በኢንጅነር ይልቃል ላይ ውሳኔ ለመስጠት ጉባዔ ሊጠራ ነው

Blue Party 5ባለፉት ሁለት ዓመታት በሰማያዊ ፓርቲ ውስጥ የተለኮሰው የፖለቲካ ትግል እየጋለ እየበረደ አንዱ አሸናፊ ሲሆን በሌላ ጊዜ ሌላው ተሸናፊ እየሆነ ብቅ የሚልበት ሂደት እንደቀጠለ ነው። በተለይ በፓርቲው ሥራ አስፈፃሚዎች እና በምክር ቤቱ መካከል ግልፅ የአሰራር ስርዓት በመከተል እና ባለመከተል ጋር በተያያዘ ያላቸው አለመግባባት ከፓርቲው የኦዲትና ኢንስፔክሽን አልፎ በአደባባይ ሲካሰሱ መክረማቸው የሚታወስ ነው። በጽ/ቤቱ ግቢ ውስጥ እስከመደባደብ የደረሱበትም አጋጣሚ የሚዘነጋ አይደለም።

ባለፈው እሁድ በነሐሴ 8 ቀን 2008 ዓ.ም. የሰማያዊ ፓርቲ ምክር ቤት በጠራው አስቸኳይ ስብሰባ የሥራ አስፈፃሚ አባላቶችን ከኃላፊነታቸው አንስቷል። የፓርቲው ሊቀመንበር ከስልጣናቸው ለማሰናበት እና በምትካቸው ሌላ ለመተካት ከአንድ ወር በኋላ ጠቅላላ ጉባኤ ለመጥራት ውሳኔ አስተላልፏል።

በምክር ቤቱ አስቸኳይ ስብሰባ በአጀንዳነት ከቀረቡት መካከል በባሕርዳር ከተማ ፓርቲው የጠራው ሰላማዊ ሰልፍ፣ የተጠራበት መንገድ እና የተጠራው ሰልፉ እንዲሰረዝ የተደረገበት አግባብ ከፍተኛ የልዩነት ሃሳብ ፈጥሯል። ፓርቲው የጠራው ሰላማዊ ሰልፉ መሰረዙ ፖለቲካዊ ኪሳራ አስከትሏል የሚል ክስ በስብሰባው ቀርቧል። ሰልፉ የተጠራበት አግባብ ጥልቅ ውይይት አልተደረገበትም፣ ከመጠራቱ በፊት ሰፋ ያለ ውይይት እንዲደረግ ሃሳብ ብናቀርብም ሰሚ አላገኘንም የሚሉ ክሶችም ቀርበዋል።

የፓርቲው ምክትል ሊቀመንበር ለውጭ የመገናኛ ብዙሃን የባሕርዳር ሰልፉን አስመልክተው በሰጡት ምላሽ፣ ከአማራ ክልላዊ መንግስት ሰላማዊ ሰልፉ ለማድረግ ፈቃድ ጠይቀው ማግኘታቸውን አስታውቀው፣ ሆኖም ግን ሰልፉ ከተጠራበት አንድ ቀን በፊት በሰማያዊ ፓርቲ የተጠራው ሰልፍ ፓርቲው መሰረዙን ለክልል ምክር ቤቱ ማሳወቃቸውን ይፋ አድርገዋል። አያይዘውም ሰላማዊ ሰልፉ የተሰረዘው በአማራ ክልል እና አዲስ አበባ በሚገኙ በፓርቲው ኃላፊዎች መካከል በተደረሰ ስምምነት መሆኑን ማስታወቃቸው የሚታወቅ ነው።

በፓርቲው ሊቀመንበር ኢንጂነር ይልቃል እና በምክር ቤቱ መካከል ያሉ ልዩነቶች እየሰፋ የመጡበት አግባብ በርካታ ናቸው። ነሐሴ 16 እና 17 ቀን 2007 ዓ.ም. ፓርቲው ካደረገው ጠቅላላ ጉባኤ በኋላ፣ ኢንጅነር ይልቃል ጌትነት ለብሔራዊ ምክር ቤቱ ካቀረቧቸው ሥራ አስፈፃሚዎች መካከል አቶ ስለሺ ፈይሳ፣ አቶ ወረታው ዋሴ እና አቶ እያስፔድ ተስፋዬ በምክር ቤቱ ድጋፍ በማጣታቸው ምክር ቤቱ ሳይቀበላቸው ቀርቷል። ይህ የምክር ቤቱ ውሳኔ ከሥራ አስፈፃሚው ጋር በተለይ ከኢንጅነር ይልቃል ጋር ቅሬታ ውስጥ ከቷቸዋል።

እንዲሁም የፓርቲው የ2008 ዓ.ም፣ የሥራ ዘመን በጀት በምክር ቤቱ ሳይጸድቅ ሥራ አስፈፃሚው ወደ ሥራ መግባቱ ሌላው የውዝግብ ምንጭ ተደርጎ የሚጠቀስ ነው። ከዚሀም በላይ ኢንጅነር ይልቃል ከምክር ቤቱ ጽ/ቤት ኃላፊ እንዲሁም ከኢዲትና ኢንስፔክሽን አባላት ጋር በተፈጠረው አለመግባባት አብረዋቸው መስራት እንደማይችሉ በግልጽ አቋም ወስደው የተወሰኑ ሥራ አስፈፃሚዎችን በመያዝ ሥራዎችን እያከናወኑ ይገኛሉ። በፓርቲው ጽ/ቤት በተደጋጋሚ በተነሳው ጠብ ምክንያት ኢንጅነር ይልቃል ከተወሰኑ የሥራ አስፈፃሚ አባላት ጋር በጋራ በመሆን ምርፋቅ ካፌ በተባለ ቦታ ሥራቸውን ለማከናወን መገደዳቸው የሚታወቅ ነው። አንዳንድ የምክር ቤት አባሎች “የካፌው ሊቀመንበር” በሚል ቅጥያ ስም ይጠሯቸዋል።

የተፈጠረው ልዩነት የፓርቲውን ሕልውና በከፍተኛ ሁኔታ እየተፈታተነው ይገኛል። በተለይ በአመራሮቹ መካከል በተደጋጋሚ ሁኔታ ለጠብ መጋበዛቸው ሁኔታዎቹን የበለጠ ውስብስብ አድርጓቸዋል። በአመራሮቹ መካከል የተፈጠረውን ልዩነቶች ለማጥበብ በርካታ ጥረቶች ተደርገዋል። በቅርቡ እንኳን መንግስት በአሸባሪነት ጠርጥሮ አስሯቸው የነበሩት የፓርቲው ም/ቤት ም/ሰብሳቢ አቶ የሺዋስ አሰፋ ከእስር ከተለቀቁ በኋላ በተካሔደው የብሔራዊ ም/ቤት ስብሰባ ላይ በመቅረብ የተሰነጣጠቁት አመራሮች እርቅ እንዲያወርዱ አንብተው ቢለምኑም ልዩነታቸው ሊጠብ አልቻለም። ኢንጅነሩም ወደ ቢሮ ገብተው እንዲሰሩ አማላጅነት ቢላኩም ሊመልሷቸው አልቻሉም።

በፓርቲው የተጀመረው የእርቅ ሒደት ይህንን በመሰለ መልኩ እየቀጠለ በነበረበት ወቅት የፓርቲው ሊቀመንበር የብሔራዊ ምክር ቤቱን ሆነ የሁሉንም ሥራ አስፈፃሚዎች ይሁንታ ሳይጠይቁ ወደ ካናዳ መጓዛቸው በሽምግልና ጥረቱ ላይ አዲስ እሳት ለኩሰውበታል። ተቀዛቅዞ የነበረው ውዝግብ የበለጠ እንዲያገረሽ ሆኗል። ከዚህ ከሊቀመንበሩ ተግባር ጋር በተያያዘ ብሔራዊ ምክር ቤቱ የሥራ አስፈፃሚው ኮሚቴ እንዲበተን እሁድ ዕለት ውሳኔ አስተላልፏል።

በብሔራዊ ምክር ቤቱ አስቸኳይ ስብሰባ ንግግር ያሰሙት የምክር ቤቱ ሰብሳቢ አቶ ይድነቃቸው “የሥራ አስፈፃሚው ኮሚቴ የሕዝቡን ትግል እና የድል ጉዞ ጠልፎ ለማደናቀፍ እየተጓዘበት ያለው መንገድ ከባድና ውስብስብ ከመሆኑም በላይ በተለይ የባሕር ዳሩ ሰልፍ ተግባራዊ ሊሆን እንደማይችል እየነገርናቸው እምቢ በማለታቸው በዚህም የተነሳ ፓርቲውን ከፍተኛ የፖለቲካ ዋጋ አስከፍለውታል” ማለታቸው በምክር ቤቱ ውስጥ ከፍተኛ ውዝግብ አስከትሎ እንደነበር ጉዳዩን የተከታተሉ ምንጮቻችን ገልፀዋል።

የምክር ቤቱ ሰብሳቢን ሃሳብ አቶ ወረታው ዋሴ ሙሉ ለሙሉ ውድቅ አድርገው ተከራክረዋል። ውይይቱ ከመክረሩም በላይ በሁለቱ መካከል የተነሳውን ጠብ ለገላጋይ በሚያስቸግር ሁኔታ ለመቆጣጠር ተችሏል። ሌሎች የምክር ቤት አባላትም ለጠብ የተጋበዙበት ሁኔታዎች ተፈጥሮ ነበር። “ሥራ አስፈፃሚውን የመበተን ስራ የተጠነሰሰው በወያኔ ነው። ይህ ግልጽ የማስወገድ እርምጃ የወያኔ ጣልቃ ገብነት ነው” በማለት ውሳኔውን የተቃወሙት አቶ ወረታው ከምክር ቤቱ ወቀሳ አስተናግደዋል። “እስካሁን ስትሸረሽረን የነበርከው አንተ ነህ። በዚህ ሚስጥራዊ ሴራ የተካንከው አንተ ነህ ወያኔ” በማለት የምክር ቤት አባላት አቶ ወረታው ዋሴን ከሰዋል። የልዩነቶቹ ሃሳቦች እየሰፉ እና ከቁጥጥር ከመውጣታቸው በፊት በቀረቡት ልዩነቶች ላይ በተሰጠው የሚስጥር ድምጽ ውጤት መሰረት የብሔራዊ ምክር ቤት አብላጫው ድምጽ ሥራ አስፈፃሚው ኮሚቴ ከኃላፊነት እንዲነሱ ወስኗል።

ኢንጅነር ይልቃል ጌትነት ከሊቀመንበርነት እና ከአባልነት ለማሰናበት የሚያስችል ውሳኔ ለማስተላለፍ ከአንድ ወር በኋላ በሚካሔደው ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ለመወሰን ምክር ቤቱ ከስምምነት ላይ ደርሷል። በባሕርዳር የተጠራውን ሰላማዊ ሰልፍ በበቂ ሁኔታ እንምከርበት እየተባለ አልሰማ ብለው ባለቀ ሰዓት ፓርቲው ሰልፉን ሰርዞታል የሚል መግለጫ የሰጡት ከኃላፊነት ለመሸሽ በመፈለጋቸው ነው የሚል ግንዛቤ በስብሰባው ላይ ተወስዷል።¾

ምንጭ፦ሰንደቅ