የአልጃዚራ ዘገባ – እዚህ ደረጃ መድረሳችን ያሳዝናል – ‪#‎ግርማ_ካሳ‬

የሚከተለዉን አልጃዚራ ላይ አየሁ ። ሕወሃቶች በሌላው ላይ የሚፈጸሙት ኢሰብ አዊ ግፍና በደል፣ ሕወሃቶች ትግሬዎች እንደመሆናቸውም፣ በትግሬዎች ላይ ያለው ጥላቻ ከመቼውም ጊዜ በላይ የጨመረ ይመስላል።

የአልጃዚራ ዘገባ – እዚህ ደረጃ መድረሳችን ያሳዝናል – ‪#‎ግርማ_ካሳ‬አስታወሳለሁ ከስድስት ሰባት አመታት በፊት፣ አቶ ስዬ አብርሃ የአንድነት ፓርቲን ሲቀላቀሉ። እርሳቸው የአንድነት ፓርቲን እንዲቀላቀሉ በጣም ይፈልጉ ከነበሩትና ግፊት ካደረጉት ወገኖች መካከል በቀዳሚነት እኔ እገኛለሁ።

በወቅቱ አንድ የአገዛዙ ደጋፊ “እነ አቶ ስዬን አንድነት ፓርቲን በማስገባቱ የበለጠ እነ መለስ ዜናዊን የሚያናድድ ነው። ስዬ ይጎዳቹሃል እንጂ አይጠቅማችሁም” አለኝ። እኔ ያለው እዉነት ሊሆን እንደሚችል ነግሬው “ፓርቲውን ሊጎዳ ቢችልም አገርን ግን ይጠቅማል” የሚል ምላሽ ነበር የሰጠሁት። የነ አቶ ስዬ የአንድነት ሃይሉን መቀላቀል ትግሉን de-ethnicizeያደርገዋል በሚል (በህዝብና በአገዛዙ መካከል ያለ እንጅ በሌላው ህዝብና በትግራይ ህዝብ መካከል እንዳለሆነ)

የአንድነት ፓርቲ በርግጥ ሁሉንም የአገሪቷ ክፍሎች ባቀፈ መልኩ፣ ሴንትሪስት የፖለቲካ ፕሮግራም በማስቀመጥ ጥሩ ሥራ መስራት ጀምሮ ነበር። አቶ ስዬ አብርሃንም ተከተሎ፣ እንደ አቶ አስራት አብርሃ፣ ሲሳሽ አዘናው፣ አስገዴ ገበረ ስላሴ ያሉ ጠንካራ የዲሞክራሲ አክቶቪስት የትግራይ ልጆች ከሌሎች የለዉጥ የአንድነት ሃይል ጋር በመሆን የጸረ-ሕወሃትን ትግል ተቀላቅለው መታገልም ጀመረው ነበር። (አሁንም እየታገሉ ነው) ሲሳይ አዘናው ታፍኖ ለብዙ ወራት በወህኒም ተሰቃይቷል።

አስታወሳለሁ በሚሊዮኖች ድምጽ ንቅናቄ ወቅት የአንድነት ፓርቲ በመቀሌ ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ ለሁለት ሳምንታት ከቀሰቀሰ በኋላ ነው፣ በሃይል የአባይ ወልዱ አሰተዳደር፣ “መቀሌ እንኳን እናንተ ቅንጅትም አልደፈራትም” በሚል የመቀሌ ህዝብ ድምጹን እንዳያሰማ አግዶ የነበረው(ያኔ በደሴ፣ በጎንደር፣ በባህር ዳር ሰልፎች ተደረጎ የነበረ ጊዜ ማለት ነው)

የሚያሳዝነው፣ እንደ አንድነት ፓርቲ ያለን፣ ሁሉን ያሰባሰበ፣ የሰለጠነ የፍቅር ፖለቲካ የሚያራምድን ፓርቲ ህወሃት በፖለቲካ ዉሳኔ ከጨዋታ ዉጭ አደረገው። እንደ ሃብታሙ አያሌው፣ አንዱዋለም አራጌ፣ ዳንኤል ሺበሺ. ናትናኤል መኮንን ያሉ በሳል የአንድነት አመራሮች “ሽብርተኛ ” ተብለው ታሰሩ።

ህወሃቶች ህዝቡን የበለጠ አማረሩት። በጥጋብ ተሞሉ። ጀነራል ሶሞራ እንዳለው “ህወሃት ማለት የትግራይ ህዝብ ነው” እያሉ መስበክ ጀመሩ። ሰው ማሰብ የማይፈለገውን ነገር እንዲያስብ፣ መሆን የማይፈለገውን ነገር እንዲሆን ወደ ጥግ ገፉት። ጥቂት የህወሃት ጉጅሌዎችን ለመጥቀም ሲባል ራሱ መከራና ስቃይ ያየውን የትግራይ ህዝብ እንዲጠላ አደረጉት። ታዲያ የትግራይ ህዝብ ጠላት ማን ነው ከተባለ ህወሃት ነው ቢባል ስህተት ይሆናልን ?

ይህ በአልጃዚራ ተፈጸመ የተባለው ያለምንም ማጋነን የሕወሃት የዘር የጥላቻና የመከፋፈል ፖለቲካ ቀጥተኛ ውጤት ነው።

ምን ችግር ነበረው፣ በዘር ላይ የተመሰረተ አወቃቀር ባይኖር ኖሮ ? ምን ችግር ነበረው በቃ ሁሉም ዘሩ ሳይጠየቅ በስብእናዉና በኢትዮጵያዊነቱ በሁሉም የአገሪቷ ክፍሎች ተከበሮ የሚኖርባት አገር እንድትኖረን ብንሰራ ኖሮ ? ምን ችግር አልነበረውም። ግን ህወሃቶች የነርሱን ስልጣን ማቆየት እንጅ ለሕዝብ የማያስቡ በመሆናቸው በዘር እንድንፋጅ እያደረጉን ናቸው።

በነገራችን ላይ በዘር ላይ የተመሰረተ ጥቃት አሁን አይደለም የተጀመረው። አማርኛ ተናጋሪዎች አገራችሁ አይደለም በሚል በአሥር ሺሆች የሚቆጠሩ የዘር ማጽዳት ወንጀል ተፈጽሞባቸዋል። ኦሮሞዎች ከሶማሌ ክልል በገፍ ተፈናቅለዋል። ዘር ተኮር ግጭቶች በየቦታው ነው ያሉት።

በአገራችን ዘላቂ መፍትሄ እንዲኖራት ከተፈለገ የዘር አወቃቀር የዘር የፖለቲካ አስተሳሰብ መቀየር አለበት። ይሄ መሬት የኦሮሞ ነው፣ ያ የአማራ ነው፣ ይሄ የትግሬ ነው …ምናምን የሚል ነገር መኖር የለበትም። የኢትዮጵያ ባለቤት ዘሮች (ብሄር ብሄረሰቦችና ሕዝቦች) የሚለው ቀርቶ የኢትዮጵያ ባሌበት የኢትዮጵያ ህዝብ ወይም ዜጎች ናቸው በሚል መስተካከል አለበት። ማንም ኢትዮጵያዎ በማንኛው የኢትዮጵያ ግዛት በማያሻማ መልኩ የመኖር መብቱ መረጋገጥ አለባት። ኢትዮጵያዉያን ኬኒያ እንደሚኖሩት ሳይሆን እንደ ራሱ አገር።

ይሄንን ደግሞ ለዉጥ ህወሃት ሊያመጣ አይችልም። ከትግራይ ህዝብ ደህንነት፣ ለተቀረው የኢትዮጵያ ህዝብ ሰላም ሲባል ሕወሃቶችን የፈጠረው የትግራይ ህዝብ ሕወሃቶች ለብሄራዊ እርቅ እንዲዘጋጁና እነርሱንም ያካተተ የሽግግር መንግስት እንዲቄቋም ግፊትና ጫና እንዲያደረግ እጠይቃለሁ። መቀሌ፣ ሽሬ ፣ አክሱም፣ ዉቅሮ …መነሳት አለባቸው። በዘጠኝ ወራት ብቻ ከዘጠኝ መቶ ኦሮሞዎች በአጋዚ ታጣቂዎች በግፍ ተገድለዋል። ታርደዋል። በባህር ዳር አንድ የሕወሃት ታጣቂ፣ ከሶስተኛ ፎቅ ኮንዶሚነይም ቢያንስ 48 የባህር ዳር ወጣቶችን ገድሏል። በጎንደር አሁንም የሕወሃት ካድሬ መለስ ዜናዊ በሞተበት ቀን ለምን የጎንደር ሕዝብ ነጭ ለበሰ በሚል፣ በአልሞ ተኳሽ መሳሪያ ሰላማዊ ዜጎችን ጥሏል። የትግራይ ህዝብ ከተቀረው ኢትዮጵያዊ ወገኑ ጋር በመሆኑ ፣ የሌላው ማሀብረሰብ ወጣቶች ደም የርሱም ደም እንደሆነ በመግልጽ ተቃዉሞዉን ማሰማት አለበት። የትግራይ ህዝብ መነሳት በእጅጉ ህወሃት የረጨውን መርዘ የማምከን ትልቅ አቅማና ጉልበት አለውና።

ለተቀረነው ኢትዮጵያውይን ደግሞ በድጋሚ ጥሪዬና አቅርባለሁ። አዎን ሕወሃቶች ትግሬዎች ናቸው። ግን ትግሬዎች በሙሉ ህወሃቶች አይደሉም። በሕወሃቶች እየተደረገ ያለው እንኳን ሰዎችን መልአኮችንም ወደ ጥላቻ የሚወስድ ነው። ይገባኛል ያለው ንዴትና ምሬት። ግን ንዴታችንና ምሬታችንን ዋናው የአገር ነቀርሳ ላይ ማድረግ ነው ያለብን።