‘’ የኢትዮጵያዊኖች ተጋድሎ! ወይስ የማን ተጋድሎ ነው…..?” [ፊልጶስ]

Woyane - satenawወያኔ  ኢትዮጵያን  እያፈራረሰና  ህዝቡን ‘ርስ በርስ እያባላ  ያለው  ብቻውን  አይደለም። የሀገሪቱ ጠላቶች፣  ሆድ-አደሮች፣  መሀል-ሰፋሪዎች፣  ግብዞችና  የመሳሰሉ  ሁሉ  አጋጣሚውን  ይጠቀማሉ። ሲጠቀሙም  ኖረዋል። ወያኔና  ግብረ – አበሮቻቸው  እኮ ኢትዮጵያን  የማፈርስረሱን  መረሀ-ግብር  የተቀበሉት  ከምዕራቡና  ከዐረቡ ዓለም ነው።   መርሳት  የሌለብን  ወያኔ  ከዚህ  ደርጃ  እንዲደርስ  የኛ  አስተዋ’ጾ መሆኑን  መቀበል አለብን።  ማርቲን  ሎተር  ይመስለኛል፤ ካልተጎነበስክላቸው  እነሱ  ከአንተ  ጀርባ  ላይ  አይወጡም !”ያለው።  ቁምነገሩ  ካለፈው  መማር  መቻላችን  ላይ ነው።

በርግጥ  አሁን  ብዙሀኑ  የወያኔን  “አሪወሳዊነት”  ከማንኛውም  ግዜ  በበለጠ  የተረዳበትና  የ40 ዓመት የከፈፍለህ  የቤት  ስራ ”ፉርሽ” የሆነበት ነው።   ይሁን  እንጂ  ብዙ  ድህረ-ገጾች፣  ዜና – ዘጋቢዎች፣ ዘፋኞች፣  ሰላምዊ  ሰልፎኞች፣  የፓለቲካ  ተንታኞች፣  መግለጫዎችና   የመሳሰሉት  በሚያሳዝንና በሚያሳፈር  ሁኔታ  ከወያኔ  የጎሳ  ወጥመድ   ያለመላቀቃችን ፤ አንድርምጃ  ወደፊት፣  አንድርምጃ ደግሞ  ወደ  ኋላ  መሆኑ  በግዜ  ሊታሰብበትና   ሊታረም   የሚገባ   ጉዳይ ነው። እናም  የምንናገረውንና  የምንጽፈውን  በጥንቃቄ   መመርመርና፤ ወያኔ  የማይቆፍረው  ጉድጎዳ፣  የማያፈሰው  ደም  እንደሌለ  ከምንግዜውም  የበለጠ   አሁን  መረዳት  ያስፈልጋል።

  • ”የአማራ ተጋድሎ!….. የኦሮሞ ተጋድሎ!….. የመሳሰሉ ዜናዎችና  መፈክሮች   የሚያመለክቱት አሁንም   ደም  እንደጎርፍ  እየፈሰሰና  ምድራዊን  ስቃይ  እየተቀብለን፣  ወያኔ  ካሰመረልን የጎሰኝነት  ስሜት  ያለመውጣታችን  የሚያመለከት ነው።  ለምንድን  ነው የኢትዮጵያኖች ተጋድሎ ! “ የማንለው?? ?….. እድግመዋለሁ፤ የኢትዮጵያዊኖች ተጋድሎ!” ። አማሮች እንዲህ…አድረጉ…  ኦሮሞዎች  እንዲህ ሆኑ………አደረጉ… ..ወዘተ…..እያልን ፤ በአንድ  አካባቢ  አንድ  ወጥ  ህዝብ   እንዳለ   አድርገን   ማቅረባችንና   መዘገባችን  ይቁም። በተለይም ኢሳት  (ቲቪና  ሬዲዮዎ )  የኢትዮጵያ ህዝብን ዓይና ጆሮ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ በዚህ ጉዳይ ግን ቢያስብበት መልካም ነው እላለሁ።

በዚች ሰዓት ጋምቤላዎች  የከፍሉት  መሰዋ’ትነና  እየከፈሉት  ያለው  ተጋድሎ፣  የኦጋዴኖችና  አንዲሁም  በተለያየ  ግዜ  በተለያዩ  የሀገሪቱ  ግዛቶች   ከወያኔ ጋር  የሚተናናቁት ሁሉ የኢትዮጵያኖች ያውም  የዚህ ኢትዮጵያዊ ትውልድ  ተጋድሎ  እንጅ  የማን   ሊባል  ይችላል?  ካላያማ  ከወያኔ  በምን  ተለየን?  የተጀመረውን  የጸረ-ወያኔ  የጎሳ ከፋፍለህ  ግዛው  እንዴት ነው  የምናከሽፈው? “የዚያ  ጎሳ  ተጋድሎ!….. የዚህ  ጎሳ  ተጋድሎ!…..” እያልን  እንዴት  አድርገን  ነው  ትግሉን  ለህዝባዊ ፣ ለሁሉሙ  ኢትዮጵያዊ  ድል  የምናበቃው?

  • ሌላው የስሞኑን  ህዝባዊ  አመጽ  ያቀጣጠለው  የወልቃይት  ጉዳይ  ነው። የወልቃይት ጥያቄ የሁሉም  ኢትዮጵያዊ  ጥያቄና  ትግል  ነው። ኢትዮጵያዊ  ዜጋ  ነኝ  የሚል ሁሉ ይመለከተዋል። ይሁን  እንጂ   ወልቃይት አማራ !…” የሚለው  አባባል፣ መፈክርና  ቀረርቶ  የወያኔ  የጎሳ ስራ መስራቱን  ነው  የሚያመለክተው።  ወልቃይት …..  የጎንደር  አንዱ  ግማድ  ነው፤ ለዚህም የህይወት  መሰዋትነት  ብቻ  አይደልም፤  የዘር  ማጥፋት  ወንጀል  እየተፈጸመበት  ያለ  ህዝብ ነው። ያ  ማለት  ደግሞ  ‘’ወልቃይት – ጎንደር፤  ጎንደርኢትዮጵያ  ነው።”’  ይህም  ማለት ኢትዮጵያ  ከሌለች   – ወልቃይትጎንደር  የለም  ሁሉም  ኢትዮጵያዊ  የሚስማመው ”  በኢትዮጵያዊያን   ተጋድሎ !….” ነው።   ትግሉ  የሁሉም  ኢትዮጵያዊ  መሆኑ  በዚህ ሰዓት መዘንጋት  የሌለበት  ጉዳይ ነው።  ለመሆኑ  የሌላው  ኢትዮጵያዊ  ተጋድሎና  መሰዋትነት  የት ሊጣል  ነው?  የአብሮነት  ትግል  ባላማካሄዳችን  አይደልም  ወይ፤  ወያኔና  ሆድ-አደሮቹ ሀገራችን  የግላቸው  እቃ  አድርገው   ህዝብን  እንደቅጠል  የሚያረግፉት።

 

  • ወያኔ ለኢትዮጵያ  ጎሳዎች  ብሎ   የጫነብን  ሰንደቅ ዓላማ፤  በየተኛውም  ኢትዮጵያዊ ተቀባይነት  አለመኖሩ  ብቻ  አይደለም ፤ ነባሩ ሰንደቅ – ዓላማ   የኢትዮጵያ ህዝብ የአንድነትና   የተጋድሎ  መግለጫ   መሆኑን  እያስመሰከረ  ነው።  ስለዚህም  በህዝባዊ  አመጽ   ወቅት  የቡድን  ወይም  የድርጅት  ሰንደቅ  ዓላማ  ይዘን  መውጣታችን  ይከፋፍለናል  እንጅ  አንድ  አያደርገንም።  በርግጥ  በአንዳንድ  የደቡብ  ክፍል  የወያኔ ካድሪዎች  የአንዳንድ ድርጅቶችን “ሰንደቅ  ዓላማ”   ይዘው  በመውጣት  ህዝብን  ለመምታትና  ለመከፋፈል  እየተጠቅሙብት  ቢሆንም፤  እኛ  ግን  አንድነታችን  በተግባር  እናስመስክር። እየተከፈለ  ያለው  የህይወት  መሰዋትነት  ነው።

 

  • ሰሞኑን  ከተቀሰቀሰው  ህዝባዊ  አመጽ ጋር  አንዳንድ  ዘፋኞች  ከትግሉ  ጋር  በተያያዘ   ነጠላ ”የቅሰቀሳና  የውዳሴ”  ዜማ ለቀዋል፡:  በተለይም  ስለ  “ወልቃይት-ጎንደር፣ …….ስለ ኦሮሚያ፣….  ወዘተ።  ይሁን  እንጂ  በ’ኔ  እይታ   ዜማዎቹ  በደንብ  የታሰበባቸው  አይደሉም። ”ኢትዮጵያዊ”  አንድምታ  የላቸውም።  ተጋድሎውና  ህዝባዊ  አመጹ  የመላው  ኢትዮጵያዊ በመሆኑ  ዜማዎቹም  የሁሉንም  ኢትዮጵያዊያን   አንድነትና  ጅግንነትን  የሚያወድሱና የሚቀሰቅሱ   መሆን  ሲገባቸው  በአካባቢያቸው  ተወስነዋል።   የወያኔች  በጎሳ  ላይ  በተመሰረተ የጥላቻና  የግብዝነት  ከበሮ -ድለቃ ፤ የምን ያህል  የወርዱና  የዘቀጡ ኅሊና   ያልፈጠረባቸው  መሆናቸውን  የሚያመለክት  ሆኖ   ሳለ፤  የ’ነሱን  ፈለግ  መከተሉ   በአንድ  አፍ  ሁለት  ምላስ  …” ይሆንብናል።   ”ወልቃይት  ብረሳሽ  ቀኜን  ይርሳኝ!..!”  ከማለት  ኢትዮጵያ ….ብረሳሽቀኜን  ይርሳኝ!”  ብሎ  ቢያንጎራጉር፤  ለአንድነታችንና   ለትግላችን   የሚኖረው  ፋይዳ  ከፍተኛ   ነው።  ለወያኔም  የራስ  ምታት  ነው።  ኢትዮጵያ  እንዳትኖርና  እንድትፈራርስ   እኮ ነው  ወልቃይትና  ሌሎችም  አካባቢዎች  ለወያኔ  የተከለሉትና  ለሱዳን  እጅ  መንሻ የሚቀርቡት።  እናም  በተቻለ  መጠን   የትግል  ዜማችን  የሁላችንም  ሀገር  ልናደርጋት  መሰዋ’ት   ለምንከፍልላት  ኢትዮጵያችንና  ህዝባችን  ይሁን።

ያለፉትም  ሆነ  አሁን  ያሉት ”ጅግኖቻችን”  የከፈሉት  መሰዋትነትና  እየከፈሉ  ያሉት  ለኢትዮጵጵያና  ለኢትዮጵያዊያን  ነው።  ታዲያ   እነዚህን  የክብር  የኢትዮጵያዊያን  ጀግኖች  ወደ  መንደርተኛነት  ማውረድ  ምን  ይሉታል?።  ቢቻል  በዚህ ሰዓት   ዘፋኞች  በህብረት  ለሁሉም  ኢትዮጵያዊ  የሚሆን  በተለያዩ   የሀገሪቱ   ቋንቋዎች  ዜማ  ቢለቁ   ለትግሉም  ሆነ  ለአንድነታችን  የበኩላቸውን  አስተዋ’ጾ  ያደርጋሉ። በዚህ ጉዳይ ላይ በተለይም  ባህር-ማዶ የምትገኙት እንደ አለምፀሀይ  ወዳጆና  ታማኝ  በየነ ያላችሁ፤ የጥበብ ሰዎችን እንደተለመደው  ብታሰተባብሩ ”ለቀባሬው ማርዳት” ባይሆንብኝም  መለዕክቴ  ይድረሳችሁ።

—//—-

ፊልጶስ / ነሀሴ 2008 / E-mail: philiposmw@gmail.com

 

Comments are closed.