሩም አብዛኛው ወጣት ከወታደሮች እይታ ውስጥ ላለመግባት ጊዜውን በቤቱ ማሳለፍን መርጧል። በአንድ ላይ ሰብሰብ ብለው መንገድ ላይ የተገኙ ወጣቶች እየተያዙ በመታሰር ላይ ናቸው። የክልሉ ጤና ቢሮ ሰራተኞች የታሰሩት ካልተፈቱ ስራ አንጀምርም ማለታቸውን ነዋሪዎች ገልጸዋል። የክልሉ ፕሬዚዳንት አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ክልሉን በብቃት አልመሩም በሚል ወሳኝ የሚባሉትን ጉዳዮች የፌደራል ባለስልጣናት መስጠት የጀመሩ ሲሆን፣ አቶ ገዱን በሂደት ከስራ እንቅስቃሴ ውጭ ለማድረግ እንቅስቃሴዎች መጀመራቸውን ምንጮች ገልጸዋል። አብዛኛውን የክልሉን እንቅስቃሴ በፌደራል ደረጃ በሚሰሩ የህወሃት ታማኞች ለመምራት የሚያስችል አሰራሮች መተግበር ጀምረዋል። በወልድያ ዛሬ የባጃጅ አሽከርካሪዎችንና ባለንብረቶችን ለመሰብሰብ የተደረገው ሙከራ እንዲበተን ተደርጓል።

በሰሜን ወሎ ዋና ከተማ ወልድያ ፣ በባህል አዳራሽ የተጀመረው ስብሰባ በክልሉ የትራንስፖርት ሃላፊ የተመራ ሲሆን ፣ ከ200 ያላነሱ ሹፌሮችና ባለሃብቶች ብቻ በስብሰባው ላይ ተገኝተዋል። ስብሰባው በጭቅጭቅ መሞላቱን ተከትሎ ተሰብሳቢዎች አዳራሹን ለቀው የወጡ ሲሆን ፣ እንደገና በልመና 30 የሚሆኑ ሰዎች ስብሰባውን ተካፍለዋል። በመጨረሻም የጸጥታ ሃላፊው አቶ ሙልቀን ማርዬ በእሁድ ስልፍ ላይ እንዳትወጡ በማለት መስጠንቀቂያ ሰጥተዋል። ተመሳሳይ ስብሰባዎች በከተማዋ የተለያዩ ቀበሌዎች ተካሂዷል። በላሊበላ ከተማም እንዲሁ ካድሬዎች በየፅ/ቤቱ፣በየቀበሌውና በየትምህርት ቤቱ ህዝቡን በመሰብሰብ በእሁዱ ሰላማዊ ሰለፍ ብትሳተፉ ወዮላችሁ እያሉ በማስጠንቀቅ ላይ ናቸው፡፡

በርካታ የገጠር ሚኒሻዎች እና የአካባቢ ፖሊሶች ከተማይቱን የወረሩ ሲሆን አቶ ግርማ የተባለ በልስ ስፌት የሚተዳደር ሰው ትቀሰቅሳለህ በሚል ተይዞ ታስሯል። በደብረብርሃን ከተማም ተመሳሳይ ስብሰባ ተካሂዶ ተበትኗል። በከተማዋ የጸጥታ ሃይሎች እየዞሩ ህዝቡን በማስፈራት ላይ ናቸው። በአዊ ዞን ቻግኒ ከተማ የሚገኙ ነዋሪዎች ትናንት የተቃውሞ ሰልፍ ለማዘጋጀት ሲሞክሩ በፖሊሶች የተዋከቡ ሲሆን፣ የተቃውሞውን ሰልፍ በሳምንቱ መጨረሻ ለማካሄድ እንዳቀዱ ተናግረዋል።

ባለፈው ቅዳሜ ከአዲስ አበባ የታፈሱ 1 ሺ የሚሆኑ ወጣቶች በአዋሽ አርባ መታሰራቸውን ለማውቅ ተችሎአል። የደህንነት ሃይሎች የታሰሩትን ለመጠየቅ የሚሄዱ ሰዎችን ገንዘብ ስጡንና እንፈታቸዋለን ማለት መጀመራቸውን ለጥየቃ የሄዱ ቤተሰቦች ተናግረዋል። ድርጊቱ ያስገረማቸው የእስረኞች ቤተሰቦች ፣ “ደህንነቶች የሚጠይቁት ገንዘብ ማንኛውም ደሃ ህዝብ ሊከፍለው የማይችለው ነው” ካሉ በሁዋላ ፣ ደህንነቶች ሁኔታው አስግቷቸው ገንዘብ መሰብሰብ የጀመሩ ይመስለናል ሲሉ ትዝብታቸውን አክለዋል።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.