እጅግ በጣም አስቸኳይ መልእክት   [ብሥራት ደረሰ]

Ethiopia - Satenawበአሁኒቷ ቅጽበት በዐማራው አካባቢ ሕዝቡ ከወያኔ ታጣቂዎች ጋር በባዶ እጁ እየተፋለመ ይገኛል፡፡ ይህ ለዓመታት ታፍኖ የነበረ የነፃነት ጥያቄ ወቅቱን ጠብቆ አሁን በቅርብ ከሞላ ጎደል በሁሉም የጎጃምና የጎንደር አካባቢዎች ፈንድቷል፡፡ ይህ የሚያሳየው ጭቆናና ምሬት በኃይል ታፍኖ ሊቀር የማይችል መሆኑን ነው፡፡

ይሁንና ነፃነት የጠማው የኢትዮጵያ ሕዝብ በጎሣና በሃይማኖት ተወስኖ የአንዱ ንቅናቄ ለሌላኛው ባይተዋር ሊሆን እንደማይገባ ሁላችንም ማሰብ ይኖርብናል፡፡ እርግጥ ነው እስካሁን ስህተቶች አልነበሩም አንልም፡፡ ንስሃ ልንገባባቸውና ይቅርታ ልንባባልባቸው የሚገቡ ስህተቶችን ሁላችንም ስንሠራ ለመቆየታችን ትልቁ ማስረጃ የወያኔ ሥልጣን ላይ ለ25 ዓመታት ተገሽሮ ሁላችንንም ሲቀጠቅጥ መቆየቱ ነው፡፡ ብንተባበር ኖሮ 25 ዓመታትን ቀርቶ 25 ቀናትንም አራት ኪሎ ምንሊክ ቤተ መንግሥት ውስጥ ወያኔ አይቆይም ነበር – ታሪካዊ ፀፀት፡፡

ስህተት አንድ – ሙስሊሙ ማኅበረሰብ የመብት ጥያቄ አንስቶ ብቻውን ሲታገል ሌላው በአብዛኛው በታዛቢ ወንበር ላይ ተቀምጦ ነበር፡፡ ያ ትልቅ ስህተት ነበር፡፡ እርግጥ ነው የሙስሊሙን ጥያቄ ከሃይማኖት አውጥቶ ወደ አጠቃላይና ሁሉንም ሊያቅፍ ወደሚችል የመታገያ መስመር ማስገባት ይቻል እንደነበር ብንጠቁም አግባብ ነው፡፡ ጥያቄዎችን ከማጥበብ ይልቅ ማስፋትና ሁሉንም አሳታፊ እንዲሆኑ ማድረግ ይገባል፤ ይቻላልም፡፡ ጠባብ ጥያቄዎችን መጠየቅ ለወያኔዎች የተናጠል ብትር ይዳርጋል፤ ማንም ደግሞ በተናጠል ጥያቄዎች ድልን ሊቀዳጅ አይችልም፡፡ በትልቅ ጥያቄ ፍቺ ውስጥ ብዙ ትንንሽ ጥያቄዎች ሊፈቱ እንደሚችሉ ባለመረዳት ወይም ለመረዳት ባለመፈለግ ብዙ ዘመን ተሞኝተናል – በዚህም ሰበብ ለወያኔ ምቹ ፈረስና መጋጃ ሆነን ለብዙ ዘመን ባጅተናል፡፡ ይህን ሞኝነታችንን ተረድተን ባፋጣኝ ካልተስተካከልን የሰሞኑ እንቅስቃሴም ከጊዜያዊ ጫጫታነት አያልፍም፡፡

ስህተት ሁለት – ኦሮሞ ኢትዮጵያውያን በተለይ ከዚህ ዓመት(2008) መባቻ ጀምሮ በየአካባቢያቸው ሰላማዊ ተቃውሞ ሲያደርጉና በወያኔ ቅልብ የአጋዚ ጦር እንደዐይጥ ሲጨፈጨፉ ሌላው ዳር ቆሞ ይታዘብ ነበር – የወንድሞቹ ቁስል አልተሰማውም ማለት ግን አይደለም፡፡ ለወያኔ የከፋፍለህ ግዛ ሥልት ተንበርክከን ራሳችንን በየግል ቋጠሮ በማስቀመጣችን ግን አልተባበርንም፤ በዚያም ምክንያት ወያኔ ተመቸውና በተናጠል መደቆሱን ቀጠለ፡፡ አሁንም እርግጥ ነው – የኦሮሞዎችን ጥያቄ ከኦሮሞ ግዛት መጥበብና መስፋት ጋር ብቻ ከማያያዝ ይልቅ እሱን በእርሾነት ይዞ ለትልቁ ሀገራዊ ነፃነት ሁሉም በአንድነት እንዲነሣ ቢደረግ ኖሮ ይሄኔ ይሄ በየአካባቢው የሚደረግ የቁጥ ቁጥ ትግል ባላስፈለገ ነበር፡፡ ይህችን ሒሣባዊ ቀመር እንዴት ማወቅ እንዳልቻልን ሳስበው ይገርመኛል፡፡ ጥቂት ወያኔዎች በአእምሮ ማለትም በተንኮል በተካነ አእምሮ በመቶ ሚሊዮን የሚቆጠር ሕዝብ ይህን ያህል እንዴት ሊበልጡ እንደቻሉ ሳስበውም እንደዚሁ ይደንቀኛል፡፡ በምን አፈዘዙን?

ስህተት ሦስት – ሰሞኑን የዐማራው ሕዝብ ፀረ ወያኔ እንቅስቀሴውን ጀምሯል፡፡ የዘገዬ ቢሆንም ጅምሩ መልካም ነው፡፡ ሆኖም በተለይ በመነሻው አካባቢ ጥያቄው ልክ እንደላይኞቹ ሁሉ ጠበበና ወይም የሚጠበቀውን ያህል ሌሎችን አሳታፊ ሆኖ የተገኘ አልሆነምና ከክልሉ ውጪ ያሉትን ለመሳብ አቅም ያነሰው መሰለ፡፡ ጎንደር ላይ “የኦሮሞ ወንድሞቻችን ደም የኛም ደም ነው” በሚል ሕዝቡ በራሱ ተነሳሽነት የኦሮሞ ወንድምና እህቶቹን ሰማዕትነት ማስታወሱ አዲስ ምዕራፍ ከፍቶ ሁለቱን የወያኔ መጫወቻ ታላላቅ ብሔሮች (በእስካሁኑ ሁኔታ ማለቴ ነው) ቢያቀራርብም አሁንም ብዙ የሚቀረው ነገር እንዳለ መገንዘብ ይገባል፡፡ ወያኔዎችና ተባባሪዎቻቸው ለዘመናት የሠሩት ዕኩይ ተግባር በአንድና በሁለት የተቃውሞ ሰልፎች የሚናድ እንዳልሆነ መገንዘብ ተገቢ ነው፡፡ ሁለትም ይሁኑ ከዚያ በላይ ትልልቅ ግንዶችን የሚያሸንፍ ቅርንጫፍ – ቅርንጫፉ ምንም ያህል ቀጭንና ላንቁሶም ይሁን – የግንዶቹን ሥሮች እንደምሥጥ እምሽክ አድርጎ በመብላት ግንዶቹን ከናካቴው ሊያጠፋቸው እንደሚችል እስካሁን ማንም አልተረዳም፡፡ ታላላቆችን ለማጥፋት ደግሞ አካላዊ ግዝፈት የግድ አይደለም – ብልጠትና መሠሪነት ብቻቸውን ብዙ ሚና ይጫወታሉ – በዚያ ላይ መካሪና ሁለገብ ረድኤት የሚሰጥ አጋዥ ኃይል ካለ አናሳዎች የጥፋት መንገዳቸው ቀኝ በቀኝ ነው የሚሆንላቸው፡፡ በዓለም 14.2 ሚሊዮን አካባቢ የሕዝብ ቁጥር ያላት እስራኤል የዓለምን ፖለቲካና ኢኮኖሚ በተቆጣጠሩ ምርጥ የኅቡኣን ድርጅቶች አባላት ልጆቿ አማካይነት የሰባት ቢሊዮኑን የዓለም ሕዝብ የዕለት ተለት ሕይወትና እስትንፋስ እንደምትቆጣጠርና እንደምትወስንም ለሚረዳ ዜጋ ከስድስት ሚሊዮን የፈለቁ ጥቂት አሰለጦች ከውጪ ረዳቶቻቸው ጋር ተዓምር አይሠሩም ብሎ መገመት ሞኝነት ነው፡፡ ብዛት ብቻውን አይጠቅምም – በራሱ ዋጋቢስ ነው፤ እንዲያውም ብዛት ያጃጅላል ይመስለኛል፡፡ የሌለህን እንዳለህ፣ ያልሆንከውን እንደሆንክ በሥነ ልቦና ጥጋብ እያሰከረ ተጠቂ ያደርግሃል – ብዛት፡፡ ስታንስ ግን ጠርጣራና ፈሪ ያደርግህና ከቢጤዎችህ ጋር እያቆራኘ – እንደሙጫ እያጣበቀ – ብዙ ትንግርት እንድትሠራ ያደርግሃል – ጥቂትነት፡፡ ዕድሜ ደጉ… ማንበብም ደጉ… ከብዙው ጥቂቱን አየን፡፡

ከቅርብ ቀናት ወዲህ የዐማራው ጥያቄ ለአጠቃላዩ ሀገራዊ ነፃነት የጥሪ ደወል ማሰማት ቢጀምርም ከፍ ሲል እንደተገለጸው በመነሻው አካባቢ በወልቃይት ዙሪያ ያጠነጥን ስለነበር ያ ጥያቄ ለጋሙጎፋውና ለአፋሩ ሩቅ መስሎ ሊታይ ቢችል አያስወቅስም ባይ ነኝ፤ ጥያቄው ሁሉን ቆንጣጭ ነበር ለማለት አያስደፍርም፡፡ አሁን መስተካከሉና ብሔራዊ አጀንዳ መያዙ ግን ደግ ነው፡፡ መስተካከሉን አምነን ታዲያ እንቀላቀለው፡፡ ምክንያቱም የዋናው ድል መቋጫ በዋናነት አዲስ አበባን ጨምሮ የሁሉም ሕዝብ ንቁ ተሣትፎ ነውና፡፡

ስህተት አራት – የዐማራው ጥያቄ ከጎጥና ከሸጥ አልፎ ሀገራዊ ቅርጽ ከያዘም በኋላ የመላዋ ኢትዮጵያ ሕዝብ ለጋራ ሀገራዊና ብሔራዊ ነፃነቱ በአንድነት “ሆ!” ብሎ እንዳይነሣ ያደረገው ነገር አለ፡፡ ይህን ነገር ሁነኛ የፖለቲካ ቡድች በአፋጣኝ አጥንተው መፍትሔ ካልተፈለገለት ይሄ አንዴ ወለጋ ሌላ ጊዜ ጎንደር የሚደረግ ሕዝባዊ የእምቢተኝነት ዐመፅና የነፃነት ትግል የትም አይደርስም፡፡ አዎ፣ የትም! ለሕወሓት ግን ሠርግና ምላሽ ነው፡፡ ለዚህ ጎጠኛ የአናሳዎች ቡድን መሠሪ ተንኮል መሸነፍ ይብቃን፡፡

ነፃነት ቆራጥነትንና እልህን ትፈልጋለች፡፡ ነፃነት ሸረኝነትና ተንኮልን ያዘለ ፉክክርን አትሻም – የነፃነት ፍልሚያ ውጤታማ እንዲሆን በቀናነትና በእኔ እብስ አንተ ትብስ የጋራ መግባባትና መተሳሰብ መቃኘት አለበት፡፡ ሁሉም እንደየአቅሙ በስሜትና በከፍተኛ ወኔ ከተሳተፈ የነፃነት ቀን ቅርብ ናት፡፡ ነገር ግን “ቆይ እነእንትና ይለይላቸው፣ እነሱ ሲያዳክሟቸው እኛ እንቀጥልና የመጨረሻ ግብኣተ መሬታቸውን እናሳያቸዋለን…” በሚል የማይረባ ሥልት በተናጠል መጓዝ ካለ መቼም ቢሆን ነፃነት አትገኝም፡፡ ነፃነት በእልህ አስጨራሽ የጋራ ትግል እንጂ በብልጣብልጥነትና ከጋራ ትግል በመሸሽ ልትገኝ አትችልም፡፡ በአንዱ ሞት ሌላው ነፃ እንዲወጣ ተደብቆ ወይ አሸምቆ ቢጠባበቅ ደግሞ ከኅሊናም ከሃይማኖትም አንጻር ወንጀልና ኃጢኣትም ነው፡፡ ሁሉም የድርሻውን ይወጣ፡፡ “ማን ይጠይቀኛል? ማንስ ያየኛል?” የሚሉት ጥያቄዎችም የጅል ፈሊጦች ናቸው፤ በመጀመሪያ ዋናው ጠያቂ ኅሊናችንና የሚሰውት ወገኖቻችን ነፍሳት ናቸው፡፡ ከዚህ ነጥብ አኳያ ሁሉም ዐይን ነውና እንዳንታለል፡፡

ስህተትን ለማስወገድ እንዲህ ቢደረግ ጥሩ ይመስለኛል፡-

ኦሮሞው፣ ዐማራውና ሌላው ጎሣ ሁሉ በተጀመረው መንገድ ለአንድ ዓላማ ይተባበር፡፡ የተናጠል ትግል የትም እንደማያደርስም ከልምድ ይረዳ፡፡ ጠላት አንድ ነው፡፡ የጥቃቱ ሰለባዎችም አንድ ናቸው ወይም ቢያንስ አንድ መሆናቸውን ሊረዱ ይገባቸዋል፡፡ ራሳቸውን እየለያዩ በተለያዬ ጊዜ ከሚጠቁ በአንድነት ተባብረው ከዘላለም ባርነት በአንዲት ጀምበር የዘላለም ነፃነታቸውን መጎናጸፍ ይችላሉ፡፡ እንደእስከዛሬው በመለያየትና የመቃብር ጉድጓድ እየቆፈሩ በዐፅምና ባለፉ ሰዎች የታሪክ ጠባሳ የሚጃጃሉ ከሆነ ግን ልክ  እንደስካሁኑ ለጠላታቸው ምቹ እንደሆኑ አንዱ ምዕተ ዓመት አልፎ ሌላው ይተካል፡፡ በሰው ሠራሽና በጠላት-ጠመድ የልዩነት ቦምቦች ፍንዳታ ጊዜያቸውን በከንቱ ማባከን የለባቸውም፡፡ ከዚህ ሞኝነታቸው ተምረው ብልኅነትን ገንዘባቸው ያድርጉ፡፡

ለምሣሌ የቋንቋና የሰንደቅ ዓላማ ልዩነቶች ወደ ውስጥ ገብተው ካጤኗቸው መሠረታዊ ችግሮች አይደሉም፡፡ ያገሬ ባላገርና ሕጻናት ልጆቹ በሕወሓት አልሞ ተኳሾች ጭንቅላታቸው እየተበተነ በቀያቸው ሥጋቸውን አሞራና ውሻ እየጎተተው ሳለ፣ ሕወሓት ኑሯችንን አመሰቃቅሎና ሰብኣዊ ተፈጥሯችንንም  ከእንስሳነትም በታች አውርዶ በነፍስ ውጪ ነፍስ ግቢ የሰቀቀን ኑሮ እየገፋን ሳለ፣ እትብቴ በተቀበረባት የገዛ ምድሬ እኔን ለመንግሥት ሥራ መቅጠሩ እንደቅንጦትና ብርቅ ይቆጠርና እንደህንድ የካስት ሲስተም ሊጨብጡኝ እንኳን እየተፀየፉኝ በምገኝበት ሁኔታ … ፖለቲከኞች ሚዛን በማይደፉ የአዛኝ ቅቤ አንጓች ዓይነት ጉንጭ አልፋ ክርክሮች ቢጠመዱ ሕዝብና ታሪክ ይቅር የማይሉት ሌላ ስህተት ነው – “ቀድሞ የመቀመጫየን” ብላለች ዝንጀሮ፡፡ ከሌላው እንቶፈንቶ ይልቅ የተበላሸን በማቃናት፣ የተሳሳተን በማረም፣ የተዛነፈን በማስተካከል … ወደ ደገኛው መንገድ እንግባና እንደቀድሟችን በቶሎ አንድ ብንሆን ሁላችን እንጠቀማለን፤ ሌላው ቀስ ብሎ ይደረስበታል፡፡

ሞኝነትንና ብልጣብልጥነትን አርቆ መቅበር ይገባል፡፡ ይህን በሕዝብ ደምና አጥንት ላይ የቆመ ከፋፋይ የወያኔ ብልሹ ሥርዓት ከሥሩ መንግሎ ከነሰንኮፉ ለመጣል ሁሉም “ሆ!” ብሎ በአንድ ወቅት መነሣት አማራጭ የሌለው የጊዜው አንብጋቢ ጉዳይ ነው – ከዳር እዳር ተነጋግሮና በጥሞና ተመካክሮ በአንድ ወቅት መነሣት!! ጎጃም የሚፈሰው ደም የአርሲው ነው፤ ወለጋ የሚፈሰው ደም የጎንደሬው ነው፡፡ የወያኔን ሤራ በጣጥሰው ካልጣሉና ሰሞኑን በተጀመረው የአንድነት መንፈስ ካልታገሉ ማንም ነፃ ሣይወጣ የወያኔ አሽከርና ደንገጡር ሆኖ የመከራ ኑሮን መግፋት ነው – እስከወዲያኛው፡፡ መጥፎ ህልም ስታልም መፍትሔው ከእንቅልፍህ መንቃት ነው – ከወያኔ ሰቆቃ ለመዳንም መፍትሔው በከፋፋይ ሤራው ላይ የማያዳግም እርምጃ ወስዶ ኅብረትን ማጽናት ነው፡፡

ያለፈ አልፏል፡፡ “ላለፈ ክረምት ቤት አይሠራም”፡፡ በእጃችን ያለችዋ ጊዜ ናት ወርቃማ ጊዜያችን፡፡ ወንድሞቻችን በጎጃምና በጎንደር እየተዋደቁ በወሎና በሸዋ እንዲሁም በአዋሣና በጋሙጎፋ የሚገኝ ሕዝብ ተኝቶ እንቅልፉን የሚደቃ ከሆነ የምትጠበቀዋ ነፃነት ቅዠት ናት – አትገኝም፡፡ ጎንደርና ባህር ዳር እየታመሱ አዲስ አበባና ናዝሬት በአሥረሽ ምቺው “ዓለማቸውን የሚቀጩ” ከሆነ የነበረችን አነስተኛ በሕይወት የመቆየት ነፃነት ራሷ ወደለዬለት ባርነት ትለወጥና ትልቁ እሥር ቤታችን – ዞን ዘጠኝ – ወደማዕከላዊ የወያኔ የ”ወንጀል ምርመራ” ዘብጥያነት ይለወጣል፡፡ ለዚህም ነው “የነብርን ጅራት አይዙም…” የሚባለው፡፡ ወያኔና የቆሰለ ነብር አንድ ናቸው፡፡ የወያኔን ተፈጥሯዊ የበቀለኛነት ስሜት አዲስ አበቤዎች በተለይ ጠንቅቀን እናውቀዋለን፡፡ ከ97 ምርጫ በኋላ ምን እንደደረሰብን እንኳንስ እኛ ሌላው ዓለምም ያውቃል፡፡ ወያኔ በየጊዜው በደም ካልዋኘ ያስተበተበው ድግምት አይሠራለትም – ትልቁ የሰይጣን ምስ ወይም ግብር ደግሞ ደም ነው፡፡ ለዚህም ነው በበቀል የሰከሩት ወያኔዎች በተለይ ዐማራውንም ሆነ ሌላውን – ዓላማቸውን የማይደግፍና የሚቃወማቸውን ትግሬም ሳይቀር – አዛዣቸው ዲያብሎስ በሉ ባላቸው ቁጥር ባልተወለደ አንጀታቸው ጭንቅል ጭንቅሉን እያሉ ለአባታቸው የሚገብሩት፡፡ እነሱ ካልጠፉ ሞታችንና አሟሟታችን እየከፋ እንጂ እየቀነሰ አይሄድም፡፡ በሰይጣን የቆረበ ሰው የተጎጂዎች አበቅቴ እስኪብት ድረስ ዘመኑ ከሚፈቅድለት የወንጀል ድርጊት ውጪ ሌላ ደግ ነገር ይሠራል ተብሎ አይጠበቅም – የባሕርዩ መገለጫ ክፋት ብቻ ነውና፡፡

ምርጫው የኛ ነው እንግዲህ፡፡ በሕዝብ መተባበር ወያኔዎች ሰሞኑን ደንግጠዋል፡፡ የድንጋጤያቸው ደረጃም ሱሪያቸው ከፊትም ከኋላም እስኪረጥብ ድረስ መሆኑን ምሥጢሩን የሚያዉቁ እየተናገሩ ነው፡፡ ይህን በጥርጣሬ ደረጃ ያለ የወያኔ መረጣጠብ ማፋጠንና የዚህን ሰው-በላ የአፓርታይድ ሥርዓት ዕድሜ በደቂቃዎች እንዲገመት ማድረግ ይቻላል፡፡ እንደዚያ የሚሆነው ግን የተጨቋኞች ዓላማና ፍላጎት አንድ ሆኖ ሁሉም በያለበት ወያኔን ሲያርበደብድ እንጂ አንዱ ከነሱ ጋር ማኪያቶ እየጠጣና ውስኪ እየጨለጠ፣ ሌላው ደግሞ በአልሞ ተኳሾች ልዩ ጥይት ጭንቅቱ እየፈረሰ አይደለም፡፡ አሁንም እርግጥ ነው – ኢትዮጵያ ኢያሪኮ እንዳልሆነች ልብ ይሏል፡፡ የኢትዮጵያ ነፃነት ካለደም እንደማትገኝ የጎንደርና የጎጃም ዐማሮች እያስመሰከሩ ነው፤ ከወያኔ ተፈጥሮ የምንረዳውም የኢትዮጵያ ሕዝብ ሙሉ በሙሉ ያልቃታል እንጂ ወያኔዎች ፈረንጆቹ ዴሞክራሲ በሚሉት ቀልድ ወይም በሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር ቤተ መንግሥት እንደማይለቁ ግልጽ ነው፡፡ ስለሆነም የነሱን ፈለግ በመከተል ሁሉም በተቻለው መፋለም ይገባዋል እንጂ በጩኸት ብቻ ወያኔ አራት ኪሎን ይለቃል ማለት ዘበት ነው፡፡ የዓለም ገዢ ኃይልም ከነርሱ ጋር ስለሆነ ሰሞነኛው ጩኸታችን ቀርቶ የገፍ ዕልቂታችን እንኳን ተገቢውን ዓለም አቀፍ ትኩረት አላገኘም – ማን እንደሰው ቆጥሮን! ይሄኔ የሮበርት ሙጋቤ የክብር ዘብ የአንድ ነጭ ዚምባብዌያዊ የሣሎን ውሻን በባረቀ ጥይት አቁስሎ ቢሆን ኖሮ የነቢቢሲና ሲኤንኤን እንዲሁም የነስካይኒውስና አልጀዚራ ቲቪዎች የአንድ ሣምንት የመክፈቻ ዜና በሆነ ነበር፤ ዘርንና ምጣኔ ሀብትን መሠረት ባደረገ መልክ ዓለም ይህን ያህል አሽቃባጭ ናትና ወደ አምላካችን ብቻ እንጩህ ይልቁንስ፡፡ ከሰው ምንም አንጠብቅ፡፡ ከራሳችን ውስጥ ብዙ ሥጋዊና መንፈሣዊ ኃይል አለ፡፡ ያን እናውጣውና እንጠቀምበት፡፡ ሕዝባችንንም እናንቃው፡፡ የምንችል እናስተምረው፡፡ ከተኛበትም እንቀስቅሰውና የጥንት የጧት አያት ቅድመ አያቶቹ የሠሩትን የመሰለ ታሪክ እንዲሠራ ለዳግም ልደት እናብቃው፡፡…

ልብ ያለው ልብ ይበል፡፡

ሕዝቡ ማናቸውንም ዓይነት ፖለቲከኛ በልጦ ሄዷል – ወያኔንም ተቃዋሚንም፡፡ ወያኔ ተጎልቶ ያለው ከ41 ዓመታት በፊት በነበረበት ደደቢት ላይ ነው – ሰውነታቸው በዐማራና በኦርቶዶክስ ሃይማኖት ጥላቻ እንደተሞላና ገድሎ በማይረካ የበቀል ስሜት እንደተምቦገቦገ፡፡ ተቃዋሚዎች ያሉት የዛሬ 160 ዓመታት ገደማ ኢትዮጵያ የነበረችበት የዘመነ መሣፍንት ወቅት ላይ ነው – በማይጨበጥ ህልማዊ ሥልጣን እርስ በርስ ሲራኮቱ፡፡ ከሞላ ጎደል ሁሉም አእምሮውን የነሣው ነገር አለ፤ ሆድ ይሁን የዝናና የታዋቂነት ልክፍት በውል ለይቼ አላውቅም፡፡ ግን ግን አሁን እኔ እምለው ሁሉም ምናልባትም አብዛኛው ራሱን መፈተሸና ከሕዝብ የነፃነት ፍላጎትና የአርነት ትግል ጎን መሰለፍ የሚችልበትን ብልሃት ባፋጣኝ መቀየስ ይገባዋል ነው – በሕዝብ መበለጡን አውቆ ራሱን “ሳያስፎግር” በቶሎ ይስተካከል – በተቃዋሚነት እያምቧተሩና በሕዝብ ስም እየቀለዱ(እየነገዱም) መኖር ከእንግዲህ የሚታሰብ አይመስለኝም፡፡ አንዳንዱ ተቃዋሚ ይህን ዓይነት ሕዝብ የሚቀድምበትን የአጣብቂኝ ወቅት የጠበቀ አይመስልም – ለዚህም ነው ተደናግጦና ፈዝዞ ጥግ ጥጉን ይዞ እንደማንኛውም ተራ ዜጋ የነገሮችን አነሳስና ጡዘት እየታዘበ የሚገኘው፡፡ በየተወሰነ ወቅት ይሰጥ የነበረው መግለጫና ፉከራ(ፉገራም ቢባል ያስኬዳል) እንግዲህ ለላንቲካው ነበር ማለት ነው፡፡ አዎ፣ ትዝብትንና ምን ይሉኝን ዕንወቅ፡፡ እንደካሮት ወደታች ሣይሆን እንደሸምበቆ ወደላይ እንደግ፡፡ የአእምሮ መካንነትን እንዋጋና ጤናማ ሰው እንሁን፡፡ ያኔ ሀገራችን ትነሣለች፡፡

… ብዙ ማሰብ፣ ብዙ መሥራት፣ መጥፎ ነገሮችን መርሳት፣ ደጋግ ነገሮች ማስታወስ፣ ፍቅርንና አንድነትን መዘከር፣ ቂምንና በቀልን እርግፍ አድርጎ መተው፣ ወንድማማችነትን መስበክ፣ ጎሠኝነትን መጠየፍ፣ ሰውኛነትን ማጉላት፣ ከሕዝብ መማር፣ በሌሎች ወንጀል ንጹሕን ሰው ከመጠየቅና በሌሎች ደግ ሥራና ምሥጉን ትውፊት ምንም ያልሠሩ ሰነፎችን ማወደስን መተው፣ … በቃ … ባጭሩ ጤናማ ኅሊና ያለው ሰው መሆን …. የሁሉንም ችግር እንደራስ ችግር መቁጠር፣ የሁሉንም የነፃነት ትግል እንደራስ ትግል አምኖ በጋራ መታገል፣ ያንደኛው መክሸፍ የሌላኛውም መክሸፍ መሆኑን ከልብ መገንዘብና የጋራ ኃላፊነትን መውሰድ … ከሌሎች ብዙ አለመጠበቅ፣ የራስንም ድርሻ መወጣት … በገንዘብም በጉልበትም በዕውቀትም በጊዜም … አቅም በቻለ ሁሉ ለዚህች የጋራ ሀገራችን መስዋዕትነትን መክፈል፣ ካለመስዋዕትነት ነፃነት እንደማይገኝ መረዳት…ነፃነት እንደቡና ቁርስ ከሙዳይ ተቆንጥራ የምትሰጥ የዳቦ ፍርፋሪ ወይም ጭብጥ ቆሎ ሣትሆን የደምና የአጥንት ግብር የምትጠይቅ መሆኗን አምኖ ለሚፈለገው ግዳጅ ሁሉ ራስን ማዘጋጀት …ገና ለገና ሥልጣን አገኝ ይሆናል በሚል ከመጠን በላይና ለትዝብት በሚዳርግ ሁኔታ በሥልጣን ሱስ/አራራ አለመስገብገብ … ከሁሉም በላይ በሕዝብ የሥልጣን ባለቤትነት ማመን … ፡፡ ወቅቱ የክተት ነው፡፡ ዐጤ ምንሊክ ወደ ዐድዋ ሲዘምቱ በዘርና በጎሣ የተከፋፈለ የውጊያ ጥሪ አላደረጉም – ይህን ዓይነት ሸንካላ ወያኔያዊ አካሄድ አያውቁትምም ነበር፡፡ ባጠፋሁ ይቅርታ … በስሜት ስትናገሪ የምታስቀይሚው ሰው ይኖራል መቼም፡፡ … ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር፡፡ ለአሁኑ በቃኝ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.