ይድረስ ለትግራይ ተወላጆች    [አገሬ አዲስ]                

 በኢትዮጵያዊነቱ የሚያምን ዜጋ በዘር ድንኳን ውስጥ አይሰገሰግም

Tigray People
ኢትዮጵያ የልዩ ልዩ ቋንቋ ተናጋሪና ልዩልዩ ባህልና ልማድ ያለው ሕዝብ የሚኖርባት አገር ነች።ኢትዮጵያን ኢትዮጵያ ያሰኛት ሕዝቧ የእምነትና የጎሳ ልዩነት ሳይለያየው በአንድ አገር ልጅነት ደሙን አፍስሶ የመጣበትን የውጭ ወራሪ ሃይል መልሶ የአንድ ነጻ  አገር ዜጋ ለመሆን በመብቃቱ ነው።ይህ በታሪክ የተረጋገጠለት ክብሩና መታወቂያው ከጥቂት ዓመታት ወዲህ እንዲበረዝና አቅመቢስ ሆኖ ለውጭ ወራሪ ሃይሎች የተመቸ እንዲሆን በገዛ ዜጎቹ የተቀመረው የጥፋት መንገድ አሁን አንድነቱን እየቦረቦረው መጥቷል።ያ በኢትዮጵያዊነቱ የሚኮራ ቋንቋና ክልሉን መውደድ እንጂ ማፍቀር የማያውቀው ዜጋ አሁን የሚያፈቃቅረውንና የክብር ካባውን ኢትዮጵያዊነቱን ጥሎ በሰፈር ጉድጓድ ውስጥ ለመጠለል ሲራኮት ማየት ትውልዱን የሚያሳብድ መርዝ የጠጣ አስመስሎታል።አሁን ትግሬነት፣አማራነት፣ኦሮሞነት፣ጋምቤላነት፣ጉራጌነት፣አፋርነት፣ሶማሌነት….የበላይነቱን እየያዘ ኢትዮጵያዊነት እየቀጨጨ መጥቷል።

የውጭ ወራሪዎች አንድ አገር ሲወሩ በመጀመሪያ የሚያደርጉት ሕዝቡን የሚያስተሳስረውን ነገር ማጥፋት ነው፤ሰንደቅ ዓላማውን ቀዶ ጥሎ በሌላ መተካት፣የሚግባባበትን አንድ ቋንቋ ሽሮ በራሳቸው ወይም በተለያዩ ቋንቋዎች እንዲንጫጫ ማድረግ፤አገራዊ ድንበሩን አፍርሶ በክልልና በሰፈር መተካትና ሕዝቡን የእዚያና የዚህ በማለት መበታተን ነበር።ጣሊያንም ኢትዮጵያን ሲወር ያደረገው ይህንን ነበር፤አሁን በስልጣን ላይ ያለው ቡድንስ ከዚህ የተለዬ ምን አደረገ?

በቀስተደመና ህብራዊ ቀለም ውስጥ ጎልቶና ደምቆ የወጣውን አረንጓዴ፣ቢጫና ቀይ ቀለም የመጀመሪያ ነጻ አገር የኢትዮጵያ መሪዎች የነበሩት አስተዋዮች ለመምረጥ ዕድሉን በማግኘታቸው ይህንን ማራኪ ቀለም አዋህደው ምልክታቸው አደረጉት። ለዘመናት ሳባውያን፣አጼ ካሌብ፣አጼ ልብነድንግል፣አጼ ዩሃንስ እንዲሁም ሌሎቹ የኢትዮጵያ መሪዎች እየተቀባበሉ አክብረው ያቆዩትን ፣የብዙ አፍሪካውያን የነጻነት አርማ ሆኖ የታዬና የተወሰደ የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ በመጀመሪያ ጣሊያን በራሱ ባንዲራ አሁን ደግሞ የጣሊያኖችና የሌሎች ቅኝ ገዢዎች ወኪል የሆነው ወያኔ በነጻነትና በእኩልነት ስም የተለያዩ ክልሎች በሚያውለበልቡት ዝብርቅርቁ በወጣ ባንዲራ ለውጦ አንድነቱን አናጋው።አንድ ቋንቋ ተናግሮ እንዳይግባባ በእኩልነትና በነጻነት ስም አደንቁሮ አራራቀው።የባቢሎንን ግንብ ታሪክ ለሁለተኛ ጊዜ በኢትዮጵያ ምድር ደገመው።

ሁሉም ኢትዮጵያዊ የሚጋራው እየጠፋ የሚለያይበት እየጎላ በመሄዱ ለጋራ ችግሩ አብሮ ለመቆም አልቻለም።በየአቅጣጫው የጎሳ ነጋሪት እየተጎሰመ የገዛ አገሩን ለማፈራረስ ግብ ግብ የገጠመ ይመስላል።እኛ የሚለው ስሜት በእኔ ነት ተተክቷል።እኛ የሚለው በእነሱ ተቀይሯል።እጅ ለእጅ ተያይዞ የገጠመውን ችግር አብሮ ከማሶገድ ይልቅ  አንዱ በሌላው ላይ ጣቱን ከመቀሰር አልፎ ቃታ ለመሳብ ተዘጋጅቷል። በዚህ ሁሉ ግርግርና የእርስ በርስ ግጭትና እልቂት የሚጠቀመው የሕዝቡን አንድነትና የአገሪቱን መኖር የማይሻው ወገን ነው።ለዚያ ደግሞ ከውጭ በሩቁ የተቀመጠው ጠላት  ሳይሆን ጉዳይ ፈጻሚው በሕዝቡ ቋንቋ እየተናገረ ስሜቱን እየቀሰቀሰ እጁን እንዲሰጥ የሚገፋፋው  አገር በቀሉ የጠላት መሳሪያ የሆነው ሃይል ነው።ያ ሃይል ላለፉት 25 ዓመታት ስልጣኑን በጉልበት ወስዶ የሚያተራምሰው ቡድን ህወሃት የተባለውና በስሩ ያሰለፈው ኢሕአዴግ የተባለ ጭፍራው ነው።

tigray -sisህወሃት በኢትዮጵያዊነቱ ኮርቶና ለኢትዮጵያም ነጻነትና ህልውና ከፍተኛ ድርሻ ያበረከተውን የትግራይ ተወላጅ እንደባህሉ ይዞት የኖረውን የኢትዮጵያዊነት ስነልቦና አሶልቆ በጠባብ ክልል እስር ቤት ውስጥ አጭቆ ከሌላው ነጥሎና ከሌላው ቀምቶ በመስጠት፣ በርካሽ ድለላዎች እያታለለ ተከታዩ አድርጎታል።ኢትዮጵያ ብትፈራርስ የማንም መብትና ሰላም እንደማይከበር እየታወቀ ዘላቂነት በማይኖረው የሃብት ዘረፋ፣የመሬት ንጥቂያ ወንጀል ውስጥ እያስገባ ከሌላው ወገኑ ጋር  እንዲቃቃር ብሎም ደም እንዲቃባ አድርጎታል።ይህንን መሰሪ ተግባር ከጥቂቱ በስተቀር ብዙሃኑ የትግራይ ተወላጅ የተገነዘበው አይመስልም። አደገኛነቱ ቢገለጽላቸውም ሰምተው ወደ ልቦናቸው አልተመለሱም።በነሱ ስም ስልጣን ላይ የተቀመጡት ከሃዲዎች በአገር ውስጥና በውጭ አገር እየዘረፉ የብዙ ሚሊየን ዶላር ንብረት ሲያካብቱ፣በውጭ አገር ባንክ ሲያስቀምጡ፣ልጆቻቸውን ለመተካት ሲያስተምሩና ሲያዘጋጁ፣እነሱ ሲበሉ በሩቁ እያገሳ መቀመጡን የመረጠ ይመስላል። ጥፋት እያዩ፣በነሱ ስም የተቋቋመው ድርጅት ህወሓት አገር ሲያፈርስ፣ወገን ሲገድል፣ ሲያቆስል፣ሲያስር፣ሲያሳድድ፣ቤት ሲያፈርስና ህዝብ ሲያፈናቅል፣አጼ ዩሃንስና እራስ አሉላ አባነጋ እንዲሁም ሌሎቹ የትግራይ ተወላጆች ከወራሪዎች ጋር ተፋልመውና በህይወታቸው ዋጋ አስከብረው ያቆዩትን ያገሩን መሬት ለሱዳን(ለደርቡሾች)ቆርሶ ሲሰጥ ለምን አላሉም።ያም በመሆኑ የጥፋት መልእክተኞቹ የልብ ልብ ተሰምቷቸዋል፤ይበልጥ የጥፋቱ አድማስ እንዲሰፋ ሌት ተቀን እየሰሩ ነው።

በሌላም በኩል በውጭ አገር በተለይም በአሜሪካና በአውሮፓ የሚኖረውን ኢትዮጵያዊ ለመከፋፈል ከፍተኛ በጀት በመመደብና የስለላ መዋቅሩን በመዘርጋት ሲንቀሳቀስ ቆይቷል፤አሁንም እየተንቀሳቀሰ ይገኛል።ከሚጠቀምበት አንዱ በኢትዮጵያዊነት አብሮ ሲያከብር የነበረውን የእስፖርትና የባህል በዓላት በጎሳ መልክ እንዲዘጋጁ ማድረግ ነው፡፤የኦሮሞ በሚለው ስር ለዓመታት ሲካሄድ እንደቆየው ሁሉ አሁን ደግሞ የትግራይ በሚል ስያሜ ተመሳሳይ ዝግጅት ለመጀመሪያ ጊዜ በሆላንድ ለማካሄድ እየተሯሯጠ ነው።ይህ ከኦገስት 18-21  “ቬስቲቫል ተጋሩ በአውሮፓ” በሚል ሽፋን የተዘጋጀ የወያኔን ደጋፊዎች የሚያዝናናና የሚያሰባስብ ዝግጅት ልዩልዩ ፕሮግራሞችን ያቀፈ ሲሆን የአባይ ቦንድ ሽያጭም የሚጧጧፍበት የገበያ አዳራሽ እንደሚሆን የወጣው መረጃ ያረጋግጣል።በጎሳ ዙሪያ በሚዘጋጀው በኳሱም ሜዳ ሆነ በባህላዊ ዝግጅቱ ላይ የሚገኘው ሕዝብ በኢትዮጵያዊነት ከሚዘጋጀው ማንኛውም በዓል ዝግጅት ያነሰ ለመሆኑና የብዙሃኑን ቀልብ ለመሳብ እንዳልቻለ በኦሮሞ ወንድሞቻችን በተደጋጋሚ ታይቷል። የሆላንዱም የወያኔ ካምፕ የሚያዘጋጀው እንዲሁ የተመናመነ ቁጥር ያለው አዘጥዛጭ ብቻ የሚሳተፍበት እንደሚሆን ከወዲሁ ምልክት እየታዬ ነው።በየዋህነት ወያኔን ሲደግፉ የነበሩት አሁን በአገራችን ውስጥ በተፈጠረው ሁኔታ በመንግሥት ላይ ጥያቄ እያነሱ እራሳቸውን በማራቅ ላይ ናቸው።

ዓይን ያወጡ ደረቆችና የጠባብነት በሽታ የለከፋቸው ጥቂት የትግራይ ተወላጆች የሞት የሽረት ትግል በማድረግ ላይ ቢሆኑም የማታ ማታ የሰፊው የኢትዮጵያ ሕዝብ እንደሚሆን ጥርጥር የለውም።

ህወሃትን እንቃወማለን በማለት በአረና ትግራይ፣በትግራይ ብሄራዊ ትብብር(ታንድ)በትግራይ ዴሞክራቲክ ንቅናቄ ስር የተደራጁት የትግራይ ልጆችም ከነዋሪው ፈቃድና ጥያቄ ውጭ በማስገደድ በትግራይ ክልል ስም  የተፈጸመውን የመሬት ነጠቃውንና መስፋፋቱን ሲቃወሙ አይሰማም፣እንደውም ለታላቋ ትግራይ ስሜት ያደሩ ይመስላል።አንዳንዶቹም አብረው የፈጸሙትን ጥፋትና እቅዱን ለማመን አልደፈሩም። ይህም በመሆኑ በመካከላቸው ያለው ልዩነትና ጠብ  የዓላማ ሳይሆን የስልጣን እንደሆነ፣ወደፊትም ታርቀው ያንኑ የተነሱበትን ኢትዮጵያን የማፈራረስ ዓላማ ሳይቀጥሉበት አይቀሩም የሚል ጥርጣሬ እየጎላ መጥቷል።ከኢትዮጵያዊነት ይልቅ ትግሬነታቸው እንደሚያሳስባቸው ምልክቶች እየታዩ ነው።ይህ ትክክል አይደለም ካሉ በግልጽ ማብራሪያ ሊሰጡ በተፈጸሙት  ወንጀሎችም ላይ ያላቸውን አቋም ሊያሰሙ ይገባቸዋል።እነሱም በስህተት ወንጀል ፈጽመው ከሆነ ይቅርታ መጠየቅ ጨዋነት ነው።በተጨማሪም የትግራይ ተወላጅ ከሌላው ጋር ተባብሮ ይህን የጋራ ጠላት እንዲሻሻልና እንዲጠገን ሳይሆን እንዲያሶግድ ቅስቀሳ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።ዝምታ የድጋፍ ያህል እንደሚቆጠር ሊያውቁት ይገባል።

መላው የትግራይ ተወላጅ ሆይ

በስምህ የሚፈጸመውን ወንጀል አውግዝ፣ህወሓት/ኢሕአዴግ በስምህ የሚነግድ፣ካልሆነለት ለአደጋና ለችግር አጋልጦህ የሚሸሽ፣ለዓለም አቀፍ ዘራፊዎች ተጠሪ የሆነ የሌቦች ስብስብ መሆኑን ተረዳ።እንኳንስ ያገሪቱን የተፈጥሮ ሃብትና መሬት ያገሪቱንም የመከላከያ ሰራዊት ዘራፊዎች በየአገሩ በሚቀሰቅሱት  የእርስ በርስ ግጭት እየማገደ የጦር ሜዳ ሸቀጥ አድርጎ የሚነግድበት መሆኑን ተገንዘብ።ሃይማኖትህን አርክሶ የፖለቲካ መሣሪያ አድርጎ መጠቀሙን ተቃወም። የፈጣሪን ቃል ጥሰው ለጥቅም ያደሩ ጳጳሳትንና ቀሳውስትን፣የእስልምና ሃይማኖት መሪ ኢማሞችን አትስማ፣አትከተል።ቤተመቅደስህንና መስጊድህን አታስደፍር።

ህወሃት ለወራሪዎች ጥቅም ሲል አንተንና ሌላውን በቋንቋ እረገድ ከልሎ ሊያጫርስህ የተዘጋጀ፣በደምህ ያቆየሃትን አገርህን ኢትዮጵያን ለማፈራረስ እንጂ ለእድገትህና ለሰላምህ የሚጨነቅ አለመሆኑን ተረዳ።የጠቀመህ መስሎ ከሌሎቹ ነጥሎ ለሚያቀርብልህ ጊዜያዊ ጥቅም አትደር።ውጤቱ የከፋ ሊሆን ይችላልና ለምን ለእኔ ብቻ ብለህ ጠይቅ።እድገት የሚቻለው የትልቅና የሰፊ አገር ባለቤት ሲሆኑ እንጂ የጠባብ ቀበሌ ኑዋሪ እስረኛ በመሆን እንዳይደለ እወቅ።አንተና ሌላው ኢትዮጵያዊ ደሙን አፍሶ ያስከበረውን የትግራይ የድንበር መሬት(ባድመን)አሳልፎ ለመስጠት የተፈራረመ ወንጀለኛ ቡድን ነገ ከእኔ ጋር ይቆማል ብለህ አታስብ።ሕዝባዊ ትግሉ ከጠነከረ ጣጥሎህ፣አንተን ለመከራ አጋልጦህ ይፈረጥጣል።አዘጋጅቶ ባስቀመጠው አገር የድሎት ኑሮውን ሊገፋ እንደሚችል አስብ።በፍርሃት ከኖርክበት ያገርህ መሬት አትኮብልል።ኢትዮጵያዊ  በተለይም አማራውና ኦሮሞው እንዲሁም የቀረው ሕዝብ ጨዋና አስተዋይ እንጂ አብሮ የኖረ ወገኑን የሚያሳድድ አውሬ ፍጡር አለመሆኑን እወቅ።ጥቃቱ በዝቶባቸው፣ ከሚችሉት በላይ ሆኖባቸው ጥቂቶች አላስፈላጊ ጉዳት ለማድረስ ቢነሱ ሁሉንም በአንድ ዓይን ተመልክተህ አትጥላ፣አትፍራ።የሕግ የበላይነት በሌለበት አገር ይህን መሳይ አደጋ ሊከሰት ስለሚችል ለዚህ ክስተት ምክንያት የሆነውን ስርዓት ለማሶገድ ከሌሎቹ ጋር ለመታገል ተሰለፍ።ለብዙሃኑ ጥቃትህ ጥቃታቸው፣ጉዳትህ ጉዳታቸው ስለሆነ አጋልጠው አይሰጡህም። አንተም የነሱ ጉዳትና ጥቃት ያንተ እንደሆነ አረጋግጥ።

ሌላው ለመብቱ ሲነሳ አንተን ለማጥፋት የተነሳ ነው የሚለውን አስበርጋጊና አስፈሪ ሰበካ(ፕሮፓጋንዳ) አትቀበል፤ሌላው የሚያደርገው በተለይም አማራው የሚታገለው እሱን ብቻ ሳይሆን አንተንና ሌላውን ኢትዮጵያዊ ከበዝባዦችና ከጨቋኞች መዳፍ ነጻ ለማውጣት መሆኑን አውቀህ ተባበር።

ተጋብተህና ተዋልደህ ለዘመናት ከኖርክበት ያገርህ መሬት በይሆናል ፍራቻ ለቀህ አትውጣ።ከሌላው ማህበረሰብ ጋር ተጋብተህና ተጋብተሽ ለተወለዱት ልጆች አስቡ።በዚህ አይነቱ ሂደት ቤተሰብ ፈራርሶ ልጆችም ካለእናት ወይም ካለአባት የሚደርስባቸው የህሊናና ስነልቦናዊ ስብራት ምን ያህል አደገኛ እንደሆነ በተመሳሳይ ደረጃ ከተከሰተው ከኤርትራውያኑ ታሪክ ተማር።ወንጀለኛ እንጂ በደል ያልፈጸመ አይሸሽም፤በሥራው ስለሚተማመን ባለበት ይቆያል።በደል የፈጸሙትን፣ሕዝብ የጎዱትን፣አገርህን ለመበታተን የሚጥሩትን ወገኖቼ ብለህ አትጠጋ፣አጋልጣቸው፤አሶግዳቸው።

ጨለማ አልፎ ብሩህ ቀን መምጣቱ አይቀርምና በዚህ የጨለማ አገዛዝ የሚፈጸመው ወንጀል የድል ጎህ ሲቀድ መታየቱ ስለማይቀር ከአገዛዙ ጋር ተባብረህ የሚፈጸመውን በደልና የምትሰጠውን ድጋፍ መርምር፤ሊያጋጥምህ ከሚችለው ታሪካዊ ቁስል ነጻ ለመሆን ዛሬውኑ ምርጫህን አስተካክል።ኢትዮጵያዊነት ወይም ትግራዊነት!ትልቅነት ወይም ትንሽነት! ለዲሞክራሲ መታገልና የነጻነት ባለቤት መሆን ወይም በጠባብ የጎሳ በረት ውስጥ ገብቶ የዘላለም መከራ ሲገፉ መኖር።ሌላ ምርጫ የለም!!

የሌላው ማህበረሰብ ተወላጅ የሆንከው ኢትዮጵያዊም ጎሰኛ በሆነው አስተዳደር በደረሰብህ በደልና ኢሰብአዊ ጥቃት ተነሳስተህ እንዳንተ በስርዓቱ ተበድሎ የኖረውን ወገንህን በቋንቋው ወይም በጎሳ ግንዱ ከጨቋኞቹ ጋር አዳብለህ አታጥቃው፡ሊያጠቁትም የሚነሱም ካሉ አይሆንም በላቸው።እስከአሁን ድረስ ያሳየኸው ጨዋነት አይለይህ።እልህ አስጨራሽ ሁኔታዎች ሊፈጠሩና ሊገፋፉህ ይችሉ ይሆናል፣ግን እጅ አትስጥ።ፈተናውን በለመደው ትእግስትህና ጨዋነት ተወጣው።ተቃውሞና ሃይልህ በገዢው ቡድንና የዚያ ተከላካይ በሆነው ተቋም ላይ ያነጣጠረ ይሁን።ሰላዮችንና የስርዓቱን አገልጋዮች ከሌላው ሰላማዊ ሕዝብ ነጥለህ ተመልከት።

ለተጨማሪ ግንዛቤ ከዚህ በታች በዩቱብ የተላለፈውን ጥሪና መልእክት ታዳምጡ ዘንድ በትህትና እጠይቃለሁ።

https፡//youtu.be/7WQcSmVdTQ8

በአንድነት ለአንድነትና ለነጻነት!!

አገሬ አዲስ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.