አሳዛኙ የኦሮምኛ ተናጋሪው ሕዝብ፣ ይህ ሕዝብ አሁንም ለቀጣይ ባርነት ለገበያ ቀርቧል [ሰርጸ ደስታ]

Ethiopians wearing traditional Oromo cos...Ethiopians wearing traditional Oromo costume ride to the Prime Minister's Palace to pay their respects in Addis Ababa on August 31, 2012. Ethiopian Prime Minister Meles Zenawi died on August 20, 2012. His body is lying in state in the city's Meskal square until his official funeral which will be on September 2, 2012. AFP PHOTO/ CARL DE SOUZACARL DE SOUZA/AFP/GettyImages

እባብ ሞኝን ሁለት ጊዜ ነደፈው አንዴ ተነዳፊው እባቡን ሳያይ ድንገት ነደፈው ሁለተኛ ጊዜ ደግሞ ከጓደኛው ጋር መንገድ እየሄዱ የተጠቀለለ እባብ ያይና ያ ባለፈው የነደፈኝ ነገር ይሄውልህ ብሎ በጣቱ እየነካ ለጓደኛው ሲያሳይ ነደፈው ይባላል፡፡ እኔ እስከዛሬ በጻፍኩዋቸው በርካታ ለሕዝብ የቀረቡ አስተያየቶቼ የኦሮምኛ ተናጋሪውን ሕዝብ ያላነሳሁበት ያለ አይመስለኝም፡፡ ለዚህ ደግሞ ዋናው ምክነያቴ ይህ ሕዝብ ኢትዮጵያን እንደ አገር ለማስቀጠል ወሳኝ እንደሆነና በኢትዮጵያ ጠላት በሆኑት ወያኔና አጋሮቹ (የኦሮሞ ነን የሚሉ ድርጅቶች) ይሄን ሕዝብ ኢትዮጵያዊነቱን በማስጣል እስከማዕዜኑ አቀመቢስና የባዘነ በማድረገ በተገዥነት ዝም ብሎ እንዲቀጥል ለማድረግ የሄዱባቸውን ሴራዎች ሁሉ ስለምረዳ ነው፡፡ እኔም ብሆን የዝሕ ሕዝብ አንዱ አካል እነደመሆኔ ድሮ የነበረውንና አሁን ያለውን ወኔ ሳይ ምን ያህል አቅም እንዳጣ አያለሁ፡፡ ዛሬ ብዙ ማለት አልፈልግም፡፡ እየሆኑ ያሉትን ጉዳዮች እንደሚከተለው ልጥቀስ፡፡

  1. የአባ ገዳዎች ስብሰባና መንግስትን አውጋዥ የሚመስለው መስመሰያ

ሰሞኑን በሶደሬ አባ ገዳ ተብዬዎች ተሰብስበው መንግስት የሚያወግዝ የሚመስል መግለጫ ሲናገሩ ሰምቼ ይች ነገር ሆን ተብላ የተቀነባበረች እንደሆነች ጠረጠርኩ፡፡ ከወራት በፊት በጠ/ሚኒስቴሩ ፊት እጥፍ ዘርጋ በማለት የኦሮሞን ሕዝብ ትግል ለማርገብ ወያኔን በተላላኪነት ለማገልገል ተስማምተው እንደነበር እናስታውሳለን፡፡ አሁን ወያኔ ባዘጋጀላቸው ምቹ ቦታ እንዲያወግዙ ከወያኔ ከራሱ በተሰጣቸው የማስመሰል ሥራ ሕዝብን ከትግሉ ለማዘናጋት ከአንተ ጋር ነን ለማለት ቀላማጅ ውስጡ የክህደት የሆነውን ድምጻቸውን ሰምተናል፡፡ ማንም አምነም አላመነም ይሄ አሁን የኦሮሞን ሕዝ ለቀጣይ ባርነት ለገበያ ያቀረቡት የአንዱ ቡድን ሥራ ነው፡፡

  1. በውጭ የሚኖሩ የኦሮሞ ድርጅቶች መሪዎችና አክቲቪስቶች

ሌላው የኦሮሞን ሕዝብ በአክሲዮንነት ለሕወሐት የወሮበሎች ቡድን እያቀረቡ የሚገኙት በውጭ የሚኖሩ የኦሮሞ ፖለቲካ ድርጅቶች መሪዎች፣ ሰበዓዊ መብት ተከራካሪ ነን ባዮችና አክቲቪስቶች ናቸው፡፡ ከዚህ በፊተ በተደጋጋሚ ኦነግና መሰል በኦሮሞ ሕዝብ ሥም የሚነግዱ ድርጅት መሪዎች ምን ያህለ ከወያኔ ጋር በቅርበትና በድብቅ አብረው እንደሚሰሩ ለመጠቆም ሞክሪያለሁ፡፡ አሁን እየሆነ ያለው ከዚህ የተለየ ሳይሆን እስካሁን ከጥቅም ተካፋይ ያልሆኑትንና አኩርፈው ሲጮሁ የነበሩትን በማካተት ሁሉንም የሰብዓዊ መብት ተክራካሪ ነን የሚሉትን ሳይቀር ጠቀም ያለ ዳረጎት በመስጠት የኦሮሞን ሕዝብ በገንዘብ ለቀጣይ ባርነት ለመሸጥ ድርድር ላይ ናቸው፡፡ ወያኔ ዋጋው አያሳሰበውም ከኦሮሞ ሕዝብ ከዘረፈው ጠብታውን ለእነዚህ የኦሮምን ሕዝብ እንወክላለን ለሚሉ የተለያዩ አካላት በመስጠት ሰፊዎን ሕዝብ ለመግዛት ነው፡፡ በአንጻሩ የሕዝቡን መሠረታዊ መብት ለማስከበር እየተንቀሳቀሱ የሚገኙ የፖለቲካ ድርጅት መሪዎችን በማፈን በመግደልና በማሰር ትግላቸውን ማምከን የዚሁ ግብይት አንዱ አካል ነው፡፡ ለዚህ ዛሬ በእስር የሚገኙት እነ በቀለ ገርባና የድርጅታቸው አባላት ዋና ኢላማ ናቸው፡፡ ለመደራደር የማይፈልጉ ስለሆነ እንጂ እነሱም ተሳታፊ ቢሆኑ የወያኔው ቡድን የሚፈልገው ነው፡፡

  1. ኦሕዴድና አባላቱ

በአንጻሩ በአብዛኛው የኦሕዴድ አባላት አሁን አሁን በወያኔ ዘንድ ያላቸው አመኔታ እየተሸረሸረ ስለሆነ ወያኔ ትኩረት እያደረገ ያለው ለጥቅም አሰፍስፈው በሚገኙ አዳዲስ አባላትን በመመልመል አሮጌዎቹን ገለል በማድረግ ነው፡፡ አንዳነዶቹም የተዘጋጀላቸው የወያኔ የጭካኔ ፍዳ ይጠብቃቸዋል ምን አልባትም የተወሰኑት መገደልን ጨምሮ፡፡ እንዲህ ያለው ሂደት በአዴን በሚባለውም ይቀጥላል፡፡ ሆኖም በአዴን ተብዬው አሁን ባለው ሁኔታ የሚሳካ አይመስልም፡፡

ከላይ የጠቆምኩዋቸው ከሞላ ጎደል የኦሮሞን ሕዝብ በገንዘብ ለመሸጥ እየተደራደሩ ያሉ አካላትን ነው፡፡ ለድርድር ሥልትነት እየቀረቡ ያሉት ጉዳዮችን ስናስብ እጅግ እናዝናለን፡፡ ሁሉም እየቀረቡ ያሉት ጎዳዮች በልግስና የሚሰጡ ሳይሆኑ ሕዝቡ በራሱ ጊዜ የራሱ የትግል ውጤትና ማንም ስለፈቀደና ስላልፈቀደ ሳይሆን ሕዝቡ ራሱ በወሰነው በሚኖሩት መብቱ ላይ ነው፡፡  የሚከተሉት ጥቂቶቹ ናቸው፡፡

  1. ዛሬ በኦሮሚያ እየተደረገ ያለው ሕዝባዊ ተቃውሞና ጥያቄ ትክክል መሆኑን ማጽደቅ፡-

ይሄን አሁን በድጋሜ እንደ አዲስ ለማስመሰል የተነሳ መደለያ እንጂ ከዚህ በፊትም ጠ/ሚኒሰቴር ተብዬው መንግስት ለተፈጠረው ችግር ሙሉ በሙሉ ኃላፊነት እንደሚወስድ ሲደሰኩር እንደነበር እናስታውሳለን፡፡ ይህን በማዘናጊያነት በሚዲያ አስነግሮ ግን ጭራሽ በተጠናከረ ሁኔታ ነበር የህዝብን ልጆች መግደል፣ ማሰር፣ ማንገላቱን የቀጠለው፡፡ እባብ ሞኝን ሁለት ጊዜ ነደፈው እንደሚባለው ነው የአሁኑ፡፡ ባለፉት 10 ወራት የደሀው ሕዝብ ልጅ በሰላማዊ መልኩ ጥያቄ ስላቀረበ ምን ያህል ለሞት ለእስርና ለስደት እንደተዳረገ ቤቱ ይቁጠረው፡፡ ዛሬ ላይ ጥያቄው ትክክል መሆኑንና አለመሆኑን ወያየኔ እንዲነግረው ሳይሆን ሕዝብ የሚፈልገው ወያኔ  የተባለውን መርዝ ከስሩ መንቀል ብቻ እንደሆነ ቁርጠኝነት ባለበት ጊዜ ነው ሌላ ማዘናጋትን ወያኔ እየሞከረ ያለው፡፡ ቆይተን ውጤቱን እናየዋለን፡፡

  1. ኦሮምኛ የአገሪቱ ተጨማሪ ብሔራዊ ቋንቋ እንዲሆን መፍቀድ

ኦሮምኛን እንደ ብሔራዊ ቋንቋ ለመወጅ በአሁኑ ጊዜ የወያኔን ሥልጣን መወገድን የሚጠብቅ እንጂ ጭራሽ ወያኔ ለድርድር የሚያቀርበው ጉዳይ አይደለም፡፡ በእኔ አምነት ማንም ከዚህ በኋላ አገሪቱን እመራለሁ የሚል ኦሮምኛን እንደ ተጨማሪ ብሔራዊ ቋንቋነት ባይቀበል ነው የሚገርመኝ፡፡ ቋንቋው አስፈላጊነቱ ደግሞ ለኦሮሞ ሕዝብ ብቻ በሚል ሳይሆን ካለውም የማሕበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ አንጻር ነው፡፡ ያም ብቻ ሳይሆን አገሪቱ ውስጥ ያሉ ቋንቋዎች ሁሉ ራሱን የቻለ አንድ የመንግስት መዋቅር ተሰርቶላቸው ሊጠበቁ ይገባል ባይ ነኝ፡፡ የኦሮምኛ ብሔራዊ ቋንቋነትን አሁን ወያኔን እየተፈታተኑ ያሉ የፖለቲካ ድርጅቶች ተስማምተውበት በቀጣይ የኢትዮጵያ መንግስት ሕዝቡ በራሱ የሚያገኘው ሙሉ መብቱ እንጂ ወያኔ የሚሰጠው አይደለም፡፡

  1. የኦሮሚያ መንግስት በአዲስ አበባ የሚኖረውን ድርሻ ማስፋት

ይሄ ጉዳይ እኔን ሁሌም እንደሻከረኝ ያለ ፍትሀዊነትን ለመዛባት ወደዘረኝነት እንዲያዘምም ሆን ተብሎ የሚሰራበት አደገኛ ስሌት ነው፡፡ ከዚህም በላይ ሕዝብን ለከፍተኛ መደንዘዝ የዳረገ የሴረኞቹ እንጂ የአዲስ አበባ ጉዳይ ለኦሮሞ ሕዝብ የተለየ ተደርጎ መታየት ባልተገባው፡፡ ተወደደም ተጠላም አዲስ አበባ አሁን ባለው ሁኔት በኦሮሚያ አስተዳደር ተጽኖ ሥር መዋል የሚችል ከተማ አይደለም፡፡ እየተስፋፋ ያለው ወደ ኦሮምያ ነው የሚለውም ሙግት አይሰራም፡፡ ኦሮምያ ለኦሮሞዎች ለሚሉት ዛሬ ሕዝብን ለድርድር ለአቀረቡት አደገኛ የወያኔ አጋሮች ልዩ ሴራዊ አስተሳሰብ እንጂ የሕዝብ መሠረታዊ ጥያቄ አይደለም፡፡ የሕዝብ መሠረታዊ ጥያቄ ፍትሕ ነው! ኦሮምያም የኦሮሞዎች ብቻ አይደለም አዲስ አበባም በኦሮምያ ሥር አይደለም፡፡ ዶሮን ሲያታልሏት ካልሆነ በቀር፡፡ እውነታውን በትክክል እንረዳ፡፡ ይልቁንም የኦሮምያ መንግስት በክልሉ አንዷ የሆነችውን ከተማ መርጦ መቀመጫው ሊያደርግ ሲገባው አዲስ አበባ ውስጥ ተወትፎ መውጫ መግቢያውን ሕወሐቶች እንዲመሩት ተመቻችቷል፡፡ የመንግስቱ መቀመጫ ከአዲስ አበባ ውጭ ሆኖ ቢሆን አንደኛ የሚቀመጥባትን ከተማ ያለማል ሁለተኛ የውስጥ አስተዳደሩንም ከወያኔ ተጽኖ በተወሰነም ቢሆን ነጻ ማድረግ በቻለ፡፡ ዛሬ የበአማራው ክልል አመራሮች ተጽኖ ፈጣሪነት ምክነያት አንዱ ከወያኔ እለት ከእለት እይታ ገለል ብሎ 500ኪ.ሜ ላይ ባሕር-ዳር ላይ መከተሙ ነው፡፡ እግረ መንገዱም ከተማይቱን በማልማት፡፡ ሁሉም ክልሎች አነሰም በዛም ያለሙት የየራሳቸው ቢያንስ አንድ ከተማ አላቸው፡፡ ኦሮምያን ግን ተመልከቱ፡፡ ለጥቂት ጊዜ አዳማ በተዛወረ ጊዜ የነበረ የከተማይቱን እንቅስቃሴ መለወጥ እናስታውሳለን የቱንም ያህል አዳማ ከአላት አቀማመጥ የተነሳ በራሷም ማደግ የምትችል ብትሆንም፡፡ ሌሎችን የኦሮምያ ከተሞች ስታዩ ከሌሎች ክልልሎች አንጻር የሚያሳዝን ነው፡፡ የኦሮምያ መንግስት አዲስ አበባ መወተፍ ሌላው ችግር መሪዎቹ ክልሉን እንደ ክልላቸው በቁጭት የሚያለሙ ሳይሆኑ አዲስ አበባና ዙሪያዋ ባሉ ጥቅሞች የተተበተቡ እንዲሆኑ ዳርጓቸዋል፡፡

የኦሮምኛ ተናጋሪው ሕዝብ እንዴት ጥንካሬ አጣ?

ይህን ጥያቄ አስመልክቶ በርካታ የራሴን ግንዛቤዎች ለመጻፍ ሞክሪያለሁ፡፡ ዋናው ጉዳይ ግን ወያኔና አጋሮቹ አብዛኛውን የዚህን ሕዝብ ክፍል ከኢትዮጵያዊነቱ ስለአራቁት የባዘነ እንዲሆን በመደረጉ ነው፡፡ እንቅስቃሴሶቹም በአላማና ለወሳኝ መዳረሻ ሳይሆን ስሜተኝነት የበዛበት ብቻ ሆኖ እናየዋለን፡፡ ሴረኞቹ ይሄንን ስለተረዱ የሚጠቀሙበት ዋናው ስልትም የሕዝቡን በተለይም የወጣቱን ሥነ ልቦና እነሱ ራሳቸው ስለሰሩት በዛው መስመር ሥነ ልቦናውን መዘወር ነው፡፡ ኦሮምያ ለኦሮሞዎች አንዱ ለዚህ ሕዝብ የቀረበለት ነው፡፡ በተግባር የማይሆን ሆነ አልሆነም ለሕዝቡ ምንም የማይፈይድ ይልቁንም በሌሎች በጎሪጥ እንዲታይ የሚያደርገውን እንዲህ ያል ሀሳብ የሚያነጸባርቅና እንደነዚህ ባሉ ጉዳዮች አቅሙን እንዲጨረስ እየተደረገ ወሳኝ የሆኑትን መብቶቹን አሳልፎ ሰጥቷል:: የሚዘወረውም ለሴረኞቹ ፍቃድ እንጂ መሠረታዊ ለሆኑት ለራሱ ነጻነት እየሆነ አይደለም፡፡ ጠላቶቹን መረዳት አልቻለም፡፡ አሊያማ ነጻነቱን 10 ወር ሳይሆን በ10 ቀን የማግኘት ኃይል ሊኖረው በተገባ፡፡ ዛሬ በአማራ በሚባለው ክልል ያለው እንቅስቃሴ እንዲህ ወያኔን ያስጨነቀው ለቁርጥ አላማ የሚታገል ሕዝብ ስለበዛበት ነው እንጂ ሌላ ሚስጢር የለውም፡፡ መሞትማ ኦሮምያ ውስጥ ወያኔ ከገባ ጀምሮ ኦነግ ምናምን እየተባለ 25 ሙሉ እየተገደለ ነው፡፡ የኦነግ መሪዎች በአውሮፕላን ተሸኝተው በውጭ እየኖሩ ለወያኔ የቆርጥ ቀን መሳሪያነት እያገለገሉ እንደሆኑ ሳያውቅ የደሀ ልጅ በኦነግ ሥም ያልቃል፡፡ አሁንም ወያኔን ተጨማሪ በርከት ያለ ገንዘብ በመጠየቅ ሕዝቡን ለእርድና ለቀጣይ ባርነት እየተደራደሩበት የሚገኙት እነዚሁ በሥማቸው እየሞተላቸው ያሉት መሪ ተብዬዎች እንደሆኑ አይረዳም፡፡ በአንጸሩ ለራሱ ነጻነት ራሳቸውን ለሞትና እስር አሳልፈው የሰጡለትን ቁርጠኛ መሪዎቹን እምብዛም አያስታውስም፡፡ እነ በቀለ ገርባ ስለ ኦሮሞ ሕዝብ ብለው ለእስር እንደተዳረጉ ብናውቅም ሥማቸው ከፍ ብሎ እንዲነሳና ዋና የሕዝብ ሁሉ መነጋገሪያ የሆኑት ጎንደሬዎቹ አደባባይ ስማቸውን ይዘው የነጻነት ታጋይነታቸውን ስለአሳወቁ እንጂ የኦሮሞ ሕዝብ እነዚህን ቁርጠኛ መሪዎቹን ረስቶ ዛሬ ለሽያጭ እያደራደሩት ያሉትን አክቲቪስቶች ማምለክ በሚያስብል ሁኔት ሲያራግብ ነበር፡፡ እንቅስቃሴው ሁሉ በሚያዋጣና ስልታዊ ሳይሆን እነዚሁ ዛሬ እየተደራደሩበት የሚገኙ አካላት በሚሰጡት ትዕዛዝ ነበር፡፡ በዚህም በዙ የደሀ ልጅ አልቋል፡፡ ያናድዳል፡፡ ዛሬ በአማራው ክልል የምናየው እንቅስቃሴን የሚመሩት ስሜተኛ ወጣቶች አይደሉም፡፡ የበሰሉ የአገር ሽማግሌዎችም እንጂ፡፡ ወያኔ በአማራው ክልል የሚደረገው እንቅስቃሴ ከምንም በላይ ስላሳሰበው የኦሮምያውን ከመጤፍ እየቆጠረው ያለ አይመስልም፡፡ ምክነያቱም የኦሮምያውን እንቅስቃሴ ዝም ለማሰኘት እንቅስቃሴው በማን እጅ እንዳለና እነዚሁን አካላት አግኝቶ ዝም ካሰኛቸው ዝም እንደሚል ያውቀዋል፡፡ በኣማራው ክልል ብዙ ባንዳዎችን ቢያሰማራም እንደዛ ያለ እድል ስለሌለው እንቅስቃሴውን ለመግታት እራስ ምታት ሆኖበታል፡፡ በጥፊያውም እንደሚሆን አሳስቦታል፡፡ በጎንደሬዎቹ ምክነያት የተቀሰቀሰው በብዙ ኦሮሞዎች ዘንድ ተዳፍኖ የቆየውን ኢትዮጵያዊነት ዳግም ለማዳፈን ከፍተኛ ጥረት እየተደረግ ይገኛል፡፡ አማራና ኦሮሞ አንድ ሆነው ይቅርና ኦሮሞ ብቻውን በሙሉ ኢትዮጵያዊነት ቢነሳ በጥቂት ቀናት ወያኔ የሚባል አደገኛ ቡድን ነበር የሚል ታሪክ ማውራት በቻልን፡፡

በመሆኑም፣ 1) የኦሮምኛ ተናጋሪው ሕዝብ ምን አይነት ሴራ እየተሰራበት እንደሆነ እንዲረዳ፤ 2)የኦሮሞን ሕዝብ እየተደራደሩበት የሚገኙትን ሚስጢራቸውን ለሕዝብ በማሳወቅ ወያኔ ለተነቃ ስልት ስለማይከፍላቸው ከሚያገኙት ጥቅም ለማስተጓጎል፡፡ 3)ሕዝብ እውነተኛ መሪዎቹን በአትኩሮት እንዲያደምጥ፣ እንዲተባበር፣ 4) ሕዝብ በራሱ ሊያገኘው ለሚችል መብት እንጂ በልግስና የሚሰጠው መብት እደሌለ አውቆ አላማ ያለው እንቅስቃሴ ማድረግ አለበት፡፡

ሌሎች ወሳኝ ማስተዋል እንዲደረግባቸው የሚያስፈልጉ የወያኔ የክት አጋሮች  

  1. 1. ሻቢያ፡ ሌላው ሕዝብ ማወቅ ያለበት ሻቢና ወያኔ በተመሳሳይ በቁርጥ ቀን የሚተሳሰቡ አደገኛ ቡድኖች እንደሆኑ ነው፡፡ ለብዙዎች ይሄ ደራማ ላይገባቸው ይችላል፡፡ በብዙ ሰራዊት እልቂት የሚዋጉት ሻቢያና ወያኔ እንዲህ ያለ ወዳጅነት አላቸው ብሎ ማመን ይከብዳል፡፡ ጉዳዩ ግን በእርግጥም ጎንደሬዎቹ ያሉት ነው፡፡ ወያኔ የሻቢያ ተላላኪ ነው፡፡ 70 ሺና ከዚያም በላይ ያለቀበት የኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ኢሳያስን በእጅ ለመያስ የማያስችል አልነበረም፡፡ ሆን ተብሎ የሕዝብ ልጅ እንዲያልቅ በማድረግ በወቅቱ ኢሳያስን ከእንዲህ ያለው አደጋ ለመከላከል በመለስ ዜናዊ የተሸረበ ሴራ እንደነበር ለብዙዎች አይገባንም፡፡ ዋናውን አሰብን ይዞ መደራደር ሲቻል ሰምተናት የማናውቃት እንዲት ባድሜ የምትባል መንደር ትልቅ ጉዳይ ሆና እስከዛሬም ይዘፈንብናል፡፡

 

የቀድሞ ሕወሐት አባላትና በትግራይ ሕዝብ ሥም የተደራጁ ፓርቲዎች፡ ሌላው  ከሕወሐት የተሰናበቱ ጀነራሎች አስተያየት በሚል ሕወሐትን ለመታደግ እያደረጉት ያለውን ጥረት አስተዛዝቦን ሳያበቃ ሰሞኑን የሕወሐት ተቃዋሚ ነኝ የሚለው አረና ተብዬ መሪዎች የተደበቀውን ማንነታቸውን እያወጡልን ነው፡፡ ነገሩ የዘሬን ብተው ይመንዝረኝ አይነት ነው፡፡ አሁን ላይ ወያኔን ተብዬውን ማንም ስለማይሰማው ሰሞኑን መተማ ላይ የደረሰውን አደጋ በትገራይ ሕዝብ ላይ ያነጣጠር ብለው እንዲናገሩለት ወያኔ የቁርጥ ቀን የክት ድርጅቱ እንደሆነ እስከዛሬ ያልገመትነው የአረና መሪዎች እንዲናገሩለት አዞ ሲያስለፈልፍብን ሰንብተናል፡፡ ከዛም በላይ የወልቃይትን ጉዳይ ሕገመንግስታዊ በሆነ መልኩ ወደ ትግራይ የተካለለ ነው በሚል ከዚሁ አረና ከሚባለው ደርጅት መሪዎች እየተነገረን ነው፡፡ ጠላትና ወዳጅን እያበጠረ የሚያወጣ ቁርጥ ቀን መጥቷል አሁን መደበቅ፡፡ የክት ሆኖ መኖር የሚቻልበት ጊዜ አይደለም፡፡ ወያኔ ሁሉንም የክትና ሚስጢራዊ አጋሮቹን በይፋ እየተጠቀመ ነው፡፡ መተማም ሆነ ሌላ ቦታ በትግራይ ተወላጅ በመሆኑ ሳይሆን ከትግራይ ሆን ከሌላ የወያኔ ደጋፊና የሕዝብ ጠላት እስከሆነ ድረስ ሕዝብ ጠላቶቹን መዋጋት አለበት፡፡ ደባርቅ፣ ዳንግላ፣ ደብረታቦርና ሌሎችም ቦታዎች በሕዝብ ጥቃት የደረሰባቸው የወያኔ አገልጋዮች የትግራይ ተወላጅ ስለሆኑ ሳይሆን ወያኔን የሚደግፉ የሕዝብ ጠላቶች ስለሆኑ ነው፡፡ አብዛኛው በሌላው ማህበረሰብ ውስጥ የሚኖር የትግራይ ተወላጅ ወያኔን የሚደግፍ ብቻም ሳይሆን በሰላይነት የሚያገለግል ለሕዝብ ልጆች እልቂት ዋና መረጃ የሚያቀብል ነው፡፡ በዚህ ምክነያት ኢላማ ቢደረግ ተጠያቂው ማን ነው፡፡ ሕዝብ ሙሉ መረጃ አለው፡፡  ጨው ለራስህ ስትል ጣፋጥ ነው፡፡

ግንቦት 7ና ብርሀኑ ነጋ፡ አሁንም ድረስ ያልተገለጠልኝ ጉዳይ ብርሀኑ ነጋ የሚባል እመራዋለሁ የሚለው ግንቦት 7 የሚባለው ቡድን ነው፡፡ ብርሀኑ ነጋንም ማንነቱን ማወቅ አልቻለኩም፡፡ አንድ ነገር አስታውሳለሁ፡፡ ብርሀኑ ነጋ እስር ቤት ሆኖ የጻፈውን መጽሐፍ ፕሮፌሰር መስፍን የራሱን ዝና የጻፈበት የማይረባ ጽሑፍ አድርገው መተቸታቸውን፡፡ ከዚያም በኋላ ያሉት እንቅስቃሴዎቹ ሁሉ ግራ የሚያጋቡ ነበሩ፡፡ አርባምንጭ ላይ አደጋ የጣልኩት እኔ ነኝ በየ አቅጣጫው ትግል ጀምረናል ሲል የተሰማው የብርሀኑ ሚስጢር በተወሰነ የተጋለጠና ሕዝብን የማታለልና ገነዘብ መሰብሰቢያ ስልት መሆኑን የተረዳን መሰለኝ፡፡ አሁንም ያልገባኝ ነገር ግን ብዙ አለ፡፡ የአርባመንጩን ጥቃት እውን ግንቦት7ም ከሆን ለምን አላማ እንዳደረገው? ይሁን እንበልና ጥቃቱ የተደረገው ወያኔን ለማስደንበር ነው ወይስ ሆን ተብሎ ወያኔ ፕሮፓጋንዳ እንዲሰራበት ከወያኔ ጋር በመተባበር የተደረገ? ልብ በሉ ሴረኞች የሚንቀሳቀሱት በዚህ ያህል ርቀት ነው፡፡ ኢሳያስና ሻቢያ የቁርጥ ቀን ወያኔ ወዳጅ እንደሆኑ ባለማወቅ ወይስ ከላይ የሰጋሁት የሴራ መረብ ወስጥ የሚደረግ ድራማ ነው? ለአንዳርጋቸው ጽጌ መያዝ ራሱ ግንቦት 7ና ሻቢያ እጁ የለበትም ብሎ ሙሉ በሙሉ ማሰብ ይቻላል? ልብ በሉ በእንድ ድርጅት ውስጥ በእውነት የሚንቀሳቀሱና በልዩ ሴራ የሚንቀሳቀሱ አባላት እንደሚኖሩት መገመት ብልሕነት ነው፡፡ ይህ ብቻም ሳይሆን በ1997 የቅንጅት መፈራረስ ወቅት ዋነኛ ምክነያቶች ምን ነበሩ? ብርሀኑ አንዱ ነበር እንደውም የብርሀኑንና የልደቱን የግል እንቅስቃሴ በወቅቱ ለቅንጅት መፍረስ እንደ ትልቅ ምክነያት ፕሮፌሰሩ ሲኮንኑ ተሰምተው ነበር፡፡  ይሄን ሚስጢር የምታውቁ አካፍሉን፡፡ መጠርጠሩ ጥሩ ነው፡፡ከእግዚአብሔር የመጣውን ግን ማንም አይመልሰውም!

እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይታደግ

አሜን!

ሰርጸ ደስታ

 

 

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.