የአለም አብያተ ክርስቲያናት ም/ቤት ውይይት እንዲደረግ ጠየቀ

የጀርመን የውጭ ጉዳይ ሚ/ር ህገ-መንግስታዊ መብቶች ይከበሩ ብሏል

woyane -9 satenaw  የአለም አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት ባለፉት ሳምንታት በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች ለተቀሰቀሱ ተቃውሞዎችና ውጥረቶች ምክንያት በሆኑ ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት እንዲያደርጉ ለኢትዮጵያ መንግስት፣ ለጸጥታ ሃይሎችና ለተቃዋሚዎች ጥሪ አቀረበ፡፡

በኢትዮጵያ የሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት መሪዎች በላኩልኝ መረጃ፣ ተቃውሞውን ተከትሎ በአገሪቱ የተፈጠረው ውጥረት አሁንም አለመርገቡንና በተቃዋሚዎችና በጸጥታ ሃይሎች መካከል የሚከሰቱ ግጭቶች እንደቀጠሉ መሆናቸውን ተገንዝቤያለሁ ብሏል – ምክር ቤቱ ትናንት ባወጣው መግለጫ፡፡ የፀጥታ ሃይሎች ባልታጠቁ ዜጎች ላይ ተመጣጣኝ ያልሆነ ሃይል እንዳይጠቀሙ የጠየቀው ምክር ቤቱ፣  ተቃዋሚዎችም ለግጭቱ መንስኤ በሆኑ ጉዳዮች ዙሪያ ከመንግስት ጋር ግልጽ ውይይት የሚደረግበትን መንገድ መሻት አለባቸው ብሏል፡፡
“በተቃውሞዎቹ ለህልፈተ ህይወት በተዳረጉት ዜጎች እንዲሁም በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በተቃዋሚዎች ላይ በተፈጸመው እስርና ድብደባ ማዘናችንን እንገልጻለን” ብለዋል፣ የምክር ቤቱ የአለማቀፍ ጉዳዮች ኮሚሽን ዳይሬክተር ፒተር ፕሮቭ፡፡

በጀርመን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የሰብዓዊ መብቶች ፖሊሲና እርዳታ ኮሚሽነር ባረቤል ኮፍለር በበኩላቸው ባለፈው ረቡዕ ባወጡት መግለጫ፣ በአገሪቱ የተከሰቱት ግጭቶች በእጅጉ እንደሚያሳስቧቸው ጠቁመው፣ ሁሉም ወገኖች ከቀጣይ ግጭቶች እንዲታቀቡና በውይይት ችግሮችን በጋራ እንዲፈቱ ጠይቀዋል፡፡
የአገሪቱ ህገ- መንግስት ለዜጎች ያጎናጸፋቸው ሃሳብን በነጻነት መግለጽና ሰላማዊ ሰልፍ ማድረግን የመሳሰሉ መብቶች መከበር አለባቸው ያሉት ኮሚሽነሩ፤ የጸጥታ ሃይሎች በተቃዋሚዎች ላይ የወሰዷቸው እርምጃዎችም የተመጣጣኝነት መርህን መጣስ አልነበረባቸውም ብለዋል፡፡

ምንጭ – አዲስ አድማስ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.