ስለነገው የአዲስአበባ ሰልፍ ሳስብ የቻይና ባምቡ ወይም ቀርከሃ ዛፍ ታወሰኝ [ያሬድ ጥበቡ]

yared 3የቀርከሃ ዛፍ ፍሬ ከተተከለ በኋላ ለአራት አመታት ከትንሽ እምቡጥ ቅጠል በቀር ምንም እድገት አያሳይም ። ተካዩ እነዚያን ሁሉ አመታት በተስፋ መጠባበቅ አለበት ። አንድ ቀን ሳይታሰብ ያቺ እምቡጥ ወደሰማይ መመዘዝ ትጀምራለች ። እነዚያን ከአፈር በላይ ያላደገችባቸውን አራት አመታት ከአፈር በታች ስታድግ፣ ስትመነደግ፣ ስትስፋፋ ስለኖረች እድገቷ እጅግ ፈጣን ነው ። በአማካይ 80 ጫማ ከፍታ ወይም 24 ሜትር ሽቅብ ትመነደጋለች ። ለካስ 4 አመት ሙሉ 24 ሜትር ቁመት ያለው ዛፍ ለመሸከም የሚያስችል ሥር ስትገምድ ነው የከረመችው ።

በቃ! ለኔም የአዲስ አበባ ሰልፍ እንደ ቻይና የባምቡ ዛፍ እድገት መስሎ ተሰማኝ ። ልዩነቱ አራት አመታት ሳይሆን የጠበቅነው 25 አመታትን ነው፣ ሩብ ክፍለዘመን ነው ። ታላቅ ቧጋችነትና ቻይነት ለአለምም ሆነ ለራሳችንም አሳይተናል ። ዝግጅቱ 25 አመታትም የወሰደብን ያለምክንያት አልነበረም ። በመሃላችን የነበረውን የኢትዮጵያዊነት ድልድይ ሰብሮ፣ እርስ በርስ በጥርጣሬ እንድንተያይ ያደረገን ዘረኛ ሥርአት መንግስታዊ ስልጣኑን ጨብጦ ስላዳከመን ነበር ። የጥርጥሬንና የፍርሃትን ገደል ተሻግረን ለመተማመንና ትከሻ ለትከሻ ተደጋግፈን አብረን ለመቆም ብዙ ጭንቀት፣ ብዙ እንቅልፍ አልባ ሌሊቶች፣ ብዙ እርስ በርስ ያለመተማመን አመታት አሳልፈን ይሄው ከዚህ ደርሰናል ። በዳያስፖራ ያሉ ወገኖቻችን የኢትዮጵያንና የገዳ ኦሮሞን ሰንደቅ ጎን ለጎን ተሸክመው፣ በአለም ህዝብ ፊት ሲሰለፉ አኩርተውናል ። የክፍፍልና ጥርጥሬ ዘመን አከተመ፣ የኢትዮጵያ ትንሳኤ ተደገመ ሲሉን ጆሮ ሰጥተን አድምጠናቸዋል ። አዲስ አበባም የሚሆነው እንደዚያው ነው ። ተከፋፍለን ወደ ሁለተኛ ደረጃ ዜግነት የወረድነበትን የ25አመታት የውርደት ህይወት ላንመለስበት ቆርጠን ተነስተናል ።

አለመተማመን፣ ጥርጣሬና ፍርሃታችን ሁላችንንም ለሁለተኛ ደረጃ ዜግነት እንደዳረገን ተረድተናል ። በሃገራችን ላይ የበይ ተመልካች ሆነናል ። በዘመናዊነት ስም ከቀዬአችን ነቅለውን ከከተማው ጥግ ሲወረውሩንና እነርሱ በመሬታችን ላይ ሰማይጠቀስ ሲሰሩበት፣ በአርምሞ ተመልክተናል ። ሆኖም ቤታችንን ብቻ ሳይሆን የደረመሱት፣ ማህበራዊ ትስስሮቻችንን ጭምር ነበር ። የዘመናት ጎረቤቶች አብረን እንዳንኖር ተበትነናል ። ይህ ሁሉ አበሳ የደረሰብን በ1997 ምርጫ ለቅንጅት ባደረግነው ድጋፍ መሆኑንም እናውቃለን ። ሊበትኑንና ማህበራዊ ኢንጂነሪንግ ሊያካሂዱብን ወሰኑ ። በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ አዲስ ሰፋሪዎች አምጥተው አሰፈሩብን ። በሎተሪ በሚያድሉን ፎቆች ውስጥ ተጠቃሚዎቹ መጤዎቹ ከመሆናቸው አልፎ፣ ከአጋዚ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ያላቸው አስተኳሾች ሆነው ተሾሙብን ። ከተማህን በመሰረተ ልማት ስላሳደግናት አሜን ብለህ ተቀበለን ፣ ሆድህ ባይሞላም ዓይንህ የኛን ፎቆችና የሴቶቻችን ሹሩባ ላይ የተነሰነሰውን የወርቅ እንክብል እያየ ይደሰት ፣ አትመቅኝ ብለው አላገጡብን ።

እንዴት እንዲህ ይሆናል የአንድ ሃገር ዜጎች ሆነን? ብለን ስንጠይቅ፣ “የባሰ ይጠብቅሃል፣ ለኦሮሞ አስረክበንህ ነው ወደመጣንበት የምንመለሰው” እያሉ ሲያስፈራሩን ኖረዋል ። አምነናቸው ነበር፣ ሆኖም የበታችነቱ ሲበዛብን፣ የነርሱም ዘረኝነትና ጥጋብ ልንሸከመው ከምንችለው በላይ ሲሆን አንድ ጥያቄ አበክረን ራሳችንን ጠየቅን ። “ኦሮሞ ቢመጣ ከሁለተኛ ደረጃ ዜግነት ባነሰ ምን እንዳያደርገን ነው ፣ እንዲህ በፍርሃት ተዋርደን የምንኖረው?” ብለን ። መልሳችንም እምቢ ለፍርሃት ሆነ ።

የኦሮሞ ህዝብ ባለፉት 25 አመታት በወያኔ አገዛዝ ሲቀጠቀጥ የኖረ ህዝብ ነው ። ታላቅ መስዋእትነትም ከፍሏል ። የትግሉም ዋነኛ መንስኤ “ሁለተኛ ደረጃ ዜግነት አልቀበልም” ማለቱ ነው ። የመሬቴ ባለቤትና ተጠቃሚ እኔው ልሆን ይገባል ነው ። ከቀዬ አልነቀልም ነው ። ከኦሮሞ ህዝባችን ጋር በደላችን ተመሳሳይ ጥያቄአችንም አንድ ነው ።እኛም በሃገራችን ላይ ሁለተኛ ደረጃ ዜግነትን ወይም ውርደትን አንቀበልም ነው የምንለው ። ይህንንም በፍፁም ሰላማዊነት ለማስከበር ቆርጠን ተነስተናል ። ባትተኩሱብንም እንወዳለን ።

የህዝብን ሰላማዊ ጥያቄ ግን በግድያ እናቆማለን ካላችሁ ምርጫው የናንተ ነው ። ሁለተኛ ደረጃ ዜጋ ሆነን ከምንኖር፣ በጥይታችሁ ልንሞት ቆርጠናል ። ለሞት የቆረጠ ህዝብ ደግሞ ተሸንፎ አያውቅም ። ማሸነፉም አይቀሬ ነው ። ሰላማዊን ህዘብ በጨፈጨፋችሁ ቁጥር ግን ችግሩን በሰላምና በእርቅ የመጨረስ እድሉን ግን እያጠፋችሁ መሆኑን እንድትገነዘቡት እንፈልጋለን ። መጨረሻችሁ ያማረ አይሆንም ። ለልጆቻችሁ ስትሉ የሰላምና የእርቅን መንገድ ተከተሉ ። በሰላም ጥያቄዎቻችንን የማቅረብ መብታችንን ተቀበሉ ። የመፍትሄው አካል የመሆን እድል አላችሁ ። አታበላሹት ። ይህ ሳይሆን ቀርቶ በሰላማዊ ህዝብ ላይ ተኩሳችሁ እልቂት ብትፈጥሩ ተኳሽ፣ አስተኳሽ፣ እዝ ሰጪ፣ ፖሊሲ አርቃቂ ወዘተ ለፍርድ የምትቀርቡበት ቀን ሩቅ አይሆንም ። ግን እዚያ ጋ መዳረስ የለብንም ። ራሳችሁን አስተካክላችሁ የመፍትሄው አካል ሁኑ ። ከዘረኝነት ፣ ከጥጋብ፣ ከእብሪት የሚገኝ ምንም ደግ ትሩፋት የለም ። በዚህ የፍፃሜው መጀመሪያ ደቂቅ ላይ ፣ ፈጣሪ ቀናውን እንዲያሳያችሁ ፀሎታችን ነው ። እባካችሁ ተለመኑ ።