ዘር ላይ መንጠልጠል ደካማነት ነው – #ግርማ_ካሳ

አብረሃ ደስታ
አብረሃ ደስታ

አብረሃ ደስታ የሚከተለውን ጽፏል። በዉጭ አገር የአረና/መድረክ ድጋፍ ማህበር እንደዚሁ አንድ መግለጫ አውጥቷል። በዚህ ላይ አንዳንድ ሐሳቦች መስጠት ፈለኩ።
========
“ዓረና” ማለት “ለነፃነታችን በአንድነት ለመታገል ተስማማን” ማለት ነው። በዓረና ትርጉም ላይ ነፃነት፣ ትግል፣ አንድነትና ስምምነት አለ። BTW ዓረና የብሄር ፓርቲ አይደለም፤ የክልል ፓርቲ ነው። ዓረና በክልል መደራጀት ለሀገራችን ህዝብ እንደማይበጅ በመገንዘብ መድረክን ለማዋሃድ ሲሰራ ቆይቷል። አሁን ደግሞ ለሀገርና ለህዝብ ደህንነትና አንድነት ሲባል አንድ ወጥ የሆነ ውሁድ ሀገራዊ አማራጭ ፓርቲ ለመመስረት ከመድረክ፣ ከሰማያዊ፣ ከመኢአድ፣ ከቀድሞ አንድነት ፓርቲ አመራር አባላትና ከሌሎች ታዋቂ ፓለቲከኞች ጋር እየተነጋገረ ይገኛል። ይሳካ ዘንድ ምኞቴ ነው።
========
አብርሃ ደስታ ትክክል ነው።አረናዎች የሕወሃት የዘር ፖለቲካ እንደማያዋጣ ፣ ሕወሃት ከትግራይ ህዝብ የወጣና ለሕወሃት ስልጣን መጨበጥ ምክንያት ቢሆንም፣ ሕወሃት ስልጣን ከጨበጠ በኋላ ግን ሕወሃት የትግራይን ህዝብ እንደካደ ነው የሚገልጹት።
እርግጥ ነው በመከላከያ ሰራዊት ከፍተኛ ሹማምንቶች 95% ትግሬዎች ናቸው። እግርጥ ነው አዲስ አበባ ሃብታምና ቱጃር ከሚባሉት መካከል አብዛኞቹ ትግሬዎች ናቸው። ከፍተኛ የትምህርት እድል፣ ስልጠናዎች ሲባሉ በብዛት ተጠቃሚ የሆኑት ትግሬዎች ናቸው። እርግጥ ነው የማይካድ፣ በግልጽ የሚታይ የትግሬዎች የበላይነት አለ። ቁልፍ በተባሉ ቦታዎች ሁሉ ከላይ ሆኖ የሚቆጣጠር አንድ የትግራይ ተወላጅ ይኖራል። አረናዎች ይሄንን የሚክዱ አይመስለኝም።
አንድ ታሪክ ልንገራችሁ ፣ እውነተኛ ታሪክ።

ከአዲስ አበባ ወጣ ብሎ በማህበር ተደራጅተው የተወሰኑ ሰዎች ቤት መስራት ፈለጉ። የኦሮሚያ ክልል ባለስልጣናት ፍቃድ ሰጥተው ስራው ሊጀመር ሲል፣ ምክንያቱ በማይታወቅ ሁኔታ ስራዉን አገዱባቸው። በጣም ተቸገሩ። በኋላ በአካባቢው ያለ አንድ የትግራይ ልጅ አለ፣ እርሱን አማከሩት። (መጀመሪያዉኑ እርሱን ማማከራቸው ለምን እንደሆነ መቼም ሁላችንም ይገባናል) እርሱ አንድ ዘመዴን እናንተ ማህበር ዉስጥ ከከተታችሁት ልረዳችሁ እችላለሁ አላቸው። እነርሱም ምርጫ ስለሌላቸው እሺ አሉ። ብዙም አልቆዩም የኦሮሚያ ክልል ሃላፊዎች ፈቀዱ። የማህበር ቤቱን ተሰራ። ይህ አይነቱ አሰራር እንግዲህ የተለመደ ነው። ነገሮችን መሸፋፈን የለብንም። የትግሬዎች የበላይነት አለ። አራት ነጥብ።

ሆኖም ግን እነዚህ ጥቂቶች ናቸው። ያንን ነው ብዙዎቻችን እየሳትን ያለነው። እነዚህ የስርዓቱ ተጠቃሚዎች በአብዛኛው፣ እንደ አዲስ አበባ ባሉ ቦታዎች ያሉ ናቸው። የነዚህ ሰዎች ልጆች ብዙዎች በዉጭ አገር ናቸው ወይንም በአዲስ አበባ በጣም ዉድ በሆኑ ት/ቤቶች ነው የሚማሩት። ብዙዎቹ የትግራይ መሬትን የማይረግጡ ናቸው። እነዚህ ለስርዓቱ ተጠቃሚ የሆኑ፣ ስል ትግራይ ክልል ምንም የማያወቁ፣ ጥቂት የትግራይ ተወላጆችን እያየን በትግራይ ክልል እየኖረ ያለው ድሃ ሕዝብ እንደተጠቀመ አድርገን መቁጠር በጣም፣ በጣም ትልቅ ስህተት ነው። ስህተት ብቻ ሳይሆን አሳዛኝም ነው።
አንዳንዶች በትግራይ ያሉ ፕሮጀክቶችን ይጠቅሳሉ። ትክክል ነው። ብዙ ፕሮጀክቶች ከሌላው ክልል በበለጠ መልኩ ትግራይ ዉስጥ እየተደረገ ነው። ግን የነዚህ ፕሮጀክቶች ተጠቃሚ አሁንም ጥቂት ትግሬዎች ናቸው። ለምሳሌ ያለፈው አመት በነበረው ድርቅ፣ 2/3ኛ ትግራይ ለአደጋ ተጋልጦ ነበር። በተለይም በምስራቅ ትግራይ በብዙ ቦታዎች የዉሃ ጉድጓዶችም አልተቆፈሩም። ሕወሃት በመቀሌ የተወሰኑ ቦታዎች፣ እንደ ሁመራ ባሉ ብዝይ ትርፍ በሚገኝባቸው ቦታዎች እንጅ በአብዛኛዉን ትግራይ አስታወሶ አያውቅም። አዲግራት ወድቃለች ። አድዋ እንኳን በአቅሟ ምንም ነገር የላትም።
ለዚህም ነው አረናዎች የሚናገሩትና የሚጽፉት ትክክል ነው ብዬ የማምነው። በጎንደር፣ በአዲስ አበባ፣ በአዳማ ..በአካባቢያችን ያሉ ትግሬዎችን እያየን ውቅሩ፣ ሃዉዜን …ያለውም ትግሬ እንደዚያ ሊመስለን አይገባም።

አረናዎች የትግራይ ህዝብ በሕወሃቶች ምክንያት እንዲጠላ እየተጠላ እንደሆነ ያውቃሉ። የትግራይ ህዝብ ደህንነቱ የሚረጋገጠው በሕወሃት ሳይሆን ከሌላው ሕዝብ ጋር በመተሳሰር መህኑን ያወቃሉ። ለዚህም ነው ከዘር ፖለቲካ በመዉጣት፣ ዜጎች በኢትዮጵያዊነታቸው ብቻ የሚመዘኑበት ጠንካራ የፖለቲክ ፓርቲ እንዲቋቋም ሲሰሩ የነበሩት። አረናዎች እኮ በዚህ አቋማቸው ” ከትግራይ ጠላቶች ጋር የሚሰሩ ዝቃጮች” እኮ እስከመባል የደረሱ ናቸው።

ከስድስት አመት በፊት ነው። መድረክ ለ2002 ምርጫ ይወዳደር ነበር። ትልቅ ስብሰባ በመቀሌ አዳራሽ ተደረገ። ወደ 5 ሺህ የመቀሌ ነዋሪ ተገኘ። በስብሰባው በርካታ የሕወሃት ካድሬዎች ተግኘተው መረበሽ ጀመሩ። አንዱ እንዲናገር ተፈቀደለት። ” እናንተ ከትግራይ ጠላቶች ጋር የምትሰሩ ከሃዲዎች ናችሁ” አላቸው። የትግራይ ጠላት እንግዲህ የሚሉት ሌላውን ማህበረሰብ ነው። ሕወሃቶች እንደዚያ ነው የሚያስቡት። ያለነርሱ፣ ያለ ትግሬው ሌላው በሙሉ ተረግጦ መገዛት ያለበት ጠላት ነው።

በወቅቱ አቶ ገብሩ ምላሽ ሰጡ። በጣም ደስ የሚል ምላሽ። ” የኔ ወንድም የሐሳብ ልዩነት ይኖራል። ከኛ በሐሳብ የተለዩትን እንደ ጠላት ማየት የኋላ ቀርነት ነው። ትግራይ የኢትዮጵያ ናት። የትግራይ መሬት የትግሬው ብቻ አይደለም። የአማራው፣ የኦሮሞውም የአፋርም ነው።፡የኦሮሞ መሬት የትግሬው ነው። የትግሬ .የኦሮሞ፣ የአማራ ብሎ ነገር የለም። እኛ አንድ ነን” ነበር ያሉት።
አረናዎች ሕወሃት የበጠሰውን ከጥንት ጀምሮ በትግሬውና በሌላው ማህበረሰ መካከል የነበረውን ትስስር እንደገና ለማደስ እየሰሩ ያሉ ወገኖች ናቸው። ለዚህ ነው መድረክ ዉስጥ ገብተው የሚሰሩት። ለዚህም ነው መድረክ ኦሮሞ ትግሬ ሳይባባል አንድ አገር አቀፍ፣ ሁሉንም የሚያሰባስብ ደርጅት ሆኖ እንዲወጣ በጣም ግፊት ሲያደርጉ የነበሩት። አረናዎች እንዳሰቡት ቢሆንላቸው ኖሮ ይሄን ጊዜ ጠንካራ ተቃዋሚ ፓርቲ ይኖር ነበር።

አሁንም የአራና ሰዎች ከመኢአድ፣ ሰማያዊ፣ የቀድሞ አንድነቶች ጋር የሚያደርጉት ንግግር ከመደገፍ ባሻገር እንዲሳካ ምኞቴን እገልጻለሁ። ሕወሃትን ማሸነፍ ከፈለግን፣ በዘር፣ በሃይማኖት ሳንለያይ መሰባሰብ አለብን። ሕወሃትን ማሸነፍ ከፈለገን በስሜት የሚያለያይ፣ የሚያራራቅ ነገር ከማድረግ መቆጠብ አለብን። ሕወሃት ማሸነፍ ከፈለገን የሕወሃትን ፖለቲክ ማሸነፍ አለብን። የሕወሃት ፖለቲክ ሁሉንም ነገር በዘር መከፋፈል ነው። ሕወሃትን ጠልተን የሕወሃትን ፖለቲካ በሌላ መልኩ የምናስተናግድ ከሆነ ህወሃትን ሸኝተን ዳግማዊ ሕወሃትን ነው ያስተናግደነው።

አንዳንዶች ለምን የትግራይ ህዝብ ተቃዉሞ አያሰማም ይላሉ ? ለምን የአዲስ አበባ ህዝብ ተቃዉሞ አላሰማም፣ ? ለምን በጂማ ዞን፣ ኢሊባቡር ዞን ..ተቃዉሞ አይሰማም ? ለምን ድረዳዋ ከተማ ተቃዉሞ አይሰማም ? ለምን ደቡብ ክልል አዋሳ በመሳሰሉት ተቃዉሞ አይሰማም ? በመራብ አርሲ ዞን እንዳለው ለምን በአርሲ ዞን (አሰላና አካባቢው) ተቃዉሞ አይሰማም ? ለምን ተቃዉሞ አይሰማም ብለን ትችት ማቅረብ ሳይሆን ተቃዉሞ እንዲሰማ ሕዝቡ እንዲነሳ እንዴት እናደራጀው? ማለት ነው ያለብን።

ለማንኛው ይሄ አስተያየት የሚያስከፋችሁ ልትኖሩ እንደምትችሉ አውቃለሁ። ያለውን ሁኔታ ግለቱ ስለጨመረ ስሜታዊነት እንደበዛ አወቃለሁ። ሆኖም ግን አተርፍ ባይ አጉዳይ እንዳንሆን፣ እንገነባከን ብከን እንዳናፈርስ ስለፈለሁ ይሄንን ጽፊያለሁ። በምንም መልክ ይሁን ይዘት ዘር ላይ ማተኮር በጣም ጎጂ ነው። የዘር ሃረጋችን ላይ ከመንጠልጠልና ጠባብ ከመሆን የሚያስተሳሰር ነገር ላይ መበርታት ያስፈለጋል።
በመጨረሻ ለአብርሃ ደስታና ለአረና ሰዎች አን መልእክት አለኝ። በሕግ የተመዘገቡ ደርጅት ናቸው። በሶሻል ሜዲያው በአማራው እና ኦሮሚያ ክልል እየሆነ ያለው አጥብቀው እያወገዙ ነው። አሁን ብቻ ሳይሆን አብርሃ ደስታ እሥር በተ ሆኖም እነ ምዶም ገብረስላሴ ለኦሮሞ ተቃዉሞ አጋር ሆነው ሲታገሉ የነበሩ ናቸው። አረናዎች ከኦፌኮዎች ጋር አብረው በመድረክ ዉስጥ እየሰሩ ናቸው። በመሆኑም ይሄንን ተቃዉሞ አድማሱን በማስፋት፣ የትግራይ ህዝብ ድምጹን የሚያሰማበትና የሚነቃነቅበትን መንገዶች እንዲያመቻቹ በአክብሮት እጠይቃለሁ።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.